በኦሮሚኛ ሙዚቃ ስመጥር በሆነው ድምፃዊ ሃጫሉ ሁንዴሳ ስም የተዘጋጀው የሙዚቃ ሽልማት ሰኔ 22 ቀን 2014 ዓ.ም. እንደሚያካሂድ የሃጫሉ ሁንዴሳ ፋውንዴሽን አስታወቀ።
የሽልማት ቀኑ በየዓመቱ ሰኔ 22 ቀን ለማካሄድ የተመረጠው ድምፃዊው ሃጫሉ ሕይወት ያለፈበት ቀን በመሆኑ እንደሆነም ተመልክቷል፡፡
ሽልማቱን አስመልክቶ ረቡዕ ሰኔ 8 ቀን 2014 ዓ.ም. በራዲሰን ብሉ ሆቴል መግለጫ የሰጡት የድምፃዊ ሃጫሉ ባለቤትና የፋውንዴሽኑ የቦርድ አባል ወ/ሮ ፋንቱ ደምሰው እንደገለጹት፣ ሽልማቱ በአሥር የሙዚቃ ዘርፎች እንደሚሰጥና ሃጫሉ ካረፈበት ዕለት ወዲህ እስከ መጋቢት 22 ቀን 2014 ዓ.ም. የወጡ የአፋን ኦሮሞ ሙዚቃዊ ሥራዎች ለውድድሩ ይቀርባሉ፡፡
በቀጣይም በሌሎች ቋንቋዎች የተዘጋጁ ሥራዎችን ለማካተት መታቀዱንም ገልፀዋል።
በውድድሩ የተካተቱት የዓመቱ ምርጥ ሙዚቃ፣ ምርጥ የሙዚቃ ክሊፕ፣ ምርጥ ዜማና ግጥም፣ ምርጥ የሙዚቃ አቀናባሪ፣ ምርጥ ሲኒማቶግራፈር እንዲሁም ምርጥ ወንድና ሴት ወጣት ድምፃውያን በዘርፉ ተካተዋል።
ከተመረጡ የሙዚቃ ሥራዎች መካከል አሸናፊዎቹ የሚለዩት የዳኞች 70 በመቶ ድምፅና የሕዝብ 30 በመቶ ድምፅ ተደምሮ መሆኑ በመግለጫው ተጠቁሟል። የሃጫሉ ሽልማትን በአፍሪካ ደረጃ ለማስተዋወቅ የሚሠራ መሆኑም ተገልጿል፡፡
በድምፃዊያኑ ቤተሰቦች ሰኔ 10 ቀን 2013 ዓ.ም. የተመሠረተው የሃጫሉ ሁንዴሳ ፋውንዴሽን፣ዋና ዓላማ በሙዚቃ፣ በድራማ፣ በፊልም፣ በሥነ ጽሑፍ፣ በሥዕል፣ በፎቶግራም፣ በቅርፃ ቅርፅና በሌሎች ዘርፎች የሚሳተፉትን ማበረታታት እንደሆነ ባለቤቱ ገልጸዋል፡፡
በሌላ በኩል ደግሞ ለተቸገሩ ወገኖች ድጋፍ መስጠት፣ የማኅበረሰብ ልማት በሚያመጡ ፕሮጀክቶችና ፕሮግራሞች ላይ መሳተፍ፣ ለተለያዩ ችግሮች የተጋለጡ ታዋቂ አርቲስቶችን ሆነ ቤተሰቦቻቸውን መደገፍ የፋውንዴሽኑ ተግባር መሆኑን ወ/ሮ ፋንቱ ተናግረዋል፡፡

የሚደረግለት ነፍስ ኄር ሃጫሉ ሁንዴሳ
ድምፃዊው ሃጫሉ ሁንዴሳ ሲገለጽ
በኦሮሚኛ ሙዚቃ ታሪክ ሁነኛ ሥፍራ እንዳለው የሚነገርለት ሃጫሉ ሁንዴሳ (1976 – 2012) በሙዚቃው ስለሕዝብ መብት፣ ፍትሕና ነፃነት በማቀንቀን ይታወቃል፡፡
በገጸ ታሪኩ እንደተመለከተው፣ ሙዚቃን በትውልድ ቦታው በአምቦ ከተማ ታዳጊ ሳለ በማንጎራጎር የጀመረ ሲሆን፣ ድምፃዊው በኦሮሞ የሙዚቃ ባህልና ትውፊትን መሠረት ያደረጉ የጌረርሳ (ቀረርቶ) ሥልት የያዙ ሥራዎቹ፣ የበርካቶችን ትኩረት እሱ ላይ እንዲያርፍ አድርገውታል፡፡ በአገር ውስጥና በውጭ አገሮች የሙዚቃ ኮንሰርት አቅርቧል፡፡
ገጣሚም የዜማ ደራሲም የሆነው ሃጫሉ በኋላ የመጀመርያውን አልበም አዲስ አበባ ላይ በማውጣት በአጭር ጊዜ ውስጥ የተለያዩ አካባቢዎች መድረስ ችሏል፡፡ የሕዝቡን ብሶት በዜማው ያቀረበ፣ ሹማምንትን እየተቸ ያቀነቀነውን ሃጫሉ፣ ‹‹በተወዳጅ ድምፁ ታግሎ ሌሎችን ያነሳሳ፣ በዘፈኖቹ አንድነትን የሰበከ›› ሲሉም ይገልጹታል፡፡
ዓምና የተለቀቀውና 14 ዘፈኖችን የያዘው ‹‹ማል ማሊሳ›› አልበሙ በበይነ መረብ ሙዚቃ በሚሸጥበት አይቲዩንስ ከተሠራጩት 100 አልበሞች ሦስተኛ ደረጃ ላይ ተመዝግቦ እንደነበረ ቢቢሲ መዘገቡ አይዘነጋም፡፡
ከአባቱ አቶ ሁንዴሳ ቦንሳና ከእናቱ ወ/ሮ ጉደቱ ሆራ በ1976 ዓ.ም. በአምቦ ከተማ 06 ቀበሌ ልዩ ስሙ አራዳ በሚባለው ቦታ የተወለደው ሃጫሉ፣ የመጀመርያና የሁለተኛ ደረጃ እንዲሁም የመሰናዶ ትምህርቱን ያጠናቀቀው በአምቦ ከተማ ነው፡፡
ከሙያው ባሻገር በተለያዩ ማኅበራዊ አገልግሎቶች ተሳታፊ የነበረውና ሰኔ 22 ቀን 2012 ዓ.ም. ከምሽቱ 3፡30 ሰዓት በአዲስ አበባ በአቃቂ ቃሊቲ ክፍለ ከተማ ገላን ኮንዶሚኒየም አካባቢ ሕይወቱ ያለፈው ድምፃዊ ሃጫሉ፣ ሥርዓተ ቀብሩ በአምቦ ከተማ ገዳመ ኢየሱስ ሐሙስ ሰኔ 25 ቀን 2012 ዓ.ም. መፈጸሙ ይታወሳል፡፡ ሃጫሉ ባለትዳርና የሦስት ሴቶች ልጆች አባት ነበር፡፡