Wednesday, May 22, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

ኪንና ባህልኮንታ እና ሊሎያ በምሥራቅ አፍሪካው ፌስቲቫል

ኮንታ እና ሊሎያ በምሥራቅ አፍሪካው ፌስቲቫል

ቀን:

በአዲስ አበባ እየተካሄደ ባለው የምሥራቅ አፍሪካ የጥበባትና የባህል ፌስቲቫል፣ ባህላቸውንና ትውፊታቸውን ለማሳየት ከመጡ የኢትዮጵያ አካባቢዎች አንዱ አዲሱ የደቡብ ምዕራብ ክልል ነው፡፡

በክልሉ ከሚገኙ ስድስት ዞኖች አንዱ ደግሞ ኮንታ ዞን ነው፡፡ በኮንታ ዞን ከሚገኙ ቀበሌዎች የኦሽካ ዲንቻና አካባቢው በሊሎያ (የብረት ማዕድን) የበለፀገ እንደሆነ የኮንታ ዞን ተወላጁ አቶ አድማሱ ኮርሾ ይናገራሉ፡፡ በኮንታ ዞን ውስጥ ኦሽካ ዲንቻ ፀራ ብሔረሰብ እንደሚኖሩ፣ የብረት ማዕድንን (ሊሎያ) በማቅለጥ ቢላ፣ ዶማ፣ መጥረቢያ የሚሠሩት ደግሞ የዲሜ ማኅበረሰብ ናቸው፡፡ ቢላ፣ ዶማና ሌሎችንም ቁሶችን ከመሥራት በተጨማሪ ማዕድኑን በቁፋሮ የማግኘት ባህላዊ ጥበብ እንዳላቸው አቶ አድማሱ ይናገራል፡፡

እነዚህ ማኅበረሰቦች በእርሻና በጥምር ግብርና የሚተዳደሩ ሲሆኑ፣ ቡና፣ ማርና በመሸጥ የሚተዳደሩ ናቸው፡፡

- Advertisement -

የዲሜ ማኅበረሰብ የብረት ማዕድንን በባህላዊ ዕውቀታቸው አነፍንፈው የማግኘት ጥበብ እንዳላቸው ይናገራሉ፡፡ የብረት ማቅለጫው ባህላዊ ጋን (ኦታ፣ ኮንቻ ናጶላ) የሚያመርቱት ደግሞ ሴቶች መሆናቸውን አቶ አድማሱ ያስረዳሉ፡፡ኮንታ እና ሊሎያ በምሥራቅ አፍሪካው ፌስቲቫል | Ethiopian Reporter | ሪፖርተር

በፌስቲቫሉ ባህላዊ ዕውቀትን ለማሳየት ከመጡት ሰባት ወንዶች በተጨማሪ የብረት ማቅለጫ ጋን የሚሠሩት ወ/ሮ ሚሲሌ ጭላጮ ናቸው፡፡

ኮምቻ፣ ጾላ ወይም ጋን በቀላሉ መሥራት እንደሚችሉ የሚናገሩት ወ/ሮ ሚሲሌ ኦታ፣ ከሸክላ የሚሠሩ ጋንና የሸክላ ድስት ለብረት ማቅለጫነት የዲሜ ማኅበረሰብ እንደሚጠቀም በነዚህም ለእርሻ፣ ለአደን፣ ለምግብ መሥሪያና ለሌሎችም የሚውሉ ምርቶችን ሲያመርት መቆየቱን ይገልጻሉ፡፡

ኮንታና አካባቢዋ በተፈጥሮ የተቸረ ከመሆኑ በተጨማሪ ሳያቋርጡ የሚፈሱ ጅረቶች ባለቤቶች ናቸው፡፡ የተለያዩ አገር በቀል ዛፎች የሚገኙበት፣ ጥምዝ፣ ኮረሪማ፣ ሌሎችም ቅመማ ቅመሞች የሚመረቱበት አካባቢ እንደሆነ አቶ አድማሱ ይናገራሉ፡፡

ለመድኃኒትነት የሚውሉ የዕፀዋት ዓይነቶች እንደሚገኙ የገለጹት አቶ አድማሱ፣ ጥናት ተደርጎበት ለሕክምና የሚጠቅሙ ዕፀዋት ማግኘት እንደሚቻል ተናግረዋል፡፡

በኦሽካ ዲንቻ የብረት ማዕድን በተጨማሪ ወርቅ እንደሚገኝ ቢነገርም፣ በጥናት አልተረጋገጠም ይላሉ፡፡

የኮንታ ዞን በገበታ ለአገር ኮይሻ የሚለማበት አካባቢ ሲሆን፣ ጨበራ ጮርጮራ ብሔራዊ ፓርክ የሚገኝበት መሆኑን ጠቁመዋል፡፡

በፌስቲቫሉ የብረት ማዕድን ባህላዊ የማቅለጫን ዘዴ ለማሳየት የመጡ ሲሆኑ፣ የብረት ማዕድን የማቅለጫውን ጋን (ኦታ) የሚሠሩት ደግሞ ሴቶች መሆናቸውን አስረድተዋል፡፡

በባህልና ስፖርት ሚኒስቴርና በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አማካይነት እየተካሄደ የሚገኘው የምሥራቅ አፍሪካ የጥበባትና የባህል ፌስቲቫል እስከ ሰኔ 12 ቀን 2014 ዓ.ም. የሚቀጥል ነው፡፡

ፌስቲቫሉ ሰኔ 7 ቀን የተከፈተ ሲሆን በማግስቱ ደግሞ በእንጦጦ ፓርክ የሥዕል ዓውደ ርዕይ ተከፍቷል፡፡ በዓውደ ርዕዩ ከ100 በላይ የሥዕልና የቅርፃ ቅርፅ ሥራዎች ቀርበውበታል፡፡

የኢትዮጵያ ሠዓሊያንና ቀራፂያን ማኅበር ፕሬዚዳንት ሠዓሊ አክሊሉ መንግሥቱ እንደተናገሩት፣ የተነገረን ከምሥራቅ አፍሪካ አገሮችም ሠዓሊያን እንደሚመጡ ነው፡፡ ማኅበሩም ሐሳቡን ተቀብሎ እየሠራ እንደነበር፣ ከሌሎች አገሮችም ይመጣሉ የተባሉ ሠዓሊያን ባልታወቀ ምክንያት እንዳልመጡ ፕሬዚዳንቱ ገልጸዋል፡፡

በፌስቲቫሉ ከምሥራቅ አፍሪካ አገሮች የተገኙት ውስን መሆናቸውን፣ ይኼም በሠዓሊያኑ በኩል ቅሬታ እንደፈጠረባቸው ጠቁመዋል፡፡

ፌስቲቫሉ የምሥራቅ አፍሪካ አገሮችን ግንኙነት በጥበብና በባህል በማስተሳሰርና የሕዝቦችን የጋራ ተጠቃሚ ለማድረግ የሚያስችል መሆኑንም ሳይገልጹ አላለፉም፡፡

የባህልና ስፖርት ሚኒስትር  ጽሕፈት ቤት ኃላፊ አቶ አህመድ መሐመድ   ‹‹በምሥራቅ አፍሪካ ጥበባትና ባህል ፌስቲቫል ትልቅ አቅም ያለን መሆኑን ያሳየንበት ነው፤›› ብለዋል፡፡ አክለውም እንደገለጹት፣ የምሥራቅ አፍሪካ የኪነ ጥበብና የባህል ፌስቲቫል በጋራ ለመሥራትና አገሮች ባህላዊ እሴቶቻቸውን፣ ልምዶቻቸውንና ታሪካዊ ሀብቶቻቸውን የሚለዋወጡበት መድረክ ይሆናል።

ዓውደ ርዕዩ የምሥራቅ አፍሪካን ሥነ ጥበባት እሴቶቻችንን ለማስተዋወቅና በአርቲስቶቻችን መካከል ያለውን የእርስ በርስ ትስስር ለማሳደግ እንደ ጥሩ አጋጣሚ እንደሆነ ገልጸዋል።

በተያያዘ ዜና የምሥራቅ አፍሪካ የጥበባትና ባህል ፌስቲቫል አካል የሆነው ዓውደ ጥናት ሰኔ 9 ቀን በኢሊሌ ሆቴል ተካሂዷል፡፡ ‹‹ባህልና ጥበብ ለቀጣናዊ ትስስር!›› በሚል መሪ ቃል በተካሄደው ዓውደ ጥናት ላይ በኢትዮጵያውያን ምሁራን ብቻ የቀረቡት ጥናቶች እንዳመለከቱት፣ የምሥራቅ አፍሪካ አገሮች በተፈጥሯዊ አቀማመጥ የተሳሰሩ፣ ባህልና ቋንቋን የሚጋሩ ሕዝቦች ያሏቸው ናቸው፡፡ ጥናቶቹ የሕዝቦችን ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነት ለማረጋገጥና ለማቀራረብ የሚያስችሉ ነባራዊ ምቹ ሁኔታዎችን ጠቋሚ መሆናቸው ተመልክቷል፡፡

በመድረኩ የቀረቡት ጥናቶች ባዬ ይማም (ፕሮፌሰር) ‹‹ቋንቋ እና ቀጣናዊ ትስስር በአፍሪካ ቀንድ ተተኳሪነት››፣ ዘላለም ተፈራ (ዶ/ር) ‹‹የብዝኃ ባህል ሚና ቀጣይነት ላለው ሰላምና ኢኮኖሚያዊ ዕድገት ግንባታ››፣ ፊሌ ጃለታ (ዶ/ር) የአገር በቀል ዕውቀት ሚና ሰላምና ደኅንነት ለማረጋገጥ፡ በምሥራቅ አፍሪካ ተተኳሪነት›› አቶ ታዲዮስ ጌታቸው ‹‹የፈጠራ ሥራዎች ኢንዱስትሪ ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታ በምሥራቅ አፍሪካ ነባራዊ ሁኔታ›› የሚሉ ናቸው፡፡

‹‹የምሥራቅ አፍሪካ የወደፊት ዕጣ ፈንታ የተሻለና ብሩህ ነው። አብረን ከሠራን በአንድነት ከፍ ብለን እንበራለን፡፡ ዕጣ ፈንታችን ተመሳሳይ በመሆኑ ህልማችንን እንደምናሳካው ተስፋ አደርጋለሁ፤›› ያሉት በዓውደ ጥናቱ ላይ የተገኙት የባህልና ስፖርት ሚኒስትር አቶ ቀጄላ መርዳሳ ናቸው፡፡ ሚኒስትሩ አያይዘውም ፌስቲቫሉ የቀጣናውን ሕዝቦች ባህላዊ፣ ታሪካዊና ተፈጥሯዊ ብዝኃነትን ለማስተዋወቅ የሚጠቅም ፋይዳ ያለው ነው በማለትም ተናግረዋል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የማዳበሪያ አቅርቦትና ውጣ ውረዱ

በቅፅል ስሙ “The Father of Chemical Warfare” እየተባለ የሚጠራው...

የኢትዮጵያ ልማት ባንክ የትርፍ ምጣኔውን ከ70 በመቶ በላይ አሳደገ

ከሁለቱ መንግሥታዊ ባንኮች መካከል አንዱ የሆነው የኢትዮጵያ ልማት ባንክ...