Sunday, October 1, 2023
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

በኢንዱስትሪ ዘርፍ ለ158 ሺሕ ዜጎች የሥራ ዕድል መፈጠሩ ተነገረ

ተዛማጅ ፅሁፎች

በሰሜኑ ጦርነት ጉዳት ከደረሰባቸው 109 ኢንዱስትሪዎች 22 ያህሉ ሥራ አልጀመሩም

በ2014 በጀት ዓመት በመላ አገሪቱ በሚገኙ ኢንዱስትሪዎች ከ215 ሺሕ በላይ የሥራ ዕድል ለመፍጠር ታቅዶ፣ 158 ሺሕ ለሚሆኑ ዜጎች ብቻ መፍጠር መቻሉን የኢንዱስትሪ ሚኒስቴር አስታወቀ፡፡

የኢንዱስትሪ ዘርፍ ከሥራ ዕድል ፈጠራ አንፃር ሊኖረው የሚችለው ሚና ከፍተኛ ቢሆንም፣ አምራች ኢንዱስትሪዎች በሚጠበቅባቸው ልክ እየተንቀሳቀሱ አለመሆኑና በተፈለገው ልክ የሥራ ዕድል እየተፈጠረ እንዳልሆነ፣ የኢንዱስትሪ ሚኒስትሩ አቶ መላኩ አለበል ሰኔ 9 ቀን 2014 ዓ.ም. የተቋማቸውን የአሥር ወራት የዕቅድ አፈጻጸም ለፓርላማ ሲያቀርቡ አስረድተዋል፡፡

በመሆኑም አምራች ኢንዱስትሪዎች እየተደገፉ በሁሉም አካባቢዎች በማስፋፋት በቂ የሥራ ዕድል ካልተፈጠረ ግጭት፣ ስደትና የኑሮ ውድነት ሊቆም እንደማይቻል አክለው ገልጸዋል፡፡

ሚኒስትሩ የፓርላማ አባላቱን፣ ‹‹የምርጫ ዘመናቸሁ እንደ አንድ ስኬት ተደርጎ እንዲወሰድላችሁ፣ ኢትዮጵያ  የአምራች ኢንዱስትሪዎችን በመደገፍ ሰፊ የሥራ ዕድል ሊፈጠርባት የምትችል አገር መገንባት ችለናል ብላቸህ ለልጆቻችሁ ታሪክ የምትነግሩበት ሁኔታ መኖር መቻል አለበት፤›› ብለዋቸዋል፡፡ ይሁን እንጂ፣ ‹‹ይህንን ካላደረግን ሌላ የድህነት አዙሪት ውስጥ ነው የምንቀጥለው፤›› በማለት ገልጸዋል፡፡

በአሁኑ ጊዜ በርካታ የኢንቨስትመንት ፍላጎቶች ቢኖሩም የሰላሙ ሁኔታ አስተማማኝ ካልሆነ፣ በተገነቡና ግንባታ ላይ ባሉ የማምረቻ አካባቢዎች ገብቶ ለማልማት፣ የሚጠበቀውን ልማትና የሥራ ዕድል መፍጠር እንደማይቻል አቶ መላኩ ተናግረዋል፡፡

ለአብነት እንኳ በቡልቡላ፣ በይርጋለምና በቡሬ የተቀናጁ አግሮ ኢንዱስትሪ ፓርኮች እስካሁን ጥቅም ላይ ያልዋለ 600 ሔክታር መሬት፣ እንዲሁም ከአግሮ ኢንዱስትሪ ፓርኮች ውጩ ባሉ ኢንዱስትሪ ፓርኮች ውስጥ 562 ሔክታር መሬት መሠረተ ልማት ተሟልቶላቸው ባለሀብቶች ያልገቡባቸውና 28 ነፃ ሼዶች ባለሀብቶች እየጠበቁ መሆናቸውን አስረድተዋል፡፡

በተለያዩ የአገሪቱ አካባቢዎች ኢንዱስትሪ ፓርክ ያስፈልጋል ተብሎ ፓርኮቹ ተገንብተው፣ አንድም ባለሀብት ያልገባባቸው በመኖራቸው መንግሥት ፓርኮቹን ለሌላ ዓላማ ለማዋል ጥናት እያደረገ መሆኑን አቶ መላኩ አብራርተዋል፡፡

በሌላ በኩል በኢትዮጵያ ካለው የካፒታል ዕጥረት የተነሳ በሁሉም አካባቢዎች በሚፈለገው ልክ ኢንዱስትሪ ማስፋፋት አለመቻሉን ያብራሩት አቶ መላኩ፣ አንድ አግሮ ኢንዱስትሪ ፓርክ ለመገንባት እስከ አሥር ቢሊዮን ብር እየጠየቀ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡

ለአብነት ያህል ኢንዱስትሪዎችን ለመገንባት ዕቅድ ተይዞ ጥናት ከተደረገባቸው 17 አግሮ ኢንዱስትሪ ፕሮጀክቶች መካከል፣ በበጀት እጥረት ምክንያት ተገንብተው ወደ ሥራ መግባት የቻሉት አራት ብቻ መሆናቸው ተገልጿል፡

በሌላ ዜና በሰሜን ኢትዮጵያ የፌዴራል መንግሥት ከሕወሓት ታጣቂዎች ጋር ባካሄደው ጦርነት ከወደሙ 190 አነስተኛ፣ መካከለኛና ከፍተኛ ኢንዱስትሪዎች መካከል 65 የሚሆኑት በሙሉ አቅማቸው እያመረቱ መሆናቸውን፣ 103 በከፊል ማምረት መጀመራቸውን፣ ቀሪዎቹ 22 ደግሞ ከፍተኛ ጉዳት የደረሰባቸው በመሆናቸው ወደ ሥራ ለመመለስ አልተቻለም ተብሏል፡፡

በከፊል ወደ ሥራ መግባት የቻሉትም ተጨማሪ የቴክኒክ፣ የፋይናንስና የውጭ ምንዛሪ ድጋፍ ካላገኙ በስተቀር እያመረቱ መቀጠል ስለማይችሉ፣ ተጨማሪ ክትትል እንደሚያስፈልጋቸው ሚኒስትሩ ተናግረዋል፡፡

በተገባደደው በጀት ዓመት ጫማና አልባሳትን በአገር ውስጥ ኢንዱስትሪዎች በማምረት ከውጭ የሚገቡ ምርቶችን ለማሰቀረት ታቅዶ 860 ሺሕ ጥንድ ጫማ ለተማሪዎች፣ እንዲሁም 1.5 ሚሊዮን ጥንድ ጫማ ለፀጥታ መዋቅሩ መሠራጨቱን ሚኒስትሩ ገልጸዋል፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች