Monday, February 26, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ማኅበራዊቀን የተቆረጠለት የኮተቤው አውራ ጎዳና ሰኔ 30 ይጠናቀቅ ይሆን?

ቀን የተቆረጠለት የኮተቤው አውራ ጎዳና ሰኔ 30 ይጠናቀቅ ይሆን?

ቀን:

መንገዱ በታሰበለት ጊዜ ባለመጠናቀቁ ለአካባቢው ነዋሪዎችም ሆነ በመንገዱ ለሚጠቀሙ ከፍተኛ ችግር እንደሆነባቸው በብስጭት ያስረዳሉ፡፡ መንገዱ ተሠርቶ ይጠናቀቃል ከተባለ ዓመታት የተቆጠሩ ቢሆንም ሰሚ አካል አጥተው በተበላሸና ለአደጋ በሚያጋልጥ መንገድ ለዓመታት መቆየታቸውንም ያክላሉ፡፡

በዚህ መንገድ መጓተትና እየደረሰ ስላለው እንግልት የአካባቢው ነዋሪዎች ‹‹መላ በሉን›› ማለት ከጀመሩም ዓመታት ተቆጥረዋል፡፡ እንኳን የአካባቢው ነዋሪ አልፎ አልፎ ለእንግድነት የሚሄድ ‹‹መቼ ነው የሚያልቀው?›› ብሎ ሳይጠይቅ የቀረበት ጊዜ የለም ማለት ይቻላል፡፡

ነዋሪዎች አቅጣጫ ቀይረውና ረዥም ተጉዘው ቤታቸው እንዲገቡ ምክንያት ሆኗል፡፡ ትራንስፖርትም አይገኝም፡፡ በችግሩ ከተማረሩት የአካባቢው ነዋሪዎች መካከልም አቶ አሚር መሐመድ አንዱ ናቸው፡፡

- Advertisement -

Video from Enat Bank Youtube Channel.

‹‹የኮተቤ መንገድ ባለመጠናቀቁ መንገላታት ደርሶብናል›› ይላሉ፡፡ አቶ አሚር የሸቀጣሸቀጥ ሱቅ ባለቤት ሲሆኑ፣ ከመርካቶ ወደ ኮተቤ ሸምቶ ለመምጣት በእጥፍ እንደሚከፍሉም ይገልጻሉ፡፡ ችግሩ ለትራንስፖርት እጥፍ በመክፈል ወይም ጭራሹኑ አጥቶ በመቸገር ብቻ የሚያበቃ እንዳልሆነም ያብራራሉ፡፡

ከአንድም ሁለት ጊዜ መንገድ ጥሶ የገባ መኪና የሰው ሕይወት እንዲጠፋና ንብረት እንዲወድም ምክንያት ሆኗል፡፡ ለአካባቢው እግረኛ ነዋሪዎችም መንገዱ አመቺ እንዳልሆነ የገለጹት አቶ አሚር፣ በክረምት ወቅት ደግሞ ችግሩ አሳሳቢ እንደሚሆንና ውኃ እንደሚያዝ፣ እንደሚያቁር ገልጸዋል፡፡ መንገዱ በተያዘለት ጊዜ ባለመጠናቀቁም በአካባቢው ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴዎች ላይ ተፅዕኖ ማሳደሩን አክለዋል፡፡

 በኮተቤ ሜትሮፖሊታን ዩኒቨርሲቲ በኩልና በታች የሚኖሩት ነዎሪዎች እንደ ልብ የመሸጋገሪያ መንገድ ባለመኖሩ ረዥም ርቀት በእግር ተጉዘው እንደሚሻገሩ፣ ነዋሪዎቹ ሲታመሙ፣ እናቶች ምጥ ሲይዛቸው ትራንስፖርት ለማግኘት አስቸጋሪ እንደሆነ፣ የንግድ ተቋማት የገቢ መጠናቸው በእጅጉ ማሽቆልቆሉንና የትራንስፖርት ዋጋ ከእጥፍ በላይ እንደሚጠየቁ ተናግረዋል፡፡

የአካባቢው ነዋሪ ወጣት ሒሩት ተስፋዬ በበኩሏ፣ የመንገድ ሥራው ከተቋረጠ ከአራት ዓመታት በላይ ሆኖታል ብላለች፡፡

ኮተቤ አዋሽ ባንክ አካባቢ ነጋዴ የሆነችው ወጣት ሒሩት፣ የመንግሥት ግብር በአግባቡ እንደምትከፍል፣ ነገር ግን መንገዱ ባለመጠናቀቁ ምክንያት የንግድ እንቅስቃሴዋ መስተጓጎሉንና በተለይም በክረምት ወቅት የአካባቢው ነዋሪዎች ተንቀሳቅሰው ለመገበያየት ከመቸገራቸው በተጨማሪም ለመኪና አደጋ ተጋላጫ መሆናቸውንም ተናግራለች፡፡

እስከ ሰኔ 21 ቀን 2014 ዓ.ም. ድረስ ይጠናቀቃል ተብሎ ቃል እንደተገባላቸው ያስረዳችው ወጣት ሒሩት፣ በአሁኑ ወቅት መንገዱ እየተሠራ መሆኑን ጠቁማለች፡፡ በሁለት ዓመታት ጊዜ ውስጥ ይጠናቀቃል ተብሎ ከዘጠኝ ዓመታት በፊት ሥራው የተጀመረው የኮተቤ መንገድ፣ የነዋሪዎችን ኢኮኖሚያዊና የማኅበራዊ መስተጋብራቸውን ከመስተጓጎሉ በተጨማሪ መንግሥትንም ለኪሳራና ላላስፈላጊ ወጪ እንዳደረገው አስረድታለች፡፡

በዩኒቨርሲቲው በኩል የሚኖሩ አንዳንድ ግለሰቦች በአካባቢው በኩል ያለው መሸጋገሪያ እንዲዘጋላቸው መፈለጋቸው ተቋራጩ የዘጋላቸው ሲሆን ይህም የትራፊክ ፍሰት ላይ ተፅዕኖ ማምጣቱን ጠቁማለች፡፡ በሥፍራው የእንግዳ ማረፊያና ሆቴል የሚገነቡ ችግር እንደሚፈጥርባቸው ምክንያት በማቅረባቸው ፕላን ተቀይሮ ሲሠራ መቆየቱን፣ የአካባቢው ማኅበረሰብ በበኩሉ ቅሬታ በማንሳቱ ፕላኑ ወደ ነበረበት እንዲመለስ መደረጉን አስረድታለች፡፡

የአገር ንብረት የባከነበት ይህ መንገድ ግንባታው ዓመታት ከማስቆጠሩም በላይ የነዋሪዎችን ሕይወት ያጎሳቆለና ስኬታማ ያልሆነ ፕሮጀክት መሆኑን ነዋሪዎቹ በምሬት ተናግረዋል፡፡

በፕላኑ መሠረት መፍረስ የነበረባቸው ቤቶች እንዳሉ፣ እዚያው ባሉበት የፕላን ለውጥ የተደረገላቸው ቦታዎች መኖራቸውን ነዋሪዎቹ ለሪፖርተር ተናግረዋል፡፡ በአሁን ጊዜ የሲሚንቶ፣ የብረትና የሌሎች ግብዓቶች ዋጋ ቢያሻቅብም መንገዱን ለማጠናቀቅ ጥረት መደረጉንም አድንቀዋል፡፡

ለረዥም ዓመታት መንገዱ ባለመጠናቀቁ በትራፊክ አደጋ ብዙዎች ሕይወታቸውን ያጡበት፣ አካል ጉዳተኛ የሆኑበት፣ የነጋዴዎች እንቅስቃሴ የተገታበት፣ ታማሚዎች የተጉላሉበት፣ ምጥ የያዛቸው እናቶች የተሰቃዩበት መሆኑን አስረድተዋል፡፡

ሥራውን የሚሠራው አካል ክረምት ሲደርስ መንገዱን ለመሥራት ብቅ እንደሚሉ ‹‹በዝናብ ምክንያት መሥራት አልቻልንም›› በማለት አቋርጠው እንደሚሄዱ፣ ነዋሪዎች ገልጸው፣ ዘንድሮም ይህ ሥጋት እንዳደረባቸው ለረዥም ጊዜያት መንገድ ተዘግቶ በመቆየቱም ነዋሪዎችም ሆኑ የንግድ ተቋማት ከፍተኛ ችግር እንዳጋጠማቸው ጠቁመዋል፡፡

ሌላኛው ሥጋታቸው አሁን መንገዱ እንደተቆፈረ ክረምት ገባ ተብሎ እንዳይቀር ሥጋታቸውን ተናግረዋል፡፡ ልዩ ስሙ ኮተቤ ፌርማታ ነዋሪ የሆነውን ሙስሊም ጀማል ክረምት ሊገባ ሲል መንገድ ለመሥራት እንደሚመጡ፣ ዝናብ ጠብ ሲል እንደሚያቋርጡ ተናግሯል፡፡

ሰሞኑን ከክፍለ ከተማ እስከ ከተማ አስተዳደር አመራሮች መጥተው መጎብኝታቸውን የግለጹት አቶ ሙስሊም፣ የዘንድሮ ሰኔ ከማለቁ በፊት ካልተጠናቀቀ ለመንግሥትም ለነዋሪውም ኪሳራ መሆኑን ገልጸዋል፡፡ መንገዱ ሁለት ፌርማታዎች እንዳሉትና ሁለቱም እንደተዘጉ፣ የትምህርት ቤትና ጤና ጣቢያ መውጪያ መግቢያዎች መዘጋታቸውን ገልጸዋል፡፡

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር መንገዶች ባለሥልጣን ዋና ዳይሬክተር ሞገስ ጥበቡ (ኢንጂነር) እንደተናገሩት፣ የኮተቤ መንገድ ስድስት ኪሎ ሜትር ርዝመትና 30 ሜትር ስፋት አለው፡፡

ነዋሪዎች መንገድ ለማቋረጥ ከ300 እስከ አንድ ኪሎ ሜትር ድረስ ተጉዘው እንደሚያቋርጡ ቅሬታ እንዳቀረቡ፣ ይህንንም ችግር መፈታቱንም ተናግረዋል፡፡ በኮተቤ ዩኒቨርሲቲ በኩል አምስት ሜትር ስፋት ያለው አዲስ መንገድ ለመክፈት በመሠራቱ ይህና ሌሎችም የሥራ ማሻሻያዎችና ችግሮች ጊዜውን እንደወሰደው፣ በፕላኑ ውስጥ ተጨማሪ የአምስት ሜትር ስፋት በመካተቱ ተጨማሪ በጀት መጠየቁን ተናግረዋል፡፡

በጀት መጨመሩን የገለጹት ኢንጂነሩ፣ በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር መንገዶች ባለሥልጣን እየተከናወነ ያለው መንገድ ሳይጠናቀቅ የዘገየው በወሰን ማስከበር ምክንያት መሆኑንና የኮተቤ መንገድ መዘግየትም ይህ አንዱ ምክንያት እንደሆነ ገልጸዋል፡፡

የመጀመሪያ ፕሮጀክቱን የያዘው ተክለብርሃን አምባዬ ሥራ ተቋራጭ ደካማ የሥራ አፈጻጸም እንደነበረውና ሁለተኛውን የመንገድ ክፍል እየሠራ እንደነበር አስታውሰዋል፡፡ ነገር ግን ሥራ አፈጻጸሙ እጅግ ደካማ በመሆኑ፣ ሙሉ በሙሉ ውል መቋረጡን አክለዋል፡፡

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ሥራ አስኪያጅ አቶ ጥራቱ በየነ እንደተናገሩት፣ የኮተቤ መንገድ የዘገየበት ምክንያት የዲዛይን ማሻሻያ የአካባቢው ነዋሪዎች በመጠየቃቸው ነው፡፡ መሸጋገሪያ መንገድ የሌላቸውን አካባቢዎች በፕላኑ ውስጥ ለማካተት፣ ቀደም ብሎ የነበረው ተቋራጭ የውል ጊዜ በመጠናቀቁም ምክንያት ሥራው ተቋርጦ እንደነበር ተናግረዋል፡፡ ችግሩንም ለመፍታት ተጨማሪ ወጪ በማድረግ የዲዛይን ማሻሻያ ተደርጎ በራስ አቅም እየተሠራ ይገኛል ብለዋል፡፡

ለዚህም በዓመቱ መጀመሪያ ላይ ከነዋሪዎቹ ጋር ውይይት መደረጉን የገለጹት አቶ ጥራቱ፣ ችግሮቻቸውን ለመፍታት ጥረት እየተደረገ እንደሚገኝና የመንገዱ አብዛኛው ሥራ መጠናቀቁን፣ ሰኔ 2014 ዓ.ም. መጨረሻ ተጠናቆ ለአገልግሎት ክፍት እንደሚሆን ጠቁመዋል፡፡ የኮተቤ መንገድ ባለመጠናቀቁ ምክንያት ነዋሪዎች ቅሬታ እንዳላቸው ያስረዱት አቶ ጥራቱ፣ ለማጠናቀቅ አስፈላጊውን ሁሉ ማድረጋቸውን ገልጸዋል፡፡

ሌላኛው ጥያቄ የነበረው ከወሰን ማስከበር ጋር የተያያዘ መሆኑን፣ ከኮተቤ ዩኒቨርሲቲ የአጥር ድንበር ወሰን ማስከበርም ምላሽ ማግኘታቸውን ጠቁመዋል፡፡ አብዛኛው የመንገዱ ሥራ መጠናቀቁንና አስፓልት የማንጠፍ ሥራው ደግሞ ክረምቱ ካልያዛቸው በስተቀር ከሰኔ 30 በፊት በማጠናቀቅ ከእግረኛና ሌሎች ተጓዳኝ ሥራዎች በስተቀር ለማጠናቀቅ ጥረት ይደረጋል ብለዋል፡፡

በጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) በተሰጠው የሥራ አቅጣጫ መሠረት የተጀመሩ ፕሮጀክቶችን ለማጠናቀቅ በሁሉም እየተረባረቡ እንደሚገኙ፡፡ የአመራር፣ የግብይት፣ የፋይናንስ ችግር እንደሌሉባቸውና በተያዘው ጊዜ ለማጠናቀቅ ችግሮች እንደሌሉ አቶ ጥራቱ ገልጸዋል፡፡

የአራራት ካራ መንገድ ማሻሻያ ፕሮጀክት በ530 ሚሊዮን ብር በጀት እንደተጀመረ ይታወሳል፡፡

ከዚሁ ጎን ለጎን የአቃቂ ቃሊቲ መንገድ ከውኃ መስመር ዝርጋታ ጋር የነበረው ችግር መቀረፉንና የተቀረው የበጀት ችግር ሲቀረፍ ወደ ሥራ እንደሚገባ ጠቁመዋል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የመጣንበትና አብረን የምንዘልቅበት የጋራ እሴታችን ለመሆኑ ነጋሪ ያስፈልጋል ወይ?

በኑረዲን አብራር በአገራችን ለለውጥ የተደረጉ ትግሎች ከመብዛታቸው የተነሳ ሰላም የነበረበት...

አልባሌ ልሂቃንና ፖለቲከኞች

በበቀለ ሹሜ በ2016 ዓ.ም. ኅዳር ማክተሚያ ላይ ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ...

አሜሪካ የኢትዮጵያ የባህር በር ጥያቄ ተገቢነት ቢኖረውም ከጎረቤት አገሮች ጋር በሚደረግ ንግግር መሆን አለበት አለች

መንግሥትን ከፋኖና ከኦነግ ሸኔ ጋር ለማነጋገር ፍላጎቷን ገልጻለች የኢትዮጵያ የባህር...