Monday, April 15, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
እኔ የምለዉበኢትዮጵያ ዘረኝነት አለ?

በኢትዮጵያ ዘረኝነት አለ?

ቀን:

በሙሉጌታ ኢተፋ (ዶ/ር)

በዚህ ጥያቄ ላይ ብዙ መወያየትና ብዙ መከራከር ይቻላል፡፡ የዘረኝነትን ምንነት በትክክል ማወቅና ማሳወቅ ተገቢ ነው፡፡ ወደ ውይይቱ ከመግባቴ በፊት በርዕሱ ላይ የእኔን አቋም መግለጽ አስፈላጊ ይመስለኛል፡፡ አቋምን ግልጽ አድርጎ መቀጠል ለአንባቢ ይበጃል፡፡ ዘረኝነት በኢትዮጵያውያን መሀል ማለታችን እንደሆነ መታወቅ ይኖርበታል፡፡ በጣሊያን ወረራ ጊዜ ዘረኝነትን ለማስፈን ብዙ ተሞክሮ ነበር፡፡ ለምሳሌ አዲስ አበባን ብንወስድ፣ መርካቶን የአገሬው ሕዝብ መኖሪያ ለማድረግና የቀሩትን ቦታዎች ደግሞ ለጣሊያኖች ለማድረግ አቅደው እንደነበረና ዕቅዳቸውን ሙሉ በሙሉ ሥራ ላይ ለማዋል ዕድል ሳያገኙ ተሸንፈው ከአገር ተባረሩ፡፡ ይህ አካባቢ አንዳንዴ በዘልማድ ‹‹መርካቶ ደጂኖ›› እየተባለ ሲጠራ ይደመጣል፡፡ በወቅቱ ጣሊያኖች ‹‹መርካቶ እንደጂኖ›› ብለው ስለሰየሙት ነበር፡፡ ‹‹ እንደጂኖ›› በጣሊያንኛ ‹‹የአገሬው ሰው›› እንደ ማለት ነው፡፡

ጣሊያኖች ኢትዮጵያውያንና ጣሊያኖችን በማለያየት ብቻ አልቆሙም፡፡ ኢትዮጵያውያንን በተለይ ደግሞ ኦሮሞና አማራን ለመለያየትና ለማጣላት ያልሞከሩት ነገር አልነበረም፡፡ አብዛኛው የኢትዮጵያ በተለይ ደግሞ አርበኞች አንከፋፈልም በማለታቸው ዕቅዳቸው ሳይሳካ ቀርቷል፡፡

- Advertisement -

Video from Enat Bank Youtube Channel.

ከዚህ በፊት በአንድ ስብሰባ ላይ ዘረኝነት በኢትዮጵያ እንዳልነበረ፣ አሁንም እንደሌለና ለወደፊትም የሕዝብ ስብጥር (demography) ካልተለወጠ በስተቀር እንደማይኖር ገልጬ ነበር፡፡ አሁንም ይህ አቋሜ አልተለወጠም፡፡ ይህን አቋም ለማጠናከር ክርክሩን በሚከተለው መልክ ለማቅረብ እሞክራለሁ፡፡

ዘረኝነትና የዘረኝነት ሁኔታ በዓለም አቀፍ ዕውቀትና ደረጃ መታየት አለበት፡፡ ዘረኝነት በእንግሊዝኛ ቋንቋ “Racism” የሚባለው ነው፡፡ ዘረኝነት በዘሮች መካከል በዓለም ደረጃ ተንሰራፍቶ ይገኛል፡፡ በመስኩ የተካኑ የዓለም ሊቃውንት ዘርን በአራት ይከፍሉታል፡፡ ይኸውም ጥቁር ዘር፣ ነጭ ዘር፣ ቢጫ ዘርና ቡናማ ዘር በማለት፡፡ የመጀመሪያዎቹ ሦስቱ ግልጽ ናቸው፡፡ ቡናማ (brown) ዘር የሚባለው ግን እነ ማንን ይመለከታል ብሎ መጠየቅ ተገቢ ይመስለኛል፡፡ ይህ አባባል ጥቁር ያልሆኑትንና ነጭ ያልሆኑትን ላቲን አሜሪካኖችንና ዓረቦችን ይመለከታል፡፡

የሰው ዘርን በተመለከተ በአንድ ወቅት በሦስት ከፍለውት ነበር፡፡ ለአከፋፈሉ የአማርኛ ቃላት ስለሌሉ እነሱ የተጠቀሙባቸውን ስያሜ መጠቀሙ ግድ ይላል፡፡ በደንብ መጤን ያለበት የጥቁር ዘርን ለሁለት በመክፈል ኒግሮይድና ኮኬሸይድ (ኮኬሽያን) ያደርጓቸዋል፡፡ በ1960ዎቹ መጀመሪያ ገደማ ለትምህርት ወደ አሜሪካ የሄድን ሰዎችን ፀጉራችንና አፍንጫችንን እያዩ ኮኬሽያን ናችሁ ይሉናል፡፡ ነጮችና ቡናማዎቹም እዚህ ውስጥ ይካተታሉ፡፡ ክፍፍሉን ኒግሮይድ፣ ኮኬሽያድና ሞንጎሎይድ ይሉታል፡፡

ነጮች ከራሳቸው ጋር ያደረጓቸውን ከፊል ጥቁሮችንና ቡናማዎችን የዘረኝነት ሰለባ ማድረጋቸው አልቀረም፡፡ ኒግሮይድና ሞንጎሎይድን ጨምሮ ሁሉም የዘረኝነት ሰለባ ናቸው ማለት ነው፡፡ ኮኬሽያን የሚባል ክፍፍል ኒግሮይድንና ሞንጎሎይድን ለብቻ ነጥሎ፣ ጥቁሮችን ለሁለት በመክፈልና በማሳነስ የነጮችን ወገን ማብዛት ላይ የተመሠረተ የማደናገሪያ ዘዴ ከመሆን የዘለለ አይደለም፡፡ በተግባር ላይ ያልዋለ ውጤት ያላመጣ አስተሳሰብ ስለነበር፣ ቀደም ብለን የጠቀስናቸው አራቱ ክፍፍል የበለጠ ትርጉም ስላለው ትኩረታችን በዚህ አቅጣጫ ማድረግ ይገባል፡፡

በግልጽ ለማስቀመጥ ያህል ዘረኝነት አንድ የጥላቻ ዓይነት ነው እንጂ ጥላቻ ሁሉ ዘረኝነት አይደለም፡፡ ዘረኝነት በዘሮች መካከል የሚከሰት መናናቅ፣ መገለልና መናቆር ነው፡፡ ዘረኝነት በአሜሪካ ጥቁሮችን ገድሎ አስከሬናቸውን የመስቀል ድርጊትን ይጨምራል፡፡ ጥቁሮችን ገድሎ አስከሬን መስቀል እነሱን የበለጠ ለማሸበርና ለማስፈራራት የሚያደርጉት ክስተት ነው፡፡ ክስተቱ በእንግሊዝኛ ሊንችንግ (lynching) ይሉታል፡፡ አሁንም በ21ኛው ክፍለ ዘመን አሜሪካኖች ስለሊንቺንግ ያወራሉ፡፡ በቅርቡ ፕሬዚዳንት ጆ ባይደን ሊንቺንግ የፌደራል መንግሥት ወንጀል እንዲሆን የሚደነግገውን ሕግ ፈርመውታል፡፡ ሁኔታዎች አሁንም ሊንቺንግ መከሰት እንደሚችል ያመለክታሉ፡፡ ሊንቺንግ ነጮች በጥቁሮች ላይ የሚያደርሱት ግፍና ሰቆቃ ነው፡፡ በነጮች መካከል ዘረኝነት አይኖርም፣ እንዲሁም በጥቁሮችና በሌሎች ዘሮች መካከል ዘረኝነት አይኖርም፣ በእያንዳንዱ ዘር መካከል ሌላ ዓይነት ጥላቻ መኖሩ ግልጽ ነው፡፡

የጥላቻን ሁኔታ ወደ ኢትዮጵያ ስናመጣ እንዳለመታደል ሆኖ አክራሪ ብሔርተኝነት፣ ጎጠኝነት፣ ጽንፈኝነት፣ ጐሰኝነትና ከፋፍሎ የመግዛት አባዜ ለዘመናት ነበሩ፣ አሁንም አሉ፡፡ ከበቂ በላይ ትኩረትን የሚሹ ችግሮች ስላሉን ዘረኝነትን መጨመር አያስፈልግም፡፡ ሰዎች በቆዳቸው ቀለም ብቻ የዘረኝነት ሰለባ ይሆናሉ፡፡ ሌላ ዓይነት ጥላቻ ግን በማየት ብቻ ሊከሰት አይችልም፡፡ ይልቁንስ በአንድ ዓይነት ዕውቀት ላይ የተመሠረተ ነው፡፡ ለምሳሌ አንድ ጎጠኛ ከአንድ አካባቢ የመጡትን የሚጠላ ከሆነ እንዲሁ ዓይቶ ከየት እንደመጡ ሊያውቅ ስለማይችል፣ በአንድ ዓይነት መንገድ ሰዎቹ ከየት እንደመጡ ማወቅ ይኖርበታል፡፡ ይህ አባባል ለጽንፈኛም፣ ለአክራሪ ብሔርተኛና ለሌሎችም በማንነት ላይ የተመሠረተ ጥላቻን ለሚያካሄዱ ይሠራል፡፡ የጥላቻ ሰለባ መሆንንና የዘረኝነት ሰለባ መሆንን ለይቶ ማየትና መፍትሔ መፈለግ ያስፈልጋል፡፡

የጥላቻ ሰለባ የመሆን መንገዶች ብዙ ናቸው፡፡ በኢትዮጵያ በብሔር ማንነት ብቻ ሳይሆን፣ በሙያ ማንነትም ሰዎች የጥላቻና የመገለል ሰለባ ይሆናሉ፡፡ ለምሳሌ በጣም የምንመካባቸውንና የምንኮራባቸውን ነገሮች የሚሠሩ ባለሙያዎች የጥላቻና የመገለል ሰለባዎች ነበሩ፡፡ አሁንም በብዙ አካባቢዎች ሁኔታው እንዳለ ይታወቃል፡፡ እነዚህም አናጢዎችን፣ ፋቂዎችን፣ ሸማኔዎችን፣ ቀጥቃጮችንና ሸክላ ሠሪዎችን ያካትታል፡፡ እነዚህ ሰዎች ግን የዘረኝነት ሰለባዎች አይደሉም፡፡ ከሁሉም ብሔር ውስጥ የሚገኙና ከሌሎች ኢትዮጵያውያን ጋር የሚመሳሰሉ በጣም ጠቃሚ ሥራዎችን የሚሠሩ እንደ ሌላው ሁሉ የጥቁር ዘር ናቸው፡፡

ዘርፈ ብዙ ጥላቻዎችን በትምህርትና በትግል ማስወገድ ነው እንጂ፣ የሌለብንን ዘረኝነትን መጨመር አያስፈልገንም፡፡ ባለማወቅና በተንኮል ላይ የተመሠረቱ ጥላቻንና ማግለልን ማስወገድ ከሰው ልጅ መብት አንፃርም ሆነ፣ ለአገር ዕድገት በጣም አስፈላጊ ስለሆነ ልንረባረብበት ይገባል፡፡

በአሁኑ ጊዜ በዩክሬን አፍሪካውያንና እስያውያን በመልካቸው ብቻ ከጦርነት ለመሸሽ በሚሞክሩበት ጊዜ እየተከለከሉ የዘረኝነት ሰለባ እየሆኑ ነው፡፡ በመሠረቱ እነዚህ ሰዎች የዩክሬንም ዜጋ ሊሆኑ ስለሚችሉ እንደ ሌላው ሁሉ አገልግሎት ማግኘት ሲገባቸው፣ በቆዳ ቀለማቸው ብቻ የዘረኝነት ሰለባ እየሆኑ ነው፡፡ ‹‹በእንቅርት ላይ ጆሮ ደግፍ›› እንደሚባለው የዘረኝነት ሰለባ መሆንና መገለል አንሷቸው የስድብ ውርጅብኝም እየደረሰባቸው ነው፡፡ ‹‹የሠለጠኑትን ዩክሬናውያንን ነው ወደ ፖላንድ የምናስገባቸው›› እያሉ ያወርዷቸዋል፡፡ ጥቁሮች ዘረኝነትን መጋፈጥ ከጀመሩ ብዙ ዘመናት አልፈዋል፡፡ በዓለም አካባቢ ሁሉ ትግሉ እንደቀጠለ ነው፡፡

በአገራችን ያለውን መናቆር በትክክለኛ ስሙ መጥራት ተገቢ ብቻ ሳይሆን፣ በዓለም ያለውን ሁኔታ በተገቢ መንገድ እንድንገነዘብ ይረዳል፡፡ በዓለም አቀፍ ደረጃ ዘረኝነት በምን መልክ ይታያል የሚለውን ማጤን እውነታውን ይበልጥ ሊያንፀባርቅ ይችላል፡፡ ለምሳሌ ሁለት ሰዎች (ከተለያዩ የኢትዮጵያ ብሔሮች የወጡ) አሜሪካ አገር ሄደው አንዱ የሌላው የዘረኝነት ሰለባ ነኝ ቢላቸው በጣም ግራ ይገባቸዋል፡፡ ለእነሱ ሁለቱም የጥቁር ዘር ስለሆኑ ልዩነት የላቸውም፡፡

በኢትዮጵያ ለሰው ቆዳ ቀለም በጣም ትኩረት እንሰጣለን፡፡ ጥቁር፣ ጠይም፣ ቀይ ዳማ፣ ቀይና በጣም ቀይ እያልን እንለያቸዋለን፡፡ ለዘረኞች ግን ሁሉም ጥቁሮች ናቸው፡፡ ከዚህ ጋር ተያይዞ ዩታ የነበሩ ኢትዮጵያውያን ተማሪዎች የነገሩኝን ብገልጽ፣ አሜሪካውያንና ኢትዮጵያውያን ስለቆዳ ቀለም ያላቸውን ልዩነት በደንብ ያስገነዝባል፡፡ አንዲት አሜሪካዊ ፕሮፌሰር ከኢትዮጵያውያን ጋር ሆና እያለች አንዱ ኢትዮጵያዊ ተማሪ ‹‹ጥቁሩን ልጅ ዓይተሻል?›› ሲላት ግራ ይገባትና ትደነግጣለች፡፡ ለፕሮፌሰሯ አጠገቧ የነበሩ ኢትዮጵውያን ሁሉ ጥቁሮች ናቸው፡፡ ዩታ አሜሪካን አገር ካሉ ክፍለ አገሮች በዘረኝነት ከሚታወቁ መሀል ነች፡፡

የዩታ ሰዎች ሞርሞን የሚባል ሃይማኖት ተከታዮች ናቸው፡፡ በአንድ ወቅት የሞርሞን መጽሐፍ ቅዱስ ለማንበብ ሞክሬ ነበር፡፡ ሃይማኖቱ ራሱ ከዘረኝነት ጋር የተያያዘ ነው፡፡ ከመጽሐፍ ቅዱሳቸው በአሁኑ ጊዜ አንድ በጣም የምትገርም ነገር ብቻ አስታውሳለሁ፡፡ ስለጽድቅ ሲናገር ጥቁር ሊፀድቅ ይችላል፣ ነገር ግን ነፍሱ በፓርጋቶሪ ቆይታ ከነጣች በኋላ ነው የሚፀድቀው ብለው ያምናሉ፡፡ እንደዚህ ዓይነት ዘረኝነት ባለበት አካባቢ ስለቆዳ ቀለም ልዩነት መናገር ስለማይበጅ ሁኔታውን መገንዘብ ብቻ ይበቃል፡፡

ከቆዳ ቀለም ጋር በተያያዘ በካይሮ የገጠመንን ነገር እዚህ መግለጽ ተገቢ ይመስለኛል፡፡ በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት በካይሮ የተዘጋጀ በሕዝብ ብዛት ላይ የሚወያይ ስብሰባ ተደርጐ ነበር፡፡ በዚህ ስብሰባ ለመሳተፍ ዶ/ር ዱሪ መሐመድና እኔ ከአቶ ታምራት ላይኔ ጋር ወደ ካይሮ ስንሄድ፣ አምባሳደር ተሾመ ቶጋ ደግሞ በግብፅ የኢትዮጵያ አምባሳደር ስለነበረ ተቀላቅሎን አራታችን የቡድን አባል ሆነን በስብሰባው እንሳተፍ ነበር፡፡ ከስብሰባው ጎን የተለያዩ ባለሥልጣናትን ማነጋገር ስለነበረብን፣ መጀመሪያ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ዋና ጸሐፊ ክቡር ዶ/ር ቡጥሮክ ቡጥሮስ ጋሊንና ክቡር ፕሬዚዳንት ሆስኒ ሙባረክን ካነጋገርን በኋላ፣ ቀጠሯችን ከግብፅ ጠቅላይ ሚኒስትር ጋር ነበር፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትሩ በጣም ሽማግሌ ነበሩ፣ በጥሩ ጨዋታና ቀልድ ተቀብለውን አስተናገዱን፡፡ በአቶ ታምራት ላይኔ መሪነት በቢሮአቸው ሆነን በምንወያይበት ወቅት የአቶ ታምራትን እጅ ለቀም አድርገው እጃቸው ጎን በማስቀመጥ፣ ‹‹ተመልከቱ እኛ ከአንድ ወንዝ የምንጠጣ ብቻ ሳይሆን አንድ ሕዝብ ነን›› አሉ፡፡ በቅላት የማንታማ ሦስታችን ተያየንና ሳቅን፡፡ በልባችንም እኚህ ጠቅላይ ሚኒስትር እኛን መርሳታቸው እያስገረመን፣ በኋላም በሰፊው ተነጋገርንበት፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ለፖለቲካ ፍጆታ ግብፅና ኢትዮጵያ አንድ ሕዝብ መሆናችንን ቢገልጹም አንድ እንዳልሆነ ልባቸው ያውቃል፡፡ በመሠረቱ የኢትዮጵያውያን መልክና ቅላት ከዓረቦች መልክና ቅላት ይለያል፡፡ እውነታው ግብፆችም ጥቁሮችን የዘረኝነት ሰለባ እንደሚያደርጉ ይታወቃል፡፡ በዓለም አካባቢ ጥቁሮች የነጮች፣ የቢጫዎችና የቡናማዎች የዘረኝነት ሰለባ መሆናቸው በገሃድ ይታወቃል፡፡ በየጊዜውም ይዘገባል፡፡ እኛ ኢትዮጵያውያን በቆዳ ቀለማችን ምክንያት በየጊዜውና በየቦታው የዘረኝነት ሰለባ የነበርን፣ ዘረኝነት በኢትዮጵያ ውስጥ አለ ሲባል ያመናል፡፡ አሜሪካ በነበርኩ ጊዜ አንድ ኢትዮጵያን በደንብ አውቃለሁ ባይ ፕሮፌሰር፣ ‹‹ኦሮሞ ስለሆን ዘረኝነት ለአንተ እንግዳ አይደለም›› ሲለኝ፣ ዘረኝነት በኢትዮጵያ እንደሌለ ጠንከር ባለ ቋንቋ እንደገለጽኩለት ‹‹ትዝታና ዝምታ…›› በሚል በጻፍኩት መጽሐፍ ውስጥ በደንብ ገልጫለሁ፣ እዚህ አልደግምም፡፡

የሚገርመው ነገር እኔን ዘረኝነት በኢትዮጵያ አለ ብሎ ሊያሳምነኝ የሞከረ ሰው ዓይነት፣ አሜሪካ ያሉትን አንዳንድ ኢትዮጵያውያን ኢትዮጵያ ያሉትንም (ጋዜጠኞች ጭምር) ዘረኝነት በኢትዮጵያ እንዳለ ያሳመናቸው ይመስላል፡፡ ምክንያቱም እነሱም ኢትዮጵያ ውስጥ ዘረኝነት እንዳለ አድርገው ይገልጻሉ፡፡

በማንነት ላይ የተመሠረተ ኢትዮጵያ ውስጥ ያለውን መናቆር ተንኮለኞች ነጮች እንደ ዘረኝነት በመቁጠር፣ እነሱ አገር ያለው ዘረኝነት በኢትዮጵያም እንዳለ ሊያሳምኑን ይፈልጋሉ፡፡ ይህ ሁኔታ የእነርሱን ‹‹ከፋፍለህ ግዛ›› ፖሊሲን ያመለክታል እንጂ የኢትዮጵያን ተጨባጭ ሁኔታ አይገልጽም፡፡

ዘረኝነት በኢትዮጵያ እንደሌለ ሲገለጽ የኢትዮጵያ ሁኔታና እውነታ እንከን የለውም ለማለት እንዳልሆነ ግልጽ መሆን አለበት፡፡ በአሁኑ ጊዜ በኢትዮጵያችን ከዘረኝነት የማይተናነስ ወይም የባሰ ነገር እየተከሰተ ነው፡፡ ይህ ደግሞ የበለጠ ያማል፡፡ ህሊና ያለው ሰው ማሰብ የማይችል ዓይነት ወንጀል እየተከሰተ ነው፡፡ ግን ዘረኝነት አይደለም፡፡ የጥቁር ዘር በጥቁር ዘር ላይ የሚያደርሰው አስከፊ ወንጀል ነው፡፡

በኢትዮጵያ ውስጥ ልዩ ልዩ ቋንቋዎች የሚናገሩ አንድ የጥቁር ዘር ነው ያለው፡፡ በአንፃሩ ደግሞ አሜሪካ ውስጥ አንድ ቋንቋ የሚናገሩ አራት ዘሮች አሉ፡፡ አንድ ቋንቋ በመናገራቸው ጥቁሮች፣ ቢጫዎችና ቡናማዎች የዘረኝነት ሰለባ ከመሆን አላዳናቸውም፡፡ በኢትዮጵያ ውስጥ ዘረኝነት ያልሆኑ ብዙ ዓይነት መገለሎች እንዳሉ ቀደም ሲል ተገልጿል፡፡ ሁሉንም በተገቢ ስማቸው መጥራት እውነታውን በተሻለ መንገድ ያንፀባርቃል፡፡ በዓለም አቀፍ ደረጃ ዘረኝነት አንድን ሰው በማየት ብቻ ይከሰታል፡፡ ሌላ ዓይነት ማግለል ግን ስለሰውዬው ማወቅን ይጠይቃል፡፡ ሁለቱም ማግለሎች አስከፊ ሊሆኑ ይችላሉ፡፡ ለማነፃፀር ሌላ ውይይትና ትኩረት ይሻል፡፡ እዚህ ላይ የተሞከረው ልዩነቱን ለመግለጽ ያህል ነው፡፡ ዘረኝነትን አታምጡብን ያሉብን ዘርፈ ብዙ ችግሮች ይበቁናል ለማለት ያህል ነው፡፡ ችግሮቻችንን በትምህርትና በትግል በአብሮነት መንፈስ ለማቃለል እንሞክር፣ የሌሎችን ችግር ወደ ኢትዮጵያ ማምጣት አያስፈልግም፡፡

ከአዘጋጁ፡- ጸሐፊው የኢትዮጵያ ሰላም ተቋም የቦርድ ሊቀመንበር ሲሆኑ፣ የቀድሞ ዲፕሎማቶች ማኅበር (Forum for The Study of Foreign Policy) ሦስት ዓመት በአባልነት ሰባት ዓመት በሊቀመንበርነት አገልግለዋል፡፡ በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት፣ በፈረንሣይ፣ በስፔን፣ በፖርቱጋል፣ በቫቲካንና በዩኔስኮ የኢትዮጵያ አምባሳደር ሆነው አገራቸውን አገልግለዋል፡፡ እንዲሁም በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በመምህርነትና በማታና በጐልማሶች ትምህርት በዲንነት አገልግለዋል፡፡ ጽሑፉ የእሳቸውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እየገለጽን፣ በኢሜይል አድራሻቸው [email protected] ማግኘት ይቻላል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ቪር ጀነራል ትሬዲንግ ኃ/የተ/የግ/ማኀበር የጨረታ ማስታወቂያ

ቪር ጀነራል ትሬዲንግ ኃ/የተ/የግ/ማኀበር በገቢ እና በውጭ ንግድ እንዲሁም...

ያልተቃናው የልጆች የንባብ ክህሎት

አንብቦና አዳምጦ መረዳት፣ የተረዱትን ከሕይወት ጋር አዋህዶ የተቃና ሕይወት...

እንስተካከል!

ሰላም! ሰላም! ውድ ኢትዮጵያውያን ወገኖቼ እንዲሁም የሰው ዘር በሙሉ፣...

የሙዚቃ ምልክቱ ሙሉቀን መለሰ ስንብት

የኢትዮጵያ ዘመናዊ ሙዚቃ በ1950ዎቹ እና በ1960ዎቹ በኪነ ጥበባትም ሆነ...