Saturday, July 13, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

የተመረጡ ፅሑፎች

አዋቂ ሲጠፋ ታዋቂ ይገናል!

የዛሬው ጉዞ ከፒያሳ ወደ ሳሪስ ነው። ሳይጀመር የሚያልቀው፣ ሳይወጠን የሚከሽፈው፣ ሳይታለም የሚፈታው ነገር ብዛት መንገዱን የሞላው ይመስላል። በመንገዱ ላይ ብቻ ሳይሆን በአገሪቱ ከልጅ እስከ አዋቂ የተራቢነት፣ የአሽሟጣጭነትና፣

የዘርጣጭነት ማዕረግ ጭኖ በፌዝ ለበቅ ይለባለባል። ግራ ዘመሙ ቀኝ ዘመሙን ‹‹ቆይ ቀንህን ጠብቅ!›› ማለቱን እንደ ቀጠለ ነው። ቀኝ ዘመሙም እንተያያለን የሚል ይመስላል፡፡ ‹‹እነሱም ይላሉ ከተኮስን አንስትም፣ እኛም እንላለን ቃታ አናስከፍትም፣ ይህን ተባብለን የተገናኘን ለት፣ ተሰብሰብ አሞራ ትበላለህ ዱለት…›› የሚለው ዕድሜ ጠገብ አባባል ይኼኔ ትዝ ቢል አይገርምም። የኅብረተሰብ መስተጋብር በሥጋትና በተስፋ፣ በማግኘትና በማጣት ውጥን ተሰፍቶ ሳለ፣ በርዶ ከመቀዝቀዝ ወይም ሞቆ ከመጋል ለብ ማለትን የመረጠው ብዙ ነው። ሁሉም በሆዱ ቋጥሮና አፍኖ ሰምቶ እንዳልሰማ ዓይቶ እንዳላየ ይኖራል። የዛሬው ተራማጅ ነገን ብቻ ተስፋ አድርጎ ይጓዛል። መኖር ደጉ መሰንበት ደጉ ጥሩ ያስተዛዝበናል። እኛ የሰው ልጆች ዛሬም በትናንቱ ጎዳና በአዲስ ተስፋ እንጓዛለን። በመቆየት ብዙ ያላየ ማን አለ? ማንም!

‹‹ሰዎች ቶሎ ቶሎ ግቡ፣ እዚሁ በቆምንበት የህዳሴው ግድብ ግንባታ ተጠናቆ ሁሉም ተርባይኖች ኃይል ሊያመነጩ እኮ ነው…›› ይላል ወያላው። ነገረ ሥራው የመዝናናት ስሜትን ያጭራል። ‹‹ጽንፈኞች አደብ ሳይገዙ ምኑን ጨረስን ወንድሜ? ምኑን አገር ገነባን?›› ይላል ድምፁ የሴት ወይዘሮ የሚመስል አንድ ወጣት። ‹‹የጉልበተኞችን ሥራ ለራሳቸው ተውላቸው። እኛ እንደሆንን ሥራችን ዜና መስማት ነው፡፡ ዜና በሚሠሩት ጣጣና ጦስ ውስጥ መግባት አያስፈልግም…›› ትላለች አንዷ ሂጃብ የጠመጠመች ወጣት። ‹‹እሱስ ቢሆን መቼ ተሳካልን?›› አንድ ጎልማሳ ጨዋታውን ተቀላቀለ። ‹‹አይዞን በ2015 ዓ.ም. የማይሳካ ነገር የለም። ብቻ እናንተ ቶሎ ቶሎ ግቡ…›› ገብስማ ፀጉሩን ዳበስ ዳበስ እያደረገ ወያላው ይለማመጣል። ‹‹በ2015 ዓ.ም. ሁሉም ይሳካል ስትል ትንቢትህ የወቅቱን ትርዒትና ስሜት ያካትታል?›› ስትል መጨረሻ ወንበር ላይ ማንነታችንን እየረጋገጠች ገብታ የተቀመጠች የቀይ ዳማ ጠየቀችው። ‹‹ሆ…ሆ… ኧረ እኛ የምንጫወተው በገዛ ሜዳችን ነው፣ በሰው ሜዳ አታጫውችኝ። ምን ይሻላል እናንተ?›› ወያላው በሰያፍ አያት። ‹‹አይዞን ጠላት ሸረኛውን ከጠበቀልን፣ ምቀኛ፣ ትምክህተኛውን፣ ጽንፈኛውንና ተንኮለኛውን ቅስሙን ከሰበረልን የማይሳካ ነገር አይኖርም…›› አለች ሂጃብ ጠምጣሚዋ። ‹‹አፈር ልብላልሽ፣ ምናለበት እንደ አንቺ በቅንነት የሚናገር ቢበረክት? ደርሶ ቅንቅን እየሆነ በነገር በልቶ የሚጨርሰን ባሰ እንጂ…›› ወያላው ታክሲው ስለሞላለት በሩን እየዘጋ የሆዱን ዘረገፈው። ታማሚና አስታማሚ በነገር አንድ አንድ ሲባባሉ መንገዱ ተጀመረ። እንዲያ ነው!

‹‹እናንተ!›› እያሉ ትልቅ ሻሽ ያሰሩ ወይዘሮ ተጣሩ። ‹‹አቤት እማማ?›› ወያላው ሌሎቻችን ወክሎ መለሰ። ‹‹ሬዲዮኑና ጋዜጣው ያኑ በርካታ ሚሊየነሮች ተፈጠሩ ብሎ ያወራው ትዝ ካላችሁ፣ እነዚያ ሚሊየነሮች የት ደረሱ?›› ብለው ጥያቄ አቀረቡ፡፡ አዛውንቷ የከነከናቸው ነገር አለ ማለት ነው። ወያላው ብዙ እንዲያወሩ ፈልጓል። ‹‹እንዴት እማማ?›› አላቸው። ‹‹ምን እንዴት ይለኛል? ስንትና ስንት ሚሊዮን ድሆችና ተመፅዋቾች ባሉባት አገራችን ሀብታሞች ነበሩ ተብሎ አድራሻቸው ሲጠፋ አያሳስብም?›› አሉ የአፍንጫቸውን ላብ በአውራ ጣታቸው አበሱ። ‹‹አይ እማማ፣ እነሱማ የድርሻቸውን አፍሰው ዞር ሲሉ፣ በእነሱ ቦታ ሌሎች መሬት እየሸጡ እየከበሩ እኮ ናቸው። ‹ሁላችንም ወደድንም ጠላንም፣ ኢኮኖሚያችን እንዴት እንደሚዘወር ካላወቅን ዋጋ የለንም…›› እያለ ወያላው ሲናገር፣ ‹‹ታዲያስ፣ ዓለም እኮ እንደ ሸንኮራ አገዳ ነው የምትቆጥረን። ከመጠጠችንና ካጣጣመችን በኋላ ወዘናችን ሲያልቅ እንደ ቆሻሻ መሬት መጣል የተካነችበት ሳይሆን አይቀርም…›› በማለት የቀይ ዳማዋ ወጣት ምላሽ ሰጠች። ‹‹አይ ዓለም አታላይ!›› የሚል ጥቅስ ሥር አፍ ያልፈታ ሕፃን ትምባሆ እያቦነነ ሲተክዝ የሚያሳይ ምሥል ደግሞ ከረዥሙ ወያላ ትከሻ ከፍ ብሎ ጣሪያው ላይ ተለጥፎ ይታያል፡፡ ማን አታላይ ማን ተታላይ እንደሆነ እንጃ እንጂ!

እየሄድን ነው። ‹‹እስኪ ሾፌር ድምፁን ከፍ አድርገው…›› አለ ጎልማሳው ጆሮውን ወደ ስፒከሩ እየጎተተ። ከወደ ስፒከሩ የሰሞኑን መነጋገሪያ ስለሆነው የውስጥ ክራሞታችን ይተነተናል። ጎልማሳው ከሁላችንም ይበልጥ ተመስጦ ሲያዳምጥ ግንባሩን ሲቋጥርና ሲፈታ ቆይቶ ከት ብሎ ሳቀ። ሾፌሩ የሬዲዮኑን ድምፅ ወዲያው ቀንሶ የሚፈልገውን ሙዚቃ ማጫወት ጀመረ። ጎልማሳው መሳቁን አላቋረጠም። ‹‹ንገረና እስቲ ምን ተገኘ?›› አሉት አዛውንቷ። ‹‹ኧረ ግድ የለም ባልናገረው ይሻለኛል። ከመናገር የተረፈን ወሬኛነት እንጂ መደማመጥና እየተሻሻለ የሚሄድ የዴሞክራሲ ባህል አይደለም…›› አላቸው። ‹‹በፈጠረህ አሁን ዴሞክራሲን ማን ጠራው እዚህ?›› አሉት። ‹‹የሚያስቀኝ እኮ እሱ ነው፣ መስማት የምንፈልገው ሌላ የሚሆነውና የሚነገረን ሌላ። በዚህ በሠለጠነ ዘመን ዓለም ወደ ዘላቂ ሰላም ትጓዛለች ሲባል ወደ ዘላቂ ብጥብጥና የጦር መድረክነት ትለወጣለች። በዚህ የሰው ልጅ አስተሳሰብና አመለካከት ደረጃ መጥቋል በሚባልበት ወቅት፣ ከሌላው ጊዜ ብሶ የሰው ልጆች መብት የመጠቀሚያና የማትረፊያ ሸቀጥ መሆኑ እያሳዘነኝ ነው…›› አላቸው። አዛውንቷ በሬዲዮ እኩል የሰማነውን የዜና ትንታኔ እያስታወሱ ጎልማሳውን አተኩረው ያዩታል። እሱ ራሱ የተቃረነች ዓለም በሚላት ዓለም እየመረጠ የሚፈልገውን ብቻ የሚያዳምጥ መሆኑን ሳያስተውሉ አልቀሩም። አቤት ግራ የተጋባው ሰውና ነገር ብዛቱ!

ጉዟችን ቀጥሏል። ከፊት ለፊታችን መኪኖች ተጋጭተው መንገዱ ተዘጋግቷል። የቀይ ዳማዋ ወጣት፣ ‹‹መጥኔ፣ በዚህ ዝናብ ስንት ሰዓት ተሠልፈን ታክሲ እንይዛለን። በመንገድ መዘጋጋትና መጨናነቅ ደግሞ ጉዟችን ይስተጓጐላል። እንዲህ ተሰቃይተን ቤታችን ስንገባ ደግሞ መብራት ይጠፋል። ኧረ መቼ ይሆን ዕፎይ የምንለው?›› በማለት እየተመናጨቀች ወደ ታክሲያችን ጣሪያ ቀና አለች። ‹‹እንግዲህ አንዳንዶች የህዳሴው ግድብ ተጠናቆ ተርባይኖቹ በሙሉ ሥራ ሲጀምሩ ብለዋል…›› አለ ወያላው። ጋቢና ከተቀመጡ ወጣቶች ደግሞ አንዷ ቀበል አድርጋ፣ ‹‹አንዳንዶች መካከለኛ ገቢ ካላቸው አገሮች ተርታ ስንሠለፍ ነው ይላሉ…›› አለች። አጠገቧ የተሰየመው ጎረምሳ ቀበል አድርጎ፣ ‹‹አንዳንዶች ደግሞ የብር ዋጋ ከዶላር ጋር እኩል ሲሆን ነው ይላሉ…›› ሲል አዛውንቷ፣ ‹‹ምን የሚሆነው?›› አሉ ተገርመው። ‹‹ደልቶን የምንኖረው ነዋ!›› ስትል የቀይ ዳማዋ፣ ‹‹አሁን ምን እያደረግን ነው?›› አሉዋት። ልጅት ከት ብላ ትስቃለች። መልሱን ለሌሎቹ ተሳፋሪዎች ሹክ ያለች ይመስል ‹‹እያኗኗርን!›› ሲሉ ሁሉም ተሳፋሪዎች ተራ በተራ መልሱን አቀበሏቸው። የተጋጩትን አውቶሞቢሎች ታኮ ለማለፍ ግማሽ ሰዓት ያህል ፈጀ። በአንዱ ግጭት የአንዱ መዘግየት፣ በአንዱ ጥፋት የሌላው ተቀጪ መሆን እንቆቅልሽ የሆነባት ዓለም ገና ብዙ ሳታባብለን አትቀርም። ዕድሜ ለመንገድ!

ወደ መዳረሻችን ተቃርበናል። ‹‹አይ ዘንድሮ!›› አሉ አዛውንቷ። ‹‹መቼ ጀመረ ገና?›› አለ ዝም ብሎ ተጎልቶ የዋለ ወጣት። ‹‹ወይድ፣ እንኳን ዘመንን የዝንብ ጠንጋራም እናውቃለን…›› አሉትና በቁጣ ዓይናቸው ለበለቡት። ‹‹ማለት? ገና ምኑንም ሳንይዝ?›› አለ ጎልማሳው ወያላ አዛውንቷ ተመችተውት። ‹‹ሳንጠራ አቤት ማለት የማይሰለቸን…›› አሉ እየቆዩ ሲሄዱ ሁሉም ነገር እንደ ሬት የመረራቸው የሚመስሉት አዛውንት። ‹‹በልዩነቱ ተቻችሎና ተከባበሮ አብሮ የኖረ ሕዝብ መስሎኝ ዛሬም ድረስ በጉጉትና በናፍቆት አብሮ የሚኖረው? አይደለም እንዴ?›› ወያላው ሊተዋቸው አልፈቀደም። ‹‹አንተ ተወኝ ብዬሃለው ዛሬ፡፡፡ የእውነተኛ አንድነት ውጤት እንደ ችቦ ነዶ አመድ የሚሆን ጊዜያዊ ነገር ነው ያለህ ማን ነው? እውነተኛዎቹማ አሁን የሉም። ከእነሱ በኋላ ምን ሆንን? ትልቁ አንድነት ካልክስ እንደ ወረት የማያልቅ፣ ብርሃኑ ሺሕ ትውልድ ድረስ የሚዘልቅና ፋይዳ ባለው ልዩነት ውስጥ ቋሚ የሆነ አንድነት ነው። አውርደኝ አሁን አታስለፍልፈኝ…›› ብለው ንግግራቸውን ቋጩ። ወያላው ‹‹መጨረሻ›› ብሎ በሩን ከፈተው። ወርደን በየፊናችን ስንጓዝ፣ ‹‹ወደኋላ እየሄድን የችግራችንን ምክንያት ካላየነው እኮ በአቋራጭ እያሳበሩ መጓዝ የትም አያደርሰንም…›› ብለው ሲጨምሩልን ልካችንን እንደ ነገሩን ገባን፡፡ የአዋቂ ያለህ የሚያሰኝ ጊዜ ላይ መሆናችን ትዝ ያለንም ነበርን፡፡ በየሬዲዮኑ፣ በየቴሌቪዥኑ፣ በየማኅበራዊ ሚዲያው ራሳቸውን በራሳቸው ታዋቂ ያደረጉ በበዙበት ዘመን አዋቂዎች ለምን ጠፋ አይባልም? ይህ ያለንበት ጊዜስ አዋቂ ጠፍቶ ታዋቂ በዛ አያሰኝም? መልካም ጉዞ!          

Latest Posts

- Advertisement -

ወቅታዊ ፅሑፎች

ትኩስ ዜናዎች ለማግኘት