Tuesday, July 23, 2024
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

የብሔራዊ ባንክ መመርያና መቋቋሚያ ካፒታል ማሟላት ያልቻሉ ባንኮች ዕጣ ፈንታ

ተዛማጅ ፅሁፎች

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ከቅርብ ዓመታት ወዲህ በርከት ያሉ ባንኮች ወደ ባንክ ኢንዱስትሪው ለመግባት ያደርጉ የነበረውን እንቅስቃሴ በመረዳት የባንኮች ዝቅተኛ የተከፈለ የካፒታል መጠን ቀደም ሲል ከነበረበት 75 ሚሊዮን ብር ወደ 500 ሚሊዮን ብር ከፍ እንዲል አደረገ።

በዚህም ሳያበቃ ባንኩ በመጋቢት ወር 2013 ዓ.ም. ባወጣው መመርያ፣ ባንክ ለማቋቋም ይጠይቅ የነበረውን የተከፈለ ካፒታል መጠን ወደ አምስት ቢሊዮን ብር ማሳደጉን በመመርያ መደንገጉ ይታወሳል፡፡ መመርያውም ነባር ባንኮች በአምስት ዓመታት ውስጥ ካፒታላቸውን አምስት ቢሊዮን ብር እንዲያደርሱ ሲደነግግ፣ በምሥረታ ላይ ያሉ ባንኮች ደግሞ በመመርያው የተደነገገውን ለማሟላት እስከ ሰባት ዓመት የጊዜ ገደብ ተሰጥቷቸው ነበር፡፡ ከዚሁ ጋር ተያይዞም መመርያው በምሥረታ ላይ ያሉ ባንኮች 500 ሚሊዮን ብር ካፒታል በስድስት ወራት ውስጥ በማሟላት ባንክ ማቋቋም የሚችሉበትን ዕድል ያሰፈረ ነበር፡፡

በተሰጠው የጊዜ ገደብ ውስጥ 500 ሚሊዮን ብር የተከፈለ ካፒታል አሟልተው ባንኩን መመሥረት ካልቻሉ ግን፣ በአዲሱ መመርያ መሠረት የግድ ባንክ ማቋቋም የሚችሉት የተከፈለ ካፒታላቸውን አምስት ቢሊዮን ብር ሲያደርሱ እንደሚሆን ብሔራዊ ባንክ በጊዜው ማሳሰቡ የሚታወስ ነው፡፡

ተቆጣጣሪ ተቋሙ በምሥረታ ላይ የሚገኙ ባንኮች በስድስት ወራት ውስጥ ሊያሟሉ ይገባል ያለው ዝቅተኛ የተከፈለ የካፒታል ማሟያ ቀነ ገደብ ጥቅምት 2 ቀን 2014 ዓ.ም. ማብቃቱ የሚታወስ ሲሆን፣ በዚህ ሒደት ውስጥ ጥቂት ባንኮች የተፈለገውን ቅድመ ሁኔታ ቢያሟሉም፣ ብዙዎቹ በምሥረታ ሒደት ውስጥ የሚገኙ ባንኮች ተፈላጊውን ቅድመ ሁኔታ ሳያሟሉ መቅረታቸው ይገለጻል፡፡

በኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ የባንክ ቁጥጥር ዘርፍ ዳይሬክተር አቶ ፍሬዘር አያሌው እንደተናገሩት፣ በፋይናንስ ዘርፉ እየተደረጉ የሚገኙ ለውጦችን ተከትሎ ባንኮች የምሥረታ ፈቃድ ለማግኘት ጥያቄ አቅርበዋል፡፡ ብሔራዊ ባንክ በጥቅምት ወር 2014 ዓ.ም. ባንክ ለመመሥረት የሚያስፈልገው ዝቅተኛ የካፒታል መጠን ከ500 ሚሊዮን ብር ወደ አምስት ቢሊዮን ብር ከፍ መደረጉን ያስታወሱት አቶ ፍሬዘር፣ አጠቃላይ መሥፈርቱን ላሟሉ ፈቃድ እየተሰጠ ይገኛል፡፡

የመመሥረቻ ፈቃድ ከጠየቁ 25 አዳዲስ ባንኮች መካከል ብሔራዊ ባንክ ያወጣውን መሥፈርት አሟልተው ለተገኙ ስምንት ባንኮች ፈቃድ መሰጠቱ የተገለጸ ሲሆን፣ ከስምንቱ ባንኮች በተጨማሪ ሦስት ባንኮች ፈቃድ የማግኘት ሒደቱን እያጠናቀቁ ስለሚገኙ ሦስት ወር ባልሞላ ጊዜ ውስጥ ፈቃድ እንደሚያገኙ ይታመናል፡፡

ባለፉት አራት ዓመታት በርካታ ባንኮች ወደ ኢንዱስትሪው ለመምጣት ያደረጉትን እንቅስቃሴ የሚያነሱት የፋይናንስ ባለሙያዎች፣ የእነዚህ ሁሉ ባንኮች ወደ ኢንዱስትሪው መግባት እንዲሁም ለመግባት የሚያደርጉት እንቅስቃሴ ለኢንዱስትሪው ጤንነትና መረጋጋት በጣም አሳሳቢ ስለሆነ፣ ብሔራዊ ባንክ ያደረገው የካፒታል ጭማሪ ሌሎች አዳዲስ ባንኮች ዘርፉን እንዳይቀላቀሉ የተደረገ ውሳኔ ሲሉ ቆይተዋል፡፡

አቶ ፍሬዘር ለሪፖርተር እንዳስታወቁት፣ ዝቅተኛ የተከፈለ የካፒታል መጠንን በስድስት ወራት ውስጥ እንዲያሟሉ ተጠይቀው ማሟላት ያልቻሉት ከዚህ በኋላ ማሟላት የሚጠበቅባቸው አምስት ቢሊዮን ብር መሆኑን ተናግረዋል፡፡ እንደ ኃላፊው ገለጻ፣ ከዚህ በኋላ የፈቃድ ሒደቱ የሚሰጠው አምስት ቢሊዮን ብር የተከፈለ ካፒታል ለሚያሟሉት ባንኮች ብቻ ይሆናል፡፡ ይህንን ማሟላት ወይም ማምጣት ያልቻሉ ባንኮች የምሥረታ ሒደት የሚቋረጥ መሆኑን አስረግጥው ገልጸዋል፡፡

ሪፖርተር ከዚህ ቀደም እንደዘገበው የአክሲዮን ሽያጭ ሲያካሂዱ የቆዩትና 500 ሚሊዮን ብር ካፒታል በማሟላት ምሥረታ ያላካሄዱ ባንኮች ከአሥር በላይ የሚደርሱ ሲሆኑ፣ በተቀመጠው ቀነ ገደብ ካፒታላቸው ሞልቶ ሳያመለክቱ በመቅረታቸው አጣብቂኝ ውስጥ እንደገቡ ሲገለፅ የቆየ ጉዳይ ነው፡፡

የፋይናንስ ባለሙያዎች እንደሚያስረዱት፣ በኢትዮጵያ አንድ ባንክ ለማቋቋም የሚጠየቀው ካፒታል አነስተኛ በመሆኑ አነስተኛ አቅም ያላቸው ባንኮች ገበያውን እንዲሞሉት ዕድል የፈጠረና መንግሥት ዘርፉን ለውጭ ገበያ ክፍት ቢያደርገው ፈጽሞ መወዳደር እንደማይችሉ በመግለጽ፣ መንግሥት አስገዳጅ ሕግ በማውጣት በሥራ ላይ ያሉት ባንኮች እንዲዋሃዱ ሊያስገድድ ይገባል የሚል ምክረ ሐሳብ ሲያቀርቡ ይሰማል፡፡

በዘርፉ ረዥም ጊዜ የቆዩት አቶ ኢየሱስወርቅ ዛፉ በአንድ ወቅት በኢትዮጵያ የሚገኙ ከ20 በላይ ባንኮችና ገና በምሥረታ ላይ ያሉትን ጨምሮ ከውጪ ከሚመጣው ጋር ለመወዳደር ቁጥራቸው ቢያንስ ወደ አምስት ወይም ወደ ሰባት መሰብሰብ እንዳለባቸው አስተያየት መስጠታቸው እንዲሁ የሚታወስ ጉዳይ ነው፡፡

ከዚህ በፊት ፈቃድ ለማግኘት የጠየቁ ባንኮች በአብዛኛው የተጠየቀውን አምስት ቢሊዮን ብር ካፒታል ማሟላት ስላልቻሉ የምሥረታ ሒደቱን ወደ ማቋረጥ ውስጥ እየገቡ መሆናቸውን ሪፖርተር ከብሔራዊ ባንክ ያረጋገጠ ሲሆን፣ እነዚህ ባንኮች ወይም አደራጅ ኮሚቴዎች የተሰበሰበውን ገንዘብ የመመለስ ሒደት ውስጥም ይገኛሉ ተብሏል፡፡ አንዳንዶቹ በምሥረታ ላይ የነበሩ ባንኮች ደግሞ ‹‹የተጠየቀውን ካፒታል እናሟላለን›› በሚል እንቅስቃሴ ላይ እንደሚገኙ አቶ ፍሬዘር ተናግረዋል፡፡

የምሥረታ ሒደቱን ያቋረጡ ባንኮች ተጨማሪ የቢሮ ኪራይና ሌሎች ወጪዎችን ላለማውጣት እንዲሁም ለምሥረታ ተብሎ የተሰበሰበውን ገንዘብ ተጨማሪ ወጪ ላይ ላለማዋል በሚል ከዚህ ቀደም  ቢሮ ከፍተው ያደርጉ የነበረውን እንቅስቃሴ ማቆማቸው ይነገራል፡፡

ዘምዘምን ጨምሮ፣ አማራ፣ ጎህ፣ ሂጂራ፣ ሲንቄ፣ ሸበሌ፣ አሃዱ፣ ፀደይ፣ ፀሐይ የተባሉት ባንኮች ብሔራዊ ባንክ ዘርፉን እንዲቀላቀሉ ይሁንታ እንደሰጣቸው የሚታወስ ሲሆን፣ ራሚስ፣ ገዳ፣ ሸገር፣ ሆሳዕና፣ ዳሞታ፣ ግዕዝ፣ ዳያስፖራ፣ ዛድ ሌሎች ተጨማሪ ባንኮችና የአነስተኛ የገንዘብ ቁጠባና ብድር ተቋማት የባንክ ፈቃድ ለማግኘት ዋዜማ ከመድረስ አንስቶ፣ አክሲዮን በመመለስ ሒደት ውስጥ ይገኛሉ፡፡

አቶ ፍሬዘር እንዳስታወቁት፣ በምሥረታ ሒደት ውስጥ የነበሩ የባንክ ባለ አክሲዮኖች የተሰበሰበ ገንዘብ ብሔራዊ ባንክ በዝግ አካውንት ያስቀመጠው ሲሆን፣  በገንዘቡ ላይ ብቸኛ የሚያዝበት ወይም ውሳኔ የሚሰጥበት አካል ብሔራዊ ባንክ እንጂ የባንኩ አደራጆቹ አለመሆናቸው ሊታወቅ ይገባል ይላሉ፡፡

ብሔራዊ ባንክ ከግለሰቦች የተሰበሰበውን የገንዘብ መጠን በአደራጆቹ በኩል እንዲጣራ ካዳረገ በኋላ በዛ መሰረት ተመላሽ እንዲሆን የሚደረግ ሲሆን፣ በመሆኑም ካፒታል ያላሟሉ ባንኮች ላይ የሚተገበረው ቀጣዩ ሒደት ይህ ጉዳይ መሆኑ ተገልጿል፡፡

ባንኮቹ የምሥረታ ሒደቱን ማቋረጣቸውን ካሳወቁ በኋላ ለባአክስዮኖቹ ገንዘብ እንዲመለስ የሚያደርገው ወይም የሚቆጣጠረው ብሔራዊ ባንክ እንደሆነ ያስረዱት አቶ ፍሬዘር፣ ይህንን ሒደት ቀደም ብሎ ማድረግ መጀመሩን ገልጸው፣ ተመላሽ ያደረጉ አንዳንድ ባንኮችም መኖራቸውን ተናግረዋል፡፡

በአደራጆች በኩል የሚመጣው መረጃ ተጣርቶ ከመጣ በኋላ ብሔራዊ ባንክ ከባንኮቹ መረጃ እንዲመጣ ያደርጋል እያንዳንዱ ባንክ ከእያንዳንዱ ባለአክሲዮን ምን ያህል ሰበሰበ? የሚለውን ተመልክቶ በዚያ መሠረት ብሔራዊ ባንክ ክፍያ እንዲፈጸም ለባንኮቹ ትዕዛዝ ይሰጣል፡፡

ብሔራዊ ባንክ እንዳስታወቀው፣ የባንክ አደራጆች ለምሥረታ ተብሎ የወጣውን ወጪ ኦዲት ማስደረግ ያለባቸው ሲሆን፣ ውጤቱንም ለባለአክሲዮኖች ይገልጻሉ፣ ትርፍ ገንዘብ ካለም ተመላሽ የሚያደርጉ መሆኑን ተመላክቷል፡፡

የኢትዮጵያ የባንክ ኢንዱስትሪ የቁጠባ አገልግሎት፣ ሐዋላ፣ ኤልሲ መክፈትና የመሳሰሉ አገልግሎቶች ላይ ያተኮረ ከመሆኑ ውጭ የተለየ ነገር የሌለው ነው በማለት ሐሳባቸውን የሚሰጡ በርካታ የዘርፉ ምሁራን፣ በአጭር ጊዜ ባንክ መሥርቶ ኢንዱስትሪ ውስጥ ሲገባ የቆየውም የተለየ አገልግሎት ስለሌለውና በጣም ተመሳሳይ ስለሆነ ነው ሲሉ ይደመጣሉ።

በሌላ በኩል ተፈላጊውን ካፒታል ሳያሟሉ አክስዮናቸውን የመለሱና በመመለስ ላይ ያሉ ባንኮች ሳይቋቋሙ መቅረታቸው የራሱ የሆነ አሉታዊ ተፅዕኖ እንዳለው የሚያነሱ ባለሙያዎች ቁጥራቸው ቀላል የማይባል ሲሆን፣ ለዚህም በማስረጃነት የሚያቀርቡት በምሥረታ ሒደት ውስጥ የተሰበሰበን ገንዘብ አክስዮን ለገዙ ሰዎች መመለሱ ወደ ባንክ ሥርዓቱ የመጣውን ገንዘብ ዳግም እንዲወጣ ምክንያት ሆኗል በማለት ነው፡፡

በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የንግድ ሥራ ኮሌጅ የአካውንቲንግና ፋይናንስ ትምህርት ክፍል ኃላፊ ዳኪቶ ዓለሙ (ዶ/ር) ለሪፖርተር በጉዳዩ ላይ በሰጡት አስተያየት እንዳታወቁት፣ ነባር ባንኮች በብሔራዊ ባንክ የወጣውን ዝቅተኛ መሥፈርት ሙሉ በሙሉ አሟልተው በማይገኙበት ሁኔታ አዳዲስ ባንኮችን ጋብዞ ወደ ዘርፉ ማስገባት በራሱ አስቸጋሪ ነው፡፡

ብሔራዊ ባንክ ጥብቅ የሆነ መመርያ ወይም አቅጣጫ መስጠቱ አስፈላጊነቱን የሚስማሙበት ዳኪቶ (ዶ/ር)፣ 500 ሚሊዮን ብር የተከፈለ ካፒታል አሟልቶ እየተንገዳገዱ ወደ ዘርፉ መምጣት በራሱ ፈተና መሆኑን በማንሳት፣ ይልቁንም እነዚህ ባንኮች የቢዝነስ ሞዴላቸውን ቀይረው መምጣታት እንደሚገባቸው፣ ይህም መንገድ ለእነሱ ብቻ ሳይሆን ለነባሮቹም የግድ የሚል ጉዳይ መሆኑን ይናገራሉ፡፡

በምሥረታ ላይ የሚገኙት ባንኮች እውነተኛ የባንክ ዘርፍ ውስጥ መሰማራት ከፈለጉ የተሻለው መንገድ ከመሰል ምሥረታ ላይ ከሚገኙ ባንኮች ጋር መዋሃድ እንደሆነ ያስረዱት ዳኪቶ (ዶ/ር)፣ ይህም የራሳቸው የሆነ ውስብስብ ተቋማዊ አሠራር ስሌላቸው ነው፡፡ ነገር ግን ነባር ባንኮችን ማዋሃድ ካለው ውስብስብ ተቋማዊ አሠራር አኳያ ከበድ የሚል መሆኑን የትምህርት ክፍል ኃላፊው ያስረዳሉ፡፡

የመንግሥት ተቆጣጣሪ የሆነ ተቋምም በበኩሉ የሚያወጣቸው ፖሊሲዎች በአንድ ጀንበር የሚወጡ ሳይሆን ለረዥም ጊዜ ታስቦበት ሊሠራ የሚገባው መሆኑን የሚነገሩት የዘርፉ ባለሙያዎች፣ ይህም ሊከለኩሉ የሚችሉ ጉዳዮች ካሉ ረዥም ርቀት ሳይጓዙ ማስቀረት ስለሚቻል ነው፡፡ 

ብሔራዊ ባንክ ባለፈው ሳምንት እንዳስታወቀው፣ በተመሳሳይ አነስተኛ የገንዘብ ተቋማት ወደ ባንክ እንዲሸጋገሩ በ2012 ዓ.ም. በብሔራዊ ባንክ ባወጣው መመርያ መሠረት መሥፈርቱን ያሟሉ ሦስት አነስተኛ የብድር ተቋማት ወደ ባንክ መሻገራቸው ተገልጿል፡፡ በተጨማሪም ሁለት አነስተኛ የገንዘብ ተቋማት ደግሞ መሥፈርቱን አሟልተው ፈቃድ ለማግኘት በሒደት ላይ ናቸው፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች