Monday, March 4, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ማኅበራዊየመተሃራው የበሰቃ ሐይቅ ታሪክ ይቀየር ይሆን?

የመተሃራው የበሰቃ ሐይቅ ታሪክ ይቀየር ይሆን?

ቀን:

ዋቅቶላ ተሻለ ይባላል፡፡ የ23 ዓመት ወጣት ሲሆን፣ ተወልዶ ያደገውም በመተሃራ ከተማ አዲስ ከተማ እየተባለ በሚጠራው ስፍራ ነው፡፡ ሃቻምና በአካውንቲንግ 3.5 ውጤት በማምጣት ዲግሪውን እንደያዘ ይናገራል፡፡

ወጣቱ ዋቅቶላ በስድስት ወጣቶች ተነሳሽነት በከተማዋ በሚገኘው በሰቃ ሐይቅ ላይ በተሠራው የወጣቶች መዝናኛ ውስጥ በካሸርነት ተቀጥሮ እየሠራ ይገኛል፡፡ ‹‹በዚህች ከተማ የወጣቶች ሥራ ማጣት እንደ ሌላ ቦታ እንደሚገኙ ወጣቶች ሥራ አጥ በመባል ብቻ የሚገለጽ አይደለም፤›› በማለት እሱና ጓደኞቹ ከተመረቁ በኋላ ያለሥራ ያሳለፉትን ሁለት ዓመታት በምሬት ያስተውላል፡፡

‹‹ትልቅ ውጤት ስላለኝ ሥራ እንደማገኝ እርግጠኛ ነበርኩ፡፡ ሥራ ሳላገኝ ጊዜው በሄደ ቁጥር ግን ራሴን በጫት፣ በሲጋራና በመጠጥ ሱስ ውስጥ ተጠምጄ አገኘሁት፡፡ አንዳንድ አቻዎቼም በዝርፊያና በሌብነት ውስጥ የገቡ ነበሩ፤›› ይላል፡፡

- Advertisement -

Video from Enat Bank Youtube Channel.

እንደ ራስታዎች አድርጎ የነበረውን ፀጉሩን ተቆርጦ፣ ዛሬ ላይ የሥራ ሰው መሆኑን ደስታ በተሞላ ፊቱ ነበር የገለጸልን፡፡ በመተሃራ የሚገኘው ቀድሞ ኢትዮጵያ በጅቡቲ በኩል የምታስወጣቸውንም ሆነ የምታስገባቸውን ዕቃዎች ተሽከርካሪዎች እንዲያመላልሱ የተገነባው አውራ ጎዳና ሐይቁን ለሁለት ከፍሎታል፡፡

ወጣት ቱሉ ንጉሤ ይባላል፡፡ ከአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ በአርክቴክቸርና በከተማ ልማት ማኔጅመንት በ2008 ዓ.ም. እንደተመረቀ ይናገራል፡፡ የዛሬ ሰባት ወር አካባቢ እሱንና ስድስት ጓደኞቹን በመሰብሰብ ለከተማዋ ትልቅ የገቢ ምንጭ ሊሆን የሚችለውን ሀብት ታቅፈው ያለሥራ መተዋቸውን በመቆጨት ሐይቁን ለማልማት እንደተሰባሰቡ ይገልጻል፡፡

600 ሜትር ርዝመት ኖሮት የከተማዋ ቆሻሻ ገንዳ ይመስል የነበረውን መንገድ በማፅዳት ነበር ሥራውን የጀመሩት፡፡ ሥራው በጣም አስቸጋሪ ፈታኝና ተስፋ አስቆራጭ እንደነበር፣ በቆሻሻ ማንሳት ጊዜም ለሞት የሚያደርስ የጤና ሕመም እንደገጠማቸው ያስታውሳል፡፡

ቱሉና ጓደኞቹ ሌላው ፈተና ያጋጠማቸው በሐይቁ ላይ በሦስት ክፍል ይሠራል ብለው ያቀረቡት አሁን ባለው ዋጋ 56 ሚሊዮን ብር ሊያወጣ የሚችለው የግንባታ ንድፍ ፕሮጀክትን ለመተግበር ማሳመኑ ነበር፡፡

የማኅበሩ ሰብሳቢ ወጣት ቱሉ፣ ከዛሬ ዓመት በፊት የተዘጋው ሐይቅ ቀድሞም ለምንም የማይረባ ተብሎ መጥፎ ስም ይዞ እንደነበርና ሲዘጋ ደግሞ በሐይቁ ላይ የሚደረጉ ሌሎች ሥራዎችን ዞር ብሎ የሚያይ ጠፍቶ እንደነበር በማስታወስ፣ ባደረጉት አጭር ጥናት ተመርኩዘው ወደ ሥራ በመግባታቸው የሐይቁ ይዞታ እየተሻሻለ መምጣቱን፣ ከፍተኛ የአሳ ምርት እየሰጠ በመምጣቱም የአካባቢው የአመጋገብ ሥርዓት ራሱ እየተሻሻለ መሆኑን ገልጿል፡፡ ሥራውን ሲጀምሩ በ60 ብር ይሸጥ የነበረው አሳ፣ አሁን ላይ 150 ሊደርስ መቻሉን አክሎ በቀንም በሐይቁ ዙሪያ ከ500 በላይ ሳጥን ምርት እየተገኘ እንደሆነ ጠቁሟል፡፡

የወጣቶች መዝናኛ አገልግሎት፣ በሐይቁ ዳርቻ ወጣቶችን በማደራጀትና መጠለያ በመገንባት ከሐይቁ የሚወጣውን አሳ በተለያየ መልኩ እያዘጋጁ ወደ ሐይቁ ለሚመጡ ጎብኚዎች እያቀረቡ ሲሆን፣ በዚህም አስፈሪ ስም የነበረው ሐይቅ ወደ መዝናኛ እየተቀየረ መምጣቱን ተናግሯል፡፡

በቀጣይ የቀረውን ፕሮጀክት በቦርድ የሚተዳደር ተቋም አድርጎ ማንኛውም የከተማ ነዋሪ ባለቤት የሚሆንበትን ሁኔታ በመፍጠር ሐይቁ ያለውን ትልቅ አቅም ማሳየት የማኅበራቸው ትልቅ ራዕይ እንደሆነ ለሪፖርተር ተናግረዋል፡፡

ግንቦት 28 ቀን 2014 ዓ.ም. ከከተማው ወደ ሐይቁ መግቢያ የሚወስደው ሥፍራም በሰውና በከባድ ተሽከርካሪ ተሞልቶ አይተናል፡፡ በሐይቁ መግቢያ ላይ በስተቀኝ ትልቅ ነጭ ድንኳን ተጥሎ የነበረ ሲሆን፣ የከተማ ወጣቶችም ደስታቸውን እየገለጹ ነበር፡፡ ከሐይቁ ዳርቻ ከሁለት እስከ አራት ሰው በሚይዘው ጎጆ በመቀመጥ ከሐይቁ በሚወጣውን ቀዝቃዛ አየርና ከአሳ የተዘጋጀ ምግብ የሚመገቡ ኢትዮ ጂቡቲ የከባድ መኪና አሽከርካሪዎች ለማየት ችለናል፡፡ ሐይቁ ለአገልግሎት በመብቃቱ ያነጋገርናቸው የከተማው ነዋሪዎች ደስተኛ መሆናቸውን ነግረውናል፡፡ በዕለቱ አንድ ጣባ ጭኮ በመነሻ ዋጋ 200 ብር ለጨረታ ቀርቦ በመጨረሻም በ30ሺሕ ብር ተሸጧል፡፡

በዕለቱ የክብር እንግዳ በመሆን የሐይቁን መከፈት ያበሰረችው ወ/ሮ ቆንጂት ሁሴን ትባላለች፡፡ ተወልዳ ያደገችው መርቲ በሚባለው ስኳር ፋብሪካ ውስጥ ሲሆን፣ በሰቃ ሐይቅ ከ500 በላይ ቤቶችን ትምህርት ቤቶችን ጤና ጣቢያዎች ጠራርጎ ሲበላ እንዳየች ትናገራለች፡፡

ዓምና ሐይቁ ሞልቶ አዲስ ከተማ የሚባለውን ቦታ በማጥለቅለቅ ብዙ መፈናቀሎችን እንዳስከተለ በሐዘን እያስታወሰች፣ ዛሬ ለሰው መጠቀሚያ ሆና በማየቴ ተደስቻለሁ ስትል ለሪፖርተር በሰጠችው አስተያየት ገልጻለች፡፡

በሰቃ ሐይቅ ውኃው አሲዳማ እሚባል በመሆኑ ልብስ ብቻ ለማጠብ ያገለገል እንደነበርና ከአርባ ምንጭ የመጡ አዞዎችን የማርባቱ ሥራ ቢሳካም የአካባቢውን ከብቶች እንዲሁም ጥቂት የሰዎችን ሕይወት ቀምተው እንደነበር የአካባቢው ሰዎች ይናገራሉ፡፡

 በቅርቡ የአዋሽ ወንዝ ሞልቶ ወደ ሐይቁ በመቀላቀሉ የአሲድ መጠኑ እንደቀነሰ የአካባቢው ተወላጆች ይገልጻሉ፡፡

እንደማሳያ የሚያነሱት በውስጡ ብዛታቸው ትንሽ የሆኑ የአምባዛ፣ የቆራሳ የተባሉ አሳ ዝርያዎች ዛሬ በብዛት ተራብተው እስከ 20 ኪሎ የሚመዝኑ አሳዎችን እያጠመዱ በመሆኑ ነው፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የአዲስ አበባ ነዋሪዎች ቁጥር ሲጨምር የሚኒባስ ታክሲዎች ቁጥር እየቀነሰ መምጣቱ ሊታሰብበት ይገባል

በአዲስ አበባ ከተማ የትራንስፖርት አገልግሎት በመስጠት ከፍተኛ የሚባለውን ድርሻ...

ሃምሳ ዓመታት ያስቆጠረው አብዮትና የኢትዮጵያ ፖለቲካ ውጣ ውረድ

የኢትዮጵያ ሕዝቦች የዴሞክራሲ ለውጥ ጥያቄ የሚነሳው ከፋሺስት ኢጣሊያ ወረራ...

በአዲስ አበባ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት የተፈጸመው ሕገወጥ ተግባር ምንድነው?

የአዲስ አበባ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት የዳይሬክተሮች ቦርድ፣...

በአዲስ አበባ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት ላይ ምርመራ እንዲደረግ ውሳኔ ተላለፈ

ፕሬዚዳንቷና ዋና ጸሐፊው ተጠያቂ ሊሆኑ ይችላሉ ተብሏል ከአዲስ አበባ ንግድና...