Thursday, February 29, 2024

ጠቅላይ ሚኒስትሩ በፍትሕ ተቋማትና በዳኞች ላይ ለሰነዘሩት ‹‹ያልተገባ ንግግር›› ማስተካከያ እንዲያደርጉ ተጠየቀ

- Advertisement -spot_img

በብዛት የተነበቡ

ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) ባለፈው ሳምንት በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ለቀረቡላቸው ጥያቄዎች በሰጡ ማብራሪያ፣ ‹‹አንደኛ ደረጃ ሌባ ዳኞች ናቸው›› በማለት ላደረጉት ንግግር ማስተካከያ እንዲያደርጉ ተጠየቀ፡፡ ጥያቄውን ያቀረበው የአማራ ክልል የዳኞች ማኅበር ነው፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ማክሰኞ ሰኔ  7 ቀን 2014 ዓ.ም ለፓርላማ ቀርበው ሌብነትን በተመለከተ ባደረጉት ንግግር፣ ‹‹አንደኛ ሌቦች ዳኞች ናቸው፣ ዋነኛ ሪፎርም የሚስፈልገው ፍርድ ቤት ላይ ነው፣ የሌቦች መናኸሪያ ሆኗል፡፡ ብዙ መረጃ የተገኘባቸው የሚያላግጡ ዳኞች አሉ፤›› ብለው ነበር፡፡

በመሆኑም በፍርድ ቤቶች ላይ ከፍተኛ የሆነ ለውጥ እንደሚያስፈልግ በመግለጽ፣ ፓርላማው በበላይነት ይዞት ለውጡን መፈጸም እንደሚገባ መናገራቸው ይታወሳል፡፡

በሌላ በኩል ጠቅላይ ሚኒስትሩ ሁለተኛ ሌቦች ያሏቸው ዓቃቤ ሕጎች ሲሆኑ፣ ‹‹ሕግ ያቅድልናል ያልነው ዓቃቤ ሕግ ሌባ መሆኑና ብር እየወሰደ መከራከር በሚገባው ልክ እየተከራከረ አይደለም፤›› በማለት የተናገሩት ዓብይ (ዶ/ር)፣ ‹‹ይህ የእኛ ጉዳይ በመሆኑ እኛ የለውጥ ሥራ እንሠራበታለን፤›› ብለው ነበር፡፡

በጠቅላይ ሚኒስትሩ ማብራሪያ በሦስተኛና በአራተኛ ደረጃ የተቀመጡት ሌቦች ፖሊስና ኦዲተሮች ሲሆኑ፣ ኦዲተር የተሰረቀ ብር አምጣ ተብሎ ተልኮ፣ ኦዲት ግኝት ይገኝብሃል በሚል ማስፈራሪያ ገንዘብ እንደሚቀበል ለምክር ቤቱ ተናግረዋል፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ ‹‹ሌብነት የሚያስቀረው ኃይል ሁሉ ነው አደገኛ እየሆነ ያለው፡፡ ስለዚህ ብር ማግኛ መንገዱ ወደ እነዚህ ተቋማትና ወደ ፀረ ሙስና ተቋም መግባት ሆኗል፡፡ እነዚህ ተቋማት ሌብነትን የሚያጠፉ ሳይሆኑ ሌብነትን የሚያስፋፉ ሆነዋል፤›› ሲሉ ወቀሳ አዘል ንግግር አድርገው ነበር፡፡

የጠቅላይ ሚኒስትሩን ንግግር በተመለከተ ሐሙስ ሰኔ 9 ቀን 2014 ዓ.ም. አመሻሽ ላይ የአማራ ክልል ዳኞች ማኅበር ባወጣው መግለጫ፣ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ሁሉም የፍርድ ቤት ዳኞች ሌቦች እንደሆኑ አድርገው በመናገራቸው ማብራሪያ እንዲሰጡበት ጠይቋል፡፡

ማኅበሩ ፍርድ ቤቶች ነፃና ገለልተኛ ሆነው ሥራቸውን እንዲሠሩ ከማስቻል ጀምሮ፣ ሥነ ምግባራቸውን ጠብቀው በማይሠሩ ዳኞች ላይ የተጠያቂነት አሠራር እንዲኖር ለማድረግ መንግሥት እየሠራ መሆኑ የሚታወቅ ቢሆንም፣ በፍርድ ቤቶች ውስጥ ባልተገባ መንገድ ፍትሕን የሚያዛቡ ውስን ዳኞች መኖራቸው የሚካድ አለመሆኑን ገልጿል፡፡

የአማራ ክልል ዳኞች ማኅበር እነዚህን ውስን ዳኞች በመለየትና ማስረጃ መሠረት በማድረግ ተጠያቂ እንዲሆኑ፣ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በመተባበር እየሠራ እንደሆነ አስታውቋል፡፡

ሙያዊ ሥነ ምግባራቸውን ጠብቀው በታማኝነትና በቅንነት ሙሉ ጊዜቸውን መስዋዕት በማድረግ ሌሊትና ቀን ኅብረተሰቡን ለማገልገል የሚሠሩ በርካታ ምሥጉን ዳኞች እንዳሉም አስረድቷል፡፡

ይሁን እንጂ ጠቅላይ ሚኒስትሩ በፓርላማ ባደረጉት ንግግራቸው በውስን ዳኞች ላይ የሚታየውን የሌብነት ድርጊት ለይተው መግለጽ ሲገባቸው፣ በታማኝነት የሚሠሩትን በርካታ ዳኞችን ጭምር በአንድ ቋት ውስጥ በማጠቃለል ዳኞች በአገሪቱ ውስጥ አንደኛ ደረጃ ሌቦች እንደሆኑ አድርገው ለምክር ቤቱ አባላትና በቴሌቪዥን በቀጥታ ለሚመለከተው የኢትዮጵያ ሕዝብ በይፋ መግለጻቸው፣ በዳኞችና በዳኝነት ተቋሙ ላይ የሚፈጥረውን አሉታዊ ተፅዕኖ ከግንዛቤ ያላስገባ መሆኑን ማኅበሩ አስታውቋል፡፡

በተለይም ዳኞች በአገሪቱ ካለው የሙስና ድርጊት ውስጥ የመጀመርያ ደረጃ እንደሆኑ ተደርጎ የተሰጠው ማብራሪያ ልዩ ጥናትና ማስረጃን የሚጠይቅ ከመሆኑ አንፃር፣ ፍረጃው ተገቢ አለመሆኑን ማኅበሩ በመግለጫው አስታውቋል፡፡

በተመሳሳይ የጠቅላይ ሚኒስትሩ ንግግር ከፍርድ ቤቶች ተፈጥሯዊ ባህሪ አንፃር በኅብረተሰቡ ዘንድ ያለውን አመኔታ የሚያሳጣና ገጽታን የሚያበላሽ፣ ንፁህና ምሥጉን ዳኞችንና ቤተሰቦቻቸውን የሚያሸማቅቅና ሞራላቸውን የሚነካ፣ የውጭ ኢንቨስተሮችም ሆኑ ባለሀብቶች በአገሪቱ የሚተማመኑበት የዳኝነት አካል መኖሩን አምነው መዋዕለ ንዋያቸውን በልማት ላይ እንዳያፈሱ አሉታዊ ተፅዕኖ እንደሚፈጥር ማኅበሩ አስገንዝቧል፡፡

የጠቅላይ ሚኒስትሩ ንግግር የክልሉን ዳኞችና ፍርድ ቤቶች ያሉበትን ሁኔታ ያላገናዘበና የንግግራቸው ይዘትም ለኅብረተሰቡ ያልተገባ ትርጉም የሚሰጥ መሆኑን ማኅበሩ እንደሚገነዘብ በመግለጽ፣ የክልሉ ዳኞች በተደረገው ንግግር ባለመታወክ የተጣለባቸውን ኃላፊነት በቅንነትና በታማኝነት እንዲያከናውኑና ጠቅላይ ሚኒስትሩም ለንግገራቸው የማስተካከያ ገለጻ እንዲያደርጉ ጠይቋል፡፡

የአማራ ክልል በፍትሕ ቢሮ ኃላፊ ማዕረግ የፕሬዚዳንቱ ዋና የሕግ አማካሪ አቶ መርሐ ጽድቅ መኮንን ለሪፖርተር እንደተናገሩት፣ የጠቅላይ ሚኒስትሩ ንግግር ዓውድ ሲታይ በፍትሕ ሥርዓቱ ላይ ያለቸውን ሥጋት ለመግለጽ እንጂ አንድ ተቋም ለመጉዳት ያለመ ነው ብሎ መውሰድ አይቻልም፡፡

‹‹ይሁን እንጂ ንግግሩ ስሜት የሚያነሳሳ ከመሆኑም በላይ ለጠቅላይ ሚኒስትሩ በጅምላ አንደኛ፣ ሁለተኛ እያሉ መፈረጅ በፖለቲካ ዕይታ ብዙ ትርጉም ላይሰጣቸው ይችል ይሆናል፡፡ ነገር ግን ይህ መልዕክት በቀጥታ የቴሌቪዥን ሥርጭት ለሕዝብ የተላለፈ በመሆኑ፣ ሕዝቡ አሁን ለፍርድ ቤቶች ካለው የተበለሸ ዕይታ አንፃር ንግግሩ ተጨምሮበት ጉዳዩ በጥንቃቄ ካልተያዘ የሚያስተላልፈው መልዕክት አደገኛ ነው፤›› ብለዋል፡፡

አቶ መርሐ ጽድቅ ችግሩን ማረም ካስፈለገ የሚጠረጠሩ አካላትንና የተቋማትን መሪዎችን በአግባቡ ጠርቶና በመድረክ አወያይቶ እንዴት እንደሚፈታ አቅጣጫ መስጠት የተሻለ እንደሚሆን፣ በቀጥታ ሥርጭት በዚህ ደረጃ መላው ሕዝብ በሚከታተለው ፕሮግራም መቅረቡ ችግሩን የበለጠ እንደሚያወሳስባው ተናግረዋል፡፡ ነገር ግን በአደባባይ በጅምላ ሌቦች ብለው ስለጠሩና ስላስቀየሙ ችግሩ የሚፈታ አለመሆኑን አስረድተዋል፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ንግግራቸው ብርቱ ጥንቃቄ የተሞላበት፣ ብዘዎችን የማያስቀይምና ‹‹መርዛማነት›› ሳይኖረው መልዕክታቸውን ማስተላለፍ ነበረባቸውም ብለዋል፡፡ ነገር ግን አሁንም በቀጣይ መፍትሔ የሚሆነውና ችግሩን ማቅለል ንግግራቸውን ሊያስተባብልና ጉዳዩን ሊያለሰልስ የሚችል ንግግር እንደሚስፈልግ አቶ መርሐ ጽድቅ ተናግረዋል፡፡

የፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ፕሬዚዳንት አቶ ብርሃነ መስቀል ዋጋሪና የአማራ ክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዚዳንት አቶ አብዬ ካሳሁን ስለጉዳዩ ሪፖርተር ማብራሪያ ጠይቋቸው፣ በጉዳዩ ላይ ማብራሪያ ለመስጠት ፈቃደኛ አልሆኑም፡፡

በተመሳሳይ የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ምክትል ፕሬዚዳንት አቶ ሰሎሞን አረዳና የፌዴራል የመጀመርያ ደረጃ ፍርድ ቤት ምክትል ፕሬዚዳንት ተስፋዬ ንዋይ በተደጋጋሚ ቢደወልላቸውም ማብራሪያ ለመስጠት ፈቃደኛ አልሆኑም፡፡

spot_img
- Advertisement -

ትኩስ ጽሑፎች

ተዛማጅ ጽሑፎች

- Advertisement -
- Advertisement -