Friday, September 22, 2023
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

የቻይና መንግሥት ለቃሊቲ መንገድ ሥራ የፈቀደው ብድር ካልተለቀቀ በመንግሥት ወጪ ይጠናቀቃል ተባለ

ተዛማጅ ፅሁፎች

የቻይና ኤግዚም ባንክ ከአምስት ዓመት በፊት ከ4.7 ቢሊዮን ብር በላይ ለተጀመሩት ሁለት የቃሊቲ መንገድ ፕሮጀክቶች የተፈቀደው ብድር እስከ ሚቀጥለው ዓመት ካልለቀቀ መንግሥት ግንባታውን በራሱ ወጪ እንደሚያጠናቅቅ ተገለጸ፡፡

ሁለቱ መንገዶች ከ50 በመቶ በላይ የሆነ ሥራቸው ቢሠራም፣ በኮንስትራክሽ ግብዓቶች ዋጋ መጨመርና ፕሮጀክቱ በመጓተቱ ከተቋራጩ የሚነሳ የዋጋ ክለሳ ቀሪ ሥራዎችን ለማጠናቀቅ የሚጠይቀውን ገንዘብ ከፍ እንደሚያደርገው የአዲስ አበባ መንገዶች ባለሥልጣን አስታውቋል፡፡

በአንድ ኪሎ ሜትር ከ235 ሚሊዮን ብር በላይ በሆነ ዋጋ በ2009 ዓ.ም. የተጀመሩት ሁለቱ የመንገድ ፕሮጀክቶች የቃሊቲ፣ ቱሉ ዲምቱ አደባባይና የቃሊቲ -ቡልቡላ-ቂሊንጦ መንገዶችን የሚያካትቱ ናቸው፡፡ ድምር ርዝመታቸው 21 ኪሎ ሜትር በላይ የሆኑት የሁለቱ መንገዶች ሥራቸው የተጀመረው ከቻይና ኤግዚም ባንክ በተገኘ ብድርና በከተማ አስተዳደሩ በጀት ነው፡፡

የአዲስ አበባ መንገዶች ባለሥልጣን ምክትል ዋና ዳይሬክተር አቶ እያሱ ሰለሞን ለሪፖርተር እንደገለጹ፣ የመንገዶቹ ሥራዎች አፈጻጸማቸው ከ50 በመቶ በላይ ከደረሰ በኋላ፣ የቻይና ኤግዚም ባንክ ብድር መልቀቅ በማቆሙ ሳቢያ ሥራው ከሁለት ዓመት በላይ በሆነ ጊዜ ተጓቷል፡፡ ብድሩ መለቀቅ ካቆመበት ጊዜ አንስቶ ከባንኩ ጋር የተደረጉ ንግግሮች እስካሁን ፍሬ አላፈሩም፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) በሳምንቱ መጀመርያ ማክሰኞ ሰኔ 7 ቀን 2014 ዓ.ም. በፓርላማ ተገኝተው ማብራሪያ በሰጡበት ጊዜ የእነዚህ መንገዶች ጉዳይ አንስተዋል፡፡ ‹‹ቃል የገባው አካል በራሱ ምክንያት ብድር ሊያፋጥን አልቻለም፤›› ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ መንገዱ ተጀምሮ በመቆሙ ሳቢያ የአከባቢ ነዋሪ መማረሩን ተናግረዋል፡፡

አክለውም ‹‹በሚቀጥለው ዓመት ኤክዚም ባንክ ባይፈቅድም በራሳችን በጀት እንጀምራለን፤›› ብለዋል፡፡

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በራሱ በጀት መሸፈን የነበረበትን 50 በመቶ የሚሆን ሥራ ካጠናቀቀ በኋላ ሥራው ከሚቆም በሚል ከስምምነቱ ባሻገር እየሠራ መሆኑን ይናገራል፡፡ የቻይና ኤግዚም ባንክ መሸፈን የነበረበትን 50 በመቶ ክፍያ እስከአሁን አለቀቀም፡፡

በዚህም በቻይና ኮንስትራክሽን ኮሙዩኒኬሽንስ ኩባንያ (ሲሲሲሲ) የሚሠራው መንገድ ሦስት  ትልልቅ ማሳለጫ ድልድዮችና አራት መኪና ማስተናገድ የሚችለው የቀኝ የአስፓልት መገንባቱን አቶ እያሱ ገልጸዋል፡፡

ምክትል ዋና ዳይሬክተሩ፣ ‹‹በኤግዚም ባንክ በኩል ያለው ነገር እንዲቀጥል ነው በከፍተኛ መጠን እየተሠራ ያለው፡፡ ይሄ ነገር የማይቻል ከሆነ በከተማ ደረጃ አማራጭ የፋይናንሰ ምንጮችን ፈልጎ በራስ አቅም የሚሠራበት መንገድ ይፈጠራል፤›› በማለት የመንግሥትን ዕቅድ አስረድተዋል፡፡

ይሁንና በከፍተኛ ዋጋ የጨመረው የኮንስትራክሽ ግብዓቶች ዋጋ መጨመር የመንገዱን ለማጠነቀቅ የሚያስፈልገውን ገንዘብ ከፍ እንደሚያደረገው አስረድተዋል፡፡

እንደ ምክትል ዋና ዳይሬክተሩ ገለጻ በግራ የመንገዱ ክፍል ያጋጠመ የወሰን ማስከበር ችግር፣ በውኃ መስመር በጊዜ አለመነሳት፣ የቴሌ መስመር ማስነሳት መጓተት ከብድሩ አለመለቀቀ በተጨማሪ ለመንገዱ ሥራ መዘግየት አስተዋጽኦ አላቸው፡፡ እነዚህ ምክንያቶች ሥራውን ለመሥራት ውል የገባው ኮንትራክተርን የሚመለከቱ ባለመሆናቸው ምክንያትም የቻይናው ሲሲሲሲ የዋጋ ክለሳ እንዲደረግለት እንደሚጠይቅ ጠቁመዋል፡፡

‹‹ወደ ግንባታ ሲገባ ድርጅቱ የሚያነሳቸው ጥየቄዎች ይኖራሉ፡፡ በመጀመርያ ግን የፋይናንስ ጉዳዩን ዕልባት ማሰጠት ላይ ትኩረት ተደርጓል፡፡ ከዚህ በኋላ የሚመጡ ሌሎች ጉዳዮች በኋላ ይታያሉ፤›› ሲሉ አቶ እያሱ ተናግረዋል፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች