Sunday, April 14, 2024
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

ኤግዚቢሽን ማዕከል በዓውደ ዓመት ባዛሮችን በራሱ ብቻ ሊያዘጋጅ ነው

ተዛማጅ ፅሁፎች

በአዲስ አበባ ኤግዚሽን ማዕከል በበዓላት ዋዜማ የሚዘጋጁ ትልልቅ የንግድ ትርዒቶችና ባዛሮችን በጨረታ በማስተላለፍ ይሠራበት የነበረው አሠራር መቋረጡ ተሰማ፡፡

የኤግዚቢሽን ማዕከልና ገበያ ልማት ድርጅት ይፋ እንዳደረገው ከዚህ በኋላ የአዲስ ዓመት፣ የገናና የፋሲካ በዓላት ባዛሮችን ማዕከሉ በራሱ የሚያካሂድ መሆኑን አስታውቋል፡፡ በተለይ የአዲስ ዓመት፣ የገናና የፋሲካ በዓላትን አስታኮ በአዲስ አበባ ኤግዚቢሽን ማዕከል ለሚዘጋጁ ባዛሮች ኩባንያዎችን በማጫረት ሲያከናውን የቆየ ቢሆንም አሁን ግን ከዚህ አሠራር ውጭ የሚጓዝ መሆኑ ታውቋል፡፡ ቀጣዩንም የ2015 ዓ.ም.  የአዲስ ዓመት ባዛር ማዕከሉ እራሱ የሚያካሂደው እንደሚሆንም የማዕከሉ ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ ጥላሁን ታደሰ አስታውቀዋል፡፡ የማዕከሉን አዲስ አሠራር በተመለከተ በዋና ሥራ አስፈጻሚ በኩል እንደተገለጸው ማዕከሉ በአዋጅ በተሰጠው ሥልጣን መሠረት ባዛሮችን ማዘጋጀት ይችላል፡፡

በነዚህ ሦስት በዓላት ዋዜማ የሚሰናዱ ባዛሮች በርካታ ጎብኝዎች ያሉዋቸው በመሆኑ፣ የበዓላት ባዛር ለማካሄድ የሚወዳደሩ ኩባንያዎች በየዓመቱ የመጫረቻ ዋጋቸውን ከፍ ሲደረጉ ቆይተዋል፡፡ ይህም የአንድ በዓል ዋዜማ ባዛርን ለማዘጋጀት ተጫራቾች ከ70 ሚሊዮን ብር በላይ ዋጋ የሚሰጡበትን አጋጣሚ የፈጠረ ጭምር ነው፡፡ አሁን ግን ማዕከሉ በራሱ ባዛሮችን ማዘጋጀቱ በነዚህ በዓላት ወቅት በቀጥታ ከጨረታ አሸናፊው የሚያገኘውን ያህል ዋጋ ላያገኝ ይችላል የሚል ሥጋት አሳድሯል፡፡  

ማዕከሉ ለዓመታት ሲሠራበት የነበረውን አሠራር ለመቀየር የተወሰነበትን ምክንያት በተመለከተ ባዛሮችና ኤግዚቢሽኖችን ማዘጋጀት ለማዕከሉ በአዋጅ የተሰጠ ሥልጣን በመሆኑ ሌሎችን በማጫረት ባዛሩን እንዲያዘጋጁ ከማድረግ ሌላ ራሱም ማዘጋጀት ስለቻለ አሁን ላይ በራሱ መንገድ ለማዘጋጀት በመወሰኑ መሆኑ ተገልጿል፡፡ በዚህም ውሳኔ መሠረት ቀጣዩን የ2015 ዓ.ም. የአዲስ ዓመት ዋዜማ ባዛር ለአዘጋጅ ኩባንያዎች ጨረታ የማይወጣና ራሱ ዝግጅቱን እንደሚያካሂድ አስታውቋል፡፡ የንግድ ትርዒቶችና ባዛሮችን በማዘጋጀት የሚታወቁ ድርጅቶች የሥራ ዕድልን ከመፍጠር አኳያ በጨረታ ሲሰጥ መቆየቱን የሚጠቁመው የማዕከሉ መረጃ ይህም በባዛሮች ላይ ከፍተኛ የሆነ የዋጋ ጭማሪ እንዲታይና ሕዝቡ እንዲማረር በማድረጉ ማዕከሉ እራሱ ወደ ማዘጋጀት መግባቱንም ይጠቅሳል፡፡

ከገና በዓል ጀምሮ ማዕከሉ ራሱ ባዛሮችን ማዘጋጀት በመጀመሩ ነጋዴዎችና ሁሉም ተባባሪ አካላት ደስተኛ መሆናቸውን፣ ማዕከሉ ያደረገው የመሸጫ ቦታ ኪራይና የመግቢያ ዋጋ ቅናሾች ገበያን ለማረጋጋት የተወሰደ ዕርምጃ እንደሆነም ማዕከሉ አስታውቋል፡፡

ይህ የማዕከሉ ውሳኔ በኤግዚቢሽን ማዕከል የንግድ ትርዒቶችንና ባዛሮችን በማዘጋጀት የሚታወቁ ኩባንያዎች ከዚህ በኋላ በማዕከሉ እነዚህን በዓላት አስታከው የሚያዘጋጁት ዝግጅት ያለመኖሩን የሚጠቁም ነው ተብሏል፡፡

በዚህ ውሳኔ ዙሪያ አስገራሚ የተባለው ጉዳይ ማዕከሉ የሚያዘጋጀው ከአዲስ አበባ ንግና ዘርፍ ጋር በመተባበር ሲሆን፣ በዚህ የባዛር ዝግጅት ግን ንግድ ምክር ቤቱን የተለየ አቋም እንዳለው ለማወቅ ተችሏል፡፡ የንግድ ምክር ቤቱ አንዱ የገቢ ምንጭ የሆነው የኤግዚቢሽን ማዕከል በመሆኑ፣ በየበዓላቱ የሚደረጉ ጨረታዎችን እሱ የሚያወጣው እንደነበር ይታወሳል፡፡

ሆኖም አሁን ማዕከሉ ለብቻው ባዛሩን ለማድረግ ውሳኔ መሳለፉ ንግድ ምክር ቤቱ አካባቢ ግርታ መፍጠሩ ታውቋል፡፡

ጉዳዩን በተመለከተ ያነጋገርናቸው የአዲስ አበባ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት ዋና ጸሐፊ አቶ ሺበሺ፣ ጉዳዩ ላይ ከቦርዱ ጋር እንደሚመክሩበት እንደሚሆን ተናግረዋል፡፡

አሁን ባለቸው መረጃ ግን ለማዕከሉ የተቋቋመው ቦርድ፣ ማዕከሉ በራሱ ባዛሩን ያዘጋጅ የሚል ውሳኔ በማስተላለፉ ጨረታውን በመተው ማዕከሉ ባዛሩን እንዲያዘጋጅ እየተደረገ መሆኑን መረጃ ማግኘታቸውን ጠቅሰዋል፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች