የቀድሞው የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ብሔራዊ ቡድን ዋና አሠልጣኝ ወልደመስቀል ኮስትሬ (ዶ/ር) በአትሌቶች ዘንድ የሚፈሩና የሚከበሩ እንደሆነ ይነገራል፡፡ በበርካታ አትሌቶች ዘንድ እንደ አባት ጭምር የሚታዩት አሠልጣኙ፣ ቆፍጣናነታቸው ያስበረግጋል፡፡ በእሳቸው ዘንድ እያንዳንዷ ሰከንድ ዋጋ አላት፡፡ ይኼን የተረዱት አትሌቶችም ልምምድ ማድረግ ሲገባቸው መከወን፣ ሰዓት ማክበር፣ አሠልጣኝን ማክበር እንዲሁም የአሠልጣኝን ትዕዛዝ ማክበር ግዴታቸው ነበር፡፡
በዚያ ዘመን የነበሩ አትሌቶች በሥነ ምግባር የማይታሙ እንዲሁም የአገራቸውን ባንዲራ በዓለም አደባባይ በማውለብለብም ይታወቃሉ፡፡ በግል ውድድር ላይ ከሚያሳዩት ብቃት ይልቅ፣ አገራቸውን ወክለው በሚካፈሉበት ሻምፒዮና ላይ ደምቀው ሲታዩ ይስተዋላል፡፡
ከጥቂት ዓመታት ወዲህ አትሌቶች መምረጥ አከራካሪ ጉዳይ እየሆነ የመጣ ሲሆን፣ ቀድሞ የነበረው ለአገር ቅድሚያ የመስጠት ባህል እየተሸረሸር መምጣቱንና አትሌቶች በግል ውድድሮች ላይ ለመካፈል ያላቸው ፍላጎት ማየሉ ይጠቀሳል፡፡
በዚህ ወር በርካታ የዙር የዳይመንድ ሊግና የጎዳና ውድድሮች ተድርገዋል፡፡ በተለያዩ ርቀቶች ላይ መካፈል የቻሉት አትሌቶቹ ክብረወሰን ጭምር በማሻሻል ማሸነፍ ችለዋል፡፡
በተለይ ሐሙስ ሰኔ 9 ቀን 2014 ዓ.ም. በተደረገው የኦስሎ ዳይመንድ ሊግ ውድድር አትዮጵያውያን በሴቶችም በወንዶችም ከአንድ እስከ ሦስት ያለውን ደረጃ በመያዝ በበላይነት አጠናቀዋል፡፡
በወንዶች 5 ሺሕ ሜትር ጥላሁን ኃይሌ 13፡03.51 አንደኛ፣ ሳሙኤል ተፈራ በ13፡04.35 ሰዓት ሁለተኛ ደረጃ ይዞ ሲያጠናቅቅ፣ ጌትነት ዋለ 13፡04.48 በሆነ ውጤት ሦስተኛ ሆነዋል፡፡ በተመሳሳይ ርቀት በሴቶችም ውድድር ዳዊት ሥዩም 14፡25.84 አንደኛ፣ ጉዳፍ ጸጋይ 14፡26.69 ሁለተኛ ሆና ስታጠናቅቅ፣ ለተሰንበት ግደይ 14፡32.17 በሆነ ጊዜ ሦስተኛ ደረጃን በመያዝ ርቀቱን በበላይነት ማጠናቀቅ ችለዋል፡፡
ከኦስሎ ድል ባሻገር በርካታ ኢትዮጵያውያን አትሌቶች በማራቶን፣ በግማሽ ማራቶን፣ በቤት ውስጥ ውድድሮች ስኬታማ ጊዜን አሳልፈዋል፡፡
ሆኖም በርካታ አትሌቶች አገራቸውን ወክለው ከሚያደርጉት ዓለም አቀፍ ውድድሮች ይልቅ፣ በግላቸው የሚያደርጉት ተሳትፎ፣ በድል ከማጠናቅቅም በላይ ክብረ ወሰኖችን ጭምር አሻሽለው ሲያጠናቅቁ ሰንብተዋል፡፡
የኮቪድ-19 ወርርሽኝ መከሰቱን ተከትሎ በውድድር ዕጥረት ተመትተው የቆዩት አትሌቶቹ፣ ወርርሽኙ ጋብ ሲል በተለያዩ ዓለም አቀፍ ሻምፒዮናዎች ላይ መካፈሉን ተያይዘውት ነበር፡፡ በአንፃሩ በግል ውድድሮች የሚያሳዩት ድንቅ ብቃት፣ አገርን ወክለው ሲወዳደሩ መደገም አለመቻሉ በበርካቶች ዘንድ ጥያቄን የሚያጭር ጉዳይ ሲሆን ይስተዋላል፡፡
ለዚህም ኮቪድ-19 ወረርሽኝን ከተከሰተ በኋላ በተሰናዳው የቶኪዮ ኦሊምፒክ ጨዋታ ላይ የተካፈለው የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ቡድን፣ እንደተጠበቀው ውጤት ማምጣት አልቻለም ነበር፡፡ የኦሊምፒክ ጨዋታ ከመጀመሩ አስቀድሞ፣ የአትሌቶች ምርጫ ሲያከራክር ቢቆይም፣ ውጤቱ ግን የምርጫውን ያክል ውኃ ያነሳ ጉዳይ አልነበርም፡፡
ለዚህም ውድድሩን በቅጡ እንኳን ሳያገባድዱ አቋርጠው የወጡ አትሌቶች ሁኔታ በምሳሌነት ይነሳል፡፡ ከዚህም ጋር ተያይዞም አትሌቶች አኅጉር አቀፍ እንዲሁም አገር አቀፍ ሻምፒዮናዎችን ለግል ውድድሮች ማሟሻነት ለማዋል እንደሚጠቀሙት ይተቻል፡፡
የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ለአኅጉሯዊ ውድድሮች የአትሌቶችን ስም ዝርዝር ይፋ ሲያደርግ፣ ሁሉም በየጎራው ትችት ሲሰነዝር የመስተዋሉ ምክንያት ከአትሌቶች ምርጫ ጀርባ የተለያዩ ፍላጎቶች መኖራቸው እንደሆነ የሚገልጹ አሉ፡፡ ይሄም መመረጥ ነበረባቸው የሚለው ጫና ከአሠልጣኞች፣ ማናጀሮች እንዲሁም ከክለቦች የሚመጣ ጫና ሳይሆን እንዳልቀር የሪፖርተር ምንጮች አስተያየታቸውን ይሰጣሉ፡፡
እንደ ምንጮቹ አስተያየት ከሆነ፣ ማናጀሮች ከስፖንሰር አድራጊ ተቋማት ጋር ያላቸው ቁርኝትና የጥቅም ትስስር፣ አትሌቶች አገራቸውን ወክለው በሚያደርጉት ውድድር ይልቅ በግል ውድድሮች ላይ ትኩረት እንዲያደርጉ ጫና እንደሚያደርጉ ይነገራል፡፡ በአትሌቶች፣ በአሠልጣኞች እንዲሁም በማናጀሮች መካከል ያለው ግንኙነት በጥቅም የተሳሰረ ከመሆኑም በላይ እንደቀድሞ አሠልጣኞች መከባበርና መደማመጥ እንደሌለ ለአትሌቲክሱ ቅርብ የሆኑ ምንጮች ለሪፖርተር ያስረዳሉ፡፡
በተለይ በተለያዩ ዓለም አቀፍ መድረኮች ላይ በተደጋጋሚ የተካፈሉና ስማቸው የገነነ አትሌቶች ለአሠልጣኞች ያለመታዘዝ ባህሪ እንደሚያሳዩ የሚጠቅሱ አሉ፡፡
በዘንድሮ የኦሪጎን ዓለም ሻምፒዮና ላይ የሚሳተፈው የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ብሔራዊ ቡድን በተለያዩ ርቀቶች ላይ የሚካፈሉ አትሌቶችን ስም ዝርዝር ይፋ አድርጓል፡፡ በዝርዝሩ ተጠባባቂ አትሌቶች ሳይቀሩ ተካተዋል፡፡ አትሌቶቹም ሰኞ ሰኔ 13 ቀን 2014 ዓ.ም. ሆቴል ገብተው ዝግጅት እንዲጀምሩ ብሔራዊ ፌዴሬሽኑ አስታውቋል፡፡
ብሔራዊ ፌዴሬሽኑ የአትሌቶችን ስም ዝርዝር ይፋ ካደረገ በኋላ የተለመደው የምርጫ ቅሬታ እየተነሳ ይገኛል፡፡ በዚህም በምርጫው መካተት የሌለባቸው አትሌቶች ተካተዋል የሚልና በአግባቡ ያልተገመገመ ምርጫ ነው የሚል ክስ እየቀረበ ነው፡፡
ሆኖም የተመረጡት አትሌቶች ከሰኞ ጀምሮ ዝግጅታቸውን አድርገው በሻምፒዮናው ላይ በግል ያሳዩትን ብቃት የአገራቸውንም ባንዲራ አንግበው ይደግሙታል የሚለው የብዙኃን ተስፋ ነው፡፡