Monday, March 4, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
የሳምንቱ ገጠመኝየ ሳ ም ን ቱ ገ ጠ መ ኝ

የ ሳ ም ን ቱ ገ ጠ መ ኝ

ቀን:

እንዲያው ያለንበት ጊዜ አንዳንድ ድርጊቶች ሲታክቱኝ ወደኋላ ሄጄ ያለፍንበትን ዘመን አስታውሳለሁ፡፡ በዚያ መነሻም እናንተም እንደ እኔ ዘመናችንን ታስቡ ዘንድ ይህንን ጻፍኩ፡፡ የዛሬ 40 ዓመታት ገደማ ብሔራዊ ቴአትር ‹‹የአዛውንቶች ክበብ›› የተሰኘውን ቴአትር ለማየት እሄዳለሁ፡፡ እንደተለመደው ሠልፍ ይዤ ቲኬት ለመቁረጥ ስጠባበቅ ድንገተኛ ትርምስ ተፈጠረ፡፡ ሦስት ወጠምሻ ጎረምሶች አንዱን የእኔ ቢጤ ኮሳሳ እያዳፉ ከሠልፉ መሀል አውጥተውት፣ መንገዱ ዳር ላይ የቆመ ላንድሮቨር መኪና ውስጥ አስገቡት፡፡ በድንገተኛው ትርምስ የተደናገጡ ሰዎች ከሠልፉ መሀል ወጥተው በተረባበሸ ስሜት ውስጥ ሆነው ሲሄዱ፣ እኔም የእነርሱ ስሜት ተጋብቶብኝ ወደ ራስ ሼል አቅጣጫ አመራሁ፡፡

ራስ ሼል ገብቼ ቀዝቃዛ ቢራ አዝዤ ምን ይሆን የተፈጠረው? በማለት ወደኋላ ዓመታትን እየቆጠርኩ ማሰብ ጀመርኩ፡፡ በዘመነ ቀይ ሽብር የተፈጸሙ ጭፍጨፋዎችና የጅምላ እስራቶችን እያስታወስኩ፣ በተለይ ያለቁትን የሠፈሬን ልጆች ማሰብ ጀመርኩ፡፡ ታሪኩ፣ አሸናፊ፣ ምንተስኖት፣ ያሬድ፣ አበባ፣ ጋሻው፣ ተስፋዬ፣ ሰለሞን፣… በቀይ ሽብር የተጨፈጨፉ ወገኖቼን ሳስብ ከየት መጣ ያላልኩት እንባ ከዓይኖቼ ላይ ተዘረገፈ፡፡ ከእነሱና መሰል ወገኖቻችን ዕልቂት በኋላ አገሪቱ የሐዘን ማቅ ለብሳ፣ ትውልዱም ሞራሉ ላሽቆ አንገታችንን ደፍተን መኖራችንን ሳስበው እልህና ሳግ የተሞላበት በስቅስቅታ የታጀበ ድምፅ ከውስጤ ሲወጣ ባሩ ውስጥ የነበሩ ሁሉ ደነገጡ፡፡

አንዱ አስተናጋጅ ተንደርድሮ መጥቶ፣ ‹‹ጋሼ ምን ነካህ? በሰላም መጥተህ ምን ገጠመህ?›› እያለ እንደ ማፅናናትም፣ እንደ ግራ መጋባትም ሆኖ ጠየቀኝ፡፡ የብዙዎቹ ዓይኖች እኔ ላይ መሆናቸውን ካረጋገጥኩ በኋላ፣ ‹‹እንዲያው ነው እባክህ… እናቴ ናፍቃኝ ነው…›› ብዬ ድምፄን ከፍ አድርጌ ስናገር፣ ከሁሉም ማለት ይቻላል የማስተዛዘኛ ምልክት የሆነው በከንፈር የሚገለጸው ድምፅ ተሰማኝ፡፡ አስተናጋጁም፣ ‹‹ይኼ ከሆነ ሄደህ ጠይቃቸው፣ አይዞህ…›› እያለ አፅናንቶኝ ሄደ፡፡ ውስጤ እየተንገበገበ የቀረበልኝን ቢራ ጠጥቼ ሒሳቤን ከፍዬ ወጣሁ፡፡

- Advertisement -

Video from Enat Bank Youtube Channel.

እንዲህ ዓይነቱን የተረበሸ ስሜት የፈጠረብኝ የዚያ ሰው በሦስት ሰዎች እየተገፈተረና እየተጎሸመ በደኅንነት ላንድሮቨር መወሰድ ነበረ፡፡ ከዓመታት በፊት በወታደር ካሚዮኖች እየተጫኑ እየተወሰዱ በርካታ ወጣቶች የደረሱበት እንደማይታወቀው ሁሉ፣ የዚህም ሰውም ዕጣ ፈንታ በጣም አሳዘነኝ፡፡ ‹‹የደርጉ መኪና ሸራ የለበሰው፣ ተራማጁን ምሁር ወዴት አደረሰው?›› ተብሎ በተዘመረባቸው ዓመታት በሺዎች የሚቆጠሩ ወጣቶች አልቀዋል፡፡ ከብሔራዊ ቴአትር በራፍ ላይ ታፍኖ የተወሰደው ያ ምስኪን ወገኔ ማን እንደሆነ ሳላውቀውና የት እንደደረሰ ሳይታወቅ ከ40 ዓመታት በላይ ነጉደዋል፡፡ በቀደም ዕለት በብሔራዊ ቴአትር በኩል ሳልፍ ነው ያ ሁሌም ከውስጤ የማይወጣው ወጣት ጉዳይ የበለጠ ትዝ ብሎኝ ይኼንን ያጻፈኝ፡፡

እኔ ከዚያ ክስተት በኋላ ብሔራዊ ቴአትር አንድም ቀን ገብቼ አላውቅም፡፡ ደጁ ስደርስ ያ ትውስታዬ ይቀሰቀስና ጥፋ ጥፋ ይለኛል፡፡ በቀደም ዕለትም በፍጥነት አልፌ ነው ራስ ሆቴል በረንዳው ላይ የደረስኩት፡፡ ወንበር ስቤ ከተቀመጥኩ በኋላ ቡና አዝዤ እንደተለመደው ስልኬን አውጥቼ የጽሑፍ መልዕክት መቀበያውን ማየት ጀመርኩ፡፡ አንድ ጓደኛዬ ድሮ የምናውቀውን የፖለቲካ ቀልድ ከሆነ ነገር ጋር አያይዞ ስለላከልኝ ማንበብ ጀመርኩ፡፡ አንብቤ ስጨርስ ብቻዬን ያለሁ ይመስል እንደ አበደ ሰው እየጮህኩ ስስቅ… በአካባቢዬ ያሉ ሰዎች ደንግጠው ያዩኛል፡፡ ከዓመታት በፊት ስቅስቅ ብዬ ያለቀስኩበት አካባቢ ዛሬ እንደ ወፈፌ ከጣራ በላይ መሳቄ እኔንም ገረመኝ፡፡ ለማንኛውም ቀልዱ ይኼ ነው፡፡

አንድ አሜሪካዊ ሩሲያን ለመጎብኘት በቱሪስት ቪዛ ይሄዳል፡፡ ሞስኮ ደርሶ ክሬምሊን ቤተ መንግሥት አካባቢ በእግሩ እየተዟዟረ ሳለ ከአንድ ሩሲያዊ ወጣት ጋር ይገናኛሉ፡፡ አሜሪካዊው ሰላም ሲለው ያኛውም በአሪፍ እንግሊዝኛ ለሰላምታው ምላሽ ይሰጣል፡፡ በዚህ ይግባቡና ጨዋታ ይጀምራሉ፡፡ ሩሲያዊው እንግዳውን በሚገባ ከተማውን ካስጎበኘው በኋላ የተለመደውን መስተንግዶ ያደርግለታል፡፡ ታዋቂ የሞስኮ መጠጥ ቤት ወስዶት ተወዳጁን ቮድካ ይጋብዘዋል፡፡ ቮድካውና ጨዋታው ሲደራ ፖለቲካ ይጀመራል፡፡

አሜሪካዊው፣ ‹‹የእኛ አገር ዴሞክራሲ ከእናንተ በፍፁም የተለየ ነው፡፡ ዴሞክራሲያችን ለሰው ልጆች የመናገር፣ የመጻፍ፣ የመሰብሰብ፣ የመቃወምና የመሳሰሉትን መብቶች አጎናፅፏል፡፡ የፈለግከውን ብትናገር ማንም ዞር ብሎ አያይህም፡፡ እኔ አሁን ከፈለግኩ ዋይት ሐውስ በራፍ ላይ ሄጄ ‹ሬገን ሌባ› ብዬ መሳደብ እችላለሁ…፡፡ ይኼ የአሜሪካ ዴሞክራሲ ለዓለም በሙሉ ትልቅ ምሳሌ ነው፡፡ አንተ አሁን እንደ እኔ መብት አለህ?›› ይለዋል፡፡ ሩሲያዊው አሜሪካዊው ተናግሮ ከጨረሰ በኋላ ከት ብሎ ይስቃል፡፡ አሜሪካዊው ተገርሞ፣ ‹‹ምን ያስቅሃል?›› ሲለው፣ ሩሲያዊው፣ ‹‹እንዴት ተቀለደ እባክህ? እኛም አገር ያለው ዴሞክራሲ ያው እንደናንተ ነው…›› ብሎ ይስቃል፡፡ አሜሪካዊው፣ ‹‹እንደ እኛ የአገር መሪ መሳደብ ትችላላችሁ?›› በማለት በትዝብት ሲያየው፣ ሩሲያዊው አሁንም እየሳቀ፣ ‹‹እኔ ከፈለግኩኝ አሁን ዓይንህ እያየ ክሬምሊን በራፍ ላይ ሆኜ ‹‹ሬገን ሌባ!›› ማለት እችላለሁ፤›› ሲለው የአሜሪካኑ ሳቅ ዋሽንግተን ድረስ ተሰማ አሉ፡፡

ይኼንን ዕድሜ የጠገበ ቀልድ ሳስብ ስንትና ስንት ደም በተገበረባት አገር፣ ስንቶች በልጆቻቸው ዕልቂት ምክንያት ማቅ በለበሱባት አገር በዴሞክራሲ ሲቀለድ አዝናለሁ፡፡ በቀይ ሽብር የተፈጁትም ሆኑ ለዴሞክራሲ ሲሉ ክቡር ሕይወታቸውን የሰጡት መስዋዕትነት ተንቆ፣ እንደ ሩሲያዊው ዓይነት በስመ ዴሞክራሲ ተንሰራፍቶ ሲቀለድ ያማል፡፡ እኔ እንኳ እነዚያ ለዴሞክራሲ ሲሉ የወደቁ የሠፈሬ ልጆች ‹ትዝ› ሲሉኝ አሁንም ድረስ ውስጤ ይታወካል፡፡ ዴሞክራሲ ለማስፈን ሲታገሉ የወደቁ ወንድሞቻቸውን ሬሳ ተራምደው ዛሬ በሕይወት ያሉት በዴሞክራሲ ሲቀልዱና በሙስና እስከ አንገታቸው ሲነከሩ ከማየት የበለጠ ምን ዓይነት በሽታ ይኖር ይሆን…? እኔ ግን ያመኛል፡፡ እናንተስ?

(ተፈራ ተዘራ፣ ከቤላ)

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የአዲስ አበባ ነዋሪዎች ቁጥር ሲጨምር የሚኒባስ ታክሲዎች ቁጥር እየቀነሰ መምጣቱ ሊታሰብበት ይገባል

በአዲስ አበባ ከተማ የትራንስፖርት አገልግሎት በመስጠት ከፍተኛ የሚባለውን ድርሻ...

ሃምሳ ዓመታት ያስቆጠረው አብዮትና የኢትዮጵያ ፖለቲካ ውጣ ውረድ

የኢትዮጵያ ሕዝቦች የዴሞክራሲ ለውጥ ጥያቄ የሚነሳው ከፋሺስት ኢጣሊያ ወረራ...

በአዲስ አበባ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት የተፈጸመው ሕገወጥ ተግባር ምንድነው?

የአዲስ አበባ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት የዳይሬክተሮች ቦርድ፣...

በአዲስ አበባ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት ላይ ምርመራ እንዲደረግ ውሳኔ ተላለፈ

ፕሬዚዳንቷና ዋና ጸሐፊው ተጠያቂ ሊሆኑ ይችላሉ ተብሏል ከአዲስ አበባ ንግድና...