Monday, March 4, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
እኔ የምለዉየሰንደቅ ዓላማችን ጉዳይ ትኩረት የሚያሻው አገራዊ አጀንዳ መሆን አለበት!

የሰንደቅ ዓላማችን ጉዳይ ትኩረት የሚያሻው አገራዊ አጀንዳ መሆን አለበት!

ቀን:

በንጉሥ ወዳጅነው

ሰንደቅ ዓላማ የአንድ አገር ሕዝብ ልዩ መታወቂያ ምልክት ነው፡፡ ሕዝቦች ማንነታቸውን የሚያንፀባርቁበት፣ አንድነታቸውን የሚያሳዩበት፣ ማኅበራዊ ትስስራቸውን የሚያጎለብቱበትና የሉዓላዊነታቸው መገለጫ ነው፡፡ በዓለም ላይ በሰንደቅ ዓላማው የማይግባባና የማይኮራ ሕዝብ ስለመኖሩ እምብዛም ሲነገር ተስምቶ አያውቅም፡፡

ወደ አገራችን ሰንደቅ ዓላማ ስንመለስ ግን በኢትዮጵያ የታሪክ ጉዞዎች ሁሉ እንደ ዘመኑ አገርና ሕዝብን በመወከል ለረዥም ዘመናት መጓዙን ነው መረጃዎች የሚያመለክቱት፡፡ እውነት ለመናገር በቀደመው የኢትዮጵያ የሥልጣኔ፣ የታሪክና የአርበኝነት ወርቃማ ዘመን የኢትዮጵያን የታላቅነትና የሥልጣኔ ምልክት ማሳያ መሆን ችሏል፡፡

- Advertisement -

Video from Enat Bank Youtube Channel.

የመንግሥት ሥርዓቶች አስከፊ ጭቆና ያደርሱበት በነበረበት ወቅትም እንኳን፣ ሕዝቡ ብሔራዊ ሰንደቅ ዓላማውን በማስቀደም በጋራ ጠላቶቹ ላይ ድል ተቀዳጅቷል፡፡ ለሰንደቅ ዓላማ ክብርም ሲባል የቀደሙት አባቶች የሕይወትና የአካል መስዋዕትነት በመክፈልና የውጭ ወራሪዎችን ድል በማድረግ፣ አገራቸውንና ሰንደቅ ዓላማቸውን አስከብረው አሁን ላለው ትውልድ አስረክበዋል፡፡ ኢትዮጵያውያን ዛሬም ቢሆን ሰንደቅ ዓላማቸውን የሉዓላዊነትና የጀግንነት ምልክት ማድረጋቸው በገቢር የተረጋጋጠ ነው፡፡

ይሁንና አገራችን ፌዴራላዊ ሥርዓት መከተል ከጀመረችባቸው ካለፉት ሦስት አሠርት ዓመታት ወዲህ በሰንደቅ ዓላማ ዙሪያ የተዘበራረቁ ስሜቶች መንፀባረቃቸው አልቀረም፡፡ በአንድ በኩል ቀደም ሲል የነበረውን አረንጓዴ፣ ቢጫና ቀይ ዓርማ ከቀድሞ ሥርዓቶች ጋር አገናኝቶ የማየትና የጭቆና ምልክት አድርጎ መቁጠር ተለምዷል፡፡ በሌላ በኩል ሰንደቅ ዓላማው የታሪክና የሉዓላዊነት ዓርማ እንደ መሆኑ መቀየር የለበትም የሚለው ወገን ትንሽ አይደለም፡፡ በላዩ ላይ የተጨመረለት ዓርማም ብዙኃንን ያግባባ አይመስልም፡፡ በዚህ መሀል ደግሞ ሁሉም ክልሎች የየራሳቸው ሰንደቅ ዓላማና መዝሙር በሥራ ላይ መዋሉ የፈጠረው አዲስ ክስተት አለ፡፡

በምንገኝበት  የለውጥ ጅማሮ ዘመንም ቢሆን የኢትዮጵያውያንን የአስተሳሰብ ከፍታ ለማሳደግም ሆነ አንድነታችንን ለማጠናከር በሚደረገው ጥረት፣ የኢትዮጵያ ሰንደቅ ዓላማ የላቀ ሚና እንዳሚኖረው ይታመናል፡፡ ግን አሁንም ውዝግቡ ተባባሰ እንጂ ወጥና የጠራ አቋም የተያዘበት አይደለም፡፡ ስለዚህ በብሔራዊ የምክክር መድረኩም ላይ ሆነ በየትኛውም የሕዝብ ውይይት ረገድ የሰንደቅ ዓላማ ጉዳይ የጋራና በብዙኃኑ አመኔታ ያገኘ መግባባት ሊንፀባረቅበት ግድ ይላል፡፡

እኔም በዛሬው ጽሑፌ የብሔራዊ ሰንደቅ ዓላማን ጉዳይ አጀንዳ ያደረግንበት ዋነኛው ምክንያት፣ በአንድ በኩል ከአምስት ዓመታት በፊት በመንግሥት ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ጽሕፈት ቤት በኩል የተከናወንን የሕዝብ ዳሰሳ ጥናት ተጠቅሜ ለምክክሩ ግብዓት ለመስጠት ነው፡፡ በሌላ በኩል ውስጥ ለውስጥ ሕዝብ እየተብሰከሰክንባቸው ካሉ አጀንዳዎች መካካል፣ አንዱን አንስቶ ነፃና ዴሞክራሲያዊ የሆነ ምክክር በመፍጠር ወደ ዘላቂው ግብ ለመሸጋገር አጀንዳውን ለመቀስቀስ ነው፡፡

በኢፌዴሪ ሰንደቅ ዓላማና ብሔራዊ ዓርማ አጠቃቀም ላይ ኅብረተሰቡ ያለውን አመለካከት ለመፈተሽ የተካሄደ የሕዝብ አስተያየት (2009 ዓ.ም.) ባለ 54 ገጽ ወረቀት ጥናት እንደሚያስረዳው፣ አሁን በሥራ ላይ ያለው ኢትዮጵያ ሰንደቅ ዓላማ የዴሞክራሲያዊ አንድነትና ብሔራዊ ኩራት መገለጫ ነው፡፡ የኢትዮጵያ ብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች የታላቅነትና የሥልጣኔ ምልክት ማሳያ፣ ሕዝቦች ለነፃነትና ለእኩልነት ባደረጉት የረዥም ጊዜ ትግል የሕዝቦች ወኔና የብሩህ ተስፋ አመላካች፣ እንዲሁም የብሔራዊ ኩራትና የኢትዮጵያን የህዳሴ ጉዞ የሚያበስርም ነው፡፡

የኢፌዴሪ ሰንደቅ ዓላማ ከላይ አረንጓዴ፣ ከመሀል ቢጫ፣ ከታች ቀይ ሆኖ በመሀሉ ብሔራዊ ዓርማ እንደሚኖረው በሕገ መንግሥቱ ላይ በግልጽ ሠፍሯል፡፡ በሰንደቅ ዓላማው ላይ የሚቀመጠውን ብሔራዊ ዓርማ የኢትዮጵያ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦች፣ ሕዝቦችና ሃይማኖቶች በእኩልነትና በአንድነት ለመኖር ያላቸውን ተስፋ የሚያንፀባርቅም ነው ይላል ጥናቱ (ይሁንና በዚህ ዓርማ ላይ ጠንካራ መግባባት ባለመፈጠሩ፣ ኦፊሴላዊ ሰንደቅ ዓላማው፣ የእምነትና የድርጅት ዓርማዎች በመደበላላቀቸው የንትርክ ምንጭ ከመሆን አልዳነም)፡፡

ሕገ መንግሥቱን መሠረት አድርጎ በወጣው የሰንደቅ ዓላማ አዋጅ ቁጥር 654/2001 መሠረት ሰንደቅ ዓላማው የሪፐብሊኩ ሉዓላዊነትና የኢትዮጵያ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች በእኩልነትና በመፈቃቀድ ላይ የመሠረቱት ዴሞክራሲያዊ አንድነት ምልክት መሆኑን ይገልጻል፡፡ ከዚህ በተጨማሪም ሰንደቅ ዓላማው ላይ ያለው ዓርማ መካከል ላይ የሚያርፈውን የክብ ዙሪያ፣ የአረንጓዴውንና የቀዩን ቀለማት ቁመት አጋማሽ አካሎ እንደሚሆንና የሰንደቅ ዓላማው ወርድ የቁመቱ እጥፍ መሆን እንዳለበት በዝርዝር ሠፍሯል፡፡

አንዳንድ ተንታኞች ይህን በጋራና በሕግ የፀደቀ ዓርማ ሁሉም የአገራችን ዜጎች ተግባብተው ከፍ አድርገው ለመዘመርና ለማክበር ለምን ይቸገራሉ በማለት ይጠይቃሉ፡፡ በሌሎች የፌዴራል ሥርዓት የሚከተሉ አገሮች እንደሚሆኑትና እንደሚያደርጉት የክልሎች ባንዲራም ሆነ፣ የፓርቲ ወይም የድርጅት ዓርማዎች ከብሔራዊ ሰንደቅ ዓላማ ጋር ቁመት መለካካታቸው ምን ሊጠቅም ይችላል ብሎ መመርመር ያስፈልጋል፡፡ እንደ አገር መነጋጋርና መመካከር በአንድ አገራዊ ሰንደቅ መሆን ሥር ነው ያለበት፡፡

ወደ ጥናቱ ቁምነገሮች እንመለስ፡፡ በነገራችን ላይ የሕዝብ አስተያየት ዳሰሳ ጥናቱ አዲስ አበባን ጨምሮ፣ በተለያዩ ከተሞችና በሥራቸው ባሉ የገጠር ወረዳዎች የሚገኙ የኅብረተሰብ ክፍሎች የጽሑፍ መጠይቅ በመሙላት የተሳተፉበት ነበር፡፡ በአጠቃላይ 746 ሰዎች የጽሑፍ መጠይቆችን በመሙላት ተሳትፈዋል፡፡ መጠይቁን በመሙላት የተሳተፉት ዕድሜያቸው ከ18 ዓመት በላይ እንዲሆኑም ተደርጓል፡፡ ይህን ማድረግ ያስፈለገው በጉዳዩ ላይ የተሻለ ግንዛቤ እንዳላቸው እምነት በመያዙ መሆኑንም በመግቢያው ላይ ተገልጿል፡፡

በዳሰሳ ጥናቱ ቀዳሚ ጥያቄ መሠረት በቀደሞው የአገራችን ሰንደቅ ዓላማ  መሀል ላይ የኮኮብ ዓርማ መደረጉ የተስማማቸው ይሁን፣ አይሁን ለማወቅ ጥረት ተደርጎ ነበር፡፡ እናም በሥራ ላይ ባለው ሰንደቅ ሙሉ በሙሉ እንደሚስማሙ የገለጹት የጥናቱ ተሳታፊዎች 47.3 በመቶ፣ በከፊል የሚስማሙት 21.0 በመቶ፣ እንዲሁም በጭራሽ የማይስማሙት ደግሞ 28.4 በመቶ ናቸው፡፡ በተጨማሪ 3.2 በመቶ ደግሞ ምላሽ ያልሰጡ ነበሩ፡፡

በብሔራዊ ዓርማው ላይ በጭራሽ እንደማይስማሙ የገለጹትን የጥናቱ ተሳታፊዎች ከክልል አንፃር ስናይ እንደ ቅደም ተከተላቸው አዲስ አበባ፣ ደቡብ፣ አማራና ኦሮሚያ ክልሎች ይጠቀሳሉ፡፡ በብሔራዊ ዓርማው ላይ በጭራሽ የማይስማሙትን የጥናቱን ተሳታፊዎች ከዕድሜ አንፃር ስናይ ደግሞ፣ ዕድሜያቸው ከ18 እስከ 29 ዓመት ያሉት በአንፃራዊነት አብላጫውን ቁጥር ይዘው ተገኝተዋል፡፡

በዚህ ብሔራዊ ዓርማ ላይ በጭራሽ እንደማይስማሙ የገለጹት የጥናቱ ተሳታፊዎች፣ ላለመስማማታቸው የተለያዩ ምክንያቶችን አስቀምጠዋል፡፡ ሰንደቅ ዓላማው ላይ ያለው ዓርማ የአምልኮ ምልክት ነው ብለው እንደሚያስቡ የገለጹት 26.6 በመቶ፣ ሰንደቅ ዓላማው በኢትዮጵያ ሕዝብ ውሳኔ የፀደቀ አይደለም ያሉት 14.4 በመቶ፣ ሰንደቅ ዓላማው ላይ ያለው ዓርማ ከአገራችን ባህል፣ ታሪክና ቅርስ ጋር የሚዛመድ አይደለም ያሉት 14.4 በመቶ፣ እንዲሁም ሰንደቅ ዓላማችን ከድሮ ጀምሮ ምንም ምልክት የሌለው ነው የሚለውን ሐሳብ የሚደግፉት 32.9 በመቶ ሆነው ተገኝተው ነበር፡፡

ሌሎች ምክንያቶች ያሏቸው የጥናቱ ተሳታፊዎች ደግሞ 8.6 በመቶ ናቸው፡፡ እነዚህም ብሔራዊ ዓርማው ላይ ምሥል መቀመጡን፣ ሕገ መንግሥቱ በሕዝቡ ሁለንተናዊ ተሳትፎ የፀደቀ አለመሆኑን፣ በመጀመሪያ የነበረው ክፍተት አለመሞላቱንና የብሔር ብሔረሰቦች እኩልነት አለመኖሩን አውስተዋል፡፡

እንደዚያም ሆኖ አስተያያት ሰጪዎቹ በሕግ ፀንቶ በአገራችን በሥራ ላይ የዋለው ሰንደቅ ዓላማ በጋራ ስምምነት እንዲፀድቅም ሆነ፣ የሚያስፈልገው ማሻሻያ ካለ እንዲሻሻል የመሻት ነገር ተንፀባርቆባቸዋል፡፡ ለዚህም የፖለቲካ ጥያቄና ሰላማዊ ሠልፍ፣ ወይም ተቃውሞ በሚከሰትበት ወቅት የፌዴራል፣ እንዲሁም የክልሎቹ ያልሆኑ ሰንደቅ ዓላማዎች መታየታቸውን እንዴት እንደሚገመግሙት ጥያቄ የቀረበላቸው የጥናቱ ተሳታፊዎች ምላሽ አንድ ማሳያ ነው፡፡

እንዲህ ያለው ድርጊት መታየቱ ሕገ መንግሥቱን የጣሰና የሕዝቦችን እኩልነት የማይቀበል ተግባር ነው ያሉት 42.4 በመቶ፣ ሕገ መንግሥቱንና የብሔር ብሔረሰቦችን እኩልነት ካለመቀበል ጋር ምንም ግንኙነት የለውም ያሉት 25.3 በመቶ፣ እንዲሁም ለመወሰን እንደሚቸገሩ የገለጹት 25.5 በመቶ ናቸው፡፡

ሌላ የተለየ ዕይታ እንዳላቸው የገለጹት የጥናቱ ተሳታፊዎች 4.6 በመቶ ናቸው፡፡ እነዚህም ሕገ መንግሥቱ የይስሙላ እንጂ በተግባር አለመተርጎሙን፣ ለሰንደቅ ዓላማ ክብር ሊሰጠው የሚገባውን ቦታ መንግሥትም አለመስጠቱን፣ የፌዴሬሽን ምክር ቤት አወቃቀር በክልሎች መካከል በደልና አድልዎ እያደረሰ መሆኑን፣ መንስዔው የመልካም አስተዳደር ችግርና መንግሥት የሕዝቦችን ጥያቄ በተገቢው ሰዓት ምላሽ አለመስጠቱ የሚሉትን ሐሳቦች ገልጸዋል፡፡

በዚህ የዳሰሳ ጥናት ማረጋጋጥ የተቻለው ሌላው ቁምነገር አሁን በሥራ ላይ ያለውን  ሰንደቅ ዓላማ ለትውልዱ ለማስገንዘብና በሕፃናት አዕምሮ ላይ ለማኖር የተሠራው ሥራ የፈተሸ ነው፡፡ ሕፃናት የነገ አገር ተረካቢ እንደ መሆናቸው መጠን ስለአገራቸው ሰንደቅ ዓላማ አመጣጥ፣ ስለቀለማቱና ስለብሔራዊ ዓርማው ትርጓሜ፣ ስለሰንደቅ ዓላማው አሰቃቀል፣ መጠን፣ ሰንደቅ ዓላማ ስለሚሰቀልበትና ስለሚወርድበት ጊዜ፣ ሰንደቅ ዓላማ ሲሰቀልና ሲወርድ ሊሰጠው ስለሚገባው ክብርና ስለሌሎች ከሰንደቅ ዓላማ ጋር በተያያዘ ዕድሜያቸውን ያማከለ ግንዛቤ የመፍጠር ሥራ መከናወን እንዳለበት ዕሙን ነው፡፡

ከዚህ ጋር በተያያዘ እንደ ቀድሞው ጊዜ ይቅርና በልኩ እንኳን ሕፃናትን ከመዋዕለ ሕፃናት ጀምሮ ስለሰንደቅ ዓላማ የተሻለ ፍቅርና ክብር እንዲሰጡ መምህራኖቻቸው እየሠሩት ያለው በቂ እንዳልነበር ታይቷል፡፡ ለዚህ ማሳያውም ሕፃናት ከመዋዕለ ሕፃናት ጀምሮ ስለሰንደቅ ዓላማ የተሻለ ፍቅርና ክብር እንዲሰጡ መምህራኖቻቸው የሠሩት ከፍተኛ ነው ያሉት 22.5 በመቶ፣ መካከለኛ ነው ያሉት 35.4 በመቶ፣ ዝቅተኛ ነው ያሉት 28.3 በመቶ መሆናቸው ነው፡፡

በዚሁ መረጃ መሠረት ምንም አልሠሩም ያሉት 10.3 በመቶ ሲሆኑ መልስ ያልሰጡት ደግሞ 3.5 በመቶ ናቸው፡፡ በሕፃናት ላይ መምህራን የሠሩት ዝቅተኛ እንደሆነ የገለጹትን የጥናቱን ተሳታፊዎች ከክልል አንፃር ለማየት ሲሞከር ቤኒሻንጉል ጉሙዝ ቀዳሚውን ደረጃ ሲይዝ፣ ትግራይና አማራ ተከታዩን ደረጃ ይዘዋል፡፡

ስለሰንደቅ ዓላማ በሕፃናት ላይ የተሠራው ዝቅተኛ ለመሆኑ ምክንያቱ መምህራኖቹ ተነሳሽነት ስለሚጎላቸው እንደሆነ የገለጹት 43 በመቶ፣ በሥርዓተ ትምህርቱ ስለሰንደቅ ዓላማው ምንም የተባለ ነገር አለመኖሩን የገለጹት ደግሞ 35.1 በመቶ መሆናቸውም እንዴት ትውልድ ከአገር ፍቅር ተናጥቦ፣ በየጊዜው በሚፈበረኩ አፍራሽ መንገዶች ሲነጉድ እንደኖረ አመላካች ነው፡፡

 በመሠረቱ ሰንደቅ ዓላማ በየትኛውም ዓለም የሚገኙ ዜጎች ከሌሎች ተለይተው የሚታወቁበት፣ የሚከበሩበትና የሚመኩበት ነው ካልን፣ የሰንደቅ ዓላማ ፍቅር መንፀባረቅ የሚጀምረው ገና በልጅነት አዕምሮ ውስጥ ነው፡፡ ሕፃናት ከቤተሰባቸው ቀጥሎ የሚያውቁት ቦታ ትምህርት ቤታቸውን መሆኑም የታወቀ ነው፡፡ ወደ ትምህርት ቤታቸው ሲሄዱ ደግሞ ቅጥር ግቢው ላይ ጎልቶና በክብር ተሰቅሎ ሲውለበለብ የሚያዩት ሰንደቅ ዓላማቸውን ነው፡፡

ከዚህ ጋር በተያያዘ ሕፃናት ከመዋዕለ ሕፃናት ጀምሮ ለሰንደቅ ዓላማ የተሻለ ፍቅርና ክብር እንዲኖራቸው በመምህራኖቻቸው መታገዝ ነው ያለባቸው፡፡ ይህን አስመልክቶ ጥናቱ እንደ ዳሰሰው የሰንደቅ ዓላማን ክብርና ጥቅምን ለሕፃናት በሚገባ መንገድ (ለምሳሌ በመዝሙር) ማስጠናት ያሉት 15.83 በመቶ፣ የሰንደቅ ዓላማን ምንነትና ዓይነት አስመልክቶ ትምህርት መስጠት ያሉት 7.37 በመቶ፣ በሰላማዊም ሆነ በጦርነት ሜዳ ስለሰንደቅ ዓላማ ፍቅር በጀግኖች የተደረጉ ተጋድሎዎችን እንደ ምሳሌ እያሳዩ ማስተማር ያሉት 3.82 በመቶ ናቸው፡፡ በሌላ በኩል እነዚህ ከላይ የተጠቀሱት ሦስቱም በትኩረት ሊሠራባቸው እንደሚገባ የገለጹት 62.89 በመቶ ናቸው፡፡ እስካሁንም ድረስ በዚህ ረገድ ምን እየተሠራ እንደሆነ ራስን መጠየቅ ከሚመለከተው ሁሉ የሚጠበቅ ትልቅ ተግባር ነው፡፡

ሌሎች የመፍትሔ ሐሳቦችን ያቀረቡት ደግሞ 4.91 በመቶ ናቸው፡፡ ከእነዚህም ሐሳቦች መካከል አረንጓዴ፣ ቢጫና ቀዩ ቀለማት በቅድመ አያቶቻችን እንዴት እንደተመረጡ በታሪክም በሃይማኖትም መንገድ ተጠንቶ ሊታወቅ ይገባል፡፡ ሰንደቅ ዓላማው ላይ ያለው ኮከብ እንደገና መጠናት አለበት፡፡ በመጀመሪያ የሰንደቅ ዓላማን ምልክቶች አምኖ መቀበል ያስፈልጋል፡፡ ሕፃናቱን ስለሰንደቅ ዓላማ ከማስተማር በፊት በጋራ መግባባት ላይ ተገቢውን ሥራ መሥራት ይገባል የሚሉት ሐሳቦች ተነስተዋል፡፡

በማንኛውም አገራዊ እሴት ላይ ለመግባባት መገናኛ ብዙኃን ያላቸው ሚናም የሚናቅ አይደለም፡፡ በተለይ በዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ግንባታ ውስጥ የመገናኛ ብዙኃን ዋነኛው ሥራ ኅብረተሰቡን ማስተማር፣ ማሳወቅ፣ መረጃ መስጠት፣ እውነተኛ መሆንና ሚዛናዊ ዘገባ ማቅረብ ነው፡፡ መገናኛ ብዙኃን ስለሰንደቅ ዓላማ ጽንሰ ሐሳቦች፣ ስለሰንደቅ ዓላማ ሥርዓትና ተቋማት ሰፊና አስተማሪ መረጃዎችን ለሕዝቡ ማቅረብ ያለባቸውም ከዚሁ አኳያ ነው፡፡

ከዚህ ጋር በተያያዘ በአገራችን ካሉ መገናኛ ብዙኃን ስለሰንደቅ ዓላማ ጽንሰ ሐሳቦች፣ አጠቃቀምና ሥነ ሥርዓት አስተማሪ መረጃዎችን ለሕዝብ በማቅረብ ረገድ የተሻለ ሥራ የሠራው ዘርፍ የትኛው እንደሆነ ጥያቄ ቀርቦ ነበር፡፡

በአገራችን ካሉ መገናኛ ብዙኃን ስለሰንደቅ ዓላማ ፅንሰ ሐሳቦችና አጠቃቀም ሥነ ሥርዓት አስተማሪ መረጃዎችን ለሕዝብ በማቅረብ ረገድ የተሻለ ሥራ ያከናወነው ቴሌቪዥን እንደሆነ የገለጹት የጥናቱ ተሳታፊዎች 32.3 በመቶ፣ ሬዲዮ ያሉት 14.3 በመቶ፣ መጽሔትና ጋዜጦች ያሉት 4.1 በመቶ፣ እንዲሁም ማኅበራዊ ሚዲያ ያሉት 11.8 በመቶ ናቸው፡፡ በሌላ በኩል እነዚህ ከላይ የተዘረዘሩት ሁሉም የሚዲያ ዘርፎች ምንም የረባ ነገር አልሠሩም በማለት ምላሽ የሰጡት የጥናቱ ተሳታፊዎች 31.2 በመቶ ነበሩ፡፡

በዳሰሳዊ ጥናቱ ቴሌቪዥን፣ ሬዲዮ፣ መጽሔትና ጋዜጣ፣ እንዲሁም ማኅበራዊ ሚዲያዎች ምንም የረባ ነገር አልሠሩም ያሉትን የጥናቱን ተሳታፊዎች ከክልል አኳያ ሲታዩም፣ እንደ ቅደም ተከተላቸው የአዲስ አበባና የሐረር ቀዳሚውን ደረጃ ይዘዋል፡፡ ትግራይ፣ አማራና ደቡብ ክልሎች ደግሞ ተከታዮቹን ደረጃዎች ይዘዋል፡፡ ከመላሾቹ 6.3 በመቶ የሚሆኑት ከሚዲው ይልቅ ሌሎች የተሻለ ጥረዋል ብለው፣ እነዚህም የድሮ አባቶችና ወታደሮች፣ በተለያዩ ቦታዎች የተካሄዱ መድረኮች፣ ትምህርት ቤትና መጻሕፍት ስለሰንደቅ ዓላማ ጽንሰ ሐሳብና አጠቃቀም አስተማሪ መረጃዎችን በአገራችን ካሉ መገናኛ ብዙኃን በበለጠ እንደ ሰጧቸው በምላሻቸው ገልጸዋል፡፡

ዳሰሳዊ ጥናቱ ከሰንደቅ ዓላማው አሰቃቀልና አጠቃቀም ሥርዓት ጋር በተያያዘ ስለሰንደቅ ዓላማው መጠን፣ አጠቃቀም፣ አሰቃቀል፣ ስለሰንደቁ ልሳን (ጫፍ)፣ የሰንደቅ የመትከያ ሥፍራ፣ ስለሚሰቀልበትና ስለሚወርድበት ጊዜ፣ ሲሰቀልና ሲወርድ ሊሰጠው ስለሚገባው አክብሮትና ሌሎችም ጉዳዮች በኢፌዴሪ ሰንደቅ ዓላማ አዋጅ ቁጥር 654/2001 የተደነገገውን አዋጅ አፈጻጸምም ለመፈተሸ ሞክሮ ነበር፡፡

በዚሁ መሠረት የኢፌዴሪ ሰንደቅ ዓላማ ሕግጋትን ለመጠበቅ ሕጎችን በልዩ ልዩ መንገዶች ለኅብረተሰቡ ተደራሽ ማድረግ መፍትሔ ነው ያሉት 8.3 በመቶ፣ ሕጉን ማክበር ማለት ከሰንደቅ ዓላማ ክብር፣ ትርጉምና ፍቅር ጋር ያለውን ግንኙነት ማስተማር ነው ያሉት 12.7 በመቶ ናቸው፡፡ የሕጉን አስፈጻሚ አካላት ሥልጣንና ኃላፊነት በዝርዝር ማስተማር ይሻላል ያሉት 2.9 በመቶ ሲሆኑ፣ ከሕጉ አፈጻጸም ጋር ያሉትን ተግዳሮቶች መለየትና ማረም ይሻላል ያሉት ደግሞ 8.2 በመቶ ናቸው፡፡ በሌላ በኩል እነዚህ ከላይ የተጠቀሱት አራቱም የመፍትሔ ሐሳቦች ጠቃሚ ናቸው ያሉት የጥናቱ ተሳታፊዎች 64.3 በመቶ ናቸው፡፡

እንዲሁም 3.6 በመቶ የሚሆኑት የጥናቱ ተሳታፊዎች ደግሞ በእኛ አገር መንግሥት ሕግ ያወጣል እንጂ ሕግ ማክበር ብዙም አይታይም፣ ስለሰንደቅ ዓላማ ግራ የሚያጋባ አመለካከት ነው ያለው፣ የብሔሩን ሰንደቅ ዓላማ ብቻ የሚጠቀመው ይበዛል፣ ሕግን ብቻ መጠበቅ ምን ዋጋ አለው? መጀመሪያ ለሰው ልጅ ክብር መስጠት ይቀድማል የሚሉትን ሐሳቦች ያነሱም መኖራቸውን ነው ጥናቱ ያረጋጋጠው፡፡

የኢፌዴሪ የሰንደቅ ዓላማ ሥርዓት በሚፈለገው መንገድ መተግበሩን የሚከታተሉት፣ እንዲሁም የሕግ ጥሰት ተፈጽሞ ሲገኝም ተገቢውን ሕጋዊ ዕርምጃ የሚወስዱትና የሚያስወስዱት የፍትሕ አካላት ናቸው፡፡ ከዚህ ጋር በተያያዘ የኢፌዴሪ የሰንደቅ ዓላማ ሥርዓት በአግባቡ መተግበሩን፣ እንዲሁም የሕግ ጥሰት ተፈጽሞ ሲገኝ ተገቢውን ዕርምጃ በመውሰድ በኩል የሕግ አስከባሪ አካላት እየሠሩት ያለውን ሥራ እንዴት እንደሚገልጹት ጥያቄ የቀረበላቸው የጥናቱ ተሳታፊዎች ምላሽም ይገኛል፡፡

የሕግ አስከባሪ አካላት የሕግ ጥሰት ተፈጽሞ ሲገኝ ዕርምጃ በመውሰድ በኩል እየሠሩት ያለው ሥራ ከፍተኛ እንደሆነ በምላሻቸው የገለጹት የጥናቱ ተሳታዎች 36.5 በመቶ፣ መካከለኛ ነው ያሉት 20.9 በመቶ፣ ዝቅተኛ ነው ያሉት ደግሞ 25.2 በመቶ ናቸው፡፡ የሕግ አስከባሪ አካላቱ ምንም ነገር አልሠሩም ያሉት ደግሞ 11.1 በመቶ ናቸው፡፡ 6.3 በመቶው ምላሽ ያልሰጡ ናቸው፡፡ ዝቅተኛ፣ መካካለኛና ምላሽ ያልሰጡትን ደምረን ስናይ ሕግ ማስተግበሩ ላይ ያለውን እንዝህላልነት እንገነዘባለን፡፡

በእርግጥ ተገቢ ዕርምጃ ላለመውሰድ እንቅፋት የሆነው የፍትሕ አካሉ ብቻ አለመሆኑን ለማሳየት ሌሎች ምክንያቶችም የጠቀሱ ነበሩ፡፡ ለአብነትም ሕዝቦች ለሰንደቅ ዓላማው የጋራ ፍቅር እንዲኖራቸው በእውነታና በተግባር ላይ የተመሠረተ እኩልነት እንዲኖር መንግሥት አለመሥራቱን፣ ግድየለሽነት መኖሩን፣ በአገር አንድነት ላይ ጥያቄ መኖሩን፣ ወደ ትምህርት ገበታ ሲገባና ሲወጣ ማስተማርና አምነው እንዲቀበሉ ማድረግ ላይ ክፍተት መኖሩን አውስተዋል፡፡

በአጠቃላይ ዳሰሳዊ ጥናቱ ያነሳቸው በርካታ ችግሮች ተለይተዋል፡፡ መረጃው ከዳሰሳ አድማስ ስፋቱም ሆነ ከወቅታዊነቱ አንፃር የተሟላ ነው ባይባልም፣ በተሰናዳበት ወቅት አብዛኛዎቹ የመንግሥት አካል፣ በሰንደቅ ዓላማ ቀን በዓል ላይ ግኝቱን ተጋርተውትም ነበር፡፡ አሁንም ቢሆን ገና ከውዝግብና ከቀውስ አልተወጣምና መንግሥትም ሆነ የሚመለከታቸው አካላት ሁሉ ሊያጤኑት ግን ግድ ይላቸዋል፡፡

በተለይ የኢፌዴሪ ሰንደቅ ዓላማ ታሪካዊ ዳራውን ሳይለቅ፣ የዛሬዋን ኢትዮጵያም አማክሎ በሁላችንም ልብ ውስጥ የሚንበለበል ዓርማ እንዲሆን በቅንነት ማሰብና መስማማት ከሁላችንም ይጠበቃል፡፡ በትውልዱ ልብ ውስጥ ማስቀረትም እንዲሁ፡፡ ሰንደቅ ዓላማውን በሰዓቱ አለመስቀልና አለማውረድ፣ የጠረጴዛ፣ የሕንፃ ወይም የሌላ ቁሳቁሶች ሸፋን ማድረግ፣ ያረጁ፣ የተበላሹ፣ ቀለማቸው የደበዘዘና የተቀደዱ ሰንደቅ ዓላማዎችን መጠቀም፣ ወዘተ የመሳሰሉ ግድፈቶችን ማረምም  ያስፈልጋል፡፡

በፌዴራል ሥርዓቱ ውስጥ ክልሎች የራሳቸው ሰንደቅ ዓላማ እንዲኖራቸው ከመደረጉ ጋር በተያያዘ የሚስተዋሉ የአመለካከት ችግሮችን ለማስተካከልም ጥረት መደረግ አለበት፡፡ የትም ሆነ መቼ ቅድሚያ ለብሔራዊው ሰንደቅ ዓላማ ተገቢውን ክብርና ሥፍራ አለመስጠት የሕግ ጥሰት መሆኑ በተጨባጭ መረጋጋጥ ይኖርበታል፡፡ ለዚህም በጉዳዩ ላይ በዝርዝር ተነጋግሮ የጋራ አቋም መያዝ ለነገ የማይባል አጀንዳ ነው እንላለን፡፡

ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እየገለጽን፣ በኢሜይል አድራሻቸው [email protected]  ማግኘት ይቻላል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የአዲስ አበባ ነዋሪዎች ቁጥር ሲጨምር የሚኒባስ ታክሲዎች ቁጥር እየቀነሰ መምጣቱ ሊታሰብበት ይገባል

በአዲስ አበባ ከተማ የትራንስፖርት አገልግሎት በመስጠት ከፍተኛ የሚባለውን ድርሻ...

ሃምሳ ዓመታት ያስቆጠረው አብዮትና የኢትዮጵያ ፖለቲካ ውጣ ውረድ

የኢትዮጵያ ሕዝቦች የዴሞክራሲ ለውጥ ጥያቄ የሚነሳው ከፋሺስት ኢጣሊያ ወረራ...

በአዲስ አበባ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት የተፈጸመው ሕገወጥ ተግባር ምንድነው?

የአዲስ አበባ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት የዳይሬክተሮች ቦርድ፣...

በአዲስ አበባ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት ላይ ምርመራ እንዲደረግ ውሳኔ ተላለፈ

ፕሬዚዳንቷና ዋና ጸሐፊው ተጠያቂ ሊሆኑ ይችላሉ ተብሏል ከአዲስ አበባ ንግድና...