Tuesday, March 5, 2024
- Advertisment -
- Advertisment -

ድርድር ሰላም ማስፈኛ እንጂ በሕዝብ ላይ መቆመሪያ አይደለም!

የሰሜን ኢትዮጵያን ጦርነት በማስቆም ሰላም ለማስፈን ያግዛል የተባለው ድርድር እንደሚጀመር ፍንጭ መሰማቱ መልካም ዜና ነው፡፡ ከድርድር በፊት ደግሞ አድካሚ የሆኑ ውጣ ውረዶች መኖራቸውን ማንም አይስተውም፡፡ ተደራዳሪ ወገኖች ከሚያቀርቧቸው ቅድመ ሁኔታዎች መካከል የአደራዳሪዎች ማንነት፣ የድርድሩ ተሳታፊዎች፣ የመደራደሪያው ሥፍራ፣ የድርድር ታዛቢዎች፣ ከድርድሩ የሚፈለጉ ውጤቶችና የመሳሰሉት ይጠቀሳሉ፡፡ እነዚህ ቅድመ ድርድር ፍላጎቶች በቅጡ ካልተያዙና በሁሉም ወገኖች መካከል መተማመን ካልተፈጠረ፣ በሌሎች አገሮች እንደታየው በጦርነቱ ወቅት ከነበረው ዕልቂትና ውድመት የባሰ ጥፋት ሊከተል ይችላል፡፡ በኢትዮጵያም ከፍተኛ ዕልቂትና ውድመት ካደረሰው ጦርነት ውስጥ ለመውጣት ከፍተኛ ትዕግሥትና ብልኃት ያስፈልጋል፡፡ ለዚህ ደግሞ ወደ አደገኛው ጦርነት ውስጥ ከከተቱ እልኸኝነትና ግትርነት በመላቀቅ፣ የአገርን ዘለቄታዊ ጥቅምና የሕዝብን ደኅንነት ያማከሉ ጉዳዮች ላይ እንዲተኮር ሁሉም ወገኖች መጠንቀቅ አለባቸው፡፡ ከጥንቃቄዎች መካከል አንደኛው የውጭ ኃይሎችን አላስፈላጊ ጣልቃ ገብነት መከላከል ነው፡፡ በድርድሩ ወቅት የሚያወዛግቡ ጉዳዮች ማጋጠማቸው አይቀሬ ቢሆንም፣ በሕጋዊ ማዕቀፍ የሚፈቱበትን አማራጭ ለመጠቀም ፈቃደኝነት መኖር ይኖርበታል፡፡ ፖለቲካዊ መፍትሔ እንዲገኝ ጥረት ማድረግ አስፈላጊ ነው፡፡

በተካሄደው ጦርነት በጥቅሉ ከሚገለጸው ሰብዓዊና ቁሳዊ ውድመት በተጨማሪ በኢትዮጵያውያን መሀል የተፈጠረው ቂም በቀልና ቁርሾ ከሚታሰበው በላይ በመሆኑ፣ ይካሄዳል በሚባለው ድርድር ሒደቶች ውስጥ ትውልድ ተሻጋሪ እርማት ለማድረግ ቁርጠኛ መሆን ካልተቻለ መከራው ይቀጥላል፡፡ የድርድሩ ዋና ዓላማ ሰላም በማስፈን ኢትዮጵያ የተረጋጋች አገር እንድትሆን ለማድረግ ከሆነ መልካም ነው፡፡ ከዚህ ውጪ ግን እንደተለመደው በሕዝብ ስም እየቆመሩ የተወሰኑ ቡድኖችን ፍላጎት ለማርካት ከሆነ ግን ፍሬ አልባ ነው፡፡ በተለያዩ አገሮች ድርድርን ጊዜ መግዣና ጠላትን ማዘናጊያ በማድረግ ከፍተኛ ጉዳቶች ደርሰዋል፡፡ አንደኛው ኃይለኛ በሆነበት ጊዜ ሌላው ከእነ ድክመቱ ለድርድር መቀመጡ የተለመደ ነው፡፡ ደካማው ኃይሉን ባሰባሰበት ጊዜም ከድርድር ማፈንገጡ ይታወቃል፡፡ በእንዲህ ዓይነቱ ውጣ ውረድ ውስጥ ደግሞ ጥቅማቸውን በማስላት ተፅዕኖ የሚፈጥሩ የውጭ ኃይሎች መከሰታቸውም የታወቀ ነው፡፡ የሰሜን ኢትዮጵያን ጦርነት ለመቋጨት ያግዛል ተብሎ በሚጠበቀው ድርድር የሚሳተፉ ወገኖች፣ ምንም እንኳ አስቸጋሪና ውስብስብ ችግሮች ማጋጠማቸው ቢታወቅም ኢትዮጵያ ከገባችበት ቀውስ ውስጥ በማውጣት ሕዝብ ዕፎይ እንዲል አድርጉ፡፡

ድርድሩ በርካታ ጥያቄዎች፣ ጭቅጭቆች፣ ያልተረጋገጡ መረጃዎችና ድምዳሜዎች ከየአቅጣጫው ሊጎርፉለት እንደሚችሉ ታሳቢ ማድረግም ተገቢ ነው፡፡ ድርድሩ ሁሉንም ወገኖች ከሞላ ጎደል አስማምቶ በቶሎ እንዲጠናቀቅ የሚፈልጉ የሚኖሩትን ያህል፣ ከድርድሩ አንደኛው ወገን የተሻለ ትርፍ እንዲያገኝ ወይም ጨርሶ እንዳይካሄድ የሚፈልጉም አሉ፡፡ እዚህ ላይ መዘንጋት የሌለበት ከድርድር በፊት የሚኖሩ በርካታ ምልልሶች መኖራቸውን ነው፡፡ በእነዚህ ምልልሶች ተስፋ ሰጪ ነገሮች ሊኖሩ የሚችሉትን ያህል፣ ከእነ አካቴው ድርድሩን በማቋረጥ ወደ ጦርነት ለመመለስ የሚያስገድዱ ተስፋ አስቆራጭ ነገሮች ሊያጋጥሙ ይችላሉ፡፡ በዚህ ጊዜ ከድርድሩ መልካም ውጤት የሚጠብቁ ወገኖች ከአፍራሽ ፕሮፓጋንዳዎች መቆጠብ አለባቸው፡፡ ይልቁንም በተለያዩ መደበኛና መደበኛ ያልሆኑ ሚዲያዎች የሚለቀቁ ሐሰተኛ መረጃዎችን በማጋለጥ፣ ሁሉም ወገኖች ለመላው የኢትዮጵያ ሕዝብ መልካም የምሥራች እንዲገኝ ከፍተኛ ጥረት ማድረግ ይጠበቅባቸዋል፡፡ ተስፋ አስቆራጭ አጋጣሚዎች በሚኖሩበት ጊዜም ድርድሩ በማቋረጥ ሌላ ዙር ጥፋት እንዳይከተል፣ ተደራዳሪዎች ለሕዝብና ለአገር ህልውና እንዲያስቡ ማግባባት ይኖርባቸዋል፡፡

የአገር ጉዳይ ከቀልድና ከቧልት በላይ የማይሆንባቸው ወገኖች ጉዳይም ያሳስባል፡፡ እነሱና መሰሎቻቸው እንደፈለጉ የሚፈነጩበት የሥርዓተ አልበኝነት ምኅዳር እስካልተፈጠረ ድረስ፣ ለአገርም ሆነ ለሕዝብ የማይጨንቃቸው ብዙ ጉዶች እንዳሉ ይታወቃል፡፡ ከሥልጣንና ከጥቅም ውጪ አገር ብትፈርስ፣ ሕዝብ ቁምስቅሉን ቢያይ ምንም የማይገዳቸው ሞልተዋል፡፡ ከማኅበራዊ የትስስር ገጾችና ከጥቅም ማሳደጃ ዩቲዩቦች በታች አገርንና ሕዝብን የሚያሳንሱ በየቦታው ተዘርተዋል፡፡ የአገር ጉዳይ የሚያሳስባቸው ሁሉ እነዚህን በመከተል የጥፋት ተባባሪ ከመሆን ይልቅ፣ ኢትዮጵያ ሰላሟን አግኝታ ልጆቿ በነፃነትና በእኩልነት የሚንቀሳቀሱባት እንድትሆን ጥረት ያድርጉ፡፡ በኢትዮጵያ ምድር የረከሰው ሞትና ውድመት እንዲያበቃ ይልፉ፡፡ በሰላም ወጥቶ መግባት ብርቅ የሆነባት ኢትዮጵያ ሰላም እንዲነፍስባት ይትጉ፡፡ በምግብና በመድኃኒት ዕጦት እየረገፉ ያሉ ወገኖችን ለመታደግ ይተባበሩ፡፡ የትምህርት፣ የጤና፣ የሥራና የሌሎች መሠረታዊ አገልግሎቶች ዕጦት የሚያሰቃያቸውን ኢትዮጵያውያን ካሉበት ችግር ለማውጣት አንድ ይሁኑ፡፡ የሰላም ዋጋ የሚታወቀው ሰላም በጠፋበት ጊዜ መሆኑን ለኢትዮጵያውያን መንገር ቀባሪውን እንደማርዳት ይቆጠራል፡፡ ከሰሜን ኢትዮጵያ በተጨማሪ በበርካታ ሥፍራዎች ሰላም የናፈቃቸው ወገኖች ብዙ ናቸው፡፡ የድርድር ሒደቱ ውጤታማ ሆኖ አስተማማኝ ሰላም ይስፈን፡፡

ይህ መልካም ምኞት ወደ ተግባር እንዲተረጎም ሲፈለግ ግን ከሰላም ይልቅ ከግጭት የሚያተርፉ ኃይሎች ጉዳይ መነሳት አለበት፡፡ ኢትዮጵያ ውስጥ ሰላም አደፍርሰው በዕርቅ ስም ጥቅም ከሚያጋብሱ ጀምሮ፣ ለተፈናቃዮች በሚል ዕርዳታ አሰባሳቢና አከፋፋይ ሆነው ዘረፋ ውስጥ የሚሰማሩ ሳይቀሩ ለሰላም መስፈን እንቅፋት ናቸው፡፡ በየቦታው በሚቀሰቀሱ ግጭቶች በቀጥታም ሆነ በእጅ አዙር ተሳትፎ ያላቸውና በተለያዩ የመገናኛ ዘዴዎች የሚያራግቡ ጭምር ሰላም እንዲሰፍን አይፈልጉም፡፡ ሰላም ሲሰፍን የሁሉም ዜጎች ፊት ወደ ልማት ስለሚዞር ለእነ ሥራ ጠሎች አይመችም፡፡ ኢትዮጵያ ሰላም አግኝታ ሰዎች በመረጋጋት ሰላማዊ ኑሮአቸውን መምራት ሲጀምሩ፣ የግጭት አጀንዳ የሚፈበርኩ የእንጀራ ገመዳቸው ስለሚበጠስ ደስተኞች አይሆኑም፡፡ ከግጭት ጠማቂዎች እስከ ሐሰተኛ መረጃ ፈብራኪዎች ጥቅማቸው የሚነካ በርካታ ስለሚሆኑ፣ ለሰላም የሚደረገው ድርድር ከጅምሩ እንዳይቀጭ ከፍተኛ ጥንቃቄ ያስፈልጋል፡፡ ሰላም ወዳዱ የኢትዮጵያ ሕዝብ በእነዚህ ኃይሎች የደረሰበት መከራ ሊያበቃ ይገባል፡፡ እነሱ ለማይጠረቃው ፍላጎታቸው ሲሉ መሰናክሎችን ስለሚደረደሩ ብልህ መሆን ተገቢ ነው፡፡

ተደራዳሪዎች ለድርድር ለመቀመጥ ከመዘጋጀታቸው በፊት በጎን ከሚያስተነፍሷቸው ፕሮፓጋንዳዎች መታቀብ ካልቻሉ፣ ድርድሩን ለጊዜ መግዣ በመጠቀም ለሰላም እንቅፋት ይሆናሉ፡፡ በዚህ ምድር ላይ ለድርድር ከማይቀርቡ ጉዳዮች ውስጥ ዋነኛው የአገር ሉዓላዊ አንድነትና የሕዝብ ሰላም ነው፡፡ ከዚያ በመለስ በሚኖሩ ፍላጎቶች ላይ መደራደር ይቻላል፡፡ ድርድር በሕግ፣ በታሪክ፣ በፖለቲካ፣ እንዲሁም በጋራ ፍላጎቶች ላይ ተመሥርቶ የሚከናውንና በሰጥቶ መቀበል መርህ የሚመራ ነው፡፡ ድርድርን በጉልበት ላይ በመመሥረት ለማካሄድ የሚደረግ ማንኛውም ሙከራ ለአገር የማይጠቅም፣ የሕዝብን የሰላም ናፍቆት ጥያቄ የማይመልስ ከንቱ ጥረት ነው፡፡ ተደራዳሪዎች ቅድመ ሁኔታ ይዘው መቅረባቸው ያለና የሚጠበቅ ቢሆንም፣ ከጋራ ተጠቃሚነት ያፈነገጡ መደራደሪያ ነጥቦችን ይዘው ሲቀርቡ ድርድሩ ሊከሽፍ እንደሚችል መረዳት ይኖርባቸዋል፡፡ በዓለም ላይ በበርካታ አገሮች የትጥቅ ተፋላሚዎች ለድርድር ተቀምጠው ያውቃሉ፡፡ ከሌሎች አገሮች ልምድ መቅሰምና ሰላም ማስፈን ይገባል፡፡ በሕዝብ ስም እየማሉ ድርድርን የተወሰኑ ኃይሎች መጠቀሚያ ወይም ፍላጎት ማርኪያ ማድረግ ወንጀል ነው፡፡ ድርድር ሰላም ማስፈኛ እንጂ በሕዝብ ላይ መቆመሪያ አይደለም!

በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች

- Advertisment -

ትኩስ ፅሁፎች

የአዲስ አበባ ነዋሪዎች ቁጥር ሲጨምር የሚኒባስ ታክሲዎች ቁጥር እየቀነሰ መምጣቱ ሊታሰብበት ይገባል

በአዲስ አበባ ከተማ የትራንስፖርት አገልግሎት በመስጠት ከፍተኛ የሚባለውን ድርሻ...

ሃምሳ ዓመታት ያስቆጠረው አብዮትና የኢትዮጵያ ፖለቲካ ውጣ ውረድ

የኢትዮጵያ ሕዝቦች የዴሞክራሲ ለውጥ ጥያቄ የሚነሳው ከፋሺስት ኢጣሊያ ወረራ...

በአዲስ አበባ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት የተፈጸመው ሕገወጥ ተግባር ምንድነው?

የአዲስ አበባ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት የዳይሬክተሮች ቦርድ፣...

በአዲስ አበባ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት ላይ ምርመራ እንዲደረግ ውሳኔ ተላለፈ

ፕሬዚዳንቷና ዋና ጸሐፊው ተጠያቂ ሊሆኑ ይችላሉ ተብሏል ከአዲስ አበባ ንግድና...

ምርጫ ቦርድ ፓርላማው ያፀደቀለትን 304 ሚሊዮን ብር አለማግኘቱን አስታወቀ

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ በመጪው ሰኔ 2016 ዓ.ም. በአራት...
spot_img

ተዛማጅ ፅሁፎች

በሰብዓዊ ቀውስና በውድመት የታጀቡ ግጭቶች በአስቸኳይ ይቁሙ!

በሰሜን ኢትዮጵያ በትግራይ ክልል ተጀምሮ አማራና አፋር ክልሎችን ያዳረሰው የሁለት ዓመቱ አውዳሚ ጦርነት በፕሪቶሪያ ስምምነት ቢገታም፣ ከነሐሴ ወር 2015 ዓ.ም ጀምሮ በአማራ ክልል የተጀመረው...

ታላቁ የዓድዋ ድል ሲዘከር የጀግኖቹ የሞራል ልዕልና አይዘንጋ!

የታላቁ ዓድዋ ድል 128ኛ ዓመት ክብረ በዓል ሲዘከር፣ ለአገርና ለሕዝብ ክብር የሚመጥኑ ተግባራት ላይ ማተኮር ይገባል፡፡ በዓድዋ ከወራሪው ኮሎኒያሊስት ኃይል ጋር ተፋልመው ከትውልድ ወደ...

ሰብዓዊ ቀውሶችን ማስቆም ተቀዳሚ ተግባር ይሁን!

በቅርቡ ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) ከአማራ ክልል የተለያዩ አካባቢዎች ተወክለው ከመጡ ሰዎች ጋር ያደረጉት ውይይት፣ በአማራ ክልልም ሆነ በሌሎች ሥፍራዎች የሚካሄዱ ግጭቶች ምን...