የፀጥታ ኃይሎች ሕይወት ሊያጠፉ ከሚችሉ ኢተመጣጣኝ ከሆነ የኃይል ዕርምጃ እንዲቆጠቡ፣ የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) ጠየቀ፡፡ ተቋሙ በፀጥታ ኃይሎች የሚፈጸሙ ሕገወጥ ድርጊቶችን በአስቸኳይ በማጣራት ተጠያቂነትን ማረጋገጥ ይገባል ሲል በመግለጫው ጠይቋል፡፡
የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ጉባዔ (ኢሰመጉ)ም በተመሳሳይ ሁኔታ ባወጣው መግለጫ የፀጥታ ኃይሎች ሕግን ያልተከተለ ዕርምጃ በአስቸኳይ መፍትሔ እንዲፈለግለት ጠይቋል፡፡ ተቋሙ እየተደጋገመ መጥቷል ያለው የፀጥታ አስከባሪዎች የሕግ ጥሰት ከሥልጠና ጀምሮ የፀጥታ አካላትን አሠራርና ሕጎችን በመፈተሽ ሊታረም እንደሚገባ አመልክቷል፡፡
ከሰሞኑ በአዲስ አበባ ከተማ በአንድ ተማሪ ላይ በፖሊሶች የደቦ ድብደባ ሲፈጸም የሚያሳይ እንዲሁም በጋምቤላ ከተማ አንድ ወጣት በፀጥታ ኃይሎች በደቦ ተኩስ ሲገደል የሚታይበት ቪዲዮዎች መሠራጨታቸውን ተከትሎ የፀጥታ ኃይሎች የኃይል ዕርምጃ አሳሳቢ መሆኑ እየተገለጸ ነው፡፡
የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን በደቦ ድብደባው የተጠረጠሩ አራት የፖሊስ አባላትን በቁጥጥር ሥር አውሎ እየመረመረ መሆኑን ያስታወቀ ሲሆን፣ የጋምቤላ ክልል ባለሥልጣናትም በደቦ የተኩስ ግድያው የተጠረጠሩ ሁለት የፀጥታ ኃይሎችን ማሰራቸውን ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡
በሁለቱ ክስተቶች ላይ መግለጫ የሰጠው የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) ከሕግ አግባብ ውጪ በፀጥታ ኃይሎች የሚፈጸሙ ያልተመጣጠኑ የኃይል ዕርምጃዎች ሊቆሙ እንደሚገባ አመልክቷል፡፡ ለሪፖርተር አስተያየታቸውን የሰጡት የኮሚሽኑ ምክትል ኮሚሽነር ራኬብ መሰለ የጋምቤላ ክልል ባለሥልጣናትም ሆኑ የአዲስ አበባ ፖሊስ በተጠርጣሪዎች ላይ ዕርምጃ መውሰዳቸውን በበጎ እንደሚመለከቱት ተናግረዋል፡፡
‹‹በቀጣይ የዕርምጃውን የፍርድ ሒደት የምንከታተለው ይሆናል፡፡ ሆኖም ከጋምቤላ ባለሥልጣናት በተነገረው ብቻ ሳይሆን በክልሉ ስላለው የፀጥታ አለመረጋጋት ተደጋጋሚ ሪፖርቶች እየመጡልን በመሆኑ በቅርበት እየተከታተልነው እንገኛለን፤›› በማለት የተናገሩት ኮሚሽነሯ በሕግ ማስከበር ሥራ ወቅት ለሰብዓዊ መብቶች ጥበቃ ተገቢው ትኩረት እንዲሰጥ ኮሚሽናቸው ማሳሰቡን ጠቅሰዋል፡፡
ስለሁለቱ ክስተቶች የተጠየቁት የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ጉባዔ (ኢሰመጉ) ዋና ዳይሬክተር አቶ ዳን ይርጋ በበኩላቸው የፀጥታ አካላትን በጥልቀት የሚፈትሽ ዕርምጃ እንዲወሰድ ጠይቀዋል፡፡
‹‹በፀጥታ አካላት ሕገወጥ ዕርምጃ ላይ መግለጫ እያወጣን ነው፡፡ ሆኖም ችግሩ እየተደጋገመ ሲሆን በጋምቤላ አሰቃቂ ግድያ እንዲሁም በአዲስ አበባ ከባድ ድብደባ በፖሊሶች ሲፈጸም እያየን ነው፡፡ በሕገወጥ ድርጊቱ የተሳተፉ የፀጥታ ኃይሎችን ተጠያቂ ከማድረግ ባለፈ ከሥልጠናና ትምህርቱ ጀምሮ አሠራሮችን ጨምሮ ችግሩ ሊፈተሽ ይገባል፤›› በማለት አቶ ዳን ተናግረዋል፡፡
የኢሰመጉ ዋና ዳይሬክተር ከዚሁ ጋር አያይዘው ‹‹የፀጥታ አካላት ሪፎርም ተደርገው ተለውጠዋል በሚባልበት በዚህ ወቅት የፀጥታ ሰዎች ሕገወጥነት ተደጋግሞ እየታየ ነውና ሪፎርሙ በተጨባጭ ቢፈተሽ፤›› ሲሉም አስተያየት ሰጥተዋል፡፡ የፀጥታ አካላት ሁሉም በጅምላ አጥፊዎች መባል እንደሌለባቸው ያሰመሩበት አቶ ዳን ሆኖም የመብት ጥሰት የሚፈጽሙ ጥቂት የፀጥታ ኃይሎች የተቋማቱን መልካም ገጽታ እንደሚያጠለሹ ነው የተናገሩት፡፡