የአገሪቱ ባንኮች ዋነኛ ተግባራቸው የሆነውን የፋይናንስ ንግድ ሥራ ረስተው በጎጥ፣ በዘርና በሃይማኖት ማሰብ ከጀመሩ የንግድ ሥራ እየሠሩ እንዳልሆነና ከዚህ ዓይነት ሐሳብ እንዲወጡ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ገዥ ይናገር ደሴ (ዶ/ር) አሳሰቡ፡፡
ይናገር (ዶ/ር) ይህንን የተናገሩት፣ የወጋገን ባንክ አክሲዮን ማኅበር 25ኛ ዓመት ክብረ በዓል ላይ ተገኝተው ለሁሉም ባንኮች ብለው ባስተላለፉት መልዕክት ነው፡፡ ‹‹ባንኮች ቢዝነሳቸውን እየረሱ በጎጥ፣ በዘር፣ በብሔርና በሃይማኖት ማሰብ ከጀመሩ የአገልግሎት አሰጣጣቸውም በዚህ ከተቃኘ ባንኮች አይደሉም፣ ቢዝነስም እየሠሩ አይደለም፤›› ያሉት ገዥው ማንኛውም የኢትዮጵያዊ ባንክ ዘር፣ ብሔር ሃይማኖት ሳይለይ ለሁሉም ማገልገል እንዳለበት አመልክተዋል፡፡
ይህንን መርህ በመጣስ በብድር አሰጣጥና በውጭ ምንዛሪ አመዳደብ አድልዎ የሚያደርግ የባንክ አመራር ካለ ሊጠየቅ እንደሚገባውም በዚሁ መልዕክታቸው ላይ አሳስበዋል፡፡ ‹‹ባንኮች አገልግሎት አሰጣጣቸው ገለልተኛ መሆን አለበት፤›› ያሉት ገዥው መሥፈርቱን አሟልቶ ለሚመጣ ማንኛውም ሰው አገልግሎት መስጠት እንደሚኖርበትም ሳያሳስቡ አላለፉም፡፡ የአገሪቱ የባንክ ኢንዱስትሪ ገና ያልተስፋፋ መሆኑን በማስታወስም አሁን ካሉት ባንኮች በተጨማሪ ሌሎች ባንኮች እንዲቋቋሙ ብሔራዊ ባንክ እንደሚበረታታ ነገር ግን በየመንደርና በሰፈር ስም ባንክ እንዲቋቋም ፍላጎት የሌላቸው መሆኑን አስታውቀዋል፡፡
በተለይ ባንክ ሆኖ ተቋቁሞ ለአንድ ብሔር አገልግሎት የሚሰጥ ከሆነ አደጋ ያለው መሆኑንም በመጠቆም ባንኮች እንዲህ ካለው አዙሪት እንዲወጡም አስጠንቅቀዋል፡፡ የአንድ አካባቢን ሰው ለማገልገል የሚሠራ ባንክ ለጊዜው ይመስላል እንጂ ዘለቄታ እንደማይኖረው፣ እንደዚያ ያለ አሠራር የሚከተል ባንክም አደጋው ለእርሱም እንደሚተርፍ ገልጸዋል፡፡ ባንኮች ለማንኛውም ኢትዮጵያዊ በራቸውን ክፍት አድርገው የአገልግሎት አሰጣጥን ብቻ መሠረት አድርገው እንዲንቀሳቀሱ መክረዋል፡፡
አያይዘውም ኢትዮጵያውያን ተሰብስበው ሀብታቸውን አቀናጅተው፣ ትልቅ ሀብት ፈጥረው፣ ትልቅ ባንክ ሆነው ከሌሎች የአፍሪካ አገሮች ባንኮች ጋር እንዲወዳደሩ ፍላጎታቸው እንደሆነ ተናግረዋል። የብሔራዊ ባንክ ገዥው አክለው እንደገለጹት፣ በቅርብ ጊዜ የሌሎች አገሮች ባንኮች ወደ ኢትዮጵያ ገብተው ቅርንጫፍ ከፍተው መሥራታቸው የማይቀር ነው። በመሆኑም በዘርና በብሔር የመሰባበሰብ አመለካከት ተይዞ መወዳደር ከባድ እንደሚሆን አመላክተዋል።
በፖሊሲ ተፈቅዶ የአገር ውስጥ ባንኮች ሌላ አገር ሔደው የሚሠሩ ከሆነ እዚያ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያንን መርጠው እንዴት ማገልገል እንዳለባቸው ሊያስቡ እንደሚችሉ በአገር ውስጥ ግን የባንኮች አግልግሎት አሰጣጥ አንዱን አቅርቦ ሌላውን ማራቅ ሊሆን የሚችልበት ምክንያት መኖር እንደሌለበት ተናግረዋል። ብሔርና ሃይማኖትን መሠረት ያደረጉ አሠራሮች አደገኛ ስለመሆናቸውም አመላክተዋል፡፡
ማንኛውም የንግድ ሥራ በውድድርና ደንበኛን በአገልግሎት በመሳብ፣ ፍትሐዊና ተጠያቂነት ያለበትን ሥራ በመሥራት ላይ መመሥረት እንዳለበት፣ የባንኮች የቢዝነስ አካሄድም በዚህ መሠረት የተቃኘ መሆን እንደሚገባው አሳስበዋል፡፡
ለሁሉም ባንኮች ብለው ሌላው ያስተላለፉት መልዕክት ደግሞ በባንኮች አካባቢ የሚፈጸሙ ወንጀሎችን የተመለከተ ነው፡፡ የትም ቦታ ወንጀል እንዳለ ሁሉ በባንኮችም አካባቢ ወንጀለኞች የሚያንዣብቡ መሆኑን በመግለጽ፣ በቅርቡ በፍት ሚኒስቴር የቀረበውን ጥናት ዋቢ አድርገዋል፡፡ በዚህ ጥናት መሠረት ከሞላ ጎደል በባንኮች የማጭበርበር ወንጀሎች ተፈጽመዋል፡፡ በዚህም ምክንያት ከባንኮች የጠፋ ገንዘብ መኖሩን አረጋግጠዋል፡፡ ይህንን ወንጀል ከውጭ ያሉ አጭበርባሪዎች ብቻቸውን የሠሩት እንዳልሆነና የውስጥ የባንክ ሠራተኞች ጭምር በተባባሪነት እንደተሳተፉበትም ተናግረዋል፡፡
ስለዚህ ሁሉም ባንኮች የባንክ ሠራተኞች ጥሩ ሥነ ምግባር ኖሯቸው ከውጭ ወንጀለኛች ጋር በማናቸውም መንገድ እንዳይተባበሩ፣ ተባብረው የተገኙም ከሆነ ከፍተኛ ቅጣት የሚደርስባቸው ስለመሆኑ አስጠንቅቀዋል፡፡ በዚህ ወንጀል ዙሪያ ከባንክ የሥራ መሪዎች ጋር መምከራቸውን በማስታወስ ይህንን ወንጀል ለመከላከል የየባንኮቹ የቦርድ አባላት የባንኮቻቸውን ጤናማነት የሚመለከት በየጊዜው መጠየቅ፣ ባንኮች በሰላም ውለው በሰላም ማደራቸውን የመከታተል ሥራ መሥራት እንደሚኖርባቸው አሳስበዋል፡፡
ይናገር ደሴ (ዶ/ር) በዚህ ክብረ በዓል ላይ ባንኮች ከዚህ በኋላ ሊተገብሩት ይገባል ብለው ያሳሰቡት ሌላው ጉዳይ ደግሞ ከብድር አሰጣጥ ጋር ያለውን ክፍተት የተመለከተ ነው፡፡
ባንኮች እጅግ ጥቂት ለሆኑ ተበዳሪዎች ብቻ ብድር እየሰጡ ሊቀጥሉ እንደማይችሉ በሚጠቁመው ንግግራቸው በአሁኑ ወቅት በኢትዮጵያ ውስጥ የባንክ ተበዳሪዎች ብዛት የሁሉም ባንኮች ተደምሮ 300 ሺሕ የማይበልጥ መሆኑን በአስረጂነት አቅርበዋል፡፡
110 ሚሊዮን ሕዝብ ባለበት አገር 300 ሺሕ ሰዎች ብቻ የባንኮች ብድር ተጠቃሚ ማድረግ በማንኛውም መመዘኛ ፍትሐዊ ያለመሆኑንና ትክክል እንዳልሆነ ሊሰመርበት እንደሚገባ አውስተዋል፡፡
ስለሆነም ባንኮች ወደ ገጠር በመሄድ አርሶ አደሩንና አርብቶ አደሩን እንዲሁም ወደ ገጠር ከተሞች በመውረድ ብድር የሚቀርብበትን ዕድል ስትራቴጂ በመንደፍ መንቀሳቀስ እንደሚኖርባቸው አሳስበዋል፡፡
እንዲህ ያለውን ስትራቴጂ መከተል ለባንኩም ሆነ ለዜጎች ይጠቅማል የሚል እምነት ያላቸው ገዥው ይህንን ማድረግ እንዲቻል በቅርቡ የተንቀሳቃሽ ንብረትና ዋስትና በማስያዝ ብድር ማግኘት እንዲፈቀድ በብሔራዊ ባንክ የወጣውን መመርያ በአግባቡ መተግበር ይኖርባቸዋል ብለዋል፡፡ በዚህ መመርያ ባንኮች ወይም ማይክሮ ፋይናንስ ተቋማት የአርሶ አደሮችን የመሬት መጠቀሚያ ደብተር በመያዝ ብድር መስጠት የሚችሉ መሆኑን፣ እንዲሁም ደን ያላቸው ደኑን አስይዘው ግመሎችና ሌሎች እንስሳት ያላቸውም በተመሳሳይ እነዚህን ተንቀሳቃሽ ንብረቶችን አስይዘው ብድር ሊሰጣቸው እንደሚገባ በዚሁ ንግግራቸው ጠቅሰዋል፡፡
ከቅርንጫፎች ማስፋፋትና ቴክኖሎጂን ከመጠቀም አኳያም ባንኮች ከዚህ በኋላ መከተል አለባቸው ያሉትን ምክር ሐሳብ ይናገር (ዶ/ር) አቅርበዋል፡፡ ይህንንም ‹‹ከዚህ በኋላ ቅርንጫፍ መክፈት የምትፈልጉ ካዋጣችሁ ክፈቱ›› በማለት ነበር የጀመሩት፡፡ እንደ እርሳቸው እምነት ግን ባንኮች በይበልጥ በቴክኖሎጂ ተደግፈው ቢሠሩ አዋጭ ይሆናሉ፡፡ 60-70 ሚሊዮን ሕዝብ ሞባይል ስላለው በዚህ መጠቀም ያስፈልጋል፡፡ ተደራሽነትን በመላ አገሪቱ ለማዳረስ ቴክኖሎጂ ላይ ርብርብ መደረግ እንደሚኖርበት ጠቁመው ይህንን ማድረጋቸው የውጭ ባንኮች ጋር ለመወዳደር ጭምር ቴክኖሎጂ ላይ መሥራት ግድ በመሆኑ ነው፡፡
‹‹የውጭ ባንኮች እንዲገቡ የቅድመ ዝግጅት ሥራዎች እየተሠሩ ናቸው፤›› ያሉት ይናገር (ዶ/ር) ከሚመጡት ባንኮች ጋር የሚደረገው ውድድር በቴክኖሎጂና በካፒታል አቅም ስለሆነ ከሚመጡት ባንኮች ጋር ሁሉን አቀፍ ቅድመ ዝግጅት እያደረጉ እንዲቆዩም ብለዋል፡፡
‹‹የእኛ አገር ባንኮች ቁጥራቸው በርከት አለ እንጂ አቅማቸው በጣም ትንሽ ነው፡፡ የሁሉም ባንኮች ካፒታልና ካፒታል ተደምሮ የሌላ አገር አንድ ትልቅ ባንክ ካፒታል እንኳን አያክልም፤›› በማለት በዚህ ቁመና ላይ ተኩኖ ከሌሎች አገር ባንኮች ጋር መወዳደር እንደማይቻል ለባንኮቹ ገልጸዋል፡፡
ይናገር ደሴ (ዶ/ር) በወጋገን የ25 ዓመት ክብረ በዓል ላይ ተገኝተው ባደረጉት ንግግራቸው ወቅታዊን ኢኮኖሚያዊ ጉዳይ ከኢትዮጵያ ፋይናንስ ተቋማት ውጤታማነት ጋር በማያያዝ አብራርተው ነበር፡፡ በዓለም ላይ የተጠረው የኢኮኖሚ ሁኔታ በመጀመርያ የኮቪድ ወረርሽኝ የዓለም ኢኮኖሚን እንዳናጋና በበርካታ አገሮች ሠራተኞች ቤታቸው መዋል መጀመራቸው፣ የምርት የማምረት ሒደት ማስተጓጎሉን ገልጸው ይህም የዓለም የኢኮኖሚ ዕድገት በኮቪድ ምክንያት በእጅጉ ሊቀንስ ችሏል ብለዋል፡፡
ከዚህ ለመውጣት ርብርብ በሚደረግበት ወቅት ደግሞ የሩሲያና የዩክሬን ጦርነት ማንም ከገመተተው በላይ የዓለም ኢኮኖሚ በእጅጉ እንደፈተነው፣ እንዲሁም በዚህ ጦርነት ምክንያት ያልጨመረ ዋና ዋና የሚባል ምርት እንደሌለም ጠቅሰዋል፡፡ ይህ ጭማሪም ከሁለት እጥፍ በላይ በመሆኑ ብዙ ነገሮች አስተጓጉሏል፡፡
በቅርብ ጊዜ የዓለም ባንክና አይኤምኤፍ የአገሮችን ዕድገት በተመለከተ ባወጣው ሪፖርት በዚህ ጦርነት ምክንያት በግማሽ መቀነሱን የጠቀሱት ገዥው እነዚህ ሁለት አገሮች የሚያቀርቡት መሠረታዊ ምርቶች በዚህን ያህል ደረጃ የዓለም ኢኮኖሚን የሚቀይር መሆኑን አስቀድሞ የገመተ አልነበረም፡፡ ጦርነቱ የኢትዮጵያንም ኢኮኖሚ በእጅጉ እየፈተነ መሆኑን የገለጹት ገዥው እንደ ምሳሌ የጠቀሱትም መሠረታዊ የሚባሉ ከውጭ የሚመጡ ምርቶች ከእጥፍ በላይ ዋጋ እየተከፈለባቸው እየገቡ መሆኑን ነው፡፡
እንዲህ ያለውን ችግር አገሪቱ እየተቋቋመች ቢሆንም በአገር ውስጥ የተፈጠሩ ግጭቶችም ኢኮኖሚው ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ ነበራቸው፡፡ ከውጭም ሆነ ከአገር ውስጥ ያሉ ችግሮችን ተቋቁሞ ኢኮኖሚው ፌሊለንት ሆኖ እያለፈ ነው ብለዋል፡፡
ኢኮኖሚው እንዲህ ባለ ሁኔታ ቢገለጽም አሁንም የፋይናንስ ተቋማት ውጤታማ አፈጻጸም በማሳየት ግንባር ቀደም መሆናቸውን ተናግርዋል፡፡ ባንኮች በዚህ አስቸጋሪም ወቅት ቢሆን የተቀማጭ ገንዘብ መጠናቸው መጨመሩን፣ የብድር መሰብሰብ አቅማቸው በምንፈልገው መጠን ያህልም ባይሆን ስለማደጉና በሌሎች የባንክ ጤናማነት መለኪያ የኢትዮጵያ ባንኮች ጤናማ ሆነው ነው እንደቀጠሉም ጠቅሰዋል፡፡ ለዚህ ውጤት መገኘት ደግሞ የባንክ ደንበኞችና የባንክ ሠራተኞች አመራሮች ትልቅ ድርሻ ስላላቸው ወጋገን ባንክ ጨምሮ ሁሉንም ባንኮች አመሠግናለሁ ብለዋል፡፡
ወጋገን ባንክ ከዚህ አኳያ ከታየ በተለያየ ሁኔታ ውስጥ ያለፈ ባንክ ቢሆንም፣ ባንክ ሆኖ እየቀጠለ ነው ብለዋል፡፡ ወጋገን ባንክ 25ኛ ዓመት ክብረ በዓሉን በማስመልከት የባንኩ ዳይሬክተሮች ቦርድ ሊቀመንበር አቶ አብዱሽ ሁሴን በበኩላቸው፣ ‹‹ወጋገን ባንክ የአገሪቱን ባንኮች የሚቆጣጠረው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ የሚያወጣቸውን ሕጎችና አጠቃላይ የአገሪቱን ሕጎች በጥብቅ ዲሲፒሊን ተከትሎ የሚሠራ ባንክ መሆኑን ተናግረዋል፡፡ ግን በ2012 ዓ.ም. በሰሜኑ የአገሪቱ ክፍል ከተከሰተው ግጭት ጋር ተያይዞ በተሳሳተ መረጃ ባንኩ ላይ ተፈጥሮ የነበረውን ሥጋት ቀላል እንዳልነበርም አክለዋል፡፡
‹‹ከግጭቱ ጋር ተያይዞ በተሳሳተ መረጃ ላይ ተመርዞ በባንካችን ላይ በኤሌክትሮኒክስና በማኅበራዊ ሚዲያ በተከፈተው የስም ማጥፋት ዜጎች ምክንያት በደንበኞቻችን ላይ ከፍተኛ ሥጋት ተፈጥሮ የነበረ ሲሆን የባንኩ መደበኛ የሥራ እንቅስቃሴም ለተወሰነ ጊዜ ተስተካክሎ ትልቅ የህልውና አደጋ ተደግኖበት ነበር፤›› ያሉት የቦርድ ሊቀመንበሩ ይህንን በርብርብ ለመቀልበስ መቻሉን ጠቅሰዋል፡፡
የባንኩ ሠራተኞች በግልና በቡድን እውነታውን ለደንበኞች በማሳወቅ ባደረጉት ጥረት እንዲሁም የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ባደረገላቸው ሁለንተናዊ ድጋፍ የጋጠመውን ሥጋት በመቀነስ አሁን ላይ ባንኩ በሁሉም መለኪያዎች የተሻለ ሁኔታ ላይ እንደሚገኝ አቶ አብዱሽ አመልክተዋል፡፡
‹‹ባንኩ በርካታ ኢትዮጵያውያን ባለሀብቶች በአራቱም ማዕዘናት በመንግሥት ላይ እምነት ጥለው ገንዘባቸውን ያፈሰሱበት ባንክ ነው፤›› ያሉት የቦርድ ሊቀመንበሩ በአንድ የፋይናንስ ተቋም ላይ የስም ማጥፋት ሲከሰት ጉዳቱ በተቋሙ ላይ ብቻ የሚቀር ባለመሆኑ ጉዳዩ ሊታሰብበት የሚገባ እንደሆነም ገልጸዋል፡፡
በወጋገን ላይ እንደተፈጸመው ዓይነት የስም ማጥፋት ዘመቻ ባለሀብቶች በግል ባንኮች ላይ ያላቸውን እምነት በመሸርሸር ገና በሩብ ክፍለ ዘመን በላይ ያልዘለቀውን የግል ባንክ ኢንዱስትሪ ዕድገት ወደ ኋላ እንደሚጎትት መታወቅ አለበትም በማለት አክለዋል፡፡
ችግሩ በአገሪቱ ኢኮኖሚና ማኅበራዊ ጉዳይ ላይ የራሱን አሉታዊ ተፅዕኖ የሚያሳርፍ በመሆኑ የመንግሥት አካላትም ልዩ ትኩረትና ድጋፍ በማድረግ አስፈላጊውን ዕርምጃ በወቅቱ ሊወሰድ እንደሚገባም አሳስበዋል፡፡
ወጋገን የአምስት ዓመት ስትራቴጂ ዕቅድ እንዳለው የገለጹት ይናገራ ደሴ (ዶ/ር)፣ ደግሞ ባንኩ በተለያየ ሁኔታ ውስጥ ያለፈ በመሆኑ በዚህ ሁኔታ ሌሎች ባንኮች ሊማሩ ይገባል ብለዋል፡፡ ምንም ይሁን ምን እውነትም ይሁን ውሸት ባንኮች ላይ የሚፈጸም ተግባር ለሁሉም ማኅበረሰብ ዘንድ መልካም እንዲሆን አሠራርና አገልግሎቶች እንደሚወስነው አመልክተዋል፡፡
ወጋገን ባንክ ባጋጠመው ማናቸውም ሁኔታ ላይ ብሔራዊ ባንክ ሲደግፈው እንደነበርና ወደፊትም የሚደግፈው መሆኑን የገለጹት ይናገር (ዶ/ር) ‹‹የምንደግፈው ግን ወደን አይደለም፤›› ብለዋል፡፡ ይህንንም ሲያብራሩ ‹‹ባንኩ ውስጥ ያለው ገንዘብና ሀብት የሕዝብ ሀብት ነው፡፡ ባለአክሲዮኖች እዚህ ውስጥ ያላችሁ ድርሻ በጣም ትንሽ ነው፡፡ ብሔራዊ ባንክ የሕዝብን ሀብት የመጠበቅ ኃላፊነት ስላለበት ነው፤›› ብለዋል፡፡ እዚያ ውስጥ ችግር ያለባቸው የማኔጅመንትና የቦርድ አባላት ሊኖሩ ይችላሉ፡፡
እንደየጥፋታቸው የሚገባቸውን ቅጣት ሊወስዱ ወይም ሊቀጡ ይገባል፡፡ የሕዝብን ሀብት ግን በምንም መመዘኛ አደጋ ላይ የሚወድቅበት ሁኔታ ካለ ሁልጊዜ የብሔራዊ ባንክ ኃላፊነት መከላከል በመሆኑ ይህንኑ እያደረገ መሆኑን አስታውቀዋል፡፡ በዚሁ መነሻነት ወጋገን ባንክ ባጋጠመው አንዳንድ ሁኔታ ብሔራዊ ባንክ ከጎኑ ሆኖ ሲደግፈው መቆየቱን፣ ወደ ፊትም የሚደግፈው መሆኑን ገልጸው ባንኩ የአምስት ዓመት ስትራቴጂካል ዕቅዱ የተሳካ እንዲሆንና ባንኩ አሁን ካለበት ሁኔታ ወጥቶ ወደ ተሻለ ሁኔታ እንዲሸጋገር የሁሉንም ርብርብ ይጠይቃል ብለዋል፡፡
ወጋገን ባንክ 25ኛ ዓመቱን በተለያዩ መንገዶች ለወራት ሲያከበር ሲሆን በበዓሉ መዝጊያ ፕሮግራም ላይ በተለያዩ መንገዶች ባንኩን ለደገፉ አካላት ዕውቅና ሰጥቷል፡፡
በተለይ የባንኩ የመጀመርያ ፕሬዚዳንት ለሆኑት ብሩክታዊት ዳዊት (በወቅቱም ብቸኛዋ ሴት ፕሬዚዳንት ነበሩ) ዕውቅና ሰጥቷል፡፡
የወጋገን ባንክ ባለአክሲዮኖች 5,600 የደረሰ ሲሆን የተከፈለ ካፒታሉ 3.4 ቢሊዮን ብር፣ ጠቅላላ ካፒታሉ ደግሞ 5.6 ቢሊዮን ብር ነው፡፡ ጠቅላላ የሀብት መጠኑም ከ41 ቢሊዮን ብር በላይ ደርሷል፡፡ ከ5,000 በላይ ሠራተኞች አሉት፡፡