በመንግሥትም ሆነ በዓለም አቀፍ የግብርና ቴክኖሎጂ አቅራቢ የልማት አጋሮች የሚቀርቡ ድጋፎች በተበታተነ መንገድ የሚቀርቡበት አሠራር ቀርቶ፣ ወጥ በሆነ ማዕቀፍ ለማቅረብ የሚያስችል ፍኖታ ካርታ እየተዘጋጀ መሆኑ ተገለጸ፡፡
‹‹ዲጂታል የግብርና ኤክስቴንሽንና የምክር አገልግሎት ፍኖተ ካርታ›› የተሰኘው ማዕቀፍ፣ አገሪቱ የተቸገረችበትን የግብርና የመረጃ አያያዝ ሥርዓት ችግር የመፍታት ዕድሉ ሰፊ መሆኑ ተገልጿል፡፡ ፍኖተ ካርታው በግብርና ዘርፉ በተለይም በቴክኖሎጂ ረገድ ድርሻ ያላቸውና በተበታተነ መንገድ የሚሠሩ አካላትን አሰባስቦ አንድ ላይ እንዲሠሩ የሚያደርግ ይሆናል ተብሏል፡፡
የግብርና ሚኒስትሩ አቶ ኡመር ሁሴን እንደተናገሩት፣ ፍኖተ ካርታው ተቋማት በየራሳቸው ቴክኖሎጂ ይዘው ወደ አርሶ አደሩ ከመሄድ በአንድ መስመር (ፕላትፎርም) እንዲሄዱ የሚያደርግ ነው፡፡ ከሁሉም በላይ ይህንን ሥራ የሚደግፉ እንደ ዓለም ባንክ፣ ቢልና ሚሊንዳ ጌትስ ፋውንዴሽንና ከሌሎችም አጋር ተቋማት የሚደግፉበትን አሠራር ወይም አተገባበር እንዴት ይሆናል? የሚለውን ለማቀናጀት ፍኖተ ካርታው ወሳኝ ነው ተብሏል፡፡
የኢትዮጵያ ግብርና ዓለም ከደረሰበት ሁኔታ ጋር እንዲጓዝ፣ እያደገ የመጣውን የግብርና መረጃ የሚመጥን ዕርምጃ ካልተደረገ፣ ዘመናዊ የመረጃ አያያዝ ሥርዓት ካልተዘረጋ፣ ከጊዜው ጋር መሄድ የሚያዳግት መሆኑን የግብርና ሚንስትሩ ገልጸዋል፡፡
ከቀበሌ እስከ ሚኒስቴር መሥሪያ ቤት ድረስ መረጃን ማምጣት ከባድ እየሆነ መምጣቱን የተናገሩት አቶ ኡመር፣ መረጃው ቢገኝም ጊዜው ያለፈበትና በማኑዋል አማራጭ የሚገኝ ይሆናል ብለዋል፡፡
‹‹መረጃዎች ከላይ ሲወርዱም ሆነ ከታች ሲላኩ የሚመጥን ዓይነት ዳታ ቤዝ ሊኖር ይገባል፡፡ በማኑዋል የሚተገበረው የመረጃ አያያዝ ከፍ ካለ የፖሊሲ ውሳኔ ሰጪዎችን የሚያሳስት፣ ዝቅ ብሎ ከተገኘ አገርን የሆነ ቦታ የሚጥል ስለሆነ የመረጃ አያያዙ ዝመና ላይ መሠራት ይገባዋል፤›› ሲሉ አቶ ኡመር ተናግረዋል፡፡
ኢትዮጵያ ያነሰባትን የምርታማነት ችግር ፍኖተ ካርታው የሚፈታ ይሆናል ያሉት የግብርና ሚንስትሩ፣ ችግሩን መፍታት ብቻም ሳይሆን በትስስር ሰንሰለት ውስጥ በአንዱ ቦታ ላይ የታነቀውን የግብርና ምርቶች የዝውውር ሥርዓት ጭምር ሊፈታ ይችላል በማለት ገልጸዋል፡፡ ይህም የሚሆነው ምርት የት ቦታ እንዳለ በቀላሉ ለማወቅ የሚያስችል ሥርዓተ ተግባራዊ ስለሚደረግበት ነው፡፡
የግብርና ትራንስፎርሜሽን ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር ማንደፍሮ ንጉሤ (ዶ/ር) እንደተናገሩት፣ የዲጂታል ፍኖተ ካርታው የአገሪቱን የግብርና ዘርፍ ለማዘመን ትልቅ አስተዋጽኦ አለው፡፡
ፍኖተ ካርታው መረጃ ማግኘትን፣ ተገኘውን መረጃ ማደራጀትና የተደራጀውን መረጃ በሚፈለገው መንገድ በማጠናከርና በመተንተን፣ ለተጠቃሚው ተደራሽ ማድረግ መሆኑን ማንደፍሮ (ዶ/ር) አስታውቀዋል፡፡
የዲጂታል ግብርና ኤክስቴንሽንና የምክር አገልግሎት ፍኖተ ካርታውን አስመልክቶ ከሰኔ 9 እስከ 10 ቀን 2014 ዓ.ም. በሸራተን አዲስ ሆቴል የፌዴራልና የክልል ከፍተኛ የመንግሥት የሥራ ኃላፊዎች፣ ጉዳዩ የሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት፣ እንዲሁም ዓለም አቀፍ የልማት አጋሮች በተሳተፉበት ውይይት ጥናቶች ቀርበዋል።
ኢትዮ ቴሌኮምን ጨምሮ በቀጣይ ወደ አገሪቱ የሚገቡ የቴሌኮም ኩባንያዎች የዲጂታል ኢኮኖሚውን ለመደገፍ እየተጫወቱ የሚገኙትን ሚና፣ የግብርናውን ዘርፍም ዲጂታል በማድረግ ምርታማነትን ለማሳደግ በቅንጅት መሥራት ይገባቸዋል የሚል ሐሳብ በውይይቱ ወቅት ቀርቧል፡፡
‹‹ዋናው ጉዳይ የፍኖታ ካርታ ዝግጅቱ ሳይሆን፣ ሥራውን መሬት ማድረስ ነው፤›› ያሉት አቶ ኡመር፣ በተለይም ዓለም አቀፍ ደጋፊ ተቋማት ከመንግሥት ወይም ከግብርና ሚንስቴር ጋር እስከ መጨረሻ ትግበራ መሄድ አለባቸው የሚል ሐሳብ አቅርበዋል፡፡