የኢትዮጵያ የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች ምክር ቤትና የኢትዮጵያ የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት፣ በሰላምና በፀጥታ ጉዳዮች ላይ በጋራ ለመሥራት የሚያስችላቸውን ሰነድ ተፈራረሙ፡፡
ሰምምነቱ አገራዊ ችግሮች ላይ ለመወያየትና ዘላቂ መፍትሔ ለማምጣት እንደሚያግዝ፣ ዓርብ ሰኔ 10 ቀን 2014 ዓ.ም. የሁለቱ ምክር ቤቶች አመራሮች በፊርማ ሥርዓቱ ላይ ተናግረዋል፡፡
የኢትዮጵያ የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት ሰብሳቢ ራሔል ባፌ (ዶ/ር)፣ ‹‹ብሔራዊ መግባባት ለማምጣትና የጋራ በሆኑ አገራዊ ጉዳዮች ላይ አብረን ለመሥራት ከስምምነት ደርሰናል፤›› ብለዋል፡፡
በመልካም አስተዳደር፣ በዴሞክራሲ ግንባታና በግጭት አፈታት ላይ ከባለድርሻ አካላት ጋር ለመሥራትና አብሮ ለመምከር ስምምነት ማድረጋቸውን አስረድተዋል፡፡
በኢትዮጵያ የተወሳሰቡ ችግሮችን ለመፍታት የተናጠል ጉዞን በመተው፣ አካታች በሆኑ ሒደቶችን መከተል አስፈላጊ መሆኑን የገለጹት ራሔል (ዶ/ር)፣ በአጭር ጊዜያት ውጤት ማምጣት ይቻላል ብለዋል፡፡
የኢትዮጵያ የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች ምክር ቤት ዋና ዳይሬክተር አቶ ሔኖክ መለሰ በበኩላቸው፣ ከዚህ ቀደም የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶችና የፖለቲካ ፓርቲዎች በአገር ጉዳይ ተቀራርቦ መሥራት እንደ ወንጀል ይታይ ነበር ብለዋል፡፡
የቀድሞ የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች አዋጅ ከፖለቲካ ፓርቲዎች ጋር ለመሥራት አሳሪ መሆኑን፣ አሁንም ሙሉ በሙሉ ባይቀረፍም ተቀራርቦ በመሥራት ችግሮችን መፍታት እንደሚችል ገልጸዋል፡፡
በአሁኑ ጊዜ በጋራ ለመሥራትና አንድ በሚያደርጉ ጉዳዮች ማለትም በአገር ግንባታ፣ በዴሞክራሲ፣ በግጭት አፈታት (መከላከል) ላይ ለመሥራት ከስምምነት ላይ መድረሳቸውን ዋና ዳይሬክተሩ ጠቁመዋል፡፡
በአንድ አገር ሊኖሩ ከሚገቡ ነገሮች አንዱ በጋራ መሥራት መሆኑን ያስረዱት አቶ ሔኖክ፣ በተናጠል ከመሥራት ይልቅ በጋራ መሥራት ዘላቂ መፍትሔ ለማምጣት አስፈላጊ ነው ብለዋል፡፡
በብሔራዊ ምክክር፣ በሰላም ግንባታ፣ በግጭት አፈታት ዘዴና በብሔራዊ አንድነት ላይ ግንዛቤ ማስጨበጥ ምክር ቤቶች በዋናነት በጋራ ለመሥራት የዘረዘሯቸው ጉዳዮች ናቸው፡፡
ስምምነቱ የሰው ሀብትን በዕውቀትና በክህሎት ለማሠልጠን፣ የፋይናንስ አቅማቸውን ለማሳደግ፣ ሕጋዊ ለሆኑ ተቋማት ድጋፍ የማድረግ ትልምን ያነገበ መሆኑን አስረድተዋል፡፡
ምክር ቤቶች በዓመት አራት ጊዜ ሥራቸውንና አፈጻጸማቸውን እንደሚገመግሙ የመግባቢያ ስምምነቱ ሰነድ ያስረዳል፡፡ የኢትዮጵያን ዘርፈ ብዙ ችግሮችን ለመፍታት ተቀራርቦ መሥራት ዋነኛ ዘዴ መሆኑን የገለጹት ዋና ዳይሬክተሩ፣ ‹‹መሠረታዊ ችግሮችን ለመፍታት የሁለቱ ምክር ቤቶች መስማማት መንገዳችንን ይጠርጋል፤›› ብለዋል፡