Monday, October 2, 2023

በጋምቤላ ሰው በጥይት ደብድቦ በመግደል የተጠረጠሩ የፀጥታ አስከባሪዎች ተያዙ

- Advertisement -spot_img

በብዛት የተነበቡ

በጋምቤላ ክልል ሰኔ 8 ቀን 2014 ዓ.ም. በፀጥታ ኃይሎች በተወሰደ ዕርምጃ፣ ያልተመጣጠነ የኃይል ዕርምጃ በመውሰድና ሰዎችን በጥይት በመግደል የተጠረጠሩ ሁለት የፀጥታ አስከባሪዎች መታሰራቸው ተነገረ፡፡

የኦነግ ሸኔና የጋምቤላ ነፃነት ግንባር ቡድን አባላት ሰኔ 7 ቀን 2014 ዓ.ም. በጋምቤላ ጥቃት መክፈታቸውን ተከትሎ፣ የፀጥታ ኃይሎች ዕርምጃ መውሰዳቸው ይታወሳል፡፡ በዚህ የፀጥታ ማስከበር ሒደት ተመጣጣኝ ያልሆነ ዕርምጃ አንዳንድ የፀጥታ አስከባሪዎች መውሰዳቸውን ያመነው የክልሉ መንግሥት፣ ሰው በጥይት ደብድቦ በመግደል የተጠረጠሩትን ማሰሩን አስታውቋል፡፡

የክልሉ የፀጥታ ኃይል ጠላት ባላቸውና ተቆርጠው በቀሩ ፀረ ሰላም ኃይሎች ላይ ዕርምጃ እየወሰደ መሆኑን ክልሉ ገልጿል፡፡ የክልሉ ፀጥታ ወደ ነበረበት ለመመለስ የፀጥታ ኃይሎች በሚወስዱት ዕርምጃ፣ ሕገወጥነት እንዳያጋጥም ከፍተኛ ጥንቃቄ እየተደረገ ነው በማለት ነው ክልሉ ያስታወቀው፡፡

ይሁን እንጂ የፀጥታ ኃይሎች በጋምቤላ ከተማ አንድ ወጣትን፣ በቡድን ሆነው በጥይት ደብድበው መግደላቸውን ከሚጠቁም መረጃ ጋር ተያይዞ የተሠራጨ አንድ ቪዲዮ ከፍተኛ መነጋሪያ ሆኗል፡፡

ይህንኑ የቪዲዮ መረጃ መመርመሩን፣ እንዲሁም ከጋምቤላ ከተማ ነዋሪዎች መረጃ መሰብሰቡን ያመለከተው የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽንም፣ በጋምቤላ እየተወሰደ ባለው የፀጥታ ማስከበር ዕርምጃ ከሕግ ውጭ ግድያ መፈጸሙን መረጃዎች እንደ ደረሱት የሚያመለክት መግለጫ አውጥቷል፡፡

ይህን በሚመለከት ምላሽ የሰጡት የጋምቤላ ክልል ኮሙዩኒኬሸን ጉዳዮች ጽሕፈት ቤት ኃላፊ አቶ ኡጉት አዲንግ ችግሩ ማጋጠሙን አምነው፣ ከሕግ ውጪ ግድያ በፈጸሙ የፀጥታ ኃይሎች ላይ ዕርምጃ መወሰዱን ገልጸዋል፡፡

‹‹ኦነግ ሸኔና የጋምቤላ ነፃነት ግንባር ኃይሎች ሲቪል ለብሰው ነበረ ሲዋጉ የነበረው፡፡ የፀጥታ ኃይሎቻችን የወሰዱባቸውን ዕርምጃ መቋቋም ሲያቅታቸው ደግሞ የነዋሪዎች ቤት ሸሽተው ገቡ፡፡ አንዳንዶቹ ልብሳቸውን በመቀየር ለማምለጥ ሲሞክሩ ተይዘዋል፡፡ ይሁን እንጂ የፀጥታ ኃይሎች በተከታታይ ቀናት ባደረጉት ለቀማ ብዙዎቹ በቁጥጥር ሥር ውለዋል፤›› ሲሉ ነው አቶ ኡጉት ስለፀጥታ ማስከበር ዕርምጃቸው የተናገሩት፡፡

በዚህ የፀጥታ ማስከበር ዕርምጃ ከነዋሪው ጋር የተመሳሰለ ልብስ ለብሰው ሲዋጉ የነበሩ የኦነግ ሸኔና የጋምቤላ ነፃ አውጪ ቡድን አባላት ለይቶ ሕጋዊ ዕርምጃ የመውሰዱ ጥረት ፈታኝ መሆኑን ኃላፊው ተናግረዋል፡፡ ‹‹በዚህ የተነሳ ጥንቃቄ ሳያደርጉ ወይም በእልህና በቁጣ ሰላማዊ ዜጎች ላይ ዕርምጃ የወሰዱ የፀጥታ አስከባሪዎች ነበሩ፤›› ሲሉ የተናገሩት አቶ ኡጉት፣ አንድ የልዩ ኃይልና አንድ የመደበኛ ፖሊስን ጨምሮ ሁለት የፀጥታ አስከባሪዎች በሕገወጥ ግድያ ተጠርጥረው መያዛቸውን አመልክተዋል፡፡

‹‹በማኅበራዊ ሚዲያ የተሠራጨውን ቪዲዮ ተከትሎ የጋምቤላ የፀጥታ ኃይሎች የሌላ ብሔርን ገደሉ የሚል ወሬ መሰራጨቱ አግባብ አይደለም፡፡ እኛ የሸኔም ሆነ የጋነግ አባል በሰላም እጅ ከሰጠ አንዳችም ጉዳት ሳይደርስበት ለሕግ እንዲቀርብ ነው የምናደርገው፤›› በማለት አቶ ኡጉት፣ የፀጥታ ኃይሎችም ሕግ ሲጥሱ እንደሚጠየቁ አስረድተዋል፡፡

የክልሉ መንግሥት ይህንን ቢልም በጋምቤላ የቀጠለው ከፀጥታ ማስከበር ዕርምጃ ጋር ተያይዞ የተፈጠረው የሰብዓዊ መብቶች ጥሰት አሳሳቢ ሆኖ እንዳገኘው ነው፣ የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን ባወጣው መግለጫ ያስታወቀው፡፡ የኮሚሽኑ ዋና ኮሚሽነር ዳንኤል በቀለ (ዶ/ር)፣ የፀጥታ ኃይሎች የጋምቤላ ፀጥታን መመለስ ተቀዳሚ ሥራቸው ቢሆንም፣ ነገር ግን የሰዎችን ሕይወት ሊያጠፋ ከሚችል ተመጣጣኝ ካልሆነ ዕርምጃ ሊቆጠቡ ይገባል ሲሉ በመግለጫቸው አሳስበዋል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ትኩስ ጽሑፎች

ተዛማጅ ጽሑፎች

- Advertisement -
- Advertisement -