Friday, September 22, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ልናገርከክልከላ ልማድ እስከ ህሊና ማጣት የዘለቀው ፖለቲካችን

ከክልከላ ልማድ እስከ ህሊና ማጣት የዘለቀው ፖለቲካችን

ቀን:

በንጉሥ ወዳጅነው

የጽሑፉ ርዕስ የጋዜጣ የማይመስልና ሰፊ መሆኑን ተረድቻለሁ፡፡ ነገር ግን  በአገራችን እየሆነና ይበልጥ እየተባባሰ ከመጣው የተሰናሰለ ችግር ጋር ሆነ፣ ቀደም ሲል ከተመለካከትኳቸው የምሁራን ጥልቅ ዕይታዎች አንፃር ነገሮችን ለማየት ነው የፈለግኩት፡፡ እናም በአገራችን በብዙዎቹ ማኅበረሰቦች ውስጥ ያሉት ከልካይና ገዳቢ አስተሳሰቦች መሬት ላይ ለሚታዩት ነፀብራቆች ያሳደሩትን አሉታዊ ጫና በማንሳት ልጀምር፡፡

የክልከላ ልማዳችን ከጓዳ እስከ ቤተ መንግሥት

በምንኖርበት ኢትዮጵያዊ ሥነ ልቦና፣ በየትኛውም ማኅበረሰብ ልማድ ይሆን በብዙዎቹ ሃይማኖቶች ዕሳቤ ልታይ ልታይ ማለት ብዙም የሚወደድ አይመስለኝም፡፡ እሱ ብቻ ሳይሆን  ለምን ማለት፣ መመራመር፣ መጠየቅ፣ ነገሮችን ገና በለጋነት ዕድሜ ለማወቅ መጓጓት እንደ መንቀዥቀዥ የሚቆጠሩ ናቸው፡፡ ሐሳብን በነፃነት መግለጽና ከየትኛውም ወገን ጋር መነጋገርም ‹‹ልጅነት መልክ ያሳምራል እንጂ፣ ንግግር አያሳምርም፤››  በሚሉ ብሂሎች ተቀንብቦ የኖረ ልማዳችን ነው፡፡

በዚህ ጉዳይ ላይ ፈቃደ አዘዘ (ዶ/ር) “ቁዘማ፣ ባህልና ልማት በኢትዮጵያ›› (1997 ዓ.ም.) በሚለው ጥልቅ ምልከታው ላይ ያነሳው ጠቃሚ ነጥብ መኖሩን አስታውሳለሁ፡፡ በተለይ “አስተውሎት ሁለት” ሲል በገለጸውና ከቤተሰብ እስከ ቤተ መንግሥት በሚለው ንዑስ ርዕሱ ያስቀመጣቸውን ጭብጦች እንመልከት፡፡ እንዲህ ይላል፡፡

‹‹…ከቀደመው ጊዜ ጀምሮ ሕፃኑ ነክቼ፣ ዳብሼ ልወቅ ሲል ከማሳየትና ከማስዳበስ ይልቅ ብዙ ጊዜ የሚቀድመው እረፍ፣ አትንካ ማለት  ነው፡፡ ለዚህም ብዙ ጊዜ ምክንያት አለው፡፡ ቤት ውስጥ አዋቂዎች ሲያወጉ፣ ነብስ የዘራው ሕፃን፣ ልጅነቱ በመራው ሊናገር ሲል ብዙ ጊዜ የሚያጋጥመው  “ጥልቅ አትበል!!” ነው፡፡ አንዳንድ ነገሮችን ለማወቅ ተግቶ ሲመለከትም ከማስረዳት ይልቅ፣ “በምን ታያለህ” የሚበረግግበት ጊዜ ጥቂት አይደለም፡፡

‹‹አዋቂዎች መስማት የለበትም ብለው የወሰኑት ነገር አንድ የነቃ ልጅ  ሲሰማ ከተገኘም፣ ግሳፄ ነው የሚተርፈው፡፡ የሕፃናትንና የልጆችን ነፃ እንቅስቃሴ፣ ነፃ ንግግር፣ ነፃ ሐሳብ የመግታትና የማገድ አዝማሚያዎች ብዙ ቤተሰብ ውስጥ አልነበሩም፣ ዛሬም የሉም ማለት አይቻልም፡፡

‹‹በእውነቱ ይህ አስተሳሰብ አሁንም ድረስ ከጓዳችን እስከ አደባባይ ለመኖሩ መንግሥት አራምደዋለሁ ከሚለው አስተሳሰብ በተቃራኒ፣ ወይም አልመች ባለ ሁኔታ አማራጭ ሐሳብ ያነሱ፣ በሚያራምዱት አመለካከት፣ ተግባር፣ እምነት ወይም የመሰላቸውን በመናገር ብቻ ፍዳ እያዩ ወይም ከተለመደው የሕግ አግባብ ውጪ ሲጉላሉ የሚታዩ ሰዎችን እንደ አብነት መጥቀስ ይቻላል፡፡

‹‹እንደ አገር የቤተሰብን፣ የአስተዳደርና የሥልጣን መዋቅር ስንነድፍም በተለምዶ   በኢትዮጵያ የምናገኘው አባት “መሪ” እንደ ፈለገ ፈላጭ ቆራጭ፣ ብዙ ጊዜ የገንዘብና የሥልጣን ምንጭ ባለቤት ነው ይባላል፡፡ እናትና ልጆችም አባት ባመጣው ገንዘብ ተጠቃሚዎችና የሥልጣኑም ማረፊያ ናቸው፡፡ የእሱ “ሕዝብ” ናቸው፤›› ማለት ይቻላል ብሏል፡፡

በጥልቀት ለፈተሸው ሰው በየትኛውም መንግሥታዊ አገልግሎት ውስጥ ወይም በመቼውም የአገራችን የፖለቲካ ሒደት፣ መንግሥታዊ ሥሪት ክልከላና መገደብ ዋነኞቹ መገለጫዎቻችን ናቸው፡፡ መቃወም፣ ሠልፍ ማካሄድ፣ ያልተስማማን ነገር መተቸት፣ ወዘተ የመንግሥትን ሥልጣን ስለሚነቀንቁ ነው የሚከለከሉት ሊባሉ ይችላሉ፡፡ በግሉ ሴክተር በተለይም በአገልግሎት፣ በትምህርትና በጤና ወይም በሌላው ዘርፍም ቢሆን “Don’t DO” የሚሉት መመርያዎችና ድንጋጌዎች መብዛትን ለተመለከተ፣ ጊዜው ቢቀያየርም የምሁሩ ሐሳብ የሚጣል አለመሆኑ ግልጽ ይሆናል፡፡

ለዚህም ይመስለኛል በአገራችን የዘመናዊ ፖለቲካ ሒደት ውስጥ በየወቅቱ ዴሞክራሲን ለማዋለድ የሚጀመረው ጥረት ንጉሡ ሄዱ፣ ደርግ መጣ፣ ኢሕአዴግ ገባ፣ ብልፅግና ተቀበለ በተመሳሳይ መንገድ “ባለህበት እርገጥ” እያለ የሚቀጥለው፡፡ ስለሆነም በዘመናዊው ዓለም እንደታየው አስተሳሰብን የመግራትና የኖረውን ሰንካይ ልማድ ከሥር ከመሠረቱ በማስወገድና በማረም በነፃነት ማሰብና መተግበር ለመጀመር ትኩረት ሰጥቶ መታገል አስፈላጊ ሆኗል፡፡

የህሊና ችግር እንደ ማሳያ

እንደ ሕዝብ ለሞራል፣ ለሥነ ምግባርና ለወገን ጥቅም አስቦ የመሥራቱ ብርቱ ኢትዮጵያዊ ሥነ ልቦናም ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተዳከመ መምጣቱን መጥቀስ ያስፈልጋል፡፡ በተለይ በአገራችን ምሁር፣ ባለሀብትና የከተማ ነዋሪ የሚባለው አብዛኛው ዜጋ (ምንም እንኳን ዓለም አቀፍ ተፅዕኖው ያለ ቢሆንም) ለሕግ፣ ለእምነትና ለህሊና ያለበትን ተጠያቂነት ሲዘነጋ ማስተዋል እየተባባሰ ነው፡፡

አንዳንድ ባለጠንካራ ሞራልና የሰብዓዊነት ጠበቃ የሆኑ ዜጎችን በሥራ አጋጣሚ ለህሊናቸው ታማኝ ሆነው ማየትና ማግኘት ቢቻልም፣ የብዙኃኑ ዜጋ ባህሪ ግን ከሚባለው በላይ ማኅበረሰባዊ ኪሳራ የሚንፀባረቅበት ነው፡፡ ለዚህ ጽሑፍ ማጠናከሪያ እንዲሆን በዋናነት በመንግሥት መዋቅሩ፣ በተለይም በጤናው ዘርፍ የሚታየውን  ሰውና ሕይወትን ከማስቀደም ይልቅ፣ ገንዘብና የራስ የማይጠረቃ ፍላጎትን ማሳደዱን እዚህም እንመለከታለን፡፡

በእርግጥ በየትኛውም መለኪያና መሥፈርት ቢሆን ሁሉንም የሙያ መስኮችና ሙያተኞቻቸውን በጅምላ ማመሥገንም ሆነ መውቀስ አይቻልም፣ አይገባምም፡፡ በሰው ልጆች መካከል ከአፈጣጠራችንና ከአስተዳደጋችን ጋር በተያያዘ ልዩነት የመኖሩን ያህል፣ በባህሪም ሆነ በተግባር አንዱ ከሌላው የተለያየ ነው፡፡

የጤናውን ዘርፍ በመሰሉ ሩህሩህነት፣ ረጂነት፣ አጋዥነትና ሕይወት አዳኝነት ግድ በሆኑባቸውና ተምሎ በሚገባባቸው ሙያዎች ውስጥ ግን፣ የሥነ ምግባር መርሆዎችና የሙያው ሕገ ደንቦችን መተግበር ብቻ ሳይሆን የህሊና ተገዥነት የብዙኃኑ መገለጫ መሆን ነበረበት፡፡ የሞራል ግዴታም ነው፡፡ በተለይ የእኛን አገር ለመሰሉ በድህንት ውስጥ ላሉ ሕዝቦች ደግሞ ከሥጋዊ እርካታ ይልቅ የመንፈስ እርካታ የሚያስከብርና የአስተሳሰብ ልዕልና ነው ትውልድን ለማሻገር የሚያስችለው፡፡

መረጃዎች እንደሚያመለክቱት ባሳለፍናቸው ሦስትና አራት ዓመታት በርካታ የአገራችን ሐኪሞችና የጤና ባለሙያዎች ራሳቸውን ለኮቪድ-19 ወረርሽኝ አጋልጠው ብዙዎችን ለመታደግ ሲረባረቡ ታይተዋል፡፡ ከሙያ ጥረታቸው ባሻገር ደም ለግሰው፣ ለተቸገሩ ከአነስተኛ ገቢያቸው አዋጥተው ድሆችን ረድተው፣ በግጭትና በጦርነት ወቅትም ግንባር ድረስ እየዘመቱ ቁስለኛን አክመው፣ የተፈናቀሉት “አይዟችሁ” ብለው ወገንነታቸውንና የህሊና ሰውነታቸውን በተግባር አረጋግጠዋል፡፡

በዚያው ልክ የሞራል ዝቅጠቱና ህሊና ቢስነቱ ድንኳን የተከለባቸው ግፈኞች በሙያው ውስጥ እዚያም እዚህም መታየታቸው አልቀረም፡፡ ተደጋግሞ እንደታየው ከቀደሙት ዓመታት ጀምሮ የመንግሥት ሆስፒታሎችና አነስተኛ ተቋማት የሕክምና መሣሪያዎች እየወጡ የግል ክሊኒኮች መጠቀሚያ ተደርገዋል፣ እየተደረጉም ነው፡፡

በቅርብ እንደሰማነው በአዲስ አበባ በጉለሌና በአቃቂ ቃሊቲ ክፍላተ ከተሞች፣ እንዲሁም የካቲትና ሚንሊክ ሆስፒታልን በመሰሉ ተቋማት ለበሽተኞች (ሕመምተኞች) ከታዘዙ መድኃኒቶች ላይ እየተቀነሰ ለግል ፋርማሲዎች የመስጠት ህሊና ቢስነት በባለሙያዎች ታይቷል፡፡ በሩቅ እደምንሰማው ደግሞ ምንም እንኳን በቀውስ ውስጥ ያለ ክልል ቢሆንም ትግራይ ክልልም ከሕዝብ ተቋማት መደኃኒቶች እየወጡ ለቸርቻሪዎች እየታደሉ ነው፡፡

የግል ክሊኒኮች ሕመምተኞችን አስተኝተው ገንዘባቸውን ካሟጠጡ በኋላ፣ ሊሞቱ ሲሉ ወደ መንግሥት ሆስፒታል የሚላኩበት አሠራርም መኖሩን የሚናገሩ ትንሽ አይደሉም፡፡ በሽተኛውን ሊሞት ሲል ወደ መንግሥት ሆስፒታል የሚልኩት፣ በእነሱ የግል ክሊኒክ ውስጥ ከሞተ በሕግ ከመጠየቃቸውም በላይ የክሊኒኩ ስም ስለሚጠፋ፣ ‹‹እገሌ ክሊኒክ የገባ በሽተኛ ሞቶ እንጂ ድኖ አይወጣም›› ስለሚባል፣ የክሊኒኮቹንና የግል ሆስፒታሎችን ገጽታ ስለሚያጠይም መሆኑም ይነገራል፡፡ ይህ ድርጊትም “ደንበኛ/ተገልጋይ ስለሚያሳጣ” በዚህም የተነሳ ጥቅማቸው ሊቀር ስለሚችል መሆኑ ነው፡፡

አንዳንድ ስማቸው የገነኑ የግል ሆስፒታሎች ደግሞ በሚያሳፍር ደረጃ ሕይወቱ ያለፈ ታካሚን ሳይቀር፣ ኤሲ ክፍል በሚሉት ማንም የማይገባበት ቦታ ለቀናት በማቆየትና እየተረዳ በማስመሰል አሰንብተው የሚሰጡ ሆነዋል፡፡ በዚህ ከግልጽነትና ከተጠያቂነት ውጪ በሆነ አካሄድም አስታማሚን ተጨማሪ ከፍተኛ ገንዘብ እያስከፈሉ፣ ኢፍትሐዊ ገቢ ከመሰብሰብ ባሻገር ተገልጋይን ሲያስለቅሱ ተደጋግሞ ታይቷል፡፡

ከመንግሥት የጤና ተቋማት ከሕዝብ ሰዓትና ጉልበት እየሰረቁ ከአንዱ የግል ሕክምና ወደ ሌላው በመፈትለክ፣ በሽርፍራፊ ሰከንዶች በአሥር ሺዎች የሚቆጠሩ ብሮችን በቀን ለማጋበስ የሚጣደፉ ሙያተኞችም ቁጥራቸው ትንሽ አለመሆኑ ይነገራል፡፡

አንዳንዱ ተልከስካሽም ከሕመሙ ውጪ የማያስፈልግ የምርመራ ዓይነት በማዘዝ የደሃውን ታካሚ ኪስ ማራቆት፣ በአልጋ፣ በምግብ፣ በማቆያና በምርመራ ሌላው ቀርቶ ነፍስ ከወጣች በኋላ በአስከሬን ምርመራና ማንሻ፣ ወዘተ. ታካሚና አሳካሚ የሚያለቅስበት ጊዜ በእጅጉ በዝቶ እየታየ ነው፡፡ ይህ እንግዲህ ህሊናን ረግጦ ለመብላት ከመኖር ውጪ ምን ሊባል ይችላል?

በእውነቱ ለበሽተኛ የታዘዘ መድኃኒት እየተቀነሰ የሚሸጥበትና የግል ጥቅም የሚካበትበት አሠራር መኖሩስ ‹‹ህሊናችን የት ሄደ? ሰብዓዊነታችንስ ወዴት ጠፋ?›› አያሰኝምን? በሽተኛው የታዘዘለትን መደኃኒት በሙሉ ቢቀር መሠረታውን ማግኘት  (ምንም እንኳን የምንዛሪ እጥረቱ የፈጠረው ጫና ቀላል እንዳልሆነ ቢታወቅም)  እንዳለበት ነጋሪ ያስፈልገናልን? መንግሥትስ እንዲህ ዓይነቱን ነገር እንዳይከሰት ማድረግ ይችላልን? ከተከሰተ በኋላ ዕርምጃ ይወስዳል እንጂ፣ ይከሰታል ብሎ ሲቃዡ ማድረስ እንዴት ይቻላል ሊሆን ይችላል? ብሎ መፈተሽ ያስፈልጋል፡፡ መፍትሔው ግን የራሳችን የሰዎች፣ በተለይም የዜጎች የራሳችን ህሊና ይህ ነገር መጥፎ መሆኑን ሲያዘን የሚገኝ ነው፡፡

አንዳንዴ እንደ አገር በብዙ ውጣ ውረዶች ውስጥ ያለፍንና አሁንም በፈተና ውስጥ ያለን ብንሆንም፣ ነውርን መፀየፍ የሚችል ህሊና ለምን አጣን? መተዛዘንና መተሳሰብን ለምን ቸል አልን? ብሎ መጠየቅም ያስፈልጋል፡፡ በሌሎች እምነቶችም እንደተደነገገ ባለመዘንጋት በታላቁ መጽሐፍ ቅዱስ የሐዋርያት ሥራ 24፡17 ላይ፣ ‹‹በእግዚአብሔርና በሰው ፊት ሁልጊዜ ነውር የሌለባት ህሊና ትኖረኝ ዘንድ እተጋለሁ›› ተብሎ መጻፉንስ ስለምን ሳትነው ብሎ መጠየቅ ግድ ይላል፡፡ ኧረ ጎበዝ ራሳችንን እንመርምር?

እንደ ሰውስ መጥፎ ነገር ሁሉ በመንግሥትና በሕዝብ ብቻ ሳይሆን በፈጣሪ ፊት እንደሚያስጠይቀንስ ህሊናችን አይመሰክርልንምን? በአንደኛ ቆሮንቶስ 1፡12 ላይ ‹‹… ህሊናችን ምስክር ነው›› የተባለውን አልሰማንምን? ነው ወይስ አይሰማም?

ከሕዝብ በተሰበሰበ ግብር በደመወዝ፣ በአበልና ‹‹በቦነስ›› ስም ከአቅማችን፣ ከችሎታችንና ከአበርክቷችን  በላይ የሚከፈለን አንሶ፣ የተሰጠንን ኃላፊነት ወይም ሕዝብ ለፍቶ ያስተማረንን ሙያ እንደ ጎራዴ እየተጠቀምን የሕዝብን አንገት የምንቀነጥሰው እስከ መቼ ነው? ያስብላል፡፡ ይህን መሬት ላይ የዋለ ያደረ ሀቅ ከዜግነትና ከሙያ ኃላፊነት መጎደልና ከህሊና መቃወስ ውጪ በምን ለማሳሰብስ ይቻላል?

የዛሬ ትኩረቴ የጤናው ዘርፍ ላይ በመሆኑ ትዝብቴ እዚያ ላይ ሆነ እንጂ፣ ጉዳዩ እንደ ሰው ሁላችንንም የሚመለከት ነው፡፡ የሰው ልጅ በሚመገበው ምግብ ላይ ባዕድ ነገር ቀላቅሎ (አንዳንዴም ገዳይ ነገር) መሸጥ፣ ደሃ አገር ባለ በሌለ አቅም የገነባችውን መሠረተ ልማት አውድሞና ዘርፎ ለመክበር መመኘትስ የከፋ ውርደት መሆኑ ለምን ይዘነጋል?

ማናችንም ከበቀልንበት ማኅበራዊ ሥሪትና ከአደግንበት ማኅበረሰብ ልማድ ውጪ ባንሆንም፣ እየተፈጸመ ካለው የህሊና ማጣትና የሥነ ምግባር መጓደል ነፃ ነን ብለን ማመን ባንችልም፣ እባካችሁ ወገኖች በመልካም ህሊና እንኑር… ህሊናችን ደካማ ከሆነ እንረክሳለን… ህሊና የሰው ብቻ ሳይሆን የፈጣሪ መብራት ነው… በንፁህ ልብና በበጎ ህሊና እንሥራ… ከሞተ ሥራችንም ህሊናችንን እናፅዳ… ከማለት ውጪ አማራጭ የለም፡፡

ነባራዊው ፖለቲዊ ሁኔታችን

የአገራችን ታሪክ ቢያወዛግብም ረጅምነቱ ላይ አለመተማመን አይቻልም፡፡ የዘመናዊው አገረ መንግሥት ፖለቲካችን የቆየበት አንድ መቶ ምናምን ዓመት ግን ከውዝግብ፣ ከአለመተማመንና ከቁርሾ የወጣ አይደለም፡፡ ለዚህ አልቦ ውህደትና መተሳሰብ የነጠፈበት አካሄድ በቅኝ ገዥዎችና በውጭ ባላንጣዎች የተጠነሰሰው ሴራ ቀላል ባይሆንም፣ ኢትዮጵያዊያንም እንደ ሕዝብ የወደቅንበት በዚህም በቀላሉ ሊፋታን እንዳልቻለ አሁናዊ ሁኔታውን መመልከት ብቻ በቂ ነው፡፡

ይህን ማኅበረሰባዊ ዝንፈት ከላይ የጠቀስኩት የፈቃደ (ዶ/ር) ጽሑፍ በአስተውሎት ሰባት፣ ‹‹ታሪክና ፖለቲካ›› በሚለው ንዑስ ርዕሱ እንዲህ ሲል ነቅፎታል፡፡ ‹‹አንዱ የአኗኗር ሥርዓት ታሪክን፣ ብዙ ጊዜ ደግሞ ሽክሸክ የታሪክ ዕውቀትን፣ በየዕለት ኑሮ ውስጥ በተለይም በፖለቲካ ውስጥ መጠቅጠቅ፣ ወይም ደግሞ በልቦናችን ውስጥ ከመጠን በላይ ቦታ መስጠታችን ተባብሷል፡፡ ይህ ደግሞ ታሪኩ ራሱ በጣም አነጋጋሪ በሆነበት ሁኔታ ስለሚከናወን አደናጋሪነቱ የጎላ ሆኗል፡፡››

የራሱን የልደት ቀን በእርግጠኝነት የማያውቅ ግለሰብ፣ እርግጠኝነቱን ለማወቅም ብዙም የማይጨነቅና የማይታክት ፍጥረት ስለጎሳው የሺሕ ሺሕ ዘመን ታሪክ ከመጠን በላይ ተለጥጦ ብዙ ያወራል፡፡ ለማረጋገጥና በትክክል ለማወቅ የሚቀለውን የአባቱን፣ የእናቱንና የራሱን ምናልባትም የገዛ ልጁን ዕድሜ በተቻለ መጠን በእርግጠኝነት ለማወቅ ከመጣር ይልቅ፣ እንዲያው በጅምላ ተነግሮት አንድ ቀን ሰምቶ የያዘውን የጎሳውንና ምናልባትም የአገሩን ታሪክ ጭምር ሲያመነዥክ የሚኖር ግለሰብ ቁጥር ትንሽ አይደለም፡፡

ምሁሩ እንዳለው ኢትዮጵያውያን ዛሬን ሆነን፣ ከትናንት ተምረን፣ ነገን ለልጆቻችንና ለልጅ ልጆቻችን የተመቻቸ ማድረግ የተሳነን የእዚህ ዓይነቱ ሰንካላ አስተሳሰብ አዙሪት ባለመበጠሱ ነው፡፡ በምንገኝበት ሁኔታ ፀጉር ስንጠቃው፣ አለመተማመኑ፣ መነጋገርና መደማመጥ የራቀው ጉዟችን አልራመድ ያለበት አንዱ ምክንያት ይህው በተሳከረ ታሪክና በጥራዝ ነጠቅ፣ ብሎም ጫፍና ጫፍ በረገጠ አስተሳሰብ በተተበተበው ዕርምጃችን ምክንያት ነው ማለት ስህተት የሚኖረው አይመስለኝም፡፡ ከዚህ እዚም እንዴት እንውጣ ብሎ መነሳት የሚያስፈልገውም ለዚሁ ነው፡፡

በአጠቃላይ እንደ አገር ከክልከላና ከዕቀባ የተላቀቀ ነፃ የዜግነት መብትን የመጠቀምና ግዴታን የመወጣት ባህል የግድ ያስፈልገናል፡፡ ህሊናና የሞራል ልዕልናን በትውልድ ላይ መፍጠርና ተበላሽቶ ያለውን አካሄድም በጠንካራ ሰብዓዊነትም ማረቅ ግድ ይለናል፡፡ ከዚህ ባልተናነሰም ከተሳከረ ትርክት ወጥቶና ተቀራርቦ የመሀሉን መንገድ መምረጥና በዕውቀትና በሚዛን መመራት የትውልድ አደራችን መሆኑን መዘንጋት የለብንም፡፡

 ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እየገለጽን፣ በኢሜይል [email protected] አድራሻቸው ማግኘት ይቻላል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የዓለም አቀፍ የሰብዓዊ መብት ባለሙያዎች ኮሚሽን ሪፖርት ምን ይዟል?

ለአሜሪካ ድምፅ አማርኛ ዝግጅት የስልክ አስተያየት የሰጡ አንድ የደንበጫ...

መንግሥት በአማራ ክልል ለወደሙ የአበባ እርሻዎች ድጋፍ እንዲያደርግ ተጠየቀ

ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በአማራ ክልል የተፈጠረው ግጭትና አለመረጋጋት በቢዝነስ...

አምናና ዘንድሮ!

እነሆ መስከረም ጠብቶ በአዲስ መንፈስ ተሞልተን መንገድ ጀምረናል። ‹‹አዲስ...