Saturday, May 18, 2024

የጠቅላይ ሚኒስትሩ የፓርላማ ማብራሪያ

- Advertisement -spot_img

በብዛት የተነበቡ

የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ትናንት ማክሰኞ ሰኔ 7 ቀን 2014 ዓ.ም. በ13ኛው መደበኛ ስብሰባ የጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድን (ዶ/ር) ማብራሪያ ሲያደምጥ ውሏል፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከፓርላማ አባላት ለተነሱላቸው ጥያቄዎች ሰፊ ማብራሪያ የሰጡበት የምክር ቤት ውሎ ብዙ ጉዳዮች የተነሱበት ነበር፡፡ ከተረኝነት ፖለቲካ እስከ የሕግ ማስከበሩ ዕርምጃ፣ ከአገራዊ ምክክር እስከ ሚዲያ አፈና፣ ከድርድር እስከ የፖለቲካ ሽግግር በርካታ አከራካሪ የሚባሉ አጀንዳዎች ተነስተዋል፡፡ ለረዥም ሰዓታት የፓርላማ አባላቱን ጥያቄ ሲያደምጡ የቆዩት ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ (ዶ/ር)፣ ፓርቲያቸው ብልፅግና ይከተለዋል ካሉት መሠረታዊ መርህ ጀምረው ለተነሱ ጥያቄዎች ሰፊ ገለጻን ሲያቀርቡ ውለዋል፡፡ ለጠቅላይ ሚኒስትሩ ጠንከር ያሉ ጥያቄዎች የቀረቡ ሲሆን፣ እሳቸውም ለጥያቄዎቹ የጠያቂዎቹን ማንነት እየጠቀሱ ጭምር ነበር ረዥም ማብራሪያ ሲሰጡ የነበሩት፡፡

የመጀመሪያው ጠቅላይ ሚኒስትሩ ያተኮሩበት ነጥብ ፓርቲያቸው ብልፅግና ይመራበታል ያሉት መሠረታዊ ፅንሰ ሐሳብ ሲሆን፣ በእንግሊዝኛው “ITS DAM” (Idea, Time, Space, Duty and Moral) ብለው ያስቀመጡት ነጥብ ቀዳሚው ነበር፡፡ ብልፅግና ሐሳብ ያለው ፓርቲ መሆኑን የተናገሩት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ ‹‹ሐሳብ ሰውን ይገነባል፣ ሰው ተቋምን፣ እንዲሁም ተቋማት አገርን ይገነባሉ፤›› በማለት የሁሉም መሠረት ሐሳብ መሆኑን አስምረውበታል፡፡ ሰው የጊዜና የቦታ ቁራኛ መሆኑን ከዚሁ ጋር አያይዘው ጠቅሰው፣ ጊዜን ሳይጠቀሙ ማባከን ለፀፀት እንደሚዳርግ አስቦ መሥራት የፓርቲያቸው መሠረት መሆኑን ገልጸዋል፡፡ ቦታን በተመለከተ ደግሞ አካባቢውንና ጓሮውን የማያፀዳና የማያለማ አገር ሊለውጥ እንደማይችል በማሰብ የመንቀሳቀስን አስፈላጊነት አስረድተዋል፡፡

‹‹ምድራችን ደግ ናት፣ ለሚሠራ ክብርን ነፍጋ እንደማታውቅ ሁሉ ለሚያወራና ችግርን ለሚበላ ደግሞ መቃብርን ነፍጋ አታውቅም፤›› ሲሉ ፍልስፍናዊ ሐሳብ አንስተዋል፡፡ ፓርቲያቸው ብልፅግና ግዴታውንና ኃላፊነቱን ጠንቅቆ አውቆ የሚንቀሳቀስ ብቻ ሳይሆን፣ በሞራል (ግብረ ገብነት) ሕዝብ የሚያገለግል እንዲሆን ብዙ መሠራቱን ነገር ግን ብዙ ጥረቶች በቂ ውጤት አለማምጣታቸውን በይፋ ተናግረዋል፡፡ ‹‹የሚሰርቅና ሌባ አመራር የምናፈራ ከሆነ ሁሉም ዕቅድና ልፋት ከንቱ ነው የሚሆነው፤›› ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ በዚህ ረገድ ግን ከግለሰብና ከቤተሰብ ጀምሮ እስከ የሃይማኖት ተቋማት ድረስ ብዙ ሥራ አገሪቱን ይጠብቃታል ብለዋል፡፡

‹‹የሃይማኖት ተቋሞቻችን ከሊዝ ነፃ የሆኑት፣ ግብር የማይከፍሉትም ሆነ ኦዲት የማይደረጉት በአገር ደረጃ ያሉብንን የሞራልና የግብረ ገብ ችግሮች ቢያንስ ይሸፍናሉ ተብሎ ቢሆንም፣ ነገር ግን አሁን ያሉ ተቋማትም ሆነ የእምነት አባቶች ይህን በማድረግ እየደገፉን አይደሉም፤›› ብለዋል፡፡ የሞራል ምንጭ የሆኑ የሃይማኖት ተቋማትና የእምነት አባቶች ከሰላም ይልቅ ግጭትና አለመግባባትን መስበክ ሥራቸው እያደረጉ መጥተዋል ሲሉ የተቹት ዓብይ (ዶ/ር)፣ መንግሥት ይህን ዝም ብሎ እንደማያልፍ ነው የጠቆሙት፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከዚህ በመቀጠል መንግሥታቸው ባለፉት አራት ዓመታት አሳክቷቸዋል ስለሚሉት የልማት ለውጥና ውጤት መዘርዝር ላይ ያተኮሩ ሲሆን፣ ከመንገድ ግንባታ ጀምረው፣ አየር መንገድ፣ ቴሌኮም፣ ኢንዱስትሪ፣ ግብርና፣ ንግድና ኢንቨስትመንት የመሳሰሉ ነጥቦችን በቅደም ተከተል አውስተዋል፡፡

‹‹መንገድ ከለውጡ በፊት በአገር አቀፍ ደረጃ ሽፋኑ 127 ሺሕ ኪሎ ሜትር ነበር፡፡ ከለውጡ በኋላ ግን 165 ሺሕ ኪሎ ሜትሮች አድርሰነዋል፤›› ብለዋል፡፡ በኢትዮጵያ መንገዶች አስተዳደር ከለውጡ በፊት የተገነባው 13 ሺሕ ኪሎ ሜትር የአስፋልት መንገድ ቢሆንም፣ ከለውጡ በኋላ ግን በአራት ዓመታት 4,700 ኪሎ ሜትር መንገድ ተሠርቷል ብለዋል፡፡ በአጠቃላይ በመላ አገሪቱ 22 ሺሕ ኪሎ ሜትር መንገድ መጀመሩን የጠቀሱት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ ከዚህ ውስጥ 8,100 ኪሎ ሜትር ግንባታው እየተካሄደ መሆኑን፣ 9,102 ኪሎ ሜትር ደግሞ ሥራው በጨረታ፣ በኮንትራትና በተለያየ ደረጃ ላይ ይገኛል ብለዋል፡፡

‹‹በመንገድና በአንዳንድ ዘርፎች የተሳኩ ሥራዎች ለእኔም ጭምር የሚያስደንቀኝ ነው፤›› ያሉት ዓብይ (ዶ/ር)፣ ‹‹በአዲስ አበባ ብቻ በሦስት ዓመታት 151 ኪሎ ሜትር አስፋልት፣ 470 ኪሎ ሜትር ኮብልስቶንና 116 ኪሎ ሜትር የእግረኛ መንገድ ገንብተናል፤›› በማለት ዘርዝረዋል፡፡

የኮሮና ወረርሽኝ ዓለምንም ኢትዮጵያንም እየፈተነ ባለበት በአስቸጋሪ ወቅት፣ የኢትዮጵያ አየር መንገድ እጅግ አስደናቂ ዕድገት ማስመዝገቡን ገልጸዋል፡፡ የአውሮፕላኖቹን ብዛት ከ100 ወደ 135፣ የሚበርባቸው መዳረሻ ቦታዎችን ከ115 ወደ 125፣ የተጓዦቹን ቁጥር በዓመት ከስድስት ወደ 22 ሚሊዮን ማድረሱንና ዓመታዊ የገቢ መጠኑን ከ3.3 ቢሊዮን ዶላር ወደ 4.8 ቢሊዮን ዶላር ማሳደግ መቻሉንም አመልክተዋል፡፡

ቴሌኮምን በተመለከተ ደግሞ የደንበኞች ቁጥርን ከ38 ሚሊዮን ወደ 65.5 ሚሊዮን ማሳደግ መቻሉን፣ በገቢ ረገድ ደግሞ ከ33.5 ቢሊዮን ብር ወደ 55 ቢሊዮን ብር ማሳደግ መቻሉን ነው ያስረዱት፡፡ በስኳር ልማት ረገድ በለውጡ አምስት ፋብሪካዎችን በማስመረቅ የስኳር ማምረቻዎችን ከአራት እስከ ዘጠኝ ማድረስ መቻሉን የተናገሩት ዓብይ (ዶ/ር)፣ የምርት መጠንንም ከ200 ሺሕ ወደ 365 ሺሕ ቶን አሳድገናል ብለዋል፡፡ ነገር ግን አሁን ቡና ብቻ ሳይሆን ጠላም በስኳር መጠጣት በመጀመሩና የሕዝቡ ፍጆታ በማደጉ ምርቱን በተፈለገው መንገድ ማዳረስ አለመቻሉን ተናግረዋል፡፡

‹‹ከለውጡ ወዲህ 2,150 ትምህርት ቤቶች ገንብተናል፣ ከ15 ሺሕ በላይ መማርያ ክፍሎችን ደግሞ ጨምረናል፤›› ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ 1.7 ሚሊዮን ታዳጊ ተማሪዎች ዛሬ በየትምህርት ቤቱ በቀን ሁለቴ እየተመገቡ ትምህርታቸውን ይማራሉ ብለዋል፡፡ ‹‹በኢንዱስትሪ ረገድ ደግሞ ሦስት ኢንዱስትሪ ዞኖች ብቻ ነበሩን፡፡ በለውጡ ማግሥት ግን ሦስት አግሮ ኢንዱስትሪዎችን ጨምሮ ወደ 12 ገንብተናል፤›› በማለት የአገሪቱ ኢንዱስትሪዎች ቢያንስ 50 በመቶ እንዲያመርቱ ዕቅድ ተይዞ እየተሠራ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

ወደ ግብርና በመሸጋገር ዘንድሮ 5,000 ትራክተሮችና ዘመናዊ ማረሻ ማሽኖችን በሥራ ላይ ማዋል መቻሉን ታላቅ ስኬት ሲሉ የጠቀሱት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ ከሚታረሰው መሬት 28 በመቶውን እንኳን በማሽን ማረስ ቢቻል ቀላል የማይባል ምርት አገሪቱ እንደምታገኝ አስረድተዋል፡፡ አሁን የኩታ ገጠም (ክላስተር) እርሻን 45 በመቶ ማድረስ መቻሉን የጠቀሱት ዓብይ (ዶ/ር)፣ ይህንን እስከ 55 በመቶ ማድረስ ከተቻለ ትልቅ እመርታ ነው ብለዋል፡፡ በሌላ በኩል በመኸር የተመረተው 336 ሚሊዮን ኩንታል ሰብል እንደነበር ያስታወሱት ዓብይ (ዶ/ር)፣ ነገር ግን በበጋ ስንዴ ልማት ብቻ ዘንድሮ በባሌ የተዘራውንና ገና ያልተሰበሰበውን 154 ሺሕ ሔክታር መሬት ጨምሮ፣ በአጠቃላይ ከ23 እስከ 24 ሚሊዮን ኩንታል ስንዴ እንደሚገኝ ይጠበቃል ብለዋል፡፡

ለግብርናው በተሰጠው ልዩ ትኩረት የተነሳ በአገሪቱ ከቀረበው 267 ቢሊዮን ብር ብድር ውስጥ 73 ቢሊዮን ብሩ ለግብርናው የተፈቀደ መሆኑን ገልጸዋል፡፡ በሌላ በኩል ለማዳበሪያ 15 ቢሊዮን ብር ድጎማ መንግሥት ማዋሉን ጠቅሰዋል፡፡ ‹‹ይህ ሁሉ በግብርናው ዘርፍ የሚደረግ ርብርብ የኮሮና ወረርሽኝንና ዓለም አቀፉን የዋጋ ጫና እንድንቋቋም አስችሎናል፤›› ያሉት ዓብይ (ዶ/ር)፣ ራስን ችሎ ስንዴ ኤክስፖርት ለማድረግ ብቸኛው መንገድም ይኼው የግብርና ርብርብ ነው ብለዋል፡፡

‹‹ሰዎች የጓሮ አትክልት እያሉ ቢያሾፉብንም፣ ዘንድሮ ብቻ 80.9 ሚሊዮን ዶላር የሚያወጣ አትክልትና ፍራፍሬን ለዓለም ገበያ አቅርበናል፤›› ብለው፣ ይህ ደግሞ ከጓሮ አትክልት ጀምሮ በሚሠራው የአረንጓዴ አሻራ ልማት የመጣ ውጤት ነው ሲሉ አስረድተዋል፡፡ ‹‹የሕዝቡን መሠረታዊ የኑሮ ጫና ለማቃለልና የዋጋ ንረትን ለመቋቋም በፍራንኮ ቫሉታ በፈቀድነው ንግድ የተነሳ በስድስት ወራት 30 ቢሊዮን ብር ከቀረጥ አጥተናል፤›› ብለዋል፡፡ የዋጋ ንረቱ አስከፊና ዝቅተኛ ገቢ ያለውን ኅብረተሰብ ክፍል የጎዳ መሆኑን፣ ኑሮ እያሉ ከማውራትና ከማማረር ይልቅ ለመፍትሔ መሥራት ነው የሚያዋጣው ሲሉም አክለዋል፡፡

‹‹በአዲስ አበባ ብቻ 627 ሺሕ የሚሆኑ ተማሪዎች በትምህርት ቤት ምገባ ተካተዋል፡፡ ከ8,000 በላይ የደሃ ዜጎች ቤቶች ተገንብተዋል፤›› ያሉት ዓብይ (ዶ/ር)፣ በየቀኑ በከተማዋ የሚጋገረውን ዳቦ ከሁለት ሚሊዮን ወደ 3.4 ሚሊዮን አሳድገናል ብለዋል፡፡ በጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት ብቻ በጓሮ አትክልት ልማቱ በወር ቢያንስ 200 ሠራተኞቹ እንደሚጠቀሙ፣ ‹‹ይህንን አሠራር ሳንንቅ በየመሥሪያ ቤቱና በየተቋሙ ብናወርደው ቀላል የማይባል ችግር ይፈታል፤›› ሲሉም አስረድተዋል፡፡

የአገሪቱን የብድር ዕዳ በጥቅል ኢኮኖሚው ላይ ከነበረበት 58 በመቶ ጫና ወደ 50.5 በመቶ ዝቅ እንዲል አድርገናል ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ የብርን የመግዛት አቅም ዝቅ እንዲል በማድረጋችን የወጪ ንግድ ዓመታዊ ገቢያችንን ወደ አራት ቢሊዮን ዶላር ከፍ እንዲል አድርገናል ብለዋል፡፡ ኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ከዓለም ኢኮኖሚ ጋር እስከ 40 ከመቶ የተሳሰረ መሆኑን፣ የብር የመግዛት አቅም በመውረዱ በሀዋላ ገንዘብ ፍሰት፣ በውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንትና በአገልግሎት ኤክስፖርት ገቢ ጭምር ዕድገት መምጣቱን ተናግረዋል፡፡

እነዚህንና ሌሎችንም ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ጉዳዮች በሰፊው በመዳሰስ ወደ ፖለቲካዊ ነጥቦች ማብራራት የገቡት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ ከምክር ቤት አባላት ለተነሱ ወቅታዊና አወዛጋቢ ጉዳዮች መልስ ያሉትን ሐሳብ አስቀምጠዋል፡፡ በመጀመሪያ የፖለቲካ ሽግግር ጉዳይን የመለሱት ዓብይ (ዶ/ር)፣ ‹‹እኔ አሻግራችኋለው ስል የነበረው እስከ ምርጫ ጊዜ ብቻ እንጂ፣ ከዚያ በኋላ ያለው በምርጫ ያገኘነው የአምስት ዓመታት ኮንትራት ነው፤›› ሲሉ ገልጸዋል፡፡ ‹‹ሁሌም ለውጥ/ሽግግር ሲባል እሰማለሁ፤›› ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ ከምርጫው በኋላ ይህ ምዕራፍ ተዘግቶ መንግሥት የአምስት ዓመት ኮንትራት በሕዝብ ተሰጥቶት አገር እየመራ ነው በማለት ጥያቄውን በአጭሩ ቋጭተውታል፡፡

ከሕወሓት ጋር መንግሥት በድብቅ ድርድር እያደረገ ነው ተብሎ ለቀረበላቸው ጥያቄ መልስ የሰጡት ዓብይ (ዶ/ር)፣ አንዳችም የተደበቀ ድርድር የለም ሲሉ ተናግረዋል፡፡ ‹‹ጦርነቱን ከሕዝብ አልደበቅንም፡፡ ስለዚህ ድርድሩንም ከሕዝብ አንደብቅም፤›› ብለው፣ በውጭ ጉዳይና ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ ደመቀ መኮንን የሚመራ ብሔራዊ ኮሚቴ በዚህ ጉዳይ ላይ ኃላፊነት ወስዶ ሥራ የጀመረ በመሆኑ፣ ሒደቱን በሚቀጥሉት አንድና ሁለት ሳምንታት ሪፖርት ያደርጋል ብለዋል፡፡ ከአማራ ሕዝብ በስተጀርባ የተደረገ ንግግር አለመኖሩን ያሰመሩበት ዓብይ (ዶ/ር) ሕወሓት የአማራ ብቻ ሳይሆን የኢትዮጵያ ጠላት በመሆኑ፣ ሕወሓትም ከውጭ የመጣ ሳይሆን ከአገር ቤት የመነጨ ጠላት በመሆኑ ድርድሩ በመላው ኢትዮጵያዊያን መካከል ነው የሚሆነው ብለዋል፡፡ መንግሥት የአማራን ጥቅም አሳልፎ እየሰጠ ነው የሚል ጥርጣሬ መነሳቱ አግባብነት እንደሌለው፣ የብሔራዊ ኮሚቴው ሰብሳቢ አቶ ደመቀ ከአማራ የወጡና የአማራን ጥቅም አሳልፈው የማይሰጡ መሆናቸውን አስረድተዋል፡፡

የኢትዮጵያ የፀጥታ ኃይል ለሕወሓት ብቻ ተብሎ የሚዘጋጅ አለመሆኑን፣ የኢትዮጵያን ህልውና ለመጠበቅ ታስቦ የሚዘጋጅ መሆኑን ጠቅሰዋል፡፡ ‹‹በዓለም ላይ በዓመት 685 ሚሊዮን የሳይበር ጥቃት በየቀኑ ይፈጸማል፣ በየሰዓቱ ደግሞ 11 ሚሊዮን ይቃጣል፣ በየደቂቃውም 190 ሺሕ ይሰነዘራል፤›› ካሉ በኋላ፣ ይህ ደግሞ በዓመት 16 ቢሊዮን ዶላር ኪሳራ በየዓመቱ በዓለም ላይ እንደሚያደርስ አመልክተዋል፡፡ ‹‹ኢትዮጵያ የዚህ መሰሉ ዓለም አቀፍ ሥጋት ሰለባ አገር ናት፤›› ያሉት ዓብይ (ዶ/ር)፣ በቅርብ ጊዜያት እስከ 6,000 የሳይበር ጥቃት መድረሱን አመልክተው ይህን መሰሉን ሥጋት ለመከላከል ታስቦ እንጂ እንደ ሕወሓት ላለው ኃይል ትንኮሳ በሚል ብቻ ኢትዮጵያ የፀጥታ ኃይሏን እንደማታዘጋጅ አስረድተዋል፡፡ ለሕወሓት የጦር ነጋሪት ጉሰማና ትንኮሳ አገሪቱ ምን ያክል ተዘጋጅታለች የሚለው ነጥብም በዚህ መንገድ መታየት እንዳለበት ጠቁመዋል፡፡

‹‹ሰላም ጎጂ ነገር ይመስል ድርድር ጀመሩ ተብሎ መንግሥት ባልተጨበጠ ወሬ መወንጀል የለበትም፤›› ሲሉ የተናገሩት ዓብይ (ዶ/ር)፣ ለሰላም ዝግጁ ወገን እስካለ ድረስ ኢትዮጵያ ምን ጊዜም ለሰላም በሯን ዝግ አታደርግም ብለዋል፡፡ ‹‹ሰላም፣ ሰላም የምንለው ከሰላም የምናተርፈው ብዙ ጥቅም ስላለ ነው፤›› ሲሉ ያከሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ ሰላም ከመጣ ደግሞ በቀዳሚነት የሚያተርፈው የትግራይ ሕዝብ ነው ብለዋል፡፡ ‹‹ምክር ቤቱ በእኛ ላይ የሚነሱ አሉባልታዎችን ለማጣራት ከሚለፋ ይልቅ፣ ለትግራይ ሕዝብ ቢቆረቆር ይሻላል፤›› ያሉት ዓብይ (ዶ/ር)፣ ሕወሓት እንደሆነ ጄኔሬተሩ ነዳጅ ካላጣና የሚበላው ካልቸገረው በስተቀር ለትግራይ ሕዝብ ኃላፊነት የሚሰማው ቡድን አይደለም ብለዋል፡፡

ወደ ሰሞነኛው የሕግ ማስከበር ዘመቻ በመሸጋገር ረዥም ጊዜ በማብራሪያ ያሳለፉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ ዘመቻው የመጣው በሕዝብ ጥያቄ ነው ሲሉ መልስ ሰጥተዋል፡፡ ብልፅግና የመጀመሪያ ጉባዔውን ባካሄደ ማግሥት ኅብረተሰቡን ወርዶ ችግሮቹን ለመስማት አመራሮቹን ማሰማራቱን፣ በዚህ ወቅትም ሕዝቡ በቀዳሚነት የሰላም፣ የኑሮ ውድነትና የመልካም አስተዳደር ጥያቄን ማንሳቱን ተናግረዋል፡፡ ይህን ሕዝቡን ጥያቄ ተከትሎም ወደ ሕግ ማስከበር መገባቱን፣ ዕርምጃው የሕዝቡን ጥያቄ የተከተለና ሕዝቡን ያስደሰተ መሆኑን በጥናት መረጋገጡን ተናግረዋል፡፡ በኦሮሚያ፣ በአማራ፣ በቤኒሻንጉል ጉሙዝ በዋናነት የፀጥታ ችግር መኖሩ፣ በሶማሌ ክልል ደግሞ የኮንትሮባንድና የአልሸባብ ጥቃት ሥጋት መኖሩ፣ እንዲሁም በአዲስ አበባ ዘረፋና ቅሚያ መበራከቱ በጥናት ተለይቶ ወደ ዕርምጃ መገባቱን አስረድተዋል፡፡

በኦሮሚያ በሁለት ወራት ውስጥ ከ1,000 በላይ የኦነግ ሸኔ ቡድን ታጣቂዎች መገደላቸውን ያመለከቱት ዓብይ (ዶ/ር)፣ በአማራ ክልል ከተያዙ 4,500 ሰዎች ውስጥ ከ3,500 ያላነሱት ከአማራ ልዩ ኃይልና ከመከላከያ ከድተው አካባቢን ሲያምሱ የቆዩ የፀጥታ ችግር ፈጣሪዎች ናቸው ብለዋል፡፡ በአማራ ክልል የተካሄደውን ኦፕሬሽን የመራው የአማራ ልዩ ኃይል መሆኑን፣ በዕርምጃው ችግርና ግድፈት ከታየም ኃላፊነቱ የክልሉ አስተዳደር ነው ብለዋል፡፡

‹‹ፋኖ የዓብይን ውዳሴም ሆነ ሙገሳ ፈልጎ ሳይሆን፣ አገሩን ለመጠበቅ ብሎ ነው የዘመተው፤›› ያሉት ዓብይ (ዶ/ር)፣ ስሙን ግን መነገጃ ማድረግ አግባብነት የለውም ብለዋል፡፡ ከስንዴ መካከል እንክርዳድ እንደማይጠፋው ሁሉ በፋኖ ስም አካባቢን የሚያተራምሱና ሕገወጥ ሥራ ሲያከናውኑ የነበሩ አሉ ብለዋል፡፡ በእነዚህ ላይ መንግሥት ሕዝቡ በጠየቀው መሠረት አግባብነት ያለው ዕርምጃ እየወሰደ ነው ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ ሕዝቡም በዕርምጃው ደስተኛ ነው ብለዋል፡፡ መከላከያን ገድሎ ማንም እጅ ያልገባ ክላሽኒኮቭ እየነጠቀ የሚሸጥ ሽፍታን በፋኖ ስም ለምን ተነካ ማለት እንደማይቻልም ተናግረዋል፡፡

በሌላም በኩል አክቲቪስትነት፣ ጋዜጠኝነትና ፖለቲከኝነት መደበላለቁን ጠቁመው፣ ታዋቂ ሰዎች የመናገርና የመንቀሳቀስ መብት አላቸው እንደሚባለው ሁሉ መደበኛ ዜጎችም ሰላም አግኝተው የመኖር መብት እንዳላቸው ሊታወቅ ይገባል ብለዋል፡፡ ሥርዓተ አልበኞችና የተከበረውን የጋዜጠኝነት ሙያ መደበቂያ የሚያደርጉ ኃላፊነት የጎደላቸውን ሰዎች ማስታገስ ያስፈልጋል ብለው፣ የሕግ ማስከበር ዕርምጃው በዚህ አግባብ መታየት አለበት ብለዋል፡፡ ‹‹በቀን  ሦስትና አራት ሰዓት እየተኛሁ ስለሠራሁ እንደ እኔ የሚሰደብ መሪ የለም፣ ከእኔ አልፎም እናቴ ጭምር በሚዲያ ትሰደባለች፤›› ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ ‹‹በኢትዮጵያ የእኔ ፌስቡክ ገጽን የሚያክል ተከታይ ያለው ገጽ ባይኖርም፣ ነገር ግን እውነተኛ መረጃ ለማስተላለፍ ሳይሆን አገር ለማተራመስ ልጠቀምበት ካልኩ አስቸጋሪም ነው ማንም አይፈቅድልኝም፤›› ብለዋል፡፡ ሚዲያ በተለይ ማኅበራዊ ሚዲያ ጥላቻ፣ ስድብና ውሸት ገቢ መሰብሰቢያ እንደሆነና ይህ ዓይነቱ የተበላሸ አካሄድ መስተካከል አለበት ብለዋል፡፡

ከዚህ ጋር በተያያዘ በአገሪቱ ፖለቲካ ላይ ተረኝነት ሰፍኗል በሚል ለቀረበላቸው ጥያቄ ምላሽ ሲሰጡ፣ ‹‹አገሪቱ ለሁላችንም የምትበቃ ሰፊ አገር ሆና ሳለ መፎካከሩና የእኔ ብቻ እያሉ መስገብገቡ ያፈርሰናል፤›› ብለዋል፡፡ በአሁኑ ወቅት በሰፊው የሚነገረውን የኦሮሞ የበላይነት ወይም ተረኝነት ሰፈነ የሚል ጉዳይን ለመፈተሽ ጥልቅ ሲቪል ሰርቪሳዊ ጥናት መካሄዱንና የተገኘው ቁጥርም ይህን እንደማይደግፍ ነው የተናገሩት፡፡

‹‹በፕሬዚዳንት፣ በጠቅላይ ሚኒስትሮችና በሁለቱ አፈ ጉባዔዎች አካባቢ ካየነው ኦሮሞ አንድ ብቻ ነው ያለው፡፡ ኦሮሞ አንድ ማግኘቱ ደግሞ የሚያንስ እንጂ የሚበዛ አይመስለኝም፡፡ ከ22 ሚኒስትሮች መካከል ስድስት ኦሮሞ፣ ስድስት አማራና ስድስት ደቡብ ናቸው፡፡ በፓርላማ፣ በፕሬዚዳንትና በጠቅላይ ሚኒስትር ቢሮዎች ባሉ ሠራተኞች ካየነው ኦሮሞ ቁጥር ሁለተኛ ነው፡፡ በሲቪል ሰርቪስ በኩል በ22 የሚኒስቴር መሥሪያ ቤቶች ውስጥ ካየነው ኦሮሞ በቁጥር ሁለተኛ ነው፡፡ በልማት ድርጅቶች ውስጥ ለምሳሌ በአየር መንገድ አመራርና ሠራተኞች መካከል 74 በመቶ አማራ፣ ትግሬና ኦሮሞ አምስት በመቶ፣ እንዲሁም 16 በመቶ ሌሎች ብሔሮች ናቸው፡፡ በውጭ በሚሠሩ ሠራተኞች ደግሞ 52 በመቶ አማራ፣ 16 በመቶ ኦሮሞ፣ 16 በመቶ ትግሬ ነው፤›› በማለትም ስታትስቲክሳዊ መረጃዎችን ዘርዝረዋል፡፡

ከዚህ በመነሳትም የኦሮሞ የበላይነት (ተረኝነት) ቀርቶ ኦሮሞ የሚገባውንም አላገኘም ሲሉ የተናገሩት ዓብይ (ዶ/ር)፣ የዓብይ አህመድ ጠቅላይ ሚኒስትርነት ሥልጣን ይቀራታል እንጂ ኦሮሞ የሚገባውን ነገር አያጣም ብለዋል፡፡ በሀብት ምንጭነት፣ በጥቅል ምርትም ሆነ በሕዝብ ብዛትም ከ35 በመቶ በላይ አስተዋጽኦ ያለው ሕዝብ መጠቀም የሚገባውን ልክም አልተጠቀመም ሲሉ ተናግረዋል፡፡ ልክ እንደ ደቡብ አፍሪካ ወይም እንደ ኬንያ የሕዝብ ስብጥርና አስተዋጽኦን መሠረት ያደረገ ሕግ ፓርላማው ማፅደቅ አለበት ያሉት ዓብይ (ዶ/ር)፣ ኦሮሞን ልክ እንደ ትግራይ በስድስት በመቶ አሳንሶ የማየት ስህተት መፈጠር የለበትም ብለዋል፡፡ ኦሮሞ ጠል የሆኑ ኃይሎች በተለይ በአዲስ አበባ የተለየ ቅስቀሳ ያደርጋሉ ሲሉ የከሰሱት ዓብይ (ዶ/ር)፣ ኦሮሚያ ላይ ቆሻሻ እየተጣለ አዲስ አበባ ላይ ኦሮሞ በዛ ይላሉ ሲሉም ተችተዋል፡፡ አላህአክበር ሲባል ክርስቲያን እንዳይሰማህ፣ ክርስቲያኑ ሲቀድስ እስላሙ እንዳይሰማህ እያሉ በሁለቱ ዋና ዋና እምነቶች መካከል መናቆርን የሚዘሩ ኃይሎች፣ ዛሬም አማራና ኦሮሞን በማናከስ ትርፍ ለማግኘት የሚራወጡ ናቸው ብለዋል፡፡ ነፃነት መጣ፣ እኩልነትና ፍትሕ ተፈጠረ ተብሎም አንዳንዶች ከልክ በላይ ለመሆን መሞከራቸው በትዕግሥት የማይታለፍ የተሳሳተ አመለካከት መሆኑን ነው የተናገሩት፡፡

አገራዊ ምክክር ለነባር አገራዊ ችግሮች ፍቱን መድኃኒትና ፈውስ እንዲሆን ታስቦ የሚደረግ አገራዊ አጀንዳ መሆኑን፣ ድርድር ነው ብሎ ማሰቡ የተሳሳተ መሆኑን አመልክተዋል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ትኩስ ጽሑፎች

ተዛማጅ ጽሑፎች

- Advertisement -
- Advertisement -