ቨቻይና ታይዋን ግንኙነት መሻከር እ.ኤ.አ. በ1940ዎቹ በቻይና ከነበረው የእርስ በርስ ጦርነት ይነሳል፡፡ ወቅቱ በእርስ በርስ ጦርነት ብቻ ሳያከትም፣ ታይዋን ይፋ ያልሆነ መንግሥት እንድትሆንም በር የከፈተ ነበር፡፡
ታይዋን ራሷን የቻለች ነፃ አገር አድርጋ ብትቆጥርም፣ በቻይና ዘንድ ተቀባይነት ሳያገኝ ከግማሽ ምዕት ዓመት በላይ ተቆጥሯል፡፡ ይህ ደግሞ ኃያላን አገሮች የፖለቲካና ኢኮኖሚ ሽኩቻ በተነሳ ቁጥር ቻይና ላይ ጣት እንዲቀስሩ አድርጓል፡፡
ቻይና ታይዋንን ባስፈለገ ጊዜ በጉልበት ተጠቅማ መጠቅለል እንደምትችል ብትናገርም፣ በታይዋን በኩል አልበገር ባይነት አለ፡፡ ታይዋን የቻይናን ‹‹አንድ መንግሥት ሁለት አስተዳደር›› የሚለውን አካሄድ ባለመቀበሏም በርካታ ጊዜያት ውዝግብ ውስጥ ገብተዋል፡፡ ምዕራባውያኑም ለታይዋን ወግነው ቻይናን ሲያወግዙ ይሰማል፡፡
ታይዋን የራሷ ሕገ መንግሥት፣ በምርጫ የተቀመጠ መሪና 300 ሺሕ ያህል ወታደሮች ቢኖሯትም በጣም ጥቂት አገሮች ናቸው እንደ አገር ዕውቅና የሰጧት፡፡ ይልቁንም በቤጂንግ ያለው የቻይና መንግሥት ተሰሚነት ያለው ሲሆን፣ አሜሪካም ከታይዋን ጋር ይፋዊ ግንኙነት የላትም፡፡ ነገር ግን ብዙውን ጊዜ ለታይዋን ድምፅ ስትሆን ትታያለች፡፡ ራስን ለመከላከል በሚልም የጦር መሣሪያ ለታይዋን ትልካለች ስትል በቻይና ትወቀሳለች፡፡
የአሜሪካ ጣልቃ ገብነት የማይዋጥላት ቻይና፣ አሜሪካን በተደጋጋሚ ‹‹በቻይናና ታይዋን መካከል ጣልቃ አትግቢ›› ስትል ስታስጠነቅቅ ዓመታትን አስቆጥራለች፡፡
ከሰሞኑ ከወደ ቻይና የተሰማውም አሜሪካ ለታይዋን ነፃ አገር መሆን የምታደርገውን ድጋፍ እንድታቆም የሚያስገነዝብ ነው፡፡ ‹‹የታይዋን ነፃ አገር መሆን ጦርነት ይቀሰቅሳል›› ስትልም ቻይና አስጠንቅቃለች፡፡
ቢቢሲ እንደዘገበው፣ አሜሪካ ታይዋንን ነፃ አገር ለማድረግ የምታርገው ማንኛውም ጥረት ቻይናን ወታደራዊ ዕርምጃ እንድትወስድ ያደርጋል ሲሉ የቻይና መከላከያ ሚኒስትር አስታውቀዋል፡፡
የቻይና መከላከያ ሚኒስትር ዊ ፊን ከአሜሪካ አቻቸው ሎያድ ኦስቲን ጋር በሲንጋፖር ከነበረው የእስያ የደኅንነት ጉባዔ ጎን ለጎን ውይይት አድርገዋል፡፡
በውይይታቸውም፣ ታይዋንን ከቻይና ለመነጠል የሚደረግን ጥረት የቻይና መከላከያ ማንኛውንም ዋጋ ከፍሎ እንዲዋጋ ያደርጋል፣ ሌላ ምርጫ የለም ብለዋል፡፡
ሚስተር ኦስቲን በበኩላቸው፣ ቻይና በታይዋን አካባቢ የምታደርገውን ወታደራዊ እንቅስቃሴ ጠብ አጫሪና አፍራሽ ብለውታል፡፡
በአካባቢው የሰላምና መረጋጋትን አስፈላጊነት ከግምት ባላስገባ መልኩ የቻይና የጦር ጀቶች የታይዋንን አካባቢ የሚቃኙ መሆናቸውንም ጠቁመዋል፡፡
ቻይና ራሷን የምታስተዳድረውን ታይዋን የራሷ ግዛት አድርጋ እንደምታይና አሜሪካ ለታይዋን የምትሸጠውን የጦር መሣሪያ እንደሚያወግዙ ሚስተር ዊ ተናግረዋል፡፡
አሜሪካ ቤጂንግ የቻይና ዋና መንግሥት መሆኗን፣ ያለውን ሁኔታ አስጠብቃ እንደምትጓዝ እንዲሁም የታይዋንን ነፃ አገር መሆን እንደማትደግፍ ሚስተር ኦስቲን ተናግረዋል፡፡ ውጥረቱን በኃይል ለማርገብ መሞከር እንደሌለበትም መክረዋል፡፡
ከቻይና ጋር አለመግባባት እንዳይፈጠርም ከቻይና መከላከያ ጋር ምሉዕ የመረጃ ልውውጥ አስፈላጊ እንደሆነ ጠቁመዋል፡፡
ከ1980ዎቹ ወዲህ እየተሻሻለ የመጣው የቻይናና የታይዋን ግንኙነት፣ አሁን ላይ በእጅጉ ሻክሯል፡፡ ቻይና አንድ አገር ሁለት ሥርዓት በሚለው አስተዳደር ለታይዋን ራሷን የማስተዳደር መብት እንዲኖር ለማድረግ፣ ከዚሁ ጎን ለጎን ታይዋን ከቻይና ጋር መልሳ ለመቀላቀል እንድትስማማ ሐሳብ አቅርባ የነበረ ቢሆንም፣ ታይዋን አልተቀበለችውም፡፡
ቻይናና ታይዋን ያላቸውን የፖለቲካ ሽኩቻ ለመፍታትም በመንግሥት ደረጃ የተደረገ ውይይት የለም፡፡ ውይይቶች ተደርገው የነበረ ቢሆንም፣ ውይይቶቹ በመንግሥት ባልተወከሉ ሰዎች መካከል ነበር፡፡
አሜሪካ ግን ባለፈው መስከረም የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ከፍተኛ ባለሥልጣኖቿን ወደ ታይዋን ልካ ነበር፡፡ ይህ በቻይና በኩል የተወገዘ ሲሆን፣ አሜሪካም ለታይዋን ነፃ አገር መሆን ከምትሰጠው ፍንጭ እንደትታቀብ ጠይቃ፣ እንዲህ ዓይነቱ አካሄድ የቻይናና አሜሪካን ግንኙነት እንደሚያበላሽ አስታውቃ ነበር፡፡