ለነዳጅ የሚደረግ ድጎማን ከሐምሌ 2014 ዓ.ም. ቀስ በቀስ ለማንሳት በዝግጅት ላይ ያለው መንግሥት፣ ከሥሌቱ በታች በአነስተኛ ዋጋ ከነዳጅ እየተሰበሰበ ያለው የኤክሳይስ ታክስና የቫት ገቢ ለታለመ የነዳጅ ድጎማ ሊያውል መሆኑ ተገለጸ፡፡
ይሁንና መንግሥት በአነስተኛ መጠን የሚሰበስበውን የኤክሳይስ ታክስና ቫት ገቢ በሕጉ መሠረት ሙሉ ለሙሉ እንዲሰበሰብ ዕቅድ አለው፡፡ ይህም የነዳጅን ዋጋ ይበልጥ ያንረዋል የሚል ሥጋት በመፍጠሩ፣ የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስቴር አሠራሩ እንዲቀጥል የውሳኔ ሐሳብ አቅርቧል፡፡
ከነዳጅ የሚሰበሰበው ይህ ኤክሳይስ ታክስና ቫት ከሰኔ 2 ቀን 2002 ዓ.ም. በተላለፈ ውሳኔ፣ እንደ ሕጉ የኤክሳይስ 30 በመቶና የቫት 15 በመቶ አይደለም፡፡ በጊዜው ነዳጅ ያሳየው ከፍተኛ ጭማሪ ተከትሎ መንግሥት 30 እና 15 በመቶ በመሰብሰብ ፋንታ፣ የነዳጅ ዋጋ ሲተመን እያንዳንዱ ሊትር ናፍጣ ላይ ሁለት ብር ከ98 ሳንቲም፣ በቤንዚን ላይም እንዲሁ ከሦስት ብር ያነሰ ጭማሪ እንዲደረግ ተወስኖ እስካሁን ቀጥሏል፡፡
መንግሥት ከዚህ ግብር የሚሰበሰበው ገቢ ከሐምሌ ወር አንስቶ ነዳጅ ላይ ለሚደረገው የታለመ ድጎማ እንዲውል መወሰኑን፣ ለጉዳዩ ቅርበት ያላቸው የመንግሥት ኃላፊ ለሪፖርተር ተናግረዋል፡፡
የነዳጅ ዋጋ ማረጋጊያ ፈንድ በ1993 ዓ.ም. ሲቋቋም ዓላማው ያደረገው በዓለም ገበያ ላይ የነዳጅ ዋጋ ጭማሪ ሲታይ፣ በፈንዱ ውስጥ የሚገኝ ገንዘብ ወጥቶ ለነዳጁ የሚወጣውን ወጪ በመደጎም የነዳጅ ዋጋን ማረጋጋት ነው፡፡ የፈንዱ ማቋቋሚያ አዋጅ ለፈንዱ የሚውል ገንዘብ ምንጭ በዓለም ገበያ የነዳጅ ዋጋ በመቀነሱ ምክንያት የሚገኝ ተራፊ ሒሳብና ከውጭ የሚገኝ ዕርዳታ መሆኑን ይጠቅሳል፡፡
ይሁንና በዓለም አቀፍ ደረጃ የነዳጅ ዋጋ በከፍተኛ መጠን በመጨመሩ ፈንዱ ‹‹ዋጋ ሲቀንስ ይገኛል›› የተባለውን ሽርፍራፊ ሳንቲም ማግኘት አቁሞ ባለ ዕዳ ሆኗል፡፡ በዚህ ዓመት ብቻ ለድጎማ የዋለው ገንዘብ ዕዳ 132 ቢሊዮን ብር ደርሷል፡፡
ይህንን አካሄድ ማስቆም የፈለገው የሚኒስትሮች ምክር ቤት ታኅሳስ 20 ቀን 2014 ዓ.ም. የነዳጅ ድጎማን ቀስ በቀስ ለማንሳት ውሳኔ አሳልፎ፣ ለዚህም የስድስት ወራት የመዘጋጃ ጊዜ ሰጥቷል፡፡ ይህንን ተከትሎም ድጎማው ሙሉ ለሙሉ ተነስቶ እስከሚጠናቀቅበት አምስት ዓመት ጊዜ ድረስ ለድጎማ የሚያስፈልገው ገንዘብ፣ ከነዳጅ ኤክሳይስ ታክስና ቫት ገቢ እንዲውል መወሰኑን ኃላፊው አስረድተዋል፡፡
‹‹መንግሥት ከዚህ ግብር የሚሰበስበውን ገንዘብ አውጥቶ ለምናቋቁመው የድጎማ ፈንድ ይሰጣል፡፡ የሚደጎሙ መኪኖች ከዚህ ግብር እየተከፈላቸው ይሄዳል፡፡ ጫናው ወደ መንግሥት አይመጣም፤›› በማለት አብራርተዋል፡፡
ይሁንና መንግሥት ቅናሽ ተደርጎበት የሚሰበሰበውን ይህንን የግብር ገቢ ከሰኔ 2002 ዓ.ም. በፊት ወደ ነበረበት መልሶ፣ ከነዳጅ ላይ 15 በመቶ ቫትና 30 በመቶ ኤክሳይስ የመሰብሰብ ዕቅድ እንዳለው ተናግረዋል፡፡
ዕቅዱ በሐምሌ ወር የሚጀምረው የነዳጅ የድጎማ መነሳት ላይ ሲደመር ከፍተኛ ጭማሪ ያስከትላል የሚል ሥጋታቸውን የሚናገሩት ኃላፊው፣ ‹‹በሕጉ መሠረት 15 በመቶ ቫትና 30 በመቶ ኤክሳይስ ታክስ ሲታሰብ ቤንዚን 103 ብር ገደማ፣ ናፍጣ 106 ብር ይመጣል፤›› በማለት አስረድተዋል፡፡
ይህንን ታሳቢ በማድረግም የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስቴር አሁን እየተሠራበት ያለው አሠራር በተወሰነ መልኩም ቢሆን እንዲቀጥል የሚል ሐሳብ፣ ውሳኔውን ለሚያስተላልፈው የሚኒስትሮች ምክር ቤት ማቅረቡን ገልጸዋል፡፡
‹‹ይህንን ግብር እንደ ድሮው በተወሰነ መጠን እንደጉመው የሚል የውሳኔ ሐሳብ በእኛ በኩል ቀርቧል፡፡ ግብሩ ሙሉ ከሚሆን ቢያንስ 25 በመቶ ቢሆን፣ ከስድስት ወራት በኋላ ደግሞ 50 በመቶ እያለ እየታየ ቢያድግ፣ ሁሉንም ባይጨምር ብለን ጠይቀናል፤›› ብለዋል፡፡
እንደ ኃላፊው ገለጻ መንግሥት አሠራሩን ወደ ቀድሞው መንገድ ለመመለስ ምክንያት የሆነው አንዱ ጉዳይ፣ ኤክሳይስ ታክስ በ2012 ዓ.ም. ተሻሽሎ መውጣቱ ነው፡፡
አዋጁ አንቀጽ ሰባት ንዑስ አንቀጽ አራት/ሀ ገንዘብ ሚኒስቴር በሚያወጣው መመርያ በልዩ ሁኔታ ካልተፈቀደ በቀር፣ የነዳጅ ምርቶች ወደ አገር ውስጥ በሚገቡበት ጊዜ የኤክሳይስ ታክስ መክፈል ግዴታ እንደሆነ ደንግጓል፡፡
አዋጁ ከወጣ ሁለት ዓመት ቢሆነውም መንግሥት እስካሁን አዲስ መመርያ ሳያወጣ የነዳጅ ኤክሳይስ ታክስና ቫትን እየሰበሰበ ያለው በ2002 ዓ.ም. በወጣው አሠራር ነው፡፡ ይህም የሆነው በነዳጅ ላይ ተጨማሪ የዋጋ ንረት እንዳይከሰት በመሠጋቱ መሆኑን ኃላፊው አስረድተዋል፡፡
አሁንም ይህ አሠራር እንዲቀጥል ሐሳብ መቅረቡን የሚስረዱት ኃላፊው፣ አሁን ባለው አሠራር ከእነዚህ ግብር ገቢዎች በወር ሦስት ቢሊዮን ብር ገደማ የሚሰበሰብ በመሆኑ ለድጎማው ከሚያስፈልገው ገንዘብ ጋር ሊመጣጠን እንደሚችለ ገልጸዋል፡፡
ሐምሌ 1 ቀን 2014 ዓ.ም. ድጎማው መነሳት ሲጀምር የነዳጅ ዋጋ ስንት ብር ይሆናል? የሚለውን ለመተመን ይህ ውሳኔ እንደሚጠበቅ አስረድተዋል፡፡
መንግሥት ለግል መኪኖች የሚያደርገውን የነዳጅ ድጎማ የማንሳት ሒደት ሐምሌ ወር ላይ ጀምሮ በየሩብ ዓመቱ እየከለሰ በአንድ ዓመት ውስጥ ለማጠናቀቅ አቅዷል፡፡ የድጎማ ተጠቃሚ እንዲሆኑ የተለዩ የሕዝብ ማጓጓዣ ተሽከርካሪዎች በአንፃሩ የሚደረግላቸው ድጎማ ሙሉ ለሙሉ ሳይነሳ ለአምስት ዓመታት ይቆያሉ፡፡