ከተጀመረ ሃያ ወራትን ያስቆጠረው የሰሜን ኢትዮጵያ ጦርነት ዘግናኝ ለሆኑ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች ብሎም በሰብዓዊነት ላይ የተፈጸመ ወንጀል ለመሆን ዕድል ላላቸው ጥሰቶች ምክንያት ስለመሆኑ ተደጋጋሚ ሪፖርቶች ወጥተዋል፡፡ የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽንና የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የሰብዓዊ መብቶች ከፍተኛ ኮሚሽነር ጽሕፈት ቤት በትግራይ ክልል የተፈጸሙ የሰብዓዊ መብቶች ጥሰቶችን አስመልክቶ ጥቅምት 24 ቀን 2014 ዓ.ም. ያወጡት ከእነዚህ ሪፖርቶች ውስጥ አንዱ ነው፡፡ ይህ ሪፖርት ይፋ በተደረገበት ዕለት ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) ባወጡት መግለጫ መንግሥታቸው የምርመራ ውጤቱን እንደሚቀበለው ገልጸው፣ በሪፖርቱ ላይ የተቀመጡ ምክረ ሐሳበችን የሚስፈጽም የሚኒስትሮች ግብረ ኃይል ማቋቋማቸውን አስታውቀዋል፡፡ በአራት ኮሚቴዎች የተዋቀረው ግብረ ኃይሉ የተፈጸሙ ጥሰቶችን የመመርመርና ክስ የመመስረት፣ የስደተኞችና ተፈናቃዮችን ጉዳይ የመከታታል፣ ከወሲባዊና ከፆታዊ ጥቃቶች ጋር የተያያዙ ሥራዎችን የመሥራትና ሀብት የማሰባሰብ ኃላፊነቶች አሉት፡፡ የሚኒስትሮች ግብረ ኃይሉ በይፋ ሥራ ከመጀመረበት ኅዳር 20 ቀን 2014 ዓ.ም. አንስቶ በእስካሁኑ ቆይታው ለመቋቋሙ መነሻ የሆነውን በትግራይ ክልል የተፈጸሙ ጥሰቶችን ምርመራ ማድረግ ባይችልም፣ የጦርነቱ መስፋትን ተከትሎ በአፋርና በአማራ ክልሎች የተፈጸሙ ጥሰቶች ላይ ምርመራ አድርጓል፡፡ የግብረ ኃይሉ ጽሕፈት ቤት ኃላፊ ታደሰ ካሳ (ዶ/ር) ስለግብረ ኃይሉ ሥራዎች፣ በሁለቱ ክልሎች ስላደረገው ምርመራ፣ ስለገለልተኝነቱና ተያያዥ ጉዳዮች አማኑኤል ይልቃል አነጋግሯቸዋል፡፡
ሪፖርተር፡- የሚኒስትሮች ግብረ ኃይል ከሰሜን ኢትዮጵያ ጦርነት ጋር በተያያዘ በተፈጸሙ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች ላይ ስላከናወናቸው ተግባራት በቅርቡ በኢትዮጵያ ለሚገኙ የአውሮፓ ኅብረት አባላት አገሮች አምባሳደሮች ገለጻ አድርጓል፡፡ ገለጻው ምን ነበር?
ታደሰ (ዶ/ር)፡- የጀመርነው ሒደት ግልጽነት ያለው መሆን አለበት የሚል መነሻ አለን፡፡ በመደበኛ መንገድ የወንጀል ተጠያቂነትን ለማረጋገጥና ሌሎች ደጋፊ ሥራዎች ለማከናወን ከምንሄድባቸው በተለየ ስታንዳርድ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በቋሚነት እየተገናኘን፣ አጠቃላይ ሒደቱ የሚመራባቸውን መሠረታዊ መርሆዎች እያስረገጥን፣ በየጊዜው የሚወሰዱ ዕርምጃዎችን ገለጻ እያደረግን የሚከናወን ሒደት ነው ብለን ነው የጀመርነው፡፡ በዚህ መሠረት አሁን የሚመለከታቸውን አካላት በየጊዜው እናገኛለን፡፡ ከአውሮፓ ኅብረት ጋር የነበረን ግንኙነት በዚህ ዓይነት ማዕቀፍ ውስጥ የሚታይ ነው፡፡ የውይይቱ ዓላማ መንግሥት ግልጽ አቋም ወስዶ የጀመረውን ይህንን ሒደት በተመለከተ ተጠያቂነትን ማረጋገጥ፣ ደጋፊ የሆኑ ሥራዎችን ማከናወንና በጦርነቱ በተፈጸሙ ጥሰቶች የደረሱ ጉዳቶችን አስመልክቶ መዋቅራዊ በሆነ አካሄድ የተወሰዱ ዕርምጃዎችን ማሳየት ነው፡፡ ከሁለትና ከሦስት ወራት በፊት ስንገናኝ ይህንን መዋቅር ዘርግተናል፡፡ እነዚህን ጉዳዮች ልንፈጽም ነው ብለን ዕቅዳችንን ነበር ያቀረብንላቸው፡፡ አሁን እነሱም የሚጠይቁትና ተፅዕኖ የሚያሳድሩት ባለፉት ሦስት ወራት ምን ሠራችሁ የሚል ነው፡፡ ባስቀመጥነው የጊዜ ቅደም ተከተል መሠረት ስለተሠሩ ሥራዎች ገለጻ አድርገናል፡፡
ሪፖርተር፡- የአውሮፓ ኅብረት የሰብዓዊ መብቶች ልዩ ተወካይ ኢመን ጊልሞር በግንቦት 2014 ዓ.ም. ወደ ኢትዮጵያ መጥተው የሦስት ቀናት ቆይታ አድርገው ነበር፡፡ ስለቆይታቸው በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ ከሰሜን ኢትዮጵያ ጦርነት ጋር ተያይዞ ያገኙትን መረጃ በሰኔ ወር ሪፖርት ለአባላት አገሮች እንደሚያቀርቡና አገሮቹም ይህንን መሠረት አድርገው ውሳኔ እንደሚያሳልፉ አስታውቀዋል፡፡ ከልዩ ተወካዩ ጋር ንግግር ነበራችሁ?
ታደሰ (ዶ/ር)፡- ለሌሎች ያደረግነው ሰፊ ገለጻ ለእሳቸውም ተደርጓል፡፡ በአገሪቱ ያለው ሥርዓት ጉዳዩን ለማስተናገድ ብቁ መሆኑን፣ የፖለቲካ ቁርጠኝነት መኖሩን፣ በምክረ ሐሳብነት የተሰጡ ጉዳዮችን ይዞ ተግባራዊ ለማድረግ እንቅስቃሴ እየተደረገና ግብረ ኃይል ተቋቁሞ መዋቅሮችም እንደተደራጁ ገለጻ ተደርጓል፡፡ የአውሮፓ አገሮችም ሆኑ አሜሪካ ጫና ማሳደር የሚፈልጉት በሁለት ጎኖች ነው፡፡ አንደኛው ጥምር ሪፖርቱ ያቀረባቸው ምክረ ሐሳቦችን አስመልክቶ ቃል የተገቡ ጉዳዮች በመደበኛ መዋቅር እንዲፈጸሙ ይፈልጋሉ፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ ተጨማሪ ዓለም አቀፍ ቡድን ምርመራ እንዲያደርግ በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ሰብዓዊ መብቶች ካውንስል በኩል የሄዱበት ርቀት አለ፡፡ በዚህ እንዲጣራ የሚፈልጉት የወንጀል ተጠያቂነት አለ፡፡ በዚህ ላይ የራሳቸው ሐሳብ ቢኖራቸውም እኛ ደግሞ ይህንን አስፈላጊ የማያደርጉትን ተጨባጭ ሁኔታዎች ከፖለቲካዊ ቁርጠኝነት እስከ ፈጽሞ ማሳየት ድረስ ዝርዝር ነገሮች ለእሳቸው አቅርበናል፡፡
ሪፖርተር፡- ግብረ ኃይሉ የተቋቋመው ጥምር ሪፖርቱን መሠረት አድርጎ ቢሆንም፣ ጦርነቱ ወደ አፋርና አማራ ክልሎች ሲስፋፋ የተፈጸሙ ወንጀሎች ላይም ምርመራ ማድረጉና ይህ ምርምራም እየተጠናቀቀ መሆኑ ተገልጿል፡፡ በዚህ ምርመራ የሠራችሁት ሥራ ምንድነው?
ታደሰ (ዶ/ር)፡- በሁለቱ ክልሎች የተደረገውን ምርምራ የምንመለከተው በሦስት የተለያዩ ደረጃዎች ነው፡፡ የተፈጸሙት ወንጀሎች ብዛት ከፍተኛ ከመሆኑ ባሻገር፣ ከባድ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች የተፈጸሙባቸው አካባቢዎች ሰፊ ስፋት ያላቸው ናቸው፡፡ አማራ ክልል ብቻ ስታስበው ከጎጃም አካባቢ ውጪ በአንድ ይሁን በሌላ ተፅዕኖው ደርሶበታል፡፡ እዚህ ላይ ትልቅ አጥኚ ቡድን ማሰማራት ብዙ ሀብትና የሰው ኃይል ይጠይቃል፡፡ ስለዚህም ሁሉም ምርመራ በአንዴ የሚሠራበት ዕድል የለም፡፡ በየደረጃው በተለያዩ አካላት የሚፈጸሙ የተለያዩ ወንጀሎችን በየጊዜው እያየን ነው የመጣነው፡፡ አሁን ለአራትና አምስት ወራት ትኩረት ያደረግነው በሕወሓት የተፈጸሙ ወንጀሎች ላይ ነው፡፡ ማስረጃዎች ከመጥፋታቸው በፊት እንዲሰበሰቡ አድርገናል፡፡ ሕወሓት ከአካባቢው ከወጣ በኋላ ምርመራውን ለማድረግ የሚከለክለን ነገር ስለሌለ በጊዜ መሰብሰብ የነበረባቸውን አካላዊ ማስረጃዎች የመሰብሰብ፣ የማይሰበሰቡትንም በቪዲዮና በፎቶግራፍ የመያዝ ሥራ ተሠርቷል፡፡ የዓይን እማኞችም አንዴ ከተበታተኑ መልሰው አይገኙም፡፡ ስማቸውና አድራሻቸው ተይዞ ትውስታው አዕምሮአቸው ውስጥ ትኩስ እንደሆነ ምስክርነታቸው ወደ ጽሑፍ ካልሰፈረ በኋላ አስቸጋሪ ይሆናል፡፡ ከዚህ አንፃር በምርመራ ሒደት ቅድመ ዝግጅት ላይ ያሉ ሥራዎች ከሞላ ጎደል ተሠርተዋል፡፡ አሁንም ያልተሠሩ አነስተኛ ሥራዎች ግን አሉ፡፡ በሁለቱ ክልሎች ብቻ ከአሥር ሺሕ በላይ ሰዎች ቃለ መጠይቅ ተደርጎላቸዋል፡፡ የአንዱ ከፍ የአንዱ ዝቅ ሊል ይችላል እንጂ፣ በሁለቱ ክልሎች ለተፈጸሙ ወንጀሎች ብዙ አካላት የተለያየ ድርሻ ነበራቸው፡፡ የተለያዩ አካላት የነበራቸው ተሳትፎ በትግራይ ክልል በነበረው መልኩ ነው የተደገመው፡፡ ጥምር ሪፖርቱም በትግራይ ክልል የተለያዩ አካላት በተለያየ ደረጃ የሚገለጽ ኃላፊነት እንዳለባቸው ነው ያሳየው፡፡ በዚህ በኩል ያለውን ከፍተኛ የሆነ ማስረጃ የማሰባሰብ ሥራ ተጠናቋል፡፡ ነገር ግን በቀጣይ ማስረጃውን መተንተን፣ የትኛው ማስረጃ የትኛውን ወንጀል ይደግፋል የሚለውን መወሰን፣ ለክስ የሚደረጉ ቅድመ ሥራዎችን መሥራትና የቀሩ ሥራዎችን ማጠናቀቅ ይጠይቃል፡፡
ሪፖርተር፡- በትግራይ ክልል የተፈጸሙ የሰብዓዊ መብቶች ጥሰትን በተመለከተ የጥምር ምርመራ ሪፖርት ያሳየው አንዱ ጉዳይ በኤርትራ ኃይሎች የተፈጸሙ ጥሰቶች መኖራቸውን ነው፡፡ ግብረ ኃይሉ የተሰጠው አንዱ ኃላፊነት ምርመራ ማድረግና ክስ መመሥረት እንደ መሆኑ፣ ኢትዮጵያውያን ያልሆኑ ኃይሎች ለፈጸሙት ወንጀል እንዴት ክስ ሊመሠረት ይችላል?
ታደሰ (ዶ/ር)፡- በትግራይ ክልል ምርመራችን ሁለት የውጭ ግንኙነትን የመንካት ዕድል ያላቸው ጉዳዮች ሊያሳይ ይችላል፡፡ አንዱ በማይካድራው ወንጀል ቀጥተኛ ተሳትፎ የነበራቸው ወጣቶችና የትግራይ ክልል አመራሮች ወደ ሱዳን ሸሽተዋል፡፡ ሁለተኛው የኤርትራ ሠራዊት አባላት በትግራይ ውስጥ ፈጽመዋቸዋል ተብለው የተገለጹ በጣም ከባድና ዘግናኝ ወንጀሎች አሉ፡፡ የእኛ አካሄድ ማናቸውም ወንጀሎች በማናቸውም አካል በየትኛውም ሁኔታ ውስጥ ቢፈጸሙ መጣራት አለባቸው የሚል ነው፡፡ እየሠራን ያለነውም በዚሁ አግባብ ነው፡፡ ትግራይ ውስጥ ፈቃድ ቢኖር የምናጣራው የትግራይ ኃይሎች የፈጸሟቸውን ወንጀሎች ብቻ አይደለም፡፡ በመከላከያ፣ በሚሊሻ፣ በልዩ ኃይልም ሆነ በየትኛውም አደረጃጀትና መሣሪያ ታጣቂ የተፈጸመ፣ የትኛውም የወንጀል ሕጋችንንና ዓለም አቀፍ ሕጎችን የሚጥስ ድርጊት ሁሉ ይመረመራል፣ ተጠያቂነትም ይረጋገጣል፡፡ በዚህ ጉዳይ የመንግሥት ቁርጠኝነትም በጣም ግልጽ ነው፡፡ በዚህ መሠረት የኤርትራ ሠራዊትም ሆነ የሳምሪ ቡድን የፈጸሙት የሚተው ወንጀል የለም፡፡ ይህንን እንዴት ታስፈጽሙታላችሁ ነው ቀጣዩ ጥያቄ፡፡ ወንጀልን መመርመር አንድ ነገር ነው፣ የኤርትራ ወታደሮችን መክሰስ ሌላ ነገር ነው፡፡ በዕቅዳችን ውስጥ ለመፈጸም ያካተትነውና የምንፈጽመውና እንደ መንግሥት ግዴታ የገባንበት ጉዳይ እንመርምረው የሚለው ነው፡፡ ከምርመራው በኋላ ግን መከተል የሚገባንን ዕርምጃ በምክረ ሐሳብ ለመንግሥት ማቅረብ ብቻ ነው፡፡ ከኤርትራ መንግሥት አንፃር የምንከተለው ፖሊሲ ምንድነው? በሱዳን የስደተኛ ጣቢያዎችና ሌሎች ቦታዎች የተጠለሉ፣ ከጦርነት እስከ ሰብዓዊነት ላይ የተፈጸመ ወንጀል የሚደርስ ሰዎችን አስመልክቶ ከሱዳን መንግሥት ጋር የምንከተለው ፖሊሲ ምን ሊሆን ይችላል? አሳልፎ መስጠት ነው? ሁለቱ አገሮች መረጃ በመለዋወጥ የራሳቸውን የፍትሕ አሠራር ተጠቅመው እንዲቀጡ ማድረግ ነው? የሚለው የመንግሥት ውሳኔ ነው፡፡ የእኛ ሥራ የሚሆነው መመርመር፣ ምርመራው የሚያሳየውን አሳማኝ መረጃ መመልከት፣ በዚህ ላይ ተመሥርተን ደግሞ ቀጣዩን ዕርምጃ የሚወስን ምክረ ሐሳብ ማቅረብ ነው፡፡ ምክንያቱም ይህ ከውጭ አገሮች ጋር ያለ ግንኙነት፣ ወዳጅነት፣ ጠላትነትና ብዙ ጉዳዮች ታይቶ የሚወሰን ውሳኔ ነው እንጂ እንደ ሌሎች በአገር ውስጥ አካላት እንደተፈጸሙ የወንጀል ዓይነቶች ብይዘውም እይዘዋለሁ፣ ካልያዝኩትም ተከሳሸ የሌለበት የሚካሄድ ችሎት (In Absentia Proceeding) አያደረግኩ እቀጥላለሁ የሚባል ጉዳይ አይደለም፡፡ በጣም ጥንቃቄ የሚሻ ጉዳይ መሆኑ ከግምት ውስጥ መግባት አለበት፡፡
ሪፖርተር፡- አሁን ባለው ሁኔታ ግብረ ኃይሉ ምርመራ ማድረግ የቻለው በአማራና በአፋር ክልሎች የተፈጸሙ ወንጀሎችን ነው፡፡ በእነዚህ ክልሎች የተፈጸሙ ወንጀሎች ደግሞ በአብዛኛው የተፈጸሙት በትግራይ ኃይሎች መሆኑ ይታወቃል፡፡ የትግራይ ኃይሎች ወደ ክልሉ የተመለሱ በመሆናቸውና ወደ ትግራይ ክልል ለመግባት ደግሞ የሚያስችል ሁኔታ ባለመኖሩ፣ ያደረጋችሁት ምርመራ ለሚያመላክታቸው ወንጀሎች ተጠያቂነትን እንዴት ታመጣላችሁ?
ታደሰ (ዶ/ር)፡- በወንጀል ተሳትፎ ኖሯቸው የተያዙ ብዙ የኃይሉ አባላት እንዳሉ ሁሉ፣ ወንጀል ፈጽመው ያልተያዙ የኃይሉ አባላትም አሉ፡፡ በግል የተፈጸሙ፣ በቡድንም የተፈጸሙ ወንጀሎች አሉ፡፡ እኛ ይህንን ጉዳይ የምናየው ከተጎጂዎች ዓይን አኳያ ነው፡፡ ለተጎጂዎች ዋነኛው ጉዳይ ፍትሕ መስፈኑ ነው፡፡ ሰውየውን ያዝከው አልያዝከው ሁለተኛ ጉዳይ ነው፡፡ ወይም ደግሞ በዚህ ድርጊት ግልጽ የሆነ ተሳትፎ የነበራቸውን፣ የትዕዛዝ መዋቅሩ ሰዎችን ለይተህ ማስቀጣትህ ነው ትልቅ ስኬት ባይ ነኝ፡፡ ከዚህ አንፃር አሁን የጠቀስከው ተግዳሮት ቢኖርም ብቸኛው ተግዳሮት አይደለም፡፡ በሌሎች የተለያዩ የክስ ሒደቶቻችን እንደሚታየው ዕድል ሲቀናህ ወንጀለኛውን የምትይዝበት ዕድል ይኖራል፡፡ ዕድል ካልቀናህ ደግሞ ወንጀለኞቹ ባይኖሩም የክስ ሒደቱ ይቀጥላል፡፡ ፍትሕ ማስፈን በዋንኛነት ወንጀለኛን ከመያዝና አለመያዝ ጋር ቀጥተኛ የሆነ ተያያዥነት ላይኖረው ይችላል፡፡ እኛም ቢሆን ዋነኛ ጉዳይ የምንለው ዓለም አቀፍ አሠራሩን ተጠቅሞ ወንጀለኝነታቸውን ማረጋገጥና ፍትሕን ማስፈን ነው፡፡ ተይዘው ስላልቀረቡ ተብሎ በቂ መረጃ እያለ የምንተውበት ሁኔታ አይኖርም፡፡
ሪፖርተር፡- በአማራና በአፋር ክልሎች ለተፈጸሙ ወንጀሎች መረጃ የማሰባሰብ ሥራ በቶሎ የተደረገበት አንደኛው ምክንያት መረጃዎች እንዳይጠፉ በሚል መሆኑን ጠቅሰዋል፡፡ በትግራይ ክልልስ ይህ ሥጋት የለባችሁም?
ታደሰ (ዶ/ር)፡- በትግራይ ሁኔታ የጥምር ሪፖርቱ ሁሉንም የትግራይ ክፍሎች ሸፍኗል ማለት ባይቻልም ሰፊ መረጃ ሰብስቧል፡፡ ትግራይ ውስጥ ትልልቆቹ ወንጀሎች ተፈጸሙባቸው የተባሉት ማይካድራና አክሱም አካባቢዎች ላይ የነበሩ ማስረጃዎች ተሰብስበዋል፡፡ የአክሱሙ ስላልተጠናቀቀ ቀጣዩን ዕርምጃ መራመድ አልተቻለም እንጂ፣ ተሳትፎ ያላቸው አካላት እነ ማን ናቸው? በምን ደረጃ ተሳትፈዋል? የሚለው ተመላክቷል፡፡ በማይካድራው የነበሩ ተዋንያን የሚያዙት ተይዘው ያመለጡትም አምልጠው የክስ ሒደቱ የደረሰበት ደረጃ ላይ ደርሰናል፡፡ ሰሜን ምሥራቅ፣ ደቡብና ምዕራብ ክፍሎች በሰፊው ተሸፍነዋል፡፡ ስለዚህ በእነዚህ ማስረጃዎች ላይ መመሥረት ይቻላል፡፡ ይህ ማለት ግን የምርመራ ሒደቱ ቀላል ነው ማለት አይደለም፡፡ ከአንድ ዓመት በኋላ አካላዊ መረጃዎችን ማግኘት፣ ተጎጂዎችን ማፈላለግ፣ ምስክሮችን ማሰባሰብ ቀላል አይሆንም፡፡ የሰብዓዊ መብት ጥሰት ምርመራ በአንድ ወይም በሁለት ምስክርነት ላይ ተመሥርቶ ጥሰት ተፈጽሟል ወይም አልተፈጸመም? ሊል ይችላል፡፡ የወንጀልን ድርጊትን ለማረጋገጥ የሚኬድበት ማስረጃ የማቅረብ ሒደት ግን ከዚህ በጣም ከፍ ያለ ነው፡፡ በአንድ በጉዳዩ ላይ ቀጥተኛ ያልሆነ ዕውቀት ያለው ሰው መረጃ ላይ ተመሥርተህ የወንጀል ምርመራ ልትጀምር አትችልም፡፡ በዚህ ደረጃ የሚጠበቀው ሥራ ከፍተኛ ነው፡፡ ለወንጀል ምርመራ እንደ እነሱ ቀጥተኛ ያልሆነ መረጃ ሰብስቦ በዚህ ወረዳ በዚህ ቀን ይህ ወንጀል ተፈጽሟል ማለት አይቻልም፡፡ ከዚህ አንፃር መረጃዎች ሁሉ ባሉበት ይኖራሉ? ወይም ጠቃሚ የሆኑ ምስክሮችን በቀላሉ ማግኘት ይቻላል? የሚለው ላይ በእርግጠኝነት ብዙ ውስብስብ ተግዳሮቶች ይኖራሉ፡፡ ይህ ግን ምርመራ አይካሄድም ማለት አይደለም፡፡ እነዚህ ሁሉ ተግዳሮቶች እያሉ መንግሥት ቁርጠኝነቱን አሳይቷል፡፡ ነባራዊ ሁኔታ ሲፈቅድ ወንጀል ምርመራ የማድረግና ፍትሕ የማስገኘት ሥራው ይቀጥላል፡፡
ሪፖርተር፡- አሁን የተካሄደው ምርመራ በሕወሓት ሥር ያልሆኑትን የምዕራብ ትግራይ አካባቢዎች ያጠቃልላል? ምርመራው እነዚህን አካባቢዎች ካጠቃለለ በቅርቡ አምነስቲ ኢንተርናሽናል ይፋ ያደረገው የምርመራ ሪፖርት ተፈጽመዋል ተብለው ከተጠቀሱት ሁነቶች ጋር የሚመሳሰል ግኝት አላችሁ?
ታደሰ (ዶ/ር)፡- የወልቃይት፣ የፀገዴና የሁመራ አካባቢ እስካሁን ምርመራ ለማድረግ ፖዘቲቭ የሆነ አስቻይ ሁኔታ አለ ለማለት በጣም ከባድ ነው፡፡ ውጥረት ያለበት አከባቢ ነው፡፡ እስካሁን የነበረው ምርመራ የሰሜን ሸዋ፣ የኦሮሞ ብሔረሰብ ልዩ ዞን፣ ኮምቦልቻ ከተማና አካባቢው፣ ደሴ ከተማና አካባቢው፣ ጃማና ወረኢሉ አካባቢው፣ ወልዲያ ከተማና አካባቢው፣ ላሊበላ ከተማና አካባቢው፣ ዋግኽምራና አካባቢው፣ እንዲሁም አፋር ናቸው፡፡ በአጠቃላይ ዘጠኝ ቡድኖች ናቸው የተሰማሩት፡፡ አሥረኛው ቡድን ደግሞ ወደ ትግራይ የሚሰማራና አስቻይ ሁኔታዎችን የሚጠብቅ ነው፡፡ ሌላ ተመሳሳይ ቡድን ደግሞ ወደ በወልቃይት፣ በፀገዴና በሁመራ አካባቢ የተፈጸሙትን ጥሰቶች ይመረምራል፡፡ አምነስቲ ኢንተርናሽናል በሰፊው ሄዶበታል፡፡ እኛ እውነት ነው አይደለም የሚለው ውስጥ መግባት አንፈልግም፡፡ በዋናነት ግን በተደጋጋሚ አንደተገለጸው መንግሥትም ራሱ ብዙ ጥሰቶች እንዳሉ ቅሬታዎች ቀርበውለታል፡፡ ሌላ ቦታ ላይ እንደሚካሄደው ማጣራት ሁሉ በዚህ ሁኔታም ማጣራት ይካሄዳል፡፡ ግን በአካባቢው ያለው የሰላምና የደኅንነት ሁኔታ ብዙ ሥራዎችን የሚጠይቅ ከመሆኑ አንፃር አሁን የሚደረግ አይደለም፡፡
ሪፖርተር፡- አሁን ምን እየሠራችሁ ነው? የምርመራችሁን ውጤት መቼ ይፋ ታደርጋላችሁ?
ታደሰ (ዶ/ር)፡- የምርመራ ሥራዎችን እያከናወንን ያለነው በደረጃ በደረጃ ነው፡፡ ሰፊ የሆነ መረጃ በተሰበሰበባቸው ዘጠኝ የምርመራ ክላስተሮች የተሠሩት ሥራዎችን በተመለከተ መረጃ አጠናቅረን ሪፖርት ለማውጣት ዝግጅት ጀምረናል፡፡ መንግሥትና ሌሎች ተቋማት እንደሚያደርጉት ሁሉ በጣም ጠንካራ የሆኑ መረጃዎች ላይ መሠረት ያደረገ፣ የክስተቶቹን አካሄድ የሚያመለክት፣ የተሳታፊዎቹን ድርሻ የሚያሳይ፣ የወንጀል ዓይነቶቹንም የከፋፈለና ዝርዝር የሆነ ሪፖርት በአንድ ወር ወይም አንድ ወር ከግማሽ ጊዜ ውስጥ ያወጣል፡፡ ይህ ሪፖርት ሌሎቹ ተቋማት እንደሚያደርጉት ሁሉ የተፈጸሙትን ወንጀሎች ዋና ዋና ክላስተሮች በቁጥር፣ በፆታና በአካባቢ ዝርዝር መረጃ ነው ይዞ የሚወጣው፡፡
ሪፖርተር፡- የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) እና የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የሰብዓዊ መብቶች ከፍተኛ ኮሚሽነር ጽሕፈት ቤት ያደረጉት ጥምር የምርመራ ሪፖርት ሲወጣ ብዙ ተቀባይነትን አግኝቶ ነበር፡፡ ሕወሓት ግን ኢሰመኮ በምርመራው ላይ መሳተፉን በመቃወም የገለልተኝነት ጥያቄ አንስቷል፡፡ የአስፈጻሚው አካል ያልሆነው ኢሰመኮ ይህ ጥያቄ ከተነሳበት ካቢኔውን የያዘው የሚኒስትሮች ግብረ ኃይል ተመሳሳይ ቅሬታ ይነሳበታበታል የሚል ሥጋት የላችሁም? ምን ያህልስ ከተፅዕኖ ነፃ ናችሁ?
ታደሰ (ዶ/ር)፡- ይህ ጥያቄ ሊነሳ ይችላል፡፡ ግብረ ኃይሉ ግን ሁለት ገጽታ አለው፡፡ አንዱ ይህ ሥራ ከመደበኛው የወንጀል ምርመራና የፍትሕ ሒደት የተለየ ነው፡፡ ከመጀመሪርያው ቀን አንስቶ ነፃነትና ገለልተኝነት ተረጋግጦ እንቅስቃሴ ካልተደረገ፣ በቀኑ መጨረሻ ዕጣ ፈንታው የሚሆነው የፖለቲካ ሒደቱ በሚያሳድረው ጫና ተገቢነትንና እምነትን ማጣት ነው፡፡ ይህንን ለማስቀረት ከፍተኛ ጥንቃቄ እያደረግን ነው ያለነው፡፡ እንደ ዕድለኝነት ደግሞ እውነቱን ለመናገር በሁሉም ዘርፍ ያሉ ሥራዎች በተቀናቀጀ መንገድ እየተካሄዱ ነው፡፡ መንግሥትም በተቻለ መጠን በትንንሽ ዝርዝሮች ደረጃ እንኳን ጣልቃ የገባበት አጋጣሚ እኔ አላውቅም፡፡ መንግሥት ያለው ‹‹የወንጀል ምርመራ ይደረግ›› ነው፡፡ ማን ላይ ትኩረት አደርገን ምርመራውን እናድርግ ሲባል ማንም ንፁህ አይደለም፣ በየትኛውም ደረጃ በየትኛውም ወንጀል ላይ ተሳትፎ ያለው የትኛውም ኃይል መጣራት አለበት ተጠያቂ መሆን አለበት ነው የተባለው፡፡ እኔ እስከማውቀው ድረስ ‹‹እኔ አልጣራም፣ እኔ አይመለከተኝም›› ብሎ ራሱን ለማራቅ የሞከረ በዝቅተኛ የመንግሥት መዋቅር ላይ ያለ አካል የለም፡፡ ይህ መንግሥት ያለውን ቁርጠኝት ያሳያል፡፡
በቅርቡ በቤኒሻንጉል ጉሙዝ የተከሰቱ ሁለት ክስተቶችን ስንመለከት፣ በአንድም በሌላ የመንግሥት የፀጥታ ኃይሎች የተሳተፉባቸው ናቸው፡፡ በሁለቱም ሁኔታ የወንጀል ክስ ለመመሥረት ዝግጅት ጨርሰዋል፡፡ በሁለቱም ሁኔታዎች ዋነኛ የተባሉት ተሳታፊዎች የመንግሥት ኃይሎች በመሆናቸው፣ አይከሰሱ ወይም ተገቢው ዕርምጃ አይወሰድባቸው የሚል አቋም የለም፡፡ መያዝ የሚገባቸው ሰዎች በተቻለ መጠን ተይዘዋል፡፡ ይህ የሚናገረው ነገር አለ፡፡ ሁለተኛው ሥራውን ከጀመርንበት ቀን አንስቶ ተገቢው የሆኑና የቴክኒክ አቅሙ ያላቸው የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ሰዎች በተቻለ መጠን ለምርመራ ቡድኑ የተለያዩ ሰፊ ሥልጠናዎች ሰጥተዋል፡፡ እስካሁን ሦስት ሥልጠናዎች ተሰጥተዋል፡፡ ሁለቱ ሥልጠናዎች በዓለም አቀፍ የወንጀል ምርመራ ላይ ትኩረት ያደረጉ ናቸው፡፡ አንዱ ሥልጠና የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የሰብዓዊ መብቶች ከፍተኛ ኮሚሽነር ጽሕፈት ቤት ከተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የአደንዛዥ ዕፆችና ወንጀል ቢሮ ጋር በጋራ በመሆን የሰጡት ነው፡፡ እነዚህ ሥልጠናዎች የሚሰጡት የወንጀል ምርመራ ሥራዎች ከሌላው ጊዜ በተለየ ሁኔታ፣ በተለየ ስታንዳርድ፣ በተለየ የገለልተኝነት አስተሳሰብና ነፃነት እንዲከናወኑ ለማድረግ ነው፡፡ ይህ ሁሉ የሒደቱን ገለልተኝነትና ነፃነት ለማረጋገጥ የሚሠራ ነው፡፡ በየሒደቱ ይህ እየተረጋገጠ ካልሄደ መጨረሻ ላይ የሚወጣው ሪፖርት ተቀባይነት አያገኝም፡፡ ስለዚህ የፖለቲካ ሒደቱ በአንድ ወይም በሌላ በምርመራው፣ የክስና የፍትሕ ሒደቱ ላይ ምንም ዓይነት ተፅዕኖ እንዳይኖረው የሚቻለንን ሁሉ እያደረግን ነው፡፡ ወንጀል በመፈጸም ሒደት ውስጥ ተሳትፎ ያለው የመንግሥትም ይሁን የመንግሥት ያልሆነ ኃይል የሚቀጣ መሆኑን በቁርጠኝነት ካሳየህ፣ ከዚህ በላይ ማንም ሰው ምንም የሚጠብቅ አይመስለኝም፡፡
ሪፖርተር፡- በዚህ ሁኔታ ደረጃ በደረጃ ያላችሁን ቁርጠኝነት እያሳያችሁና ምንም ተፅዕኖ እንደማይደርስባችሁ እያረጋገጣችሁ መሄዳችሁን ገልጸዋል፡፡ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅቶች ሥልጠና በመስጠት ዕገዛ እያደረጉ መሆናቸውንም አውስተዋል፡፡ ይሁንና የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የራሱን ምርመራ ለማድረግ ውሳኔ አሳልፎ ዋና መርማሪም ሾሟል፡፡
ታደሰ (ዶ/ር)፡- ይህንን ያደረገው የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ነው ለማለት እቸገራለሁ፡፡ ይሄንን የወሰነው የሰብዓዊ መብቶች ካውንስል ነው፡፡ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት በተለያዩ ጉዳዮች ላይ የተለያዩ ሥልጣን ያላቸው ብዙ ድርጅቶች አሉት፡፡ ስለዚህ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅትንና የሰብዓዊ መብቶች ካውንስሉን እንደ አንድ መውሰድ ከባድ ነው፡፡ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ከመቶ በላይ የሆኑ አገሮችን በአባልነት ሲይዝ፣ ካውንስሉ የጥቂት አገሮች ስብስብ ነው፡፡ ድርጅቶቹ በአንድ ወይም በሌላ አይገናኙም ማለት ግን አይደለም፡፡ የሰብዓዊ መብቶች ካውንስሉ ከፍተኛ ፖለቲካዊ ጫና ባለበት ሁኔታ በተወሰነ ውሳኔ የባለሙያዎች ስብስብን አዋቅሮ ለማሰማራት እንቅስቃሴ ላይ መሆኑ የሚታወቅ ነው፡፡ ይህ ትክክል ነው ወይስ አይደለም? ለሚለው ብዙ ክርክር ሊነሳ ይችላል፡፡ ነገር ግን በትንሹ እንኳን በአገሪቱ ውስጥ ላለው የፍትሕ ሥርዓት ዕድል ሊሰጥ ይገባ ነበር፡፡ ምክንያቱም አንደኛ ዕድሜው አጭር ቢሆንም በንፅፅር ገለልተኛ ሊባል የሚችለው የአገሪቱ የሰብዓዊ መብቶች ተቋም፣ ብዙ ልምድ ካለው የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ጋር ተጣምሮ ያወጣው የምርመራ ሪፖርት ምክረ ሐሳብ እንደገና እንዲሠራና እንዲመረመር የሚያስችል ውሳኔ በመርህ ደረጃ እንኳን የማይመስል አካሄድ ነው፡፡ አንድ ኤጀንሲ ከአገሪቱ የሰብዓዊ መብቶች ተቋም ጋር የሠራውን ሥራ ሌላኛው በድጋሚ ልሥራው ማለቱ ሚዛናዊ አካሄድ ነው ወይ የሚለው ላይ ጥያቄ አለኝ፡፡
ሁለተኛና ትልቁ ነገር ጥምር ሪፖርቱ ሲወጣ መንግሥት፣ ‹‹ይህንን አልቀበልም፣ ሒደቱና ውጤቱ ችግር ያለበት ነው፣ ሚዛናዊም አይደለም፣ አልፈጽመውም፤›› አላለም፡፡ ይህ ቢሆን፣ ‹‹የአገሪቱ ሥርዓት ብቃት የለውም ወይም ፈቃደኛም አይደለም፡፡ የአገሪቱ ሥርዓት የማይመልሰው በመሆኑ ወደ ሁለተኛው አማራጭ ዙሬ ዓለም አቀፋዊ ሥርዓት ልዘርጋ›› የሚለውን ለማሰብ ዕድል ይኖር ነበር፡፡ በዚህ ሁኔታ ግን መንግሥት ማለት የሚገባውን ነገር በሙሉ ብሏል ነው የምለው፡፡ መንግሥት በጥምር ምርመራው ሒደቶች ላይ አንዳንድ ቅሬታዎች ቢኖሩትም የወንጀል ተጠያቂነትና ፍትሕን ማስፈን ብሎ አደረጃጀት መሥርቶ፣ ሀብት መድቦ፣ 158 ባለሙያዎች ለአምስትና ለስድስት ወራት አሠማርቶ እየሠራ በሚገኝበት ሁኔታ፣ ተመሳሳይ የሆነ አካል ለማቋቋም የተሄደበት ርቀት እኔ በግሌ ንፁህ ከሆነ የሰብዓዊ መብት ዕሳቤ የመጣ ነው የሚለው ላይ ሥጋት አለኝ፡፡ የዓለም አቀፍ ሕግ ሀሁ የሚነግረን አንዱና መሠረታዊ ነገር ዓለም አቀፋዊው ሥርዓት የአጋዥነት ድርሻ ብቻ እንደሚኖረው ነው፡፡ በአገሪቱ ውስጥ ያለው ሥርዓት ሊሠራ ባልቻለበት ወይም ፈቃደኛ ባልሆነበት ሁኔታ ብቻ አገልግሎት ላይ የሚውል ነው፡፡ የሰብዓዊ መብቶች ካውንስል ውሳኔ ይህንን መሠረታዊ አሠራር አልፎ የወጣ ነው ነው የምለው፡፡ ይህ ግላዊ አቋሜ ነው፡፡
ሪፖርተር፡- ግብረ ኃይሉ ሲቋቋም በትግራይ ክልል የተፈጸሙትን ጥሰቶች በዳሰሰው ጥምር ምርመራ ላይ ተመሥርቶ ቢሆንም፣ በኋላ የሥራ አድማሱን ወደ አማራና አፋር ክልሎች አስፍቷል፡፡ በሰሜኑ ጦርነት ደረጃ ያህል ባይሆንም በኦሮሚያ ክልልም መንግሥት ከታጣቂዎች ጋር እየተዋጋ ነው፡፡ ግብረ ኃይሉ የኃላፊነት አድማሱን ወደ ኦሮሚያ ክልልም የማስፋት ዕድል ይኖረዋል?
ታደሰ (ዶ/ር)፡- የለውም፡፡ የሚኒስትሮች ግብረ ኃይሉ ሥራው በግልጽ የተቀመጠ ነው፡፡ ሥራው በጥምር ሪፖርቱ ላይ መመሥረትና በአማራና በአፋር ክልሎች ለተፈጸሙ ሁሉም ጥሰቶች ተጠያቂነት ማምጣትና ፍትሕ ማስፈን ነው፡፡ ከዚህ ውጪ ያሉት በመደበኛው የፍትሕ ሥርዓት ነው የሚታዩት፡፡
ሪፖርተር፡- ግብረ ኃይሉ ከተሰጡት አራት ኃላፊነቶች ውስጥ አንደኛው፣ ስደተኞችንና የአገር ውስጥ ተፈናቃዮችን የሚመለከት ነው፡፡ በዚህ ዘርፍ ለተፈናቃዮች የሕግ ማዕቀፍ ለማዘጋጀት ሥራ ጀምራችኋል፡፡ መነሻችሁ ምንድነው?
ታደሰ (ዶ/ር)፡- የእኛ አካሄድ የአገር ወስጥ ተፈናቃዮች ጉዳይ እጅግ ትኩረ የሚሻ በመሆኑ፣ ምላሽ ለመስጠት የሚያስችልና ከመጀመርያ እስከ መጨረሻ የተዘረጋ ሥርዓት ያስፈልጋል የሚል ነው፡፡ ለአገር ውስጥ ተፈናቃዮች ተብሎ የተዘጋጀ ሕግ ባይኖርም፣ የብሔራዊ አደጋ ሥጋት ሥራ አመራር ኮሚሽን የተሰጡት ኃላፊነቶች ይህንን ለመሥራት የሚያችሉ ናቸው፡፡ ነገር ግን በተለያዩ ምክንያቶች ኮሚሽኑ ትከረት ያደረገው የአደጋ ጊዜ ዕርዳታ ሥራዎች ላይ ብቻ ነው፡፡ እኛ ስለአገር ውስጥ ተፈናቃዮች ስናወራ በዚህ ደረጃ ብቻ ያለ ተቋምና አሠራር የትም አያደርሰንም በሚል ነው፡፡ ተፈናቃዮች በተመለከተ ቁልፍ የሚባሉትን ተግባራት ማለትም ተፈናቃዎችን የመመለስ ሥራ፣ ተፈናቅለው ባሉበት ቦታ መሰግሰግ (Local Integration)፣ መልሶ የማቋቋምና ማስፈር፣ እንዲሁም በኢኮኖሚ የማቋቋም ጉዳዮችን የሚይዝ ኃላፊነት ያለው፣ ከተፈናቃዮች ጋር ተያይዞ የሚፈለጉ መብቶችን ማስከበር የሚስችል ቁመና ያለው ተቋማዊ አደረጃጀትና ሕግ ሊኖር ያስፈልጋል ብለን ነው የጀመርነው፡፡ ለዚህ የመጀመርያው ዕርምጃ የሆነው የካምፓላ ኮንቬንሽን የመብት ማዕቀፎችን መተንተን ነው፡፡ የካምፓላን ኮንቬንሽን አፅድቀን ሒደቱ አንድ ደረጃ ሲቀረው ባለቤት በማጣትም አቁመነዋል፡፡ ሰላም ሚኒስቴር ይዞት ነበር፣ በኋላ ላይ የተፈናቃዮች ጉዳይ ከሚኒስቴሩ የኃላፊነት ዝርዝር ውስጥ ወጥቷል፡፡ አሁን ኃላፊነቱ የስደተኞችና ተመላሾች አገልግሎትና የብሔራዊ አደጋ ሥጋት ሥራ አመራር ኮሚሽን መካከል ነው ያለው፡፡
አሁን ሁለት ሥራዎች መከናወን አለባቸው፡፡ አንደኛው ኮንቬንሽኑን የማፅደቅ ሒደቱን ለማጠናቀቅ የሚያስፈገውን ጥናት አጥንቶ ለመንግሥት ማቅረብና እንዲወስን ማድረግ ነው፡፡ ሁለተኛው የኮንቬንሽኑን ማስፈጸሚያ መሣሪያ ማዘጋጀት ነው፡፡ ኮንቬንሽኑ በአዋጅ፣ በደንብ ወይም በመመርያ ይሁን የሚለውን የሚያቀርብ በሰላም ሚኒስቴር የሚመራ መሪና የቴክኒክ ኮሚቴ ተቋቁሟል፡፡ ኮሚቴው በሥሩ የስደተኞችና ተመላሾች አገልግሎት፣ የብሔራዊ አደጋ ሥጋት ሥራ አመራር ኮሚሽንና ሌሎች ዓለም አቀፍ ተቋማትን ይዟል፡፡ ከዚህም ባሻገር ከተፈናቃዮች ጋር የሚያያዙትን አራት ቁልፍ ጉዳዮች የሚመለከት ግልጽ የሆነ ስትራቴጂ፣ ተቋማዊ አደረጃጀትና የፋይናስ ማሰባሰብ ሥርዓት ካልተዘረጋ የተፈናቃዮች ጉዳይ የተጓተተ ይሆናል፡፡ ይህ አንዳይሆን ብሔራዊ የአገር ውስጥ ተፈናቃዮች ስትራቴጂ ለመሥራት ተወስኖ እየተዘጋጀ ነው፡፡ በጀመርናቸው ሥራዎች ኮንቬንሽኑን የማፅደቅ ሒደት እንዲጠናቀቅ ካደረግን፣ ማስፈጸሚያ የሕግ ማዕቀፍ ካወጣንና ስትራቴጂ ካዘጋጀን ትልቅ ስኬት ይሆናል፡፡ ከዚህ በኋላ ጉዳዩ ባለቤት፣ ግልጽ የሕግ ማዕቀፍና መብትና ግዴታቸውን የሚዘረዝር መሣሪያ ስለሚኖር ኃላፊነቱ የሚሰጠው ተቋም የተናጠል ሥራዎችን ብቻ ሳይሆን፣ ከመጀመርያው እስከ መጨረሻው ያሉ ሥራዎችን ማከናወን ይችላል፡፡ መፈናቀሉ ከተከሰተበት ቀን አንስቶ እስከ ወደ መኖሪያ የመመለስና በኢኮኖሚ ማቋቋምን የሚሠራ ተቋም ይኖራል ማለት ነው፡፡
ሪፖርተር፡- ተፈናቃዮችን ወደ መኖሪያቸው የመመለስ ጉዳይ ሲነሳ፣ ከዚህ ቀደም አብሮ ሲኖር የነበረ ሕዝብ በተፈጸሙት ከባድ ወንጀሎች የተነሳ መቃቃር ውስጥ ገብቷል የሚል ሐሳብ ይነሳል፡፡ በጦርነቱ ሳቢያ ከመኖሪያቸው የተፈናቀሉ ሰዎችን ወደ ተፈናቀሉበት ሥፍራ የመመለስ ሥራ ሲታሰብ ይህ ችግር ሊያጋጥም ይችላል የሚል ሥጋት አላችሁ?
ታደሰ (ዶ/ር)፡- አዎ፡፡ የዚህ መልሱ የሽግግር ፍትሕ ነው፡፡ ሌላ ምላሽ የለውም፡፡ የሽግግር ፍትሕ አሁን ላይ በጣም አስፈላጊ ነው፡፡ እስካሁን ድረስ ይህንን ሐሳብ በደንብ አላስተዋወቅነውም፡፡ የሽግግር ፍትሕ ጉዳይ አገራዊና ተለቅ ያለ ጉዳይ ነው፡፡ በአገር አቀፍ ደረጃ ማን በምን ደረጃ ነው ምሕረት የሚሰጠው? ለሚለውም መለኪያ የለም፡፡ ከጦርነቱ ጋር ተያይዞ በተፈጸሙ ጥሰቶች ከተሳተፉት ውስጥ የተወሰነው አካል ጉዳዩ በወንጀል ተጠያቂነት ሥር መታየት አለበት፡፡ የተወሰነው አካል ደግሞ በጥሰቱ ውስጥ ቢሳተፍም፣ ጉዳዩ ሰፊ በሆነ የይቅርታና የሰላም ግንባታ ሒደት መታየቱ የማይቀር ነው፡፡ አሁን በተጠቀሰው ሁኔታ ደግሞ ትክክለኛ የሆነ ዕርቅ ሥራ ይፈልጋል፡፡ የተለያዩ ባለድርሻ አካላት በተፈጠሩት ሁኔታ ማኅበረሰብና ማኅበረሰብ እንዲቃቃር ምክንያት ሆኗል፡፡ የፍትሕ ሥርዓትን በመጠቀም የተፈጸሙትን ሁሉንም ወንጀሎች በክስ ሒደት ለመፍታት መሞከር ዘላቂ የሆነ ሰላም ለማምጣት የሚኖረው ዕድል አነስተኛ ይሆናል፡፡ ስለዚህ የማኅበረሰብና ማኅበረሰብ ንግግር፣ የሰላም ግንባታ ሒደቶችና የዕርቅ ሒደቶች ያስፈልጋሉ፡፡ ይህንን የሚመራ ስትራቴጂ ተዋውቆ ካልተተገበረ በቀር ሙሉ የሆነና ይህንን ሥጋት የሚያስወግድ አሠራር የለም፡፡ ፍትሕ ሚኒስቴር ከአሁኑ ኢትዮጵያ ውስጥ የሽግግር ፍትሕ ቢተገበር ምን ሊመስል ይችላል? የሚለው ላይ ትልቅ ጥናት ሠርቶ በውስጥ እያወያየ ነው፡፡ ይህ አንድ ዕርምጃ ከተራመደ ለብሔራዊ የፖሊሲ ማዕቀፋችንን ግብዓት የሚሆን ሰነድ ሊሆን ይችላል፡፡ የሽግግር ፍትሕ ከወንጀል ተጠያቂነት ባልተናነሰ አስፈላጊ ነው፡፡ ውጥረቶችን ለማርገብና አሁን ካለንበት ወደፊት ለመራመድ ሲታሰብ ከሽግግር ፍትሕ ውጪ የሚቻል አይሆንም፡፡ ተመሳሳይ የሆነ አካል ለማቋቋም የተሄደበት ርቀት እኔ በግሌ ንፁህ ከሆነ የሰብዓዊ መብት ዕሳቤ የመጣ ነው የሚለው ላይ ሥጋት አለኝ፡፡