ከመንገድ ተጠልፋ…በጠላት ብትወድቅም..
ጀርባዋን ተገርፋ…ሰንበር ብታተርፍም…
በመከራ ታማ…የማትድን ብትመስልም…
አገር ሙሽራ ነች…ውበቷ የሚጎላ
እንደቀድሞው አምራ…ደስታን የምትሞላ
ሰንሰለት በጥሳ…ድል አርጋ የምትመጣ
ታዳሚን አክባሪ…ደምቃ የምትወጣ::
በረሃብ በድካም…በስቃይ ብታልፍም
ሃዘኗ አይሎ….እንባ ብታፈሰም
ብርታት ማሸነፍን …በልቧ የከተበች
ተስፋ የማትቆርጥ….አገር ሙሽራ ነች::
ከትልቁ ድንኳን …ብርሃን ከሞላው
ሃር ከለበሰው ….የሚለይ ከሌላው
ከድግሱ ስፍራ …ሲደርስ ሰርገኛው
እንደ እንቁ አምራ …የምታልፍ ታጅባ
አገር ሙሽራ ነች….በድል የምትገባ::
- ሳምሶን ጌትነት