Friday, July 19, 2024

ሰላም ከሚነሱ ድርጊቶች መቆጠብ ይገባል!

የኢትዮጵያ የፖለቲካ ምኅዳር ውስጥ ተሸጉጠው ከሚያስቸግሩ ነገሮች ውስጥ አንዱ አለመተማመን ነው፡፡ አገር የሚያስተዳድረው መንግሥት የራሴ የሚለውን እውነት ሲናገር፣ የሚቃወመው አካል በፍፁም ሊሰማው አይፈልግም፡፡ ገዥው አካል በገሃድ የሚታየውን ጥፋቱን ዓይኔን ግንባር ያድርገው ብሎ ሲክድ፣ በዚህኛው በኩል ያለው ደግሞ በመረጃና በማስረጃ ለማጋለጥ ያለው አቅም በጣም ደካማ ነው፡፡ በዚህም ምክንያት ሐሜትና አሉባልታ የበላይነት ይዘው አድራሻቸው በማይታወቅ መረጃዎች አገር ትናጣለች፡፡ ገዥው ፓርቲ ብልፅግና አገር የሚያስተዳድርበት የመንግሥት ሥልጣን መገራት ያለበት በሕግ መሆን ሲገባው፣ ከሕግ በላይ የመሆን አዝማሚያ ሲያሳይ ፈር ማስያዝ የግድ ነው፡፡ ሌላውም አካል ከሕግ በላይ ሆኖ ለመንጠራራት ሲፈልግ በሕግ ማለት ተገቢ ነው፡፡ ለዚህ ደግሞ የሠለጠነ ፖለቲካ ያስፈልጋል፡፡ ከሴራና ከአሻጥር የፀዱ ሐሳቦች የሚንሸራሸሩበት ምኅዳር መፈጠር አለበት፡፡ አገር ሰላም የምትሆነው በዚህ መንገድ ለመንቀሳቀስ ፈቃደኝነት ሲኖር ነው፡፡ ይህ ፈቃደኝነት መመሥረት ያለበት በመተማመን ላይ ነው፡፡ መተማመን ለሰላም መስፈን ትልቅ ቁልፍ ነው፡፡ ገዥው ፓርቲም ሆነ ተፎካካሪዎቹ ሰላም እንዳይደፈርስ ለመተማመን ቅድሚያ ይስጡ፡፡  

ሌላው አስቸጋሪ ነገር ጥላቻ ነው፡፡ ከጊዜያዊ ኩርፊያ በላይ ተሻግረው መሄድ የማይገባቸው ልዩነቶች ከመጠን በላይ እየተለጠጡ፣ ኢትዮጵያውያንን ለምን እርስ በርስ የሚያፋጥጧቸውና የሚያስተናንቋቸው ችግሮችን ማባዛት እንደሚፈለግ ግራ ያጋባል፡፡ አሁንም በየቦታው ከብሔር፣ ከእምነት፣ ከፖለቲካ አቋምና ከመሳሰሉት በላይ ሰብዓዊ ፍጡርነት እየተዘነጋ ነው፡፡ በዚህም ምክንያት በመኖሪያ መንደር፣ በሥራ ቦታም ሆነ በሌላ ሥፍራ ሰዎች ሰብዓዊ ፍጡርነታቸው ተዘንግቶ በብሔርና በእምነት ማንነታቸው አጥር ውስጥ ብቻ ሲከለሉ ያስደንቃል፡፡ እንዲህ ዓይነቱ ነገር ያተረፈው ቢኖር ለሴረኛ ፖለቲከኞች ጥቅም ማጋበሻ መፍጠር ነው፡፡ በኢትዮጵያውያን መካከል መጠራጠር በመፍጠር ለጥላቻ በር መክፈት በመለመዱ፣ ኢትዮጵያ ሰላም እንድታጣ ሰበብ ሆኗል፡፡ ለኢትዮጵያ አንዲት እሴት የማይጨምሩ ነገር ግን የተገኘውን ነገር ሁሉ ለመጠቅለል የሚፈልጉ ፖለቲከኞች፣ እያንዳንዱን ልዩነት ወደ ጠርዝ በመግፋት ለፍጅትና ለዕልቂት ሲያመቻቹ አብሮ መነዳት መዘዙ ከባድ ነው፡፡ እንደ ሴራ ፖለቲከኞች ፍላጎት ቢሆን ኖሮ አገር ፈርሳ፣ ከፍተኛ ዕልቂት ደርሶ ሕዝብ በየአቅጣጫው ተሰዶ ነበር፡፡ ኢትዮጵያውያን ለጥላቻ ከሚዳርጉ ከንቱ ቅስቀሳዎች ራሳቸውን ቢያርቁ ይመረጣል፡፡ 

ሰላም በሌለበት ፍትሕና እኩልነት አይኖሩም፡፡ ሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶች የሚረጋገጡት ሰላም ሲኖር ነው፡፡ ሰላም እንዲሰፍን ግን የሰዎችን ክብር፣ ማንነት፣ እምነት፣ የንግግርና የጽሑፍ ነፃነት፣ የፖለቲካ አቋምና የመሳሰሉትን ተፈጥሯዊ መብቶች ማክበር የግድ ነው፡፡ ሰዎች በተፈጥሯቸው በወልም ሆነ በግል የሚፈልጓቸው የተለያዩ ጉዳዮች ቢኖሩም፣ በእርስ በርስ መስተጋብራቸው አንዳቸው የሌላቸውን ነፃነትና መብት ማክበር ይጠበቅባቸዋል፡፡ ስለፍትሕ፣ እኩልነትና ዴሞክራሲ ስንነጋገር አንዱ ከሌላው የተለየ መብት እንዳለው ማሰብ ፈፅሞ አይቻልም፡፡ በዚህ ወቅት ኢትዮጵያ ውስጥ በተለይ ከሰፊው ሕዝብ ይልቅ፣ በግራም በቀኝም በተሠለፉት ልሂቃን ዘንድ የሚስተዋሉ ግራ አጋቢ ነገሮች ፈር መያዝ አለባቸው፡፡ አገርን ከሚመራው ገዥው ፓርቲ ብልፅግና ጀምሮ ተፎካካሪ ፓርቲዎችና የፖለቲካው አጃቢዎች፣ ለአገር ሰላም ፋይዳ ከሌላቸው ድርጊቶች ለመቆጠብ የሚያስችሉ መልካም ተግባራት ላይ ቢያተኩሩ ይመረጣል፡፡ ለሥልጣንና ይዞት ለሚመጣው ጥቅማ ጥቅም ሲባል ብቻ መዋሸት፣ ማጭበርበር፣ ማደናገር፣ በሕዝብ ስም መቆመርና አገርን የማትወጣው ቀውስ ውስጥ መክተት መቆም አለበት፡፡ በግጭት ሥጋትና በመሪር የኑሮ ውድነት እየተሰቃየ ያለውን ሕዝብ ሰላም መንሳት ይቁም፡፡

ኢትዮጵያ ታላላቅ ታሪካዊ ክንውኖች የተካሄዱባት ጥንታዊትና በዓለም ልዩ ሥፍራ ይሰጣት የነበረች አገር ናት፡፡ በመጽሐፍ ቅዱስ ስሟ ተደጋግሞ የተጠቀሰ፣ ነቢዩ መሐመድ ተከታዮቻቸውን መጠጊያ እንዲያገኙ የመረጧት፣ ተደጋግሞ እንደተነገረው በየዘመኑ የተነሱ ወራሪዎችንና ኮሎኒያሊስቶችን አሳፍራ የመለሰች፣ በታላቁ የዓድዋ ጦርነት ድል ምክንያት የዓለም ጥቁር ሕዝቦችንና በቅኝ አገዛዝ ይማቅቁ የነበሩትን ያበረታች፣ ለፓን አፍሪካኒዝም እንቅስቃሴ መንስዔ የሆነች፣ በቀድሞው ሊግ ኦፍ ኔሽንስም ሆነ በአሁኑ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት (ተመድ) ከአፍሪካውያን ወገኖቿ በፊት ቀድማ የተሳተፈችና የመሠረተች፣ አፍሪካውያን ከቅኝ አገዛዝ ነፃ እንዲወጡ ሁለገብ ድጋፍ ያደረገች፣ ለዝነኛው ፀረ አፓረታይድ ታጋይ ለደቡብ አፍሪካዊው ኔልሰን ማንዴላ ወታደራዊ ሥልጠና የሰጠችና በሌሎች መልካም ተግባሮቿ ስመ ጥር የሆነች ታላቅ አገር ናት፡፡ ይህችን ታላቅ አገር በመናኛ አስተሳሰቦችና ፍላጎቶች በመመራት ገጽታዋን ማበላሸት ያሳፍራል፡፡ እስካሁን ለተፈጸሙ ነውረኛ ድርጊቶች በመፀፀት የዚህ ዘመን ኢትዮጵያውያን ከብሔር፣ ከእምነት፣ ከዕብሪትና ከጉልበተኝነት ከፋፋይ ፍላጎቶች መላቀቅ አለባቸው፡፡ ኢትዮጵያን አንገቷን በኃፍረት ከሚያስደፉ ከንቱ ድርጊቶች መራቅ ያስፈልጋል፡፡

ለዘመናት በኢትዮጵያውያን ዘንድ ትልቅ ግምት ከሚሰጣቸው ጉዳዮች መካከል እውነት ቀዳሚውን ሥፍራ ይይዛል፡፡ ማንም ሰው ልጁ ውሸት እንዲናገር አይፈልግም ነበር፡፡ ዋሾነት በየማኅበረሰቡ የሚያስንቅ ስለሆነ ሰዎች ውሸታም ላለመባል ይጠነቀቃሉ፡፡ በዚህ ምክንያት አንድ ችግር ሲያጋጥም እንኳ እከሌ/እከሊት የሚመዘኑት በሚታወቁበት ባህሪያቸው ነው፡፡ በማኅበረሰቡ ውስጥ እውነተኝነት ትልቅ ክብር ያሰጣል፡፡ በዚህም ምክንያት ነው ‹‹ከእንጨት መርጦ ለታቦት ከሰው መርጦ ለሹመት›› የሚባለው ዕድሜ ጠገብ አባባል ፀንቶ የሚኖረው፡፡ ካለፉት ሃምሳ ዓመታት ወዲህ ግን ፖለቲካ ውስጥ ያሉ ሰዎች በሙሉ አይታመኑም፡፡ ሕዝቡ ውስጥም ‹‹ፖለቲካ ማለት ውሸት ነው›› የሚል እምነት በመስረፁ፣ ፖለቲከኞች ሲናገሩ የሚደመጡት በድርበቡ ነው፡፡ በተለያዩ አስከፊ ድርጊቶቻቸውም እነሱም አስመስክረዋል፡፡ ከዘመነ ቀይና ነጭ ሽብር እስካሁን ድረስ ያለውን ሴራና ክፋት ማስታወስ በቂ ነው፡፡ በሁሉም ፖለቲከኞች ዘንድ ለግልጽነትና ለተጠያቂነት መርህ የሚሰጠው ዋጋ አናሳ በመሆኑ፣ ከሕዝቡ ጋርም ሆነ እርስ በርስ ያላቸው ግንኙነት ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተበላሸ ነው፡፡ ሰላም እየጠፋ ያለው ውሸት በመግነኑ ነው፡፡

በገዛ አገሩ ውስጥ የተፈናቀለ ከአምስት ሚሊዮን በላይ ሕዝብ ሜዳ ላይ ተበትኖ፣ በርካታ ሚሊዮኖች የምግብ ያለህ እያሉ፣ በአስመራሪው የኑሮ ውድነት የሚሰቃዩ ሚሊዮኖች ተስፋቸው እንደ ጉም ተበትኖ፣ ከዩኒቨርሲቲዎችና ከኮሌጆች በዲግሪ የተመረቁ በጣም ብዙ ወጣቶች ሥራ አጥ ሆነው፣ ኢትዮጵያውያን በሙሉ ከጥቂቶች በስተቀር በሐዘንና በግራ መጋባት አንገታቸውን ደፍተው ባሉበት በዚህ አስከፊ ጊዜ ክፋትና ሴራ ጉንጎና ውስጥ መገኘት ያሳፍራል፡፡ ኢትዮጵያ ምንም ሳይጎድልባት በልሂቃን ልጆቿ ስግብግብነትና ራዕይ አልባነት ምክንያት የመከራ አገር መሆኗ ያስቆጫል፡፡ ኢትዮጵያን በተባበረ ክንድ ከዚህ አዘቅት ውስጥ ማስወጣት የግድ መሆን አለበት፡፡ በብሔር፣ በእምነትና በሌሎች ፍላጎቶች እየተቧደኑ ከፍትሕ፣ ከእኩልነት፣ ከነፃነትና ከዴሞክራሲ ጋር መጣላት ለጊዜው ነው እንጂ ዘለቄታዊ ዋስትና የለውም፡፡ ኢትዮጵያንና ሕዝቧን ከሥልጣንና ከጥቅማ ጥቅም በታች በማድረግ መንጠራራት የትም አያደርስም፡፡ ከሰብዓዊነት ጋር በመጋጨት የገዛ ወገንን መጥላት፣ መርገም፣ ማሳደድና መድረሻ ማሳጣት በታሪክ ያስጠይቃል፡፡ አገርንና ሕዝብን ሰላም ከሚነሱ ድርጊቶች መቆጠብ ይገባል!      

በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች

- Advertisment -

ትኩስ ፅሁፎች

አቶ ሰብስብ አባፊራ የኢትዮጵያ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት ፕሬዝዳንት ሆነው ተመረጡ

ከአዋጅና መመሪያ ውጪ ለዓመታት ሳይካሄድ የቆየው የኢትዮጵያ ንግድና ዘርፍ...

ቀጣናዊ ገጽታ የያዘው የኢትዮ ሶማሊያ ውዝግብ

ከአሥር ቀናት ቀደም ብሎ በተካሄደው የፓርላማ 36ኛ መደበኛ ስብሰባ፣...

የኢንሹራንስ ኩባንያዎች በዓረቦንና የጉዳት ካሳ ክፍያዎች ላይ ተጨማሪ እሴት ታክስ መጣሉን ተቃወሙ

በአዲሱ ተጨማሪ እሴት ታክስ አዋጅ ውስጥ የኢንሹራንስ ከባንያዎች ለሚሰበስቡት...

የዘንድሮ ነገር!

ጉዞ ከስድስት ኪሎ ወደ ካዛንቺስ፡፡ ከእንጦጦ በኩል ቁልቁል እያስገመገመ...
spot_img

ተዛማጅ ፅሁፎች

ለሕዝብ መሠረታዊ ፍላጎቶች ልዩ ትኩረት ይሰጥ!

በዚህ ዘመን ለሰው ልጅ የሚያስፈልጉ ነገሮች ብዛታቸው እየጨመረ ቢመጣም፣ በኢትዮጵያ ተጨባጭ ሁኔታ ግን መሠረታዊ የሚባሉ ፍላጎቶች ከመቼውም ጊዜ በላይ ትኩረት ሊቸራቸው ይገባል፡፡ በአሁኗ ኢትዮጵያ...

ሚዲያው በሕዝብ የህሊና ችሎት ከተዳኘ በቂ ነው!

መሰንበቻውን ድንገት ሳይታሰብ ያለ ማስጠንቀቂያ ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) የተገኙበት የሚዲያ ሽልማት ሥነ ሥርዓት መካሄዱ ይታወሳል፡፡ ‹‹ለብሔራዊ ጥቅም መከበር ለሠሩ የአገር ውስጥና የውጭ...

ከሕዝብ ጥቅምና ፍላጎት ተፃራሪ ላለመሆን ጥንቃቄ ይደረግ!

ኢትዮጵያ ውስጥ ድብልቅልቅ ስሜት የሚፈጥሩ በርካታ ሁነቶች ማጋጠማቸው አዲስ ነገር ባይሆንም፣ በዚህ ወቅት ከተለያዩ ፍላጎቶችና ዓላማዎች ጋር የተሸራረቡ ሥጋት ፈጣሪ ችግሮች በብዛት እየተስተዋሉ ነው፡፡...