የሕዝብ እንደራሴው አቶ ክርስቲያን ታደለ፣ በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት 1ኛ ዓመት የሥራ ዘመን 13ኛ መደበኛ ስብሰባውን ሰኔ 7 ቀን 2014 ዓ.ም. ሲያካሂድ ለጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ ጥያቄ ባቀረቡበት ወቅት የተናገሩት፡፡ የፓርላማው የመንግሥት ወጪ አስተዳደርና ቁጥጥር ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢው አቶ ክርስቲያን፣ ሕግ ማስከበር ሲባል ዜጎች በአገራቸው በማንነታቸው ቤተኛና ባይተዋር ሳይደረጉ የሚኖሩባት ሰላማዊ አገር መፍጠር ብቻ ሳይሆን ለደረሰ ጥፋትም ተጠያቂነት ማስፈን ሲቻል ነውም ብለዋል። ባለፉት አራት ዓመታት ንጹኃን ዜጎች ላይ ያለመታከት የጅምላ ግድያና ማፈናቀል ሲፈፀም፣ የመንግሥት ያለህ ስንል የኖርነው፣ ሕግ ማስከበር የመንግሥትነት ሥነ ፍጥረት መሆኑን ስለምንረዳ ነው ያሉት እንደራሴው፣ ይሁንና መንግሥት ሕግ የማስከብር መብት ብቻ ሳይሆን ግዴታ አለበት ሲባል ማስከበርና መጠበቅ ያለበትን ሕግ የመጣስና የማፍረስ መብት አለው፣ ይኑረው ማለት አይደለም ሲሉ በአፅንዖት ተናግረዋል።