Saturday, July 13, 2024

‹‹የምናካሂደው ሪፎርም ለማመን የሚከብዱ ውጤቶች እያመጣ ነው›› ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር)

- Advertisement -spot_img

በብዛት የተነበቡ

በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ከአባላቱ ለተነሱላቸው ጥያቄዎች ምላሽ የሰጡት ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር)፣ መንግሥታቸው እያካሄደ ባላው ሪፎርም የሚያስደምምና ለማመን የሚከብድ ውጤት እያመጣ መሆኑን ተናገሩ፡፡

ፓርላማው ሰኔ 7 ቀን 2014 ዓ.ም. ባካሄደው 13ኛ መደበኛ ጉባዔው ለጠቅላይ ሚኒስትሩ በቁጥር የተመጠነ ጥያቄ ካቀረቡ 21 የምክር ቤት አባላት መካከል ጠቅላይ ሚኒስትሩ መልስ ለመስጠት ከፈጀባቸው አጠቃላይ ሦስት ሰዓት አካባቢ አመዛኙን ጊዜያቸውን ከተፎካካሪ ፓርቲዎች የተነሱ ጥያቄችን ለመመለስ ተጠቅመዋል፡፡

ለአብነት ጥያቄ ካነሱ የምክር ቤት አባላት መካከል የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ (አብን) ተወካይ ደሳለኝ ጫኔ (ዶ/ር) በመጋቢት 2010 ዓ.ም. ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) ወደ ሥልጣን ሲመጡ ባደረጉት ንግግር የአገሪቱ የዴሞክራሲ ሽግግር ሒደት ላይ ማሻሻያዎችን ለማድረግና የተለያዩ የለውጥ ዕርምጃዎችን እንደሚወስዱ መናገራቸውን አስታውሰዋል፡፡

በዚህ ሒደት የተቋማት ሪፎርምና ገለልተኛ ተቋማት ግንባታ፣ የዴሞክራሲ ምኅዳሩን ማስፋትና ዴሞክራሲያዊ ምርጫ ማካሄድ፣ ሐሳብን በነጻነት የመግለፅና የፕሬስ ነፃነት፣ የማንነትና የወሰን ጥያቄዎችን ሰላማዊ ዕልባት እንዲያገኙ የማድረግ፣ ተጀምረው የነበሩ ግዙፍ ፕሮጀክቶችን እንደ ህዳሴ ግድብ፣ የስኳር ፋብሪካዎች እንዲጠናቀቁ ለማድረግ እንደሚሠሩ በመጀመሪያ ንግግራቸው ቃል መግባታቸውን አውስተዋል፡፡

በተጨማሪም አገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያ በማድረግ የኢትዮጵያውያን የኑሮ ሁኔታ እንዲሻሻል ለማድረግና የዋጋ ንረት ቢያንስ ካለበት ዝቅ እንዲል እንደሚሠራ ተናግረው እንደነበር አንስተዋል፡፡

ደሳለኝ (ዶ/ር) ባለፉት አራት ዓመታት የተገለጹት የለውጥ ተግባራት ምን ያህል ተፈጽመዋል? ለውጡና አገራዊ ሪፎርሙ በሃዲዱ እየሄደ ነው ወይስ ሃዲዱን ስቶ ከመስመር ወጥቷል? ወይም አንዳንዶች እንደሚገልጹት ከሽፏል ወይ? ሲሉ ለጠቅላይ ሚኒስትሩ ጥያቄያቸውን አቅርበዋል፡፡

‹‹እንደ አገር ከገባንበት ችግር ለመውጣት አሁንስ የጋራ የሽግግር ፍኖተ ካርታ ያስፈልጋል ብለው ያስባሉ? ወይስ አሁንም እኔ አሻግራችኋለሁ በሚለው አቋምዎ እንደፀኑ ነው?›› ሲሉም አክለው ጠይቀዋል፡፡

በተመሳሳይ የኢትዮጵያ ዜጎች ለማኅራዊ ፍትህ (ኢዜማ) ተወካይ አቶ አብርሃም ደስታ፣ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ወደ ሥልጣን ሲመጡ የአንድ ዶላር የምንዛሪ ዋጋ ከነበረበት 28 ብር አሁን ወደ 50 ብር መድረሱን በመጥቀስ በቀጣይ አሁን ላይ እየወጡ ያሉ መረጃዎች እንደሚያሳዩት ገበያ ላይ ያለው ምንዛሪ ወደ 65 ብር ሊደርስ እንደሚችል እየተነገረ መሆኑን አንስተዋል፡፡

ባለፉት ዓመታት ኢኮኖሚውን ለማረጋጋት አገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያዎች ላይ ዕርምጃ ተወስደዋል ቢባልም የዋጋ ግሽበቱና የኑሮ ውድነቱ ሊቀረፍ አለመቻሉንና ሕዝቡ በኑሮ ውድነት እየተሰቃየ መሆንኑን አቶ አብርሃም አንስተዋል፡፡

በመሆኑም መንግሥት የዋጋ ግሽበቱንና የኑሮ ውድነቱን እንዲስተካከል በተግባር የሚታይና ሕዝቡን አሁን ካለበት ችግር የሚያወጣ አሠራር ስለመኖሩ ጠቅላይ ሚኒስትሩን ጠይቀዋል፡፡

በሌላ በኩል የገዥው ፓርቲ ብልፅግና ፓርቲ ተወካይ አቶ ኑርዘማን ጅብሪል ኢትዮጵያ በተፈጥሮና ሰው ሠራሽ ፈተናዎች እያለፈች እንደሆነ በመግለጽ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ የመጣውን የኑሮ ውድነት ሕዝቡን በእጅጉ እያሰመረረው በመሆኑ ችግሩ ለሕዝቡ ሥጋት ሆኖ እንዳይቀጥል መንግሥት ምን ዓይነት ተግባራትን እያከናወነ ነው? ሲሉ ጥያቄ አቅርበዋል፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከአባላት ለተነሱ ጥያቄዎች ምላሽ ሲሰጡ ‹‹ምክር ቤቱ ከግምት ውስጥ እንዲያስገባና የዕይታ መነፀሩን ሊያስተካክል የሚገባው ባለፉት አራት ዓመታት ቀደም ሲል ከነበረው ጊዜ በተለየ ሁኔታ የገጠሙንን ከበድ ከበድ ያሉ ሰው ሠራሽና የተፈጥሮ ፈተናዎች መልሶ ማስታወስ ያስፈልጋል ነገር ግን እነዚህን ፈተናዎችና ችግሮችን በደንብ ካልተረዳን ዓውዱ ይበላሻል፤›› በማለት የመነሻ ሐሳብ አቅርበዋል፡፡

በመሆኑም እንዲህ ብሎ ነበር እንዲህ አልሆነም ብሎ ለማለት በተለየም በድንገት የተከሰቱ የተፈጥሮ ተግዳሮቶች የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ፣ አንበጣ፣ ድርቅ፣ ጎርፍ እንዲሁም ሰው ሠራሽ የሆኑ ችግሮች በአገር ውስጥ አገሪቱን የገጠማት ውጊያ፣ የራሽያና ዩክሬን ግጭትና ያልተገባ የውጭ ጫናዎቻቸውን በደንብ ማስተዋል ሲቻል፣ ከዕቅዶቻችን ምን ያህሉን አሳካን፣ ምን ያህሉን ደግሞ አልተሳካምና የገጠሙንን ፈተናዎች እንዴት አለፍናቸው ብሎ ለመገምገም ይረዳል ሲሉ ማብራሪያ ሰጥተዋል፡፡

ይሁን እንጂ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ‹‹የሪፎርም ሥራችን ለማመን የሚከብዱ ውጤቶች እያመጣ ነው፣ ለእናንተ አይደለም ለእኔ ለራሴ የሚገርሙ፣ በፈጣሪ ቸርነት ደግነት የሚከናወኑና የመጨረሻ ውጤት የሚታይባቸው አስደማሚ ውጤቶች በሪፎርሙ እየመጡ ነው፤›› ብለዋል፡፡

በማኅበራዊ ሚዲያ ዩቱብና ፌስቡክ ላይ የሚወራውን ሳይሆን መሬት ላይ ያለውን ውጤት በመንገድ፣ በትምህርት፣ በቴሌኮም፣ በኢትዮጵያ አየር መንገድ፣ በግብርና፣ በኢንዱስትሪና ንግድ እንዲሁም በውጭ ምንዛሪ ረገድ ተገኙ ያሏቸውን መልካም ውጤቶች አብራርተዋል፡፡

ከ15 ዓመት በፊት የውጭ ንግድ አንድ ቢሊዮን ዶላር ገባ ብሎ የኢትዮጵያ ካቢኔ ሻምፓኝ ከፍቶ ማክበሩን የገለጹት ጠቅላይ ሚነስትሩ፣ ዛሬ ላይ ወደ ውጭ የሚላከው የኢትዮጵያ ቡና ብቻ አንድ ቢሊዮን ዶላር መግባቱን ተናግረዋል፡፡ ይሁን እንጂ ከለውጡ በፊት የኢትዮጵያ ንግድ ለሰባት ዓመታት ማደግ አቅቶት እያሽቆለቆለ የነበረ ቢሆንም ባለፉት ሁለት ዓመታት በተደረገ የለውጥ ሥራ በሁለት ዓመታት ውስጥ ወደ አራት ቢሊዮን ማድረሱን አክለው ገልጸዋል፡፡

የብር ከዶላር ጋር ያለውን የምንዛሪ መጠን ማሽቆልቆልን በተመለከተ ሲናገሩ፣ አሁን እየታየ ላለው ለውጥ መምጣት ብር ከዶላር ጋር ያለውን መጠን መቀነስ በመቻሉ እንደሆነና በዚህም ሥራ አገሪቱ የነበረባትን ዕዳ መክፈል መቻሏን፣ ወደ ውጭ የሚለካው ምርትና አገልግሎት መጠን እንዲጨምር ማድረጉን፣ የውጭ ኢንቨስትመንት መሳቡን፣ ከውጭ የሚላከው ሪሚታንስ ከፍ ማለቱን አብራርተዋል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ትኩስ ጽሑፎች

ተዛማጅ ጽሑፎች

- Advertisement -
- Advertisement -