Tuesday, March 5, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ተሟገትኧረ በሕግ አምላክ!

ኧረ በሕግ አምላክ!

ቀን:

በገነት ዓለሙ

ዝክረ ነገር የተባለው የታወቀውና በዓይነቱ አምሳያ የሌለው የ19ኛ እና 20ኛ ምዕተ ዓመት መጀመርያ የኢትዮጵያን ሕጎች የሚያቋቁሙ ሰነዶችን አሰባስቦ ከማብራሪያዎቻቸውና መግለጫዎቻቸው ይዞ የታተመው መጽሐፍ ደራሲ ብላቴን ጌታ ማኅተመ ሥላሴ ወልደ መስቀል፣ በ1958 ዓ.ም. ሌላኛው ጽሑፋቸው ስለ ‹‹የቀድሞ ዘመን ጨዋ ኢትዮጵያዊ ጠባይና ባህል›› ይናገራሉ፡፡ ስለኢትዮጵያ ጥናት ሦስተኛው የኢንተርናሲዮናል ጉባዔ (ኮንፈረንስ) ላይ የቀረበውና መጋቢት 25 ቀን 1958 ዓ.ም. በአማርኛና በፈረንሣይኛ ቋንቋ በታተመው በዚህ አጭር ጽሑፋቸው ብላቴን ጌታ ማኅተመ ሥላሴ ወልደ መስቀል (ያኔ ባላምባራስ) የኢትዮጵያን ሕዝብ፣ ‹‹አራት ዓይነተኛ ጠባዮች›› ይተነተናሉ፡፡ ከእነዚህ መካከል አንዱ ፍርድን የሚመለከት ነው ይላሉ፡፡

ይህንንም ሲያስረዱ፣ ‹‹የኢትዮጵያ ሕዝብ ስለፍትሕ ጥልቅ የሆነ ስሜት ወይም ዝንባሌ አለው፡፡ ይህንንም ዙር በደም እንደሚተላለፍ ሁሉ እንደ ቅርስ ካባቶቹ ይወርሰዋል፡፡ የተጣላን ለማስታረቅም የተበደለን ለማስካስም ሆነ ዳኝነት ለማየት በተቀመጠበት ሸንጎ ሁሉ ቃል ሲሰነዝር ከእውነት እንዳይርቅ በጣም በመጠንቀቅና በመጨነቅ ነው፡፡ ፍርድ የተለየ የእግዚአብሔር ቅዱስ ገንዘቡ ስለሆነ ፊት ዓይቶ፣ ወቀሳ ፈርቶ ቃሉን አያዛባም፡፡

- Advertisement -

Video from Enat Bank Youtube Channel.

‹‹ተረቶቹንና ምሳሌዎቹን ብንመረምራቸው ጉልህ የሆነ የተጨበጠ ልማደ ሕግን ይዘው እናገኛቸዋለን፡፡ ወላጆች በተረት፣ በፈሊጥና በዘዴ እያደረጉ ዳኝነት ትክክለኛ ሚዛን መሆን እንዳለበት ለልጆቻቸው ያስተምራሉ፡፡ ከችሎት ላይ የተሰጠው ውሳኔ ምናልባት የሚያጠግበው ካልሆነና ህሊናው ተረታህ ካላላው ከአንዱ ዳኛ ወደ ሌላው በይግባኝ እየተራመደ ከመሄድ አይታገስም፡፡

‹‹የኢትዮጵያ ሕዝብ ፍትሕ ሲጓደል በብርቱ ያዝናል፡፡ ምንም የተወሰደው ሀብት ዋጋው ያነሰ ቢሆን በዳኝነት መዛባት እጅግ አድርጎ ይቆጫል፡፡ ይህንንም ‹በፍርድ ከሄደቸው በቅሎየ ያለ ፍርድ የሄደችው ጭብጦዬ ታሳዝናለች› የሚል ምሳሌው ሊያስረዳ ይችላል፤››  ይሉና ከተዋሀዱት አራቱ ታላላቅ ጠባያት ፍርድ የአንደኝነትን ቦታ ይዞ ይገኛል ብል የተሳሳትኩ አይመስለኝም እያሉ ጥናታቸውን ያቀርባሉ፡፡

ዛሬ በምንገኝበት ልዩ ሁኔታ ውስጥ የባላምባራስ ማኅተመ ሥላሴ ወልደ መስቀል ‹‹ምስክርነት››፣ የእሳቸው ‹‹የኢትዮጵያ ባህል ጥናት››፣ ወዘተ አወዛጋቢ ሊሆን ይችላል፡፡ የጋራ መግባቢያችንም ባይሆን አያስደንቅም፡፡ ኢትዮጵያ ከጥንት ጀምሮ በዚያው በዘመኑ በራሱ መለኪያ የሕግና የፍርድ አገር መሆኗን ግን የሚመሰክሩት፣ እንደ ማኅተመ ሥላሴ ወልደ መስቀል ያሉ ዛሬ በደረስንበት ‹‹የዕድገት ደረጃ›› እዚህ ወይም እዚያ ጎራ ውስጥ የመፈረጅ አሳዛኝ ዕጣ ፈንታ የሚያጋጥማቸው ሰው ብቻ አይደሉም፡፡

በዓለም ውስጥ ከሚገኙት ሃይማኖቶች መካከል በቁጥር ከፍተኛ ተከታይ ያለው ከክርስትና ቀጥሎ እስልምና ነው፡፡ ዛሬ የእስልምና ሃይማኖት ተከታዮች ብዛት ግምት 1.8 ቢሊዮን ነው፡፡ ከዓለም ሕዝብ ውስጥ 24 በመቶ ያህሉ ማለት ነው፡፡ ይህን ያህል ተከታይ ያለው ሃይማኖት ኢትዮጵያን የመጀመሪያዋ የመሸሸጊያና የመጠጊያ ቦታ አድርጎ ያውቃል፡፡ ስደተኞችን የተቀበለች አገርና ሕዝብ ብቻ ሳይሆን፣ አሳዳጆችንና ተሳዳጆችን የግራ ቀኝ ክርክር ሰምታ ዳኝነት ዓይታ ተሳዳጆችን የፍርድ ባለመብት አድርጋ፣ እውነትም የትክክለኛ ፍትሕና ፍርድ አገር መሆኗን ያረጋገጠች አገር ናት፡፡

አንድ ሃይማኖት፣ ሃይማኖትን ያህል ግዙፍ ተቋም ይህን ያህል ግዙፍ ተከታይ ያለው፣ ሃይማኖት ይህን ያህል ዓምደ የሃይማኖት ያህል የማይናወጥ ግምት አለው በኢትዮጵያ ላይ፡፡

እኛም የየትኛውም ሃይማኖት ወይም እምነት ተከታይ ሆንን (አልሆንን) በሕግ አምላክ፣ ኧረ በሕግ ማለት ከሞላ ጎደል ሁለተኛ ሃይማኖታችን ወይም ሁለተኛ ተፈጥሯችን ነው ማለት ይቻላል፡፡ ‹‹እግዚአብሔር ያሳይዎ ክርስቶስ ያመልክትዎ›› የአቤቱታዎቻችን ሁሉ መግቢያዎችና መንደርደሪያዎች ናቸው፡፡ ‹‹የተበደለ ከነጋሽ የተጠማ ከፈሳሽ›› አሁን ሥራ ላይ ባለው ሕገ መንግሥት አንቀጽ 30 (የመሰብሰብ ሰላማዊ ሠልፍ የማድረግ ነፃነትና አቤቱታ የማቅረብ መብት)፣ እንዲሁም አንቀጽ 37 (ፍትሕ የማግኘት መብት) የጥንት የጠዋት ዝርያዎች ናቸው፡፡ በተለያዩ የአገራችን ቋንቋዎችም ተመሳሳይና ይህን የራሱን አቻ አገልግሎት የሚሰጡ ያሸበረቁና ያጌጡ ምሳሌያዊ አነጋገሮች ሞልተዋል፡፡ ሁሉም ከበሕግ አምላክአደራ ሕጊዝባን መንግሥቲ፣ ወዘተ የሚመነጩ ናቸው፡፡ በሦስቱ ቋንቋዎች የተወሰንኩት ለምሳሌነት እነዚህ ይበቃሉ ብዬ ሳይሆን ከዚህ በላይ ስለማላውቅ ነው፡፡

ለማንኛውም ግን አገራችን በየትኛውም ቋንቋ ቢሆን፣ በሁሉም ቋንቋዎቻችን በሕግ አምላክ የሚባልባት አገር ሆናለች፡፡ ሕግ ማክበርና ማስከበር የአገር ዋነኛው አጀንዳ ነው፡፡ ይህንን የአገራችን ችግር ከተቻለ በሙሉ ለመረዳት ሕግ ማስከበርና ማክበር ለምን አጀንዳ ሆነ? ለምንስ ችግር ሆነ? ለምንስ ገደደ? ለምን ጭንቅ ጥብ ሆነ? በሚሉ ጥያቄዎች አማካይነት አገላብጠን ማየት ያለብን ይመስለኛል፡፡

ሕግና ሥርዓት የማስከበርና የሕዝብ ደኅንነት የመጠበቅ የመንግሥት አቋምና አቅም፣ በተለያዩ የኢፌዴሪ ምክር ቤቶች ውስጥ የተለያየ ልክና መልክ እንደነበረው ማስታወስ ተገቢ ነው፡፡

በ2007 ዓ.ም. ምርጫ አማካይነት የተቋቋመውና ኢሕአዴግ መቶ በመቶ ያሸነፈበት፣ ሥራውንም ከ2008 ዓ.ም. የጀመረው አምስተኛው ምክር ቤት ሕግ ማስከበር አበሳ የሆነበት ገና በሁለተኛና በሦስተኛው ወር ውስጥ ነው፡፡ በ2008 ዓ.ም. ሥራውን በጀመረው በዚህ የፓርላማ ዘመን ከወታደራዊው መንግሥት ወዲህ በኢትዮጵያ በተለይም በኢፌዴሪ ታሪክ ውስጥ፣ የመጀመሪያውና ሁለት ጊዜ የአስቸኳይ ጊዜ ሁኔታ አዋጅ የወጣበት ጊዜ ነበር፡፡ በግንቦት 7 ቀን 1997 ዓ.ም. የምሽት ሁለት ሰዓት ዜና አማካይነት የታዘዘውና በኢትዮጵያ ውስጥ ሠልፍና ስብሰባን ለአንድ ወር ከማገድ በላይ፣ አስደንግጦና ‹‹እንደ ሾተላይ›› አድርጎ የዘለቀው ዕርምጃ እዚህ ውስጥ ከቁጥር ያላስገባሁት ያ ‹‹ፎርማል›› ማለትም ደንበኛውን የሕግ አወጣጥ መልክ ያልያዘ የ‹‹ጉልበት›› ሥራ በመሆኑ ነው፡፡ የኢትዮጵያ የፖለቲካ ሰላም በአፈናና በጥርነፋ ሲጠበቅ የነበረ በመሆኑ፣ ኢሕአዴግ በተለይም ከምርጫ 97 ወዲህ ለጉዞው እንቅፋት ይሆናል ያለውን ሁሉ በማፈንና ደብዛ በማጥፋት፣ በሰበብ አስሮ በማሰቃየትና በመሳሰሉት የብቀላ ሥልቶች ባለሙያ ሆኖ በመሠልጠኑ፣ ‹‹ዓለም አቀፋዊ ማኅበረሰብም›› ውስጥ እነ ሱዛን ራይስንና አገራቸውን አሜሪካ የመሰለ ወዳጅ ስለነበረው ሕግ ማስከበር ሰጥለጥ፣ ፀጥ ረጭ አድርጎ መግዛት ችግሩ አልነበረም፡፡

በዚሁ አምስተኛ ፓርላማ ውስጥ በለውጡ ማግሥት ምንም እንኳን ሕጋዊ ምርጫ ተደርጎ አዲስ ጠቅላይ ሚኒስትር ቢሰየምም፣ አዲሱ ተመራጭ ጠቅላይ ሚኒስትር ቢሮ ሲገባ የጠቅላይ ሚኒስትርነት ሥልጣኑን ጭምር መቀዳጀት አልቻለም፡፡ የዚህ ምክንያት ደግሞ ኢሕአዴግ ሲገዛ የኖረው በሕወሓት ቁጥጥርና ባለቤትነት ሥር በነበረ መንግሥታዊ አውታር ላይ በመሆኑ ነበር፡፡ ከ2008 ዓ.ም. ኅዳር በኋላ የተቀጣጠለው ትግል የሕወሓትን የበላይነትና አቅጣጫ ነዳፊነት ሲያናጋ፣ ከቁንጮ ገነት ተንሸራቶ ሰሜን ኢትዮጵያ ላይ ‹‹አዲስ በተቋቋመው›› ኃይል በኩል ምን ታመጣላችሁ ባይነትና ትርምስ ደጋሽነት ሲከታተል፣ በዚህም ምክንያት ከዚህ ቀደም የተቀፈቀፉ ነገር ግን በጥርነፋና በስቀዛ ታፍነው የነበሩ ጥያቄዎችና ቅሬታዎች ሲዘረገፉ ፀጥታና ሰላም ማስከበር አስቸጋሪ ሆነ፡፡ ሕግና ሥርዓት፣ ፀጥታና ሰላም ማስከበር አበሳ የሆነበት ወቅት ደግሞ ለውጡ የነባርና የአዲስ ገቢ ፓርቲዎችን ርብርብና ትብብር ገና ያላገኘበትም ጊዜ  ነበር፡፡ በዚህ ላይ ፀጥታ የማስከበር ሥራው የአገሪቱን የፀጥታና የደኅንነት ተቋማት ፓርቲዎች፣ ብልሽትና ስንኩልነት የማሻሻል የተደራረበ ሥራ ያለበት ጊዜ ነበር፡፡

ባሳለፍነው ሳምንት በተካሄደው የፓርላማው 13ኛ መደበኛ ስብሰባ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ሲጠየቁና መልስና ማብራሪያም ሲሰጡ፣ አገር እንዳለ ሲያዳምጥ በትንሹም ቢሆን የመመልከት ዕድል አጋጥሞኛል፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ለፓርላማ ጥያቄ መልስ ይሰጣሉ ማለት ራሱ ኢትዮጵያን የሚመለከቱ የውጭ ሚዲያዎች ጭምር ዜና ነበር፡፡ የፓርላማው የጥያቄና የመልስ አሠራር ራሱ ኢሕአዴግ ባስለመደው አሠራርና ባወረደው ሕግ መሠረት የሚመራ ነው፡፡ ይህ ይለወጥ ማለት ከዚያም ሻልና ላቅ ባለ መንገድ እንዲህ እንዲህ ሆኖ ይሻሻል ማለት ከገዥው ፓርቲም፣ ከተቃዋሚዎችም በኩል አለመምጣቱ የምንገኝበትን የአረንቋ ልክ ራሱን የሚያሳይ ነው፡፡

በዚህ የፓርላማ ውሎ ‹‹ለውጡና ሪፎርሙ በሀዲዱ እየሄደ ነው? ወይስ ሀዲዱን ስቶ ከመስመር ወጥቷል? ወይስ ከሽፏል?›› የሚል ጥያቄ ጭምር ሲነሳ ሰምተናል፡፡ ይህንን ጥያቄ ከመመለስ ለጊዜው ‹‹ገለልተኛ›› ሆነን እንቆይና ሲጀመር የምንገኝበትን ወይም እንገኝበት የነበረውን ምዕራፍ የለውጥና የሽግግር ነው የምንለው፣ ከአምባገነንነት ወደ ዴሞክራሲ የማለፍ ጉዞ አለብን ብለን ነው፡፡ አምባገነንነት ሕገ መንግሥታዊ መብቶችንና ነፃነቶችን አሰነካክሎ ኖሯል፡፡ ገዥዎችን ከሕገ መንግሥት በላይ አድርጎ ኖሯል፡፡ ሕጋዊና ሰላማዊ ትግል ተኮላሽቶ ኖሯል፡፡ የገዥዎች ሕግ የመጣስና የተቃውሞ ማጥቂያ አድርጎ የመገልገል ባህል ራሱ ሕግና የሥርዓቱ ሥልት ሆኖ ኖሯል፡፡ ሽግግሩ ከዚህ ሁኔታ ወደ ዴሞክራሲ ማለፍ ነው፡፡

ለውጡ ሲመጣ አፈናውና ጥርነፋው ገለል ሲል ታፍነው የኖሩ ከራሱ ከሥርዓቱ የተቀፈቀፉ የጥቅም፣ የመዋቅር፣ የወሰን ጥያቄዎችና ውዝግቦች መዘርገፍ ጀመሩ፡፡  ትናንት በገዥነቱ ቁንጮ ላይ በነበረበት ጊዜ የሰቀዛቸውን መብቶች አሁን በሽግግሩ ምጥ ውስጥ ግፋ በለው እያለ ትርምስ አምራቹ ራሱ ሕወሓት ሆነ፡፡ ቅድመ ለውጥ እነዚህን ጉዳዮች በገፍ ያላየናቸው በአፈናው ምክንያት ነው፡፡ ይህና ሌላውም ተደራርቦ መንግሥት ላይ ያልተለመደ ጥያቄ አስነሳ፡፡ መንግሥት ለምን ሕግ ማስከበር አቃተው ማለት የመሰለ ጥያቄ በይፋና በአደባባይ ሲመለስ የሰማነው፣ በፓርላማ ጠቅላይ ሚኒስትሩ እንኳን ሕግ ላስከብር ራሴን መጠበቅ እኮ አልችልም ነበር ብለው ከጦርነቱ በኋላ በነበረው የፓርላማ ውሎ ሊመልሱ ነው፡፡ ለውጡና ሽግግሩ ይህን የመሰለ የተወዘፈ ዕዳ ነበረበት፡፡ አውታረ መንግሥቱን ወይም የመንግሥት ዓምዶችን ከፓርቲነት አፅድቶ ገለልተኛ አድርጎ የማነፅ ሥራ፣ አሁንም የሁሉንም የፖለቲካ ፓርቲዎች ስምምነትና ርብርብ አላገኘም፡፡ መንግሥትን ወይም የለውጡን መሪዎች እጀ ሰባራ ያደረጋቸው ይህ ሥራ የአገር ዋና ተግባርና ግዳጅ ሆኖ፣ በሙሉ ልብና በሙሉ ኃይል ባለመሠራቱና አንዳንድ ቦታም ባለመታወቁ ነው፡፡

በዚህ ረገድ የመንግሥትም ሆነ የራሱ ችግርና አስተዋጽኦ ዝም ብሎ የሚተላለፍ አይደለም፡፡ ሕግ የማስከበር የመንግሥት ሥልጣንና ተግባር የገዛ ራስንም የመንግሥትን ሕግ አክባሪነት በእጅጉ ይጠይቃል፡፡ ይህንንም ከበላይ ሆኖ የሚያይና የሚቆጣጠር ተቋም ያስፈልጋል፡፡ ይህ የአዲስ ተቋማትን መኖር አይፈልግም፡፡ ፍርድ ቤቶች የዚህ ሥልጣን ብቸኛ ባለቤቶች ናቸው፡፡ የዳኝነት ሥልጣን የፍርድ ቤቶች ብቻ ነው ይላልና ሕገ መንግሥቱ፡፡ በተለይም በምንነጋገርበትና አንገብጋቢ በሆነው በዚህ ርዕሰ ጉዳይ ውስጥ ሕግ አለ፣ ተቋምም አለ፡፡ ለምሳሌ የዋስትና መብት ጉዳይ ከሚገዛው ሕግም ሆነ ከባለመብቱ ፍርድ ቤት አንፃር የመያዝንና የማሰርን ሕግ ያህል አስቸጋሪ አይደለም፡፡ ነባሩ የአገር ሕግ ራሱ በቂ ነው፡፡ ፖሊስ በዋስ መልቀቅ ይችላል፡፡ ይህ ሳይሆን ሲቀር የትኛውም ፍርድ ቤት የዋስትና ጥያቄን አስተናግዶ በአስቸኳይ (በሕጉ ቋንቋ ደግሞ ሳይዘገይ) ውሳኔ መስጠት አለበት፡፡ ከ48 ሰዓት መብለጥ የለበትም፡፡ በዋስትና ላይ የተሰጠ ውሳኔ ይግባኝ ጉዳይ ሌላው ችግራችን ነው፡፡

በኢትዮጵያ ሕግ መሠረት የኢሕአዴግ መንግሥት የሙስና ወንጀልን አስመልክቶ የ1993 ዓ.ም. ሕግን እስኪያወጣና ያንንም በ1997 ዓ.ም. እስካሻሻለው ድረስ በዋስትና ተለቀቀብኝ ብሎ ይግባኝ ማለት የማይታወቅ ነገር ነበር፡፡ በየ1954 ዓ.ም. የወንጀሉ መቅጫ ሕግ ሥነ ሥርዓትም ያቋቋመው የሕግ አሠራር፣ መስከረም 2014 ዓ.ም. በሚኒስትሮች ምክር ቤት ፀድቆ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የቀረበውም አዲሱ ሕግ የሚደነግገውና ይግባኝ የሚፈቅደው ‹‹በዋስትና የመለቀቅ ጥያቄን ፍርድ ቤት ያልተቀበለው እንደሆነ›› እንጂ፣ በዋስትና ተለቀቀብኝ ብሎ አቤቱታ ኢትዮጵያ ሕግ ውስጥ የለም፡፡ የለም ብቻ ሳይሆን ክልክል ነው፡፡ የዋስትና ጥያቄ ለየትኛም ፍርድ ቤት መቅረቡ ቀርቶ፣ ‹‹ባለ መብት ፍርድ ቤት›› ሲፈለግ ስናይ የፖሊስ ወይም የዓቃቤ ሕግ ይግባኝም/አቤቱታም (ሰው በዋስ ተለቀቀ ተብሎ) እስከ ሰበር ችሎት ደረሰ ሲባል ስንሰማ ዕውን አገር ለዴሞክራሲያዊ ለውጥና ሽግግር ብቁ፣ ስንዱና ዝግጁ ሕግ ሳይሆን፣ በጀት የተመደበለት መሥሪያ ቤት ሳይሆን፣ ‹‹ሰው›› አላት ወይ የሚያሰኝ ሐዘን ውስጥ ይከታል፡፡

ሰኔ 7 ቀን 2014 ዓ.ም. በተከታተልነው የፓርላማ ውሎ ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር)፣ አገሪቱ ውስጥ ያስቸገሩትን የ‹‹የሌብነት›› እና የ‹‹ሌቦች›› ዓይነት ሲዘረዝሩ እውነቱን ለመናገር ደንግጫለሁ፡፡ ያስደነገጠ አገር የገባችበት የምዝበራ የብኩንነትና የሙስና ልክ አይደለም፡፡ የጠቅላይ ሚኒስትሩ ቋንቋ (ሌባ ዳኞች፣ ሌባ ዓቃቤ ሕጎች፣ ሌባ ፖሊሶች፣ ወዘተ)  ከተቋም ግንባታ አዲስና አምሳያ የለሽ ምኞታችን ጋር ይጋጫል፡፡ ይህንን የምለው ሳይጠየቁ መቅረትን ለመመረቅ አይደለም፡፡ ይልቁንም ሳይጠየቁ መቅረት በተለይም በእነዚህ ተቋማት ውስጥና ከእነሱም ውጪ ሥርዓታዊና የሥርዓት ግንባታው አካል መሆን አለበት፡፡ ሕግና ደንብ እንዳመቸ የሚጥሱ የገዥዎችንና የባለሥልጣናት ተግባር በፅናት መዋጋት፣ ማንም ግለሰብ፣ ሹምና ባለሥልጣን የሚፈጸመውን ከሕግ የወጣና ያፈነገጠ ያልተገባ ተግባር፣ ሕገወጥነትና አጥፊነት ከሥልጣን ሲወርድ፣ ከሥልጣን ከወረደ በኋላ ብቻ ሳይሆን ሥልጣን ላይ እያለም ሀይ መባልና መጠየቅ መቻል አለበት፡፡ ሳይጠየቁ መኖር ይቻላል ማለት ጥፋቶችንና ነውሮችን እየተደጋገሙና እየተባባሱ ላለመፈጸማቸው ዋስትና የለም፡፡ ተጠያቂነትን ማረጋገጥ ይበልጥ የሥርዓት ግንባታችንን እያጠናከረ ይመጣል፡፡ ችግርና ብልሽት፣ ጥፋትና ወንጀል እንዳይከሰት ጠባቂው፣ ሲከሰትም አጋላጭና ተፈራጅ እንዲበዛ ያደርጋሉ፡፡

ሕግ የማስከበር የመንግሥት ሥልጣንና ግዳጅ ሕግ የማስከበር ግዴታ፣ ለሕጋዊነት መጨነቅንና መጠበብን ያህል ምግባርና ጨዋነት ይጠይቃል፡፡ ይህም ከቋንቋና ከንግግር ይጀምራል፡፡ ተከታታይ መንግሥታት ይህችን አገርና የመንግሥትንም ሥልጣን የዝርፊያ ማዕድን የግፍ ማሳ አድርገው በኖሩበት በዚህ ውጤትነት፣ የኅብረተሰቡ የሕግና ሥርዓት የሥነ ምግባር ውቅራቶች ፍርስርሳቸው በወጣበት ሕይወት በተገኘው ማናቸውም አቋራጨና አጋጣሚ ሁሉ የመጠቀም ታላቅ ቁማር ሆኖ፣ መንግሥት ራሱ ወይም ቋንቋው ሁሉ ብልሽትሽቱ በወጣበት ወቅት እንኳን የመሪዎቻችንን ቋንቋ ዝም ብለን አላለፍንም፡፡ ይኮረኩረንና ይቆጨን ነበር፡፡ ይህንን የምለው ከሕግ ማስከበር ወግና ሕግ  አኳያ ጭምር ነው፡፡ ፍርድ ቤቶች የሕዝብን ልብ ይረቱ ዘንድ የመታመን ክብር ሊጎናፀፉ ይገባል፡፡ ፍርድ ቤቶች ይህንን የመሰለ ፍጥርጥር ላይ እንዲደርሱ የተጀመረው ርብርብር አግኝቶ መዝለቅ አለበት፡፡ ፍርድ ቤቶችን ገለልተኛ አድርጎ መልሶ የማነፅ ተግባር ከሌሎች መካከል ሕግ ማክበርን፣ ለሕጋዊነት መርህና ወግ መጨነቅን፣ የፍርድ ቤቶችን ውሳኔና  ትዕዛዝ ባይሰማመብትም እንኳ እየመረረም እያንገፈገፈም እንኳን የግድ መፈጸምን፣ በፍርድ ቤት ፍርድ፣ ውሳኔና ትዕዛዝ ላይ ያለንና የሚሰማን ስሜት የመግለጽ መብትና ነፃነታችን የተገደበ መሆኑን ይጨምራል፡፡ ፍርድ ቤቶች በሕገ መንግሥቱና በሌሎችም ሕጎች የሠፈሩ መብቶችንና ነፃነቶችን ማስከበሪያና መከላከያ ናቸው፡፡ ይህም ውሳኔዎቻቸውን አክብሮ፣ በፀጋና በክብር የሚቀበል ሕዝብ፣ ትዕዛዞቻቸውንና ፍርዳቸውን የሚያስፈጽም መንግሥት የግድ አስፈላጊ ነው፡፡ ይህን የመሰለ አክብሮትና ግዴታ ቋንቋችንንም አንደበታችንምም ይመለከታል፡፡ በዳኝነት ሥርዓቱ ላይ ያለንን ቅሬታ (ይህ የኖርንበትንና ያለፍንበትን ጊዜ ያህል ብዙና ሥር የሰደደ ነው) የምንፈልገውንና የምንገነባውን የነፃና የገለልተኛ አካል ግንባታ እንዲሸረሸር ማድረግ አይገባም፡፡

እና በሕግ አምላክ ስንል ተራውን ዜጋ ብቻ ሳይሆን ጉልበተኞችንም፣ መግሥትንም፣ የመንግሥት የተለያዩ የሥልጣን አካላትንም ጭምር ነው፡፡ እነዚህን ሁሉ በሕግ አምላክ ስንል ደግሞ እየለመንን ፍላጎታችንን እየተነጋገርን የእነሱን በጎ ፈቃድ እየጠየቅን አይደለም፡፡ ለሕጉ የመገዛት ግዴታ ከተጠያቂነት ጋር አለባችሁ እያልን ነው፡፡

ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊዋን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እንገልጻለን፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የአዲስ አበባ ነዋሪዎች ቁጥር ሲጨምር የሚኒባስ ታክሲዎች ቁጥር እየቀነሰ መምጣቱ ሊታሰብበት ይገባል

በአዲስ አበባ ከተማ የትራንስፖርት አገልግሎት በመስጠት ከፍተኛ የሚባለውን ድርሻ...

ሃምሳ ዓመታት ያስቆጠረው አብዮትና የኢትዮጵያ ፖለቲካ ውጣ ውረድ

የኢትዮጵያ ሕዝቦች የዴሞክራሲ ለውጥ ጥያቄ የሚነሳው ከፋሺስት ኢጣሊያ ወረራ...

በአዲስ አበባ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት የተፈጸመው ሕገወጥ ተግባር ምንድነው?

የአዲስ አበባ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት የዳይሬክተሮች ቦርድ፣...

በአዲስ አበባ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት ላይ ምርመራ እንዲደረግ ውሳኔ ተላለፈ

ፕሬዚዳንቷና ዋና ጸሐፊው ተጠያቂ ሊሆኑ ይችላሉ ተብሏል ከአዲስ አበባ ንግድና...