Sunday, September 24, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ማኅበራዊየግብርና ችግርን ያቃልላል የተባለው ውድድር

የግብርና ችግርን ያቃልላል የተባለው ውድድር

ቀን:

በኢትዮጵያ እየታየ ያለውን የኑሮ ውድነት ለመታደግና በዘርፉ ላይ የሚታየውን ችግር ለመቅረፍ መንግሥት ግብርናውን ማዘመን እንዳለበት ይታመናል፡፡ በተለይም ዘመናዊ ቴክኖሎጂን የተላበሰ አሠራር በመዘርጋት እንዲሁም ለአርሶ አደሮች ምቹ ሁኔታዎችን በማመቻቸት የግብርና ዘርፍን ማሳደግ እንደሚያስፈልግ ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) በተደጋጋሚ ሲናገሩ ይደመጣል፡፡

የጠቅላይ ሚኒስትሩን ሐሳብ በመጋራት የግብርና ኢንዱስትሪው ላይ ከተሠራ አሁን ኢትዮጵያ ያለችበትን ኢኮኖሚያዊና ማኅበራዊ ዕድገት ወደፊት አንድ ዕርምጃ እንድትጓዝ መንገድ ይከፍታል በማለት ሐሳባቸውን የሚሰነዝሩ ምሁራንም አልጠፉም፡፡

ይህንን ችግር ለመቅረፍ ‹‹አዩቴ ኢትዮጵያ ቻሌንጅ›› የተሰኘና ከሁሉም ክልሎች የተወጣጡ 535 ወጣቶች የተሳተፉበት ውድድር ሰኞ ሰኔ 6 ቀን 2014 ዓ.ም. ላይ ተካሂዷል፡፡

ውድድሩን አስመልክቶ የኢፊዲ አፍሪካ ሪጅን ኢንተርናሽናል የኢትዮጵያ ካንተሪ ዳይሬክተር አቶ ቴዎድሮስ አየለ ለሪፖርተር እንደገለጹት የግብርና ዘርፉን ለማዘመንና ማነቆ የሆኑ ችግሮችን ለመፍታት በቴክኖሎጂ የታገዘ አሠራር መዘርጋት ይገባል፡፡

ውድድሩ የግብርና ኢንዱስትሪው ላይ ብቻ መሠረት ያደረገ ሲሆን፣ ኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂን ይዘው የመጡ ወጣቶች የተሳተፉበት ፕሮግራም መሆኑን ካንትሪ ዳይሬክተሩ ገልጸዋል፡፡

በአፍሪካም ሆነ በኢትዮጵያ የግብርና ዘርፉ የዘመነ ካልሆነ የምግብ እጥረት መቅረፍ እንደማይቻል የገለጹት አቶ ቴዎድሮስ፣ ይህንንም ለመታደግ ያሉትን ችግሮች ለመቅረፍ በቴክኖሎጂ የታገዘ ግብርና ያስፈልጋል ብለዋል፡፡

ወጣቶች በቴክኖሎጂ የታገዘ ግብርናን ለመፍጠር ትልቅ አማራጭ መሆናቸውን ገልጸው፣ ለዘርፉ የሚሆኑ የፈጠራ ውጤቶችን እንዲያመጡና ችግሩን እንዲቀርፉ ከተለያዩ ክፍሎች የተወጣጡ 535 ወጣቶች የተሳተፉበት ውድድር ለማካሄድ መቻሉን አስረድተዋል፡፡

ውድድሩ ለመጀመርያ ጊዜ እንደተካሄደ ያስታወሱት አቶ ቴዎድሮስ፣ የራሱ የሆነ መሥፈርት ያለውና ከ18 እስከ 29 ዓመት የዕድሜ ክልል ላይ የሚገኙ ሴት ልጆች ሆነ ወንዶች የሚሳተፉበት እንደሆነ አክለዋል፡፡

በውድድሩን ለመሳተፍ ፍላጎት ያላቸው ወጣቶች አብዛኛዎቹ ይዘዋቸው የመጡት የቴክኖሎጂ ውጤቶች ግብርናውን የሚያሳድግና የሚያበረታታ መሆኑን ጠቅሰው፣ ውድድሩ ከተጀመረበት ጊዜ አንስቶ እስከ መጨረሻው ድረስ የነበሩ ተወዳዳሪዎችን በመለየት ከአንደኛ እስከ ሦስተኛ ለወጡ ተወዳዳሪዎች የገንዘብ ሽልማት ሊበረከትላቸው እንደቻለ ጠቁመዋል፡፡

ውድድሩ ከመጀመሩ በፊት የሚያመለክቱ ተወዳዳሪዎች ቁጥር አነስተኛ  እንዳይሆን ሥጋት እንደነበራቸው፣ አብዛኛውን ወጣቶች የግብርና ዘርፉ ላይ ይሳተፋሉ ተብሎ እንዳልታመነ ተናግረዋል፡፡

ለውድድሩ አሸናፊዎች 20,000 ዶላር ተዘጋጅቶ እንደነበር የገለጹት ካንትሪ ዳይሬክተሩ፣ በዚህም መሠረት አንደኛ ለወጣው 10,000 ዶላር ሁለተኛ ለወጣው 6,500 ዶላር ሦስተኛ ለወጣው 3,500 ዶላር ሽልማት እንደተበረከተላቸው አስታውሰዋል፡፡

ለአራት ተከታታይ ዓመታት ውድድሩ የሚካድ ይሆናል ያሉት አቶ ቴዎድሮስ፣  ውድድሩ በሚዘጋጅበት ወቅት ከተለያዩ ባለድርሻ አካላት ጋር በመናበብ እንደሚሆን ጠቁመዋል፡፡

የማኅበረሰቡን የዕለት ከዕለት ጉርስና የኢንዱስትሪ ጥሬ ዕቃዎችን ምርት ከማቅረብ አኳያ ትልቁን ድርሻ የሚይዘው የግብርና ዘርፍ ነው ያሉት ደግሞ የሥራ ሥምሪትና ገበያ ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ አቶ ንጉሡ ጥላሁን ናቸው፡፡

ተቋሙም በዓመት ዕቅዱ ውስጥ አብዛኛውን ጊዜ የሥራ ዕድል ይፈጠርባቸዋል ተብሎ ከሚታሰቡት ውስጥ ከፍተኛውን ድርሻ የሚይዘው ግብርና 45 በመቶን እንደሚይዝ አቶ ንጉሡ አስረድተዋል፡፡

ተቋሙ የግብርና ዘርፉን በቴክኖሎጂ የታገዘ ለማድረግ እየሠራ ቢሆንም፣ ውጤት ተኮር አሠራር ተዘርግቷል ማለት ግን ይቸግራል ብለዋል፡፡

አብዛኛውን ጊዜ በግብርና ዘርፉ ላይ የሚሳተፍ የሰው ኃይል መጠን በዕቅድ ላይ ቢያዝም፣ ግብርና ላይ የሚሰማሩት በአገልግሎት ዘርፍ እንደሆነ ይህንንም ችግር ለመፍታት መንግሥት ትኩረት ሰጥቶ እንደሚሠራ አቶ ንጉሡ ገልጸዋል፡፡

ችግሩን ለመቅረፍና ወደ ተሻለ ደረጃ ለማምጣት በግብርና ሚኒስቴርና በሥራ ዕድል ፈጠራ ሚኒስቴር በኩል የሚተገበር የጋራ ዕቅድና ስምምነት መደረጉን ጠቁመዋል፡፡

ቀደም ሲል በግብርና ሚኒስቴር ሥር ተጠሪ የነበሩ አምስት ኮሌጆች እንዳሉ፣ ኮሌጆቹም ሥልጠናቸውን ለወጣቶች የሥራ ዕድል የሚፈጥሩበት አድርገው እንደሚሰጡ  ጠቅሰው፣ በተለይ የግብርና ኤክስቴሽን ባለሙያዎችን በብቃት የሚያሠለጥኑበትና ባለሙያዎችን የሚያፈሩበት ለማድረግ ተቋሙ እየሠራ እንደሚገኝ አብራርተዋል፡፡

ወጣቶች ወደ ግብርና ሕይወት አለመግባታቸው ላይ ያለው ክፍተት ለማወቅ ጥናት መደረግ እንዳለበት ያስታወሱት አቶ ንጉሡ፣ ይኼንንም ለማሳካትና የግብርና ዘርፉን ለማሳደግ ከመሬት ጀምሮ ግብዓት በማቅረብና ብድርን ከማሻሻል አኳያ መሻሻል ያሉባቸው ነገሮች እንዳሉ አስምረውበታል፡፡

በፌዴራል ደረጃም ሆነ በታችኛው መዋቅር የሥራ ዕድል ፈጠራ ላይ ተልዕኮ የተሰጣቸው ተቋሞች ምቹ ሁኔታዎችን በመፍጠር ያሉትን ችግሮች መታደግ ይኖርባቸዋል ብለዋል፡፡

ይኼንንም ችግር ለመፍታት በተቋሙ በየዓመቱ ሦስት ሚሊዮን ያህል ቋሚና ዘላቂ የሥራ ዕድሎች ካልተፈጠሩ በከተማዋ የሚታየውን የሥራ አጥነት ችግር በዘላቂነት መፍታት አይቻልም የሚል ጥናት እንዳለ ተናግረዋል፡፡

ከዚህም ጥናት በመነሳት በአሥር ዓመታት ዕቅድ ውስጥ ለሃያ ሚሊዮን  ዜጎች የሥራ ዕድል ለመፍጠርና ከዚህ ውስጥ በ2017 ዓ.ም. ላይ ለ14 ሚሊዮን ዜጎች የሥራ ዕድል ለመፍጠር እየተሠራ እንደሆነ ገልጸዋል፡፡

በዚህም መሠረት 11 ዘርፎች ላይ ያተኮረ አሠራር መዘርጋቱን የገለጹት አቶ ንጉሡ፣ ከእነዚህም ዘርፎች መካከል የዶሮ እርባታና የአትክትልትና ፍራፍሬ ዘርፎች ላይ ከፍተኛ የሆነ የሥራ ዕድል የሚፈጠርባቸው መሆናቸውን አስረድተዋል፡፡

በውድድሩም አንደኛ የወጣችው መስከረም የማነ ለሪፖርተር እንደገለጸችው፣ ከውድድሩ መነሻ ጀምሮ እስከ ፍጻሜ ድረስ የግብርና ዘርፉን የሚያግዝ ቴክኖሎጂን ይዛ ተገኝታለች፡፡

በውድድሩም ዘመናዊነት የተላበሰ ሽታ አልባ የዶሮ ማርቢያ ቴክኖሎጂ ይዛ መቅረቧን፣ ብዙ ፉክክር ማየቷንና በቀጣይ ዲዛይኑንና ማቴሪያሉን በማዘጋጀት በሰፊው ለማምረት ቅድመ ዝግጅት ማድረጓን ጠቁማለች፡፡

አሁን ካለው የገበያ ሁኔታና የኑሮ ውድነት አንፃር ለዶሮ ማርቢያ ቴክኖሎጂ የሚሆኑ ግብዓቶች ውድ መሆናቸውን፣ ይህንን ለመታደግ ከሌሎች ባለድርሻ አካላት ጋር በጋራ ለመሥራት ፍላጎት እንዳለት አስረድታለች፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የቤት ባለንብረቶች የሚከፍሉትን ዓመታዊ የንብረት ታክስ የሚተምን ረቂቅ አዋጅ ተዘጋጀ

በአዋጁ መሥፈርት መሠረት የክልልና የከተማ አስተዳደሮች የንብረት ታክስ መጠን...

እንደ ንብረት ታክስ ያሉ ወጪን የሚያስከትሉ አዋጆች ከማኅበረሰብ ጋር ምክክርን ይሻሉ!

የመንግሥትን ገቢ በማሳደግ ረገድ አስተዋጽኦ እንዳላቸው የሚታመኑት የተጨማሪ እሴት...

ለዓለምም ለኢትዮጵያም ሰላም እንታገል

በበቀለ ሹሜ ያለፉት ሁለት የዓለም ጦርነቶች በአያሌው የኃያል ነን ባይ...