Sunday, April 21, 2024

ከአሜሪካ የውኃ ደኅንነት ፖሊሲ ጋር ተቀናጅቶ ኢትዮጵያን ዒላማ ያደረገው አዲሱ የግብፅ ውጥን

- Advertisement -spot_img

በብዛት የተነበቡ

የኢትዮጵያ መንግሥት ታላቁ የህዳሴ ግድብን ሦስተኛ ዙር የውኃ ሙሌት በመጪው ሐምሌ ወር ለማከናውን ዝግጅት ላይ መሆኑን ተከትሎ፣ የግብፅ መንግሥት ባለሥልጣናት የተለመደ ተቃውሞ መሰማት ጀምሯል።

በተጠናቀቀው ሳምንት የግብፅ የሚዲያ ባለሙያዎችን አግኝተው ያነጋገሩት የአገሪቱ ፕሬዚዳንት አብዱል ፋታህ አል ሲሲ የኢትዮጵያ መንግሥት የታላቁ ህዳሴ ግድብ የውኃ ሙሌትና አለቃቀቅን በተመለከተ አስገዳጅ ስምምነት እንዲደረስ የቀረበውን የግብፅ ጥያቄ ባለመቀበል ሦስተኛ ዙር የውኃ ሙሌት ለመካሄድ በመሰናዳት ላይ መሆኑን በመጠቆም፣ ግብፅ በአባይ ውኃ ላይ ያላት ድርሻን የሚጎዳ ማንኛውንም ተግባር እንደማይቀበሉ ገልጸዋል። 

የግብፅ መንግሥት በታላቁ ህዳሴ ግድብ ላይ ያለውን ውዝግብ በትዕግሥትና በዲፕሎማሲ ለመፍታት በያዘው አቋም እንደሚቀጥልም ፕሬዚዳንቱ በአጽንኦት ተናግረዋል።

ከሳምንት በፊት የታንዛኒያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር የሆኑትን ሊበርታ ሙላሙላ በካይሮ አግኝተው ያነጋገሩት የግብፅ ፕሬዚዳንት አል ሲሲ፣ መንግሥታቸው ግብፅ በዓባይ ውኃ ላይ ያላትን ታሪካዊ የውኃ ድርሻና የመጠቀም መብት ከማስከበር ወደ ኋላ እንደማትል ተናግረዋል።

ግብፅና ሱዳን በታላቁ ህዳሴ ግድብና በዓባይ ውኃ አጠቃቀም ዙሪያ የሚያነሱትን ጥያቄ በመወገን ተደጋጋሚ መግለጫዎችን በማውጣት የሚታወቀው የዓረብ ሊግም፣ ሦስተኛው ዙር የህዳሴ ግድብን ውኃ ሙሌት አስመልክቶ ተመሳሳይ መግለጫውን በተጠናቀቀው ሳምንት አውጥቷል። 

የዓረብ ሊግ ዋና ጸሐፊ የሆኑት አቡል ጊይት በሰጡት መግለጫ ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ በተለይም የተባበሩት መንግሥታት የፀጥታው ምክር ቤት፣ ታላቁ የህዳሴ ግድብን አስመልክቶ ለሚያነሱት ሥጋት መፍትሔ ባለመስጠቱ፣ በሁለቱ አገሮች ላይ ለሚደርስ ማንኛውም ጉዳት ተጠያቂ ነው ሲሉ ከሰዋል። 

ላለፉት በርካታ ዓመታት ሲካሄድ የነበረውን የታላቁ ህዳሴ ግድብ ድርድር በቅርበት የተከታተሉ አንድ የኢትዮጵያ መንግሥት ባለሥልጣን፣ ታላቁ የህዳሴ ግድብ ግንባታ እስካልቆመ ድረስ የውኃ ሙሌቱን አለማከናወን እንደማይቻልና ይህንንም የግብፅና የሱዳን ባለሥጣናት ጠንቅቀው እንደሚያውቁት ለሪፖርተር ገልጸዋል። 

ነገር ግን በህዳሴ ግድቡ ላይ ያለው አለመግባባት መፍትሔ ባላገኘበት ሁኔታ ውስጥ፣ የውኃ ሙሌት ሊከናወን ዝግጅት እየተደረገ መሆኑን እያወቁ ዝም ማለት አይችሉም የሚሉት ኃላፊው፣ እንዲያውም መነጋገሪያ ሊሆን የሚችለው ዝም ቢሉ ነው ሲሉ ያስረዳሉ። 

የውኃ ሙሌት እየተካሄደ ዝም ቢሉ በህዳሴ ግድቡ ላይ ያላቸው ሥጋት እንደተፈታ ዓለም ግንዛቤ ሊወስድ ይችላል፣ ከማኅበረሰቦቻቸውም ተቃውሞ ይገጥማቸዋል የሚሉት ኃላፊው፣ ተቃውሞ ማሰማት መጀመራቸው የሚጠበቅ እንደሆነ ነገር ግን ይህ የኢትዮጵያን ዕቅድ እንዳለፉት ሁለት የግድቡ የውኃ ሙሌት ተግባራት እንደማያስተጓጉል ተናግረዋል። 

የዓረብ ሊግ በታላቁ ህዳሴ ግድብ ላይ የሚያወጣው መግለጫ በሙሉ በግብፅ ተረቆ የሚሰጥ መሆኑ፣ በኢትዮጵያ መንግሥት በኩል በግልጽ የሚታወቅና በቅርቡ የወጣው መግለጫም በዚሁ መንገድ የተቀናበረ እንደሆነ ገልጸዋል። 

ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ከፍተኛ ጫና የገጠመው እ.ኤ.አ. በ2021 መሆኑን የጠቆሙት ኃላፊው፣ የኢትዮጵያ መንግሥትና ሕዝብ የተቀናጀ ዲፕሎማሲያዊ ዘመቻ አድርገው ያንን ፈታኝ ወቅት በአሸናፊነት እንዳለፉት አስታውሰዋል። 

‹‹ተመሳሳይ የፈተና ጊዜ ከዚህ በኋላ አይመጣም ማለት አይደለም፣ ነገር ግን በህዳሴ ግድቡ ላይ ሊመጣ የሚችልን ጫና እንዴት መወጣት እንደምንችል ያስተማረ በመሆኑ፣ አሁንም በንቃትና በልዩ ትኩረት ተዘጋጅቶ በመንቀሳሰቀስ መመከት ይችላል፤›› ሲሉ እምነታቸውን ገልጸዋል።

ባለፈው ወር የውጭ ጉዳይ ሚኒስትርን የዘጠኝ ወራት የሥራ አፈጻፈም ሪፖርት ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የሰላምና የውጭ ግንኙነት ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ  ያቀረቡት ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ አቶ ደመቀ መኰንን ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብን በተመለከተ የተሠሩ የዲፕሎማሲ ተግባራትንና ቀጣይ የዲፕሎማሲ አቅጣጫዎችን እንዲያብራሩ በኮሚቴው ተጠይቀው በሰጡት ምላሽ፣ ታላቁ የህዳሴ ግድብ ‹‹ገብቶበት ከነበረበት ቅርቃር›› ውስጥ ለማስውጣት ከፍተኛ ጥረት ተደርጎ ማሳካት እንደተቻለ አመላክተዋል። 

‹‹በአንድ ወቅት በአደገኛ ሁኔታ ቅርቃር ውስጥ ገብቶ የነበረውን የህዳሴ ግድብ ፖለቲካ በከፍተኛ ዲፕሎማሲያዊ ጥረት ወደ አፍሪካ ኅብረት እንዲመለስ ማድረግ ተችሏል፤›› ብለዋል። 

ታላቁ የህዳሴ ግድብ ጉዳይ የዓለም አቀፍ ፖለቲካ አካል ሆኖ እንደነበርና በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት (ተመድ) የፀጥታ ምክር ቤት ውስጥ ጭምር የመወያያ አጀንዳ ሆኖ እንደነበር ያነሱት አቶ ደመቀ፣ በተደረገው ከፍተኛ ዲፕሎማሲያዊ ተጋድሎ ከገባበት ቅርቃር በማውጣት በአፍሪካ ኅብረት ሥር እንዲታይ መደረጉን ጠቅሰዋል። ይህም በዲፕሎማሲው ዘርፍ የተገኘና መላው ኢትዮጵያ በተለይም የኢትዮጵያ ዲያስፖራ አባላት አስደናቂ ተሳትፎ የተገኘ ትልቅ ስኬት መሆኑን ገልጸዋል። 

አሁንም የተገኘውን ስኬት ጠብቆ ማቆየትና የታላቁ ህዳሴ ግድብ ጉዳይ በሦስቱ አገሮች ተሳትፎ በአፍሪካ ኅብረት የአደራዳሪነት ሚና እንዲቀጥል ማድረግ የኢትዮጵያ መንግሥት አቋም መሆኑን ጠቅሰው፣ አስተዋጽኦ ማድረግ የሚፈልጉ አካላት በዚሁ ማዕቀፍ ውስጥ ድርሻቸውን መወጣት እንደሚችሉ ገልጸዋል። 

ወደፊት የታላቁ ህዳሴ ግድብ ጉዳይ በአፍሪካ ኅብረት አደራዳሪነት እንዲቀጥል ሲደረግም መሠረታዊው የድርድር ማዕቀፍ መሆን ያለበት በሦስቱ አገሮች እ.ኤ.አ. በ2015 የተፈረመው የትብብር ማዕቀፍ እንደሚሆን ተናግረዋል።

ላለፉት ዓመታት ሲካሄድ በነበረው ድርድር ላይ በመሳተፍ ጭምር የታላቁ ህዳሴ ግድብ የውዝግብ ፖለቲካን በቅርበት የሚያውቁት ከፍተኛ ባለሥልጣን፣ በህዳሴ ግድቡ የቴክኒክ ጉዳይ ላይ ከግብፅም ሆነ ከሱዳን መንግሥት ባለሥልጣናት ጋር ለመግባባት አዳጋች እንዳልሆነ ይገልጻሉ። 

ሁለቱ አገሮች የሚፈልጉት ግድቡን በተመለከቱ ቴክኒካዊ ጉዳዮች ላይ መፍትሔ ማግኝት ቢሆን ኖሮ፣ በቀላሉ መፍታት ይቻል እንደነበር የሚጠቅሱት ኃላፊው፣ የግብፅ መንግሥት ፍላጎት ፖለቲካዊና የኢትዮጵያን በዓባይ ውኃ የመጠቀም አሁናዊ መብት እንዲሁም የቀጣይ የኢትዮጵያ ትውልድን የመጠቀም መብት ማሳጣት በመሆኑ የህዳሴ ግድቡ ጉዳይ ለግብፅ ፖለቲካዊ መሆኑን ያስረዳሉ። 

ግብፅ ይህንን ጉዳይ ወደ ተባበሩት መንግሥታት የፀጥታ ምክር ቤት የወሰደችውም በዚሁ ምክንያት እንደሆነ በመጥቀስ አሁንም ቢሆን በአፍሪካ ኅብረት የአደራዳሪነት ሚና መፍትሔ ለማግኘት እንደማትሻ ገልጸዋል። 

ግብፅ የታላቁ ህዳሴ ግድብን ጉዳይ መልሳ ወደ ዓለም አቀፍ የፖለቲካ መድረክ መውሰዷ እንደማይቀርና ይህንንም የሚያመላክቱ ፍንጮች በግልጽ እየታዩ እንደሆነ አስረድተዋል። በተለይም በመጪው ኅዳር 2015 በግብፅ የሚካሄደውን ዓለም አቀፍ የአየር ንብረት ለውጥ ጉባዔ በመጠቀም ታላቁ የህዳሴ ግድብን ጨምሮ በዓባይ ውኃ ላይ ያላትን ፍላጎት ከአየር ንብረት ለውጥ ጋር የተያያዘ የደኅንነት ሥጋት አድርጋ ለማቅረብ ሰፊ ዝግጅቶችን እያደረገች እንደሆነ ገልጸዋል። 

ለዚህ ውጥኗም የአሜሪካና የአውሮፓ አገሮች እያሠለፈች መሆኑን የገለጹት እኚሁ ባለሙያ፣ በተለይም የአሜሪካ መንግሥት እ.ኤ.አ. ጁን 1 ቀን 2022 ካፀደቀው ዓለም አቀፍ የውኃ ደኅንነት ፖሊሲ ጋር በማቀናጀት፣ የህዳሴ ግድቡን ጉዳይ ዳግም ወደ ዓለም አቀፍ መድረክ ለመውሰድ ሰፊ እንቅስቃሴ ላይ መሆኗን ጠቁመዋል። 

የኢትዮጵያ መንግሥት ይህንኑ የግብፅ ጥረት የተገነዘበው መሆኑንና ተገቢውን ምላሽ ለመስጠትም ዝግጅት እያደረገ መሆኑን፣ ነገር ግን እንደ ቀደመው ጊዜ ከመንግሥት ውጪ በአገር ውስጥም ሆነ በውጭ አገሮች ያሉ የኢትዮጵያ ባለሙያዎችን ማንቀሳቀስ እንደሚገባ ገልጸዋል።

የአሜሪካ የውኃ ደኅንነት ፖሊሲ ድርጊት መርሐ ግብር 

የአሜሪካ ምክትል ፕሬዚዳንት ካሜላ ሐሪስ ከሁለት ሳምንት በፊት ይፋ ያደረጉት የአሜሪካ የውኃ ደኅንነት ፖሊሲ/የድርጊት መርሐ፣ ግብር የአሜሪካ መንግሥት የውኃ ደኅንነት ጉዳይ የአገሪቱ የውጭ ግንኙነት ፖሊሲ አካል እንዲሆንና በዓለም አቀፍ ደረጃ ግጭትን ለመከላከልና ፍትሐዊ የኢኮኖሚ ዕድገትን ለማስፈን ቅድሚያ ተሰጥቶት የሚተገበር እንደሆነ ያመለክታል። 

በዓለም ዙሪያ ከሁለት ቢሊዮን በላይ የሚሆኑ ሕዝቦች የውኃ ደኅንነት ጉዳይ በሚያስጨንቃቸው አገሮች እንደሚኖሩ በመጥቀስ፣ ይህ ሁኔታ በዓለም ዙሪያ ባሉ የአሜሪካ ጥቅሞች ላይ ከፍተኛ ተፅዕኖ እንደሚያስከትል ያመለክታል። 

ከፍተኛ የውኃ እጥረት የተረጋጋ ዓለም አቀፍ ሁኔታ እንዳይኖር በማድረግና ብዙዎችን ለስደት በመዳረግ ግጭቶችን የመፍጠር ከፍተኛ አቅም እንዳለው ይጠቁማል። ይህንን ሁኔታ በገንዘብም የአሜሪካ መንግሥት White House Action Plan on Global Water Security የተሰኘ በአገሪቱ የውጭ ግንኙነት ፖሊሲ ውስጥ ቅድሚያ ተሰጥቶት የሚተገበር የድርጊት መርሐ ግብር መፅደቁን ምክትል ፕሬዝዳንቷ ሐሪስ እ.ኤ.አ. ጁን 1 ቀን 2022 ይፋ አድርገዋል። ይህ ፖሊሲ በአሜሪካ የውጭ ግንኙነት ፖሊሲ ውስጥ ቅድሚያ ተሰጥቶት እንዲተገበር መወሰኑን ለተግባራዊነቱም ከአሜሪካ መንግሥት የውጭ ጉዳይ ፖሊሲ ጋር የሚሰሩ ዓለም አቀፍ አጋሮች መለየታቸውን አመልክተዋል።

ለትግበራውም ሦስት ዓለም አቀፍ አጋሮች የተለዩ ሲሆን፣ እነዚህም የቡድን ሰባት አገሮች (G7)፣ የቡድን 20 አገሮች (G 20) እና የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት (ተመድ) መሆናቸውን ይፋ የተደረገው የድርጊት መርሐ ግብር ያመለክታል። 

የድርጊት መርሐ ግብር ሰነዱ ላይ ‹‹የችግሩ መግለጫ›› ተብለው ከተዘረዘሩት ነጥቦች መካከል መሠረታዊ የሚባሉት 

ውጤታማነት በጎደለው የውኃ ሀብት አስተዳደር ምክንያት የውኃ ዕጦት በብዙ የዓለም ክልሎች መከሰቱንና በዚህም በአገሮቹ ከውኃ እጥረት ጋር የተያያዘ ውጥረት እንደሚታይ ይገልጻል። ከውኃ እጥረት ጋር በተያያዘ በተለያዩ የዓለም ክፍሎች ለተፈጠረው ውጥረት ከጠቀሳቸው ተጨማሪ ወይም ገፊ ምክንያቶች መካከል አንዱ ቁልፍ ወንዞችን ወይም የውኃ መሠረተ ልማቶች የሚገኙባቸው አገሮች እነዚህን ሀብቶች የአገር ውስጥ ፍላጎታቸውን ለማሟላት ወይም በታችኛው ተፋሰስ አገሮች ላይ ጫና ለመፍጠር በብቸኝነት ሊቆጣጠሯቸው ይችላሉ የሚለው ሥጋት ሌሎቹን አገሮች ውጥረት ውስጥ እንደከተተ ይገልጻል።

ከሰነዱ ጋር የተያያዘው አባሪ ችግሩ ይታይባተዋል የሚላቸውን የዓለም ክፍሎች በጥቅሉ ለይቶ ያስቀመጠ ሲሆን፣ ከነዚህ መካከልም መካከለኛው ምሥራቅና ሰሜን አፍሪካ ቀጣና በዓለም ላይ ከፍተኛ የውኃ እጥረት ጭንቀት ያለበት እንደሆነ ይገልጻል። በዚህ ቀጣና በሚገኙ አገሮች ላይ ያለው የውኃ እጥረት ላይ የሕዝብ ቁጥር መጨመር፣ የኢኮኖሚ ዕድገትና ዘላቂነት የሌለው የውኃ አስተዳደር ሲታከልበት በሚቀጥሉት አሥር ዓመታት ውስጥ የነፍስ ወከፍ የውኃ አቅርቦት በአሳሳቢ ደረጃ እንደሚቀንስ ይተነብያል። በተጨማሪም በዚሁ ቀጣና ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የአየር ንብረት ለውጥ የፈጠረው እክል  እንዲሁም ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው ግድቦች መገንባት የውኃ ዕጦትን እንዳባባሰው ይገልጻል። በዚህም የተነሳ ቀጣናው በዓለም ላይ ከፍተኛውን የጨው ማስወገጃ መሠረተ ልማቶች የሚገነቡበት እንዳደረገው፣ የጨው ማስወገጃ መሠረተ ልማቶቹ የአካባቢን የውኃ ጭንቀት ለመቀነስ የሚረዱ ቢሆንም፣ ሙሉ በሙሉ ችግሩን ሊፈታ እንደማይችል፣ ይልቁንም የጨው ማስወገጃ መሠረተ ልማቶችን በዓለም አቀፍ የውኃ አካላት ላይ ለመገንባት ፉክክርን በመፍጠር አገሮቹን ወደ ግጭት ሊስብ እንደሚችል ያትታል።

የድርጊት መርሐ ግብር ሰነዱ አባሪ ሆኖ በቀረበው ማብራሪያ በውኃ እጥረት ምክንያት የደኅንነት ውጥረት ይታይባቸዋል ተብለው ከተጠቀሱት ቀጣናዎች መካከል የሰሃራ በታች የአፍሪካ ቀጣና ተጠቅሷል።

ከሰሃራ በታች ባሉ የአፍሪካ አገሮችም በተመሳሳይ ከውኃ እጥረት ጋር የተያያዘ ውጥረት እንደሚስተዋል የሚጠቅሰው ይኸው ሰነድ በዚህ አካባቢ ላለው የውኃ እጥረት መሠረታዊ ምክንያት የውኃ መሠረተ ልማት አለመኖር፣ መሠረተ ልማቶችን ለመገንባት የፋይናንስ ችግርና ሙስና መሆናቸውን ያትታል። 

ይህ የአሜሪካ መንግሥት የውኃ ደኅንነት ድርጊት መርሐ ግብር የውኃ ጉዳይን ከአየር ንብረት ለውጥና ከፀጥታና ደኅንነት ጋር ያቆራኘ ሲሆን፣ ግብፅ በመጪው ኅዳር 2015 ዓ.ም. በምታዘጋጀው 27ኛው የዓለም የአየር ንብረት ለውጥ ጉባዔ ላይም ትኩረት የሚሰጠው አጀንዳ እንደሚሆን መረጃዎች ያመለክታሉ። 

የግብፅ መንግሥትም ይህንን ልዩ አጋጣሚ ለህዳሴ ግድቡ ፖለቲካ ለማዋል ሰፊ የሚባል እንቅስቃሴ ውሰጥ ይገኛል። ለዚሁ ጉባዔ ዝግጅት ይረዳ ዘንድ እየተካሄዱ ከሚገኙ ቅድመ ስብሰባዎች መካከል አንዱ ከሁለት ሳምንት በፊት በአዲስ አበባ በአፍሪካ ኅብረት አዳራሽ ተከናውኗል። የዚህ ስብሰባ ዋነኛ ዓላማ በህዳሩ ጉባዔ የአፍሪካ አገሮችን የሚወክል ወጥ አቋም ለመያዝ የታለመ ሲሆን፣ የስብሰባው የውይይት ርዕስም Climate, Peace and Security: Africa Common Position የተሰኘ ነበር። 

የግብፅ የአካባቢ ጥበቃ ሚኒስትር ያስሚን ፉአድ ከሦስት ሳምንት በፊት በካይሮ ከጣሊያን አምባሳደር ሚሼል ኳሮኒ ጋር ባደረጉት ውይይት፣ ግብፅ በኅዳሩ 27ኛው ዓለም አቀፍ የአየር ንብረት ለውጥ ጉባዔ (COP27) ወቅት የውኃ ጉዳይን አዲስ አጀንዳ አድርጋ እንደምታነሳ ተናግረዋል። 

እኝሁ የግብፅ የመስኖ ሚኒስትር ለአገሪቱ የቴሌቪዥን ጣቢያ ተመሳሳይ መግለጫ ከሳምንታት በፊት የሰጡ ሲሆን፣ ግብፅ በምታስተናግደው የኅዳሩ 27ኛው የአየር ንብረት ለውጥ ጉባዔው [COP27] መድረክ ላይ የአፍሪካ ጉዳዮች ቅድሚያ የምትሰጣቸው ጉዳዮች እንደሚሆኑና ለመጀመርያ ጊዜም በዚህ ጉባዔ የውኃ ጉዳይ ልዩ ትኩረት እንደሚኖረው ተናግረዋል። በዚህ ጉባዔ ላይም ግብፅ የውኃ እጥረት፣ የድርቅና የጎርፍ ወቅቶች እንዲሁም የዝናብ ቦታና መጠን መቀያየር ከዓለም ሰላምና ደኅንነት አንፃር ትኩረት እንዲያገኝ እንደምትሠራ ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ መንግሥት ስለ ጉዳዩ ምን አስቧል?

የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ፖሊሲ ውስጥ ልዩ ትኩረት እንዲያገኝ ተደርጎ የተቀረፀው አዲሱ የውኃ ደኅንነት ድርጊት መርሐ ግብር፣ የግብፅን ጥቅም ከማስከበር ጋር የተቆረኛ አንድምታ እንደሚኖረው፣ ግልጽ ግንዛቤ በኢትዮጵያ መንግሥት በኩል መያዙን ሪፖርተር ከተመለከተው አንድ የመንግሥት የውስጥ ሰነድ መረዳት ችሏል።

የአሜሪካ የውጭ ግንኙነት ፖሊሲ ውስጥ እንደ አዲስ የተካተተው የውኃ ደኅንነት የድርጊት መርሐ ግብር፣ ግብፅ የህዳሴ ግድብና የዓባይ ውኃን በተመለከተ ለረዥም ጊዜ ስታራምደው ከነበረው ጉዳዩን ዓለም አቀፋዊ የፖለቲካ አጀንዳ (Internationalization) እና የብሔራዊ ደኅንነት ጉዳይ (Security) የማድረግ ፖሊሲ ጋር የሚዛመድ እንደሆነ ሰነዱ ያመለክታል። 

‹‹በመሆኑም ተመድን ጨምሮ በተለያዩ ዓለም አቀፍ መድረኮች በኢትዮጵያ ላይ ጫናዎች ሊበረቱ እንደሚችሉ ግምት በመውሰድ ጥንቃቄ የተሞላበት ዝግጅት መደረግ አለበት፤›› ሲል ይመክራል።

ይህ የአሜሪካ ፖሊሲ በመካከለኛው ምሥራቅ ሰላም ለማምጣት ከነደፈችው የአብራሃም አኮርድ (ስምምነት) እና የክፍለ ዘመኑ ስምምነት (Deal of the Century) ከተባለው በፕሬዚዳንት ዶናልድ ዘመን ከተፈረመው የመካከለኛው ምሥራቅ የሰላም ስምምነት ጋር በቀጥታ ግንኙነት ሊኖረው እንደሚችል ይኸው የመንግሥት ሰነድ ይጠቁማል። 

በዚህም ምክንያት አሜሪካ የመካከለኛው ምሥራቅ ፍላጎቷን ለመፈጸም ስትል ከታላቁ ከህዳሴ ግድብ ጋር በተገናኘ በግልጽ ከኢትዮጵያ አቋም በተቃራኒ የመቆሟ አዝማሚያ ሰፊ በመሆኑ፣ በኢትዮጵያ መንግሥት በኩል ይህንን ታሳቢ ያደረገ ጥቅል ውይይት፣ ጥናትና ዝግጅት እንዲደረግ ይመክራል። 

ሪፖርተር ያነጋገራቸው ባለሥልጣን እንደሚሉት ከሆነ ደግሞ አሜሪካ በቅርቡ የአፍሪካ ቀንድ መልዕክተኛ አድርጋ የሰየመቻቸው የቀድሞ የዴሞክራቲክ ኮንጎ አምባሳደር፣ የህዳሴ ግድቡን በተመለከተ በተለያዩ መድረኮች የግብፅን ፍላጎት የሚያንፀባርቅ አቋም ሲያራምዱ እንደነበረ በመጥቀስ፣ አዲሱ ኃላፊነታቸውም ለሰሜኑ ግጭት መፍትሔ ከመፈለግ ይልቅ ለዚህ የህዳሴ ግድብ ጉዳይ ሊሆን እንደሚችል ገልጸዋል።

አሜሪካ በህዳሴ ግድቡ ውዝግብ በግብፅ ወገን መቋሟ በኢትዮጵያ ላይ የሚያስከትለው ጫና ከፍተኛ እንደሚሆን የጠቆሙት ኃላፊው፣ በተለይም ከሰሜኑ ጦርነት ጋር ተያይዞ አሜሪካ ምዕራባውያኑን በማስተባበር በኢትዮጵያ ላይ የፈጠረችው የኢኮኖሚ ጫና ተጠናክሮ ሊቀጥል እንደሚችል ጠቁመዋል። 

በመሆኑም ይህንን ያገናዘበ መፍትሔ ማበጀት በመንግሥት በኩል እንደሚጠበቅ የገለጹት ኃላፊው፣ ጫናውን ለማርገብ ሊወሰዱ ከሚችሉት ጉዳዮች አንዱ በራሳቸው በምዕራባውያኑ አሜሪካንን ጨምሮ እንዲሁም በተመድ ጭምር ዕውቅና የተሰጠውን የሴኔጋል ወንዝ ተሞክሮ በመፍትሔነት በማቀበል፣ ከራሳቸው አቋም ጋር እንዲጋጩ ወይም እንዲመርጡ ማድረግ እንደሚቻል ጠቁመዋል። 

spot_img
- Advertisement -

ትኩስ ጽሑፎች

ተዛማጅ ጽሑፎች

- Advertisement -
- Advertisement -