Monday, July 15, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ማኅበራዊከዓምናው በ16 በመቶ የጨመረውን የወባ በሽታ ሥርጭት ለመግታት

ከዓምናው በ16 በመቶ የጨመረውን የወባ በሽታ ሥርጭት ለመግታት

ቀን:

ወባ የጤና ዕክል ብቻ ሳይሆን የማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ችግር ሊያስከትል የሚችል በሽታ ነው፡፡ ሥርጭቱም ዓለም አቀፍ ደረጃ ያለው ሲሆን በተለይ ከሰሃራ በታች ባሉ አገሮች ውስጥ ያጎላል፡፡ በሽታው በወረርሽኝ መልክ ሲነሳ ደግሞ ጎዳቱ ከፍተኛ ነው፡፡

እንደ ዓለም ጤና ድርጅት መረጃ፣ የወባ ሥርጭት ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረና እየከፋ በመምጣት ላይ ነው፡፡ በተለይ በ2021 በዓለም አቀፍ ደረጃ የወባ ታማሚዎች ቁጥር በ2020 ከነበረው በአሥራ አራት ሚሊዮን ጨምሯል፡፡ ከ90 በመቶ በላይ ጭማሪ የተመዘገበው ደግሞ ከሰሃራ በታች ባሉ አገሮች ውስጥ ነው፡፡

የጤና ሚኒስትር ዴኤታ ደረጀ ድጉማ (ዶ/ር) እንደገለጹት፣ ኢትዮጵያ ውስጥ ከ75 በመቶ በላይ የሚሆነው መልክዓ ምድር ለወባ መራቢያና ሥርጭት ተስማሚና ምቹ ነው፡፡ በእነዚህም ቦታዎች የሚኖሩ ማኅበረሰቦች ከ52 በመቶ በላይ ሲሆኑ፣ አብዛኛውም ማኅበረሰብ በሥርጭቱ ሳቢያ ለከፋ ጉዳት የተጋለጠ ነው፡፡

ከመስከረም እስከ ታኅሣሥ ያሉት ወራት ከፍተኛ የወባ ሥርጭት የሚታይባቸውና በአንፃሩ ደግሞ አብዛኛው ምርት የሚሰበሰብበት ነው፡፡ የወባ መከሰት ደግሞ አርሶ አደሮች ምርታቸውን በአግባቡ እንዳይሰበስቡና ተማሪዎችም ወደ ትምህርት ቤታቸው እንዳይሄዱ የሚያደርግ ነው፡፡

በኢትዮጵያ ውስጥ በ2012 ዓ.ም. 1.7 ሚሊዮን፣ በ2013 ዓ.ም. ደግሞ 1.2 ሚሊዮን የወባ ታማሚዎች እንደነበሩ፣ በ2014 ዓ.ም. በአሥር ወራት ውስጥ 1.3 ሚሊዮን ዜጎች በወባ እንደተያዙ፣ በእነዚህም ወራት በበሽታው የተያዘው ሰው ቁጥር ከዓምናው በ16 በመቶ እንደጨመረ ጭማሪውም የታየው በተወሰኑ ክልሎችና ዞኖች እንደሆነም ተናግረዋል፡፡

ዘንድሮ ከፍተኛ የወባ ሥርጭት ከታዩባቸው አካባቢዎች መካከል በደቡብ ብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ክልል ጋሞጎፋ፣ ወላይታ፣ ከምባታና ጠምባሮ ዞኖች ይገኙበታል፡፡ ከዚህም ሌላ በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ክልልም ከፍተኛ ቁጥር መመዝገቡን፣ በኦሮሚያ ክልል ምዕራብ አርሲ፣ ኢሉ አባቦራና ምዕራብ ወለጋ፣ በአማራ ክልል ማዕከላዊና ምዕራብ ጎንደር ከፍተኛ የወባ ታማሚዎች የተገኙባቸው አካባቢዎች  እንደሆኑ ጠቁመዋል፡፡

በተጠቀሱት አካባቢዎች የወባ ሥርጭት እንዲጨምር ያደረጉትም ምክንያቶች አንደኛው በዓለም አቀፍም ሆነ በኢትዮጵያ ደረጃ ለወባ ትንኝ መራባት ምቹ የአየር ሁኔታ እየተፈጠረ መምጣቱ ነው፡፡ በተለይም በምሥራቅ ኢትዮጵያ ተከስቶ ከነበረው ድርቅ በኋላ የዘነበው ዝናብ ለወባ ትንኝ መራባት ተስማሚ ሆኗል፡፡ በአጠቃላይ ሞቀትና ዝናብ ተቀላቅሎ ሲመጣ፣ ለበሽታው መስፋፋት ጥሩ መደላደልን ይፈጥራል ብለዋል፡፡

የወባ ችግር ባለበት ቦታ ላይ ወባን የመከላከሉና የመቆጣሩ ፕሮግራም ደከም እያለ መምጣቱ፣ በእነዚህ ቦታዎች ላይ አስፈላጊው ግብዓት በወቅቱ አለመድረስ፣ የጤና ባለሙያዎቹ መዘናጋት፣ በጤና ጣቢያና ኬላ የሚከናወኑ ሥራዎች ትንሽ ደከም ብሎ መታየት ለበሽታው መስፋፋት አስተዋጽኦ እንዳደረገ ሳይገልጹ አላለፉም፡፡

ማኅበረሰቡ የአልጋ አጎበር በበቂ ቁጥር ቢኖረውም ብዙ ቦታ ላይ ሲታይ አጠቃቀሙ ደካማ እንደሆነ፣ የአካባቢ ቁጥጥር ሥራ ላይም ውኃ ያቆሩ ቦታዎችን ማዳፈንና ማፋሰስ ላይ ሰፊ ክፍተቶች መኖራቸው ለወባ መስፋፋት ምቹ መደላደል መፍጠራቸውን ጠቁመዋል፡፡

እንደ ደረጀ (ዶ/ር)፣ ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው የወባ ታማሚዎች በተመዘገቡባቸው ቦታዎች ላይ ተገቢና አስፈላጊ ምላሾች ተሰጥተዋል፡፡ ከተሰጡትም ምላሾች መካከል 5.5 ሚሊዮን ፈጣን የወባ መመርመርያ ኪቶችና 4.5 ሚሊዮን ሰዎችን ማገልገል ወይም ማከም የሚችል ፀረ ወባ መድኃኒት ወደ የክልሎቹ ወርዷል፡፡

እንዲሁም ሃቻምና እና ዓምና ከ20 ሚሊዮን በላይ የአልጋ አጎበሮች በየክልሉ የተሠራጩ ሲሆን፣ ዘንድሮ ወረርሽኙ በተከሠተባቸው አካባቢዎች 2.9 ሚሊዮን የአልጋ አጎበር እንዲሠራጭ መደረጉ ከተሰጡት ምላሾች ይገኝበታል፡፡

እነዚህ ምላሾች በተከናወኑበት ወቅት በርካታ ተግዳሮቶች ተደቅነው እንደነበር፣ ከእነሱም መካከል የመንገድ መሠረተ ልማት በሌሉባቸውና ከፍተኛ ዝናብ ባሉባቸው ቦታዎች ላይ መድኃኒቶችንና የተለያዩ ቁሳቁሶችን ለጤና ተቋማት ለማድረስ አዳጋች መሆኑ ይገኙበታል፡፡ ያቆሩ ውኃዎችን አለማፋሰስና አለማፅዳት፣ ወባ ጠፍቷል ወይም ቀንሷል ከሚል አስተሳሰብ የተነሳ በአብዛኛው ቦታ ላይ አመራሩ ትኩረት አለመስጠትም የችግሩ አካል ናቸው፡፡  

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ሚዲያው በሕዝብ የህሊና ችሎት ከተዳኘ በቂ ነው!

መሰንበቻውን ድንገት ሳይታሰብ ያለ ማስጠንቀቂያ ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ...

የባህር በር ጉዳይ

በታምሩ ወንድም አገኘሁ ድሮ ድሮ ገና ልጅ ሆኜ ፊደል እንደቆጠርኩ...

አገሩ ፖለቲካዊ ስክነትና መደማማጥ ያስፈልገዋል

በንጉሥ ወዳጀነው    ኢትዮጵያ የሁላችንም የጋራ ቤት ነች፡፡ ‹‹ጥያቄዬ ተመለሰልኝ››፣...

የመንግሥት የሰብዓዊ መብት ተቋም ለምን የመንግሥት ሚዲያን ማስተማር አቃተው

በገነት ዓለሙ የአገራችን የ2016 የበጀት ዓመት መሰናበቻና የአዲሱ የ2017 በጀት...