Monday, December 4, 2023
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

ዋና ተቋራጮች ንዑስ ተቋራጮችን እንዲያሳትፉ የሚያስገድድ መመርያ ሊዘጋጅ ነው

ተዛማጅ ፅሁፎች

ንዑስ ተቋራጮች ተጠያቂ የሚሆኑበት አሠራር ይዘረጋል ተብሏል

በኮንስትራክሽን ዘርፍ የተሰማሩ የአገር ውስጥም ሆኑ የውጭ ሥራ ተቋራጮች፣ በሥራቸው ንዑስ ሥራ ተቋራጮችን እንዲያሳትፉ ለማድረግ የሚያስችል መመርያ ወይም የአሠራር ሥርዓት ለመዘርጋት ጥናት እየተደረገ መሆኑን፣ የኢትዮጵያ ኮንስትራክሽን ማኔጅመንት ኢንስቲትዩት አስታወቀ።

ጥናቱ በኮንስትራክሽን ማኔጅመንት ኢንስቲትዩትና በኢትዮጵያ አርክቴክቸር ሕንፃ ግንባታና ከተማ ልማት ተቋም እንደሚከናወን፣ በአጠቃላይ 2.7 ሚሊዮን ብር እንደተመደበለት በኮንስትራክሽን ማኔጅመንት ኢንስቲትዩት የጥናት ክፍል ዳይሬክተር ወ/ሮ ዘሃራ አብዱላሂ ገልጸዋል።

በስድስት ወራት እንደሚጠናቀቅ የሚጠበቀው ጥናቱ ትልልቅ ፕሮጀክቶችን የሚይዙ ዋና ተቋራጮች ንዑስ ሥራ ተቋራጮችን እንዲያሳትፉ የሚያደርግ ሥርዓትን ለመዘርጋት ያለመ ነው ብለዋል። ይህም ለንዑስ ተቋራጮች ከሚፈጥረው ዕድል በተጨማሪ ፕሮጀክቶች በተያዘላቸው ጊዜ እንዲጠናቀቁና የጊዜና የገንዘብ ብክነትን ለማስቀረት እንደሚረዳ ገልጸዋል።

አሁን ባለው አሠራር ንዑስ ተቋራጮችን ማሳተፍ በፍላጎት ላይ ብቻ የተመሠረተ መሆኑን የገለጹት ወ/ሮ ዘሃራ፣ በተለይም ከውጭ የሚመጡ ተቋራጮች በአገር ውስጥ የሚገኙ የግንባታ ድርጅቶችን አቅም የሚያጎለብቱበት አሠራር ያስፈልጋል ብለዋል።

በተጨማሪም ንዑስ ተቋራጮች ለሚወስዱት ሥራ በጊዜም ይሁን በገንዘብ ለሚደርሰው ኪሳራ ተጠያቂ የሚሆኑበት አሠራር ባለመኖሩ ዋና ተቋራጮች ሥራውን በጋራ ለመሥራት ያላቸው ፍላጎት እንዲቀንስ ማድረጉን ገልጸው፣ ለዚህም ንዑስ ተቋራጮች ተጠያቂ የሚሆኑበት ሥርዓት ይዘረጋል ብለዋል።

ከጨረታ ሒደቱ ጀምሮ ከውጭ የሚመጡም ይሁኑ በአገር ውስጥ የግንባታ ሥራዎችን የሚሠሩ ተቋራጮች በሥራቸው የሚይዟቸውን ንዑስ ተቋራጮች እንዲያሳውቁ ማድረግም፣ ከጥናቱ በኋላ በሚወጣው የአሠራር ሥርዓት ውስጥ የሚካተት መሆኑን ጠቁመዋል። ጥናቱ በመጪው መስከረም ወር 2015 ዓ.ም. እንደሚጠናቀቅና መመርያው እንደሚዘጋጅ ተናግረዋል፡፡

በአብዛኛው ከደረጃ አራት በታች የሆኑ ተቋራጮች በንዑስ ሥራ ተቋራጭነት የሚሳተፉ ሲሆን፣ በዚህም በኤሌክትሪክ ሥራ፣ በቀለምና በሌሎችም የተመዘገቡ ከ45 ሺሕ በላይ ድርጅቶች መኖራቸውን ከኢንስቲትዩቱ የተገኘው መረጃ ያሳያል።

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች