- በአገሪቱ የተከሰተውን ኢንፍሌሽንና ተስፋ ሰጪ ተግባራት አስመልክቶ ለምናቀርቀበው ሪፖርት ምን ቢካተት ጥሩ ይመስልሃል?
- ክቡር ሚኒስትር ተሰፋ ሰጪ ተግባራት የሚለው እንኳ የሚያስኬድ አይመስለኝም።
- ለምን?
- ክቡር ሚኒስትር ችግሩ ኢንፍሌሽን ብቻ ተብሎ የሚገለጽ አይመስለኝም፣ ከዚያም በላይ እየሄደ ነው።
- በግጭቶች የሚፈጠረውን ኢንፍሌሽን ተወውና በኢኮኖሚያዊ ምክንያት የተከሰተው ኢንፍሌሽን አሁን ያለበት ደረጃና ተስፋ ሰጪ ተግባሮቻችን ላይ እናተኩር።
- የገጠመን አስቸጋሪ ኢንፍሌሽን መሠረታዊ ምክንያት ግጭት አይደለም ክቡር ሚኒስትር።
- ስለእሱ አልጠየኩህም፣ ኢንፍሌሽኑ አሁን ያለበት ደረጃና ተስፋ ሰጪ ተግባሮቻችን ላይ እንድታተኩር ነው የጠየኩህ፡፡
- እኔም እሱን ነው ለማንሳት የሞከርኩት ክቡር ሚኒስትር።
- ወደ ግጭት ሳትገባ ቀጥል።
- ክቡር ሚኒስትር የገጠመን ኢንፍሌሽን ወደ ስታግፍሌሽን (stagflation) ደረጃ እየተሸጋገረ እንደሆነ ግልጽ ነው።
- ምንድነው ደግሞ እሱ?
- ስታግፍሌሽን?
- እ…
- የኢኮኖሚ ዕድገት ማሽቆልቆል፣ የሥራ አጥነት መስፋፋትና ኢንፍሌሽን በአንድ ላይ አንድ ኢኮኖሚ ውስጥ መከሰታቸውን የሚያመለክት ነው።
- ጤነኛ አይደለህም?
- አጠፋሁ ክቡር ሚኒስትር?
- በጎ በጎውን ጠየቅኩህ እንጂ እንጥቀስ ከተባለማ ብዙ መጥቀስ ይቻላል።
- ኢኮኖሚው ውስጥ የተከሰተው ይኼ ነው፣ ከዚህ ሌላ ምን ልንጠቅስ እንችላለን?
- ሸኔስ? እሱ ችግር አይደለም? ስታግፍሌሽን ያልከው ላይ ሸኔ ቢጨመርበት ምን ሊባል ነው?
- እሱ ኢኮኖሚያዊ ምክንያት አይደለም ብዬ ነው ክቡር ሚኒስትር፡፡
- ለዚህ እኮ ነው በጎ በጎውን፣ ተስፋ ሰጪውን እናንሳ የምልህ፡፡
- ተስፋ ሰጪ ለማለት የሚያስችለን ነገር ያለ አይመስለኝም ክቡር ሚኒስትር፡፡
- አማካሪ ስትባሉ ጨለማ ብቻ ነው እንጂ የሚታያችሁ፣ የእንትን ዋጋ እንዳሽቆለቆለ መጥቀስ አይቻልም?
- የምን?
- የእንቁላል…
- እሱማ የዶሮ በሽታ በመከሰቱ የተፈጠረ የዋጋ ቅናሽ ነው።
- ቢሆንስ? በእንቁላል ዋጋ ላይ ቅናሽ አልታየም?
- እሱማ ከፍተኛ የዋጋ ቅናሽ ታይቷል።
- በል ተስፋ ሰጪ ተግባራት በልና ያዝልኝ።
[የአረንጓዴ አሻራ ፕሮግራም ላይ የዋሉት ክቡር ሚኒስትሩ ወደ መኖሪያ ቤታቸው ሲገቡ በጭቃ የተለወሰ ጫማቸውን የተመለከቱት ባለቤታቸው ግራ ተጋብተው ምን እንደተፈጠረ መጠየቅ ጀመሩ]
- ምን ገጥሞህ ነው? ምንድነው?
- ምኑ?
- ጫማህን አላየኸውም?
- ምን ሆነ?
- እንዴ ሱሪህም እኮ በጭካ ተለውሷል፡፡
- እ… ስንበረከክ የነካኝ…
- ለምንድነው የምትንበረከከው?
- ዛሬ የካቢኔ አባላት በሙሉ በአለቃ ፕሮግራም ላይ ነበር የዋልነው።
- ፕሮግራሙ የመንበርከክ ነው?
- የአለቃችን የአረንጓዴ አሻራ ፕሮግራም ዛሬ ነበር እኮ።
- ነው እንዴ?
- አዎ፣ ምነው በቴሌቪዥን አልተላለፈም እንዴ?
- ገና ችግኝ ማሳየት ሲጀምር ተናድጄ ዘጋሁት።
- ምነው?
- ሕዝቡ በስንት ነገር እየተማረረ እናንተም ቴሌቪዥኑም ቅድሚያ የምትሰጡትን ነገር ማየት ሕመሜን ይቀሰቅስብኛል።
- እንዴት?
- ምን እንዴት አለው? ንፁኃን ዜጎች በየከተማውና በየመንደሩ ሲገደሉ ዝም ያለ ቴሌቪዥን በሙሉ፣ እናንተ ችግኝ ስትተክሉ ተዓምር ይመስል በቀጥታ ያስተላልፋል።
- ገብቶኛል፣ ግን ምን ይደረግ በቅድሚያ የተያዘ ፕሮግራም ነው።
- ቢሆንስ? ከ400 በላይ ንፁኃን በግፍ ተገድለው ምንም እንዳልተፈጠረ እንዴት ዝም ይባላል?
- ምን ማድረግ ነበረብን? መንግሥት በደረሰው ጉዳት ሐዘን እንደተሰማው ወዲያውኑ ገልጿል።
- አልገለጸም፣ የት ነው የገለጸው?
- አለቃም ሆኑ ሌሎቻችን በማኅበራዊ ትስስር ገጾቻችን የተሰማንን ሐዘን ገልጸናል።
- በማኅበራዊ ትስስር ገጽ? ብሔራዊ ቴሌቪዥን ጣቢያ እያለ?
- ዋናው ተደራሽነት ነው።
- እንዴት? ምን ማለትህ ነው?
- የእኛን ያህል በተለይም የአለቃን የሚያህል ተከታይ ያለው የማኅበራዊ ትስስር ገጽ በኢትዮጵያ የለም።
- ይሁን… ግን እንዴት ፓርላማው እንኳን ለአንድ ቀን ብሔራዊ ሐዘን አያውጅም?
- ተቃዋሚ ፓርቲዎች ሞክረው እንደነበር ሰምቻለሁ፡፡
- ምንድነው የሞከሩት?
- ፓርላማው የሐዘን ቀን እንዲያውጅ መሰለኝ፡፡
- እንዴት ሰማህ? ችግኝ ተከላ ላይ ነበርኩ አላልክም እንዴ?
- ቢሆንም የሚፈጠረውን እንሰማለን።
- እሺ… እና የሐዘን ቀን ታወጀ?
- እንዴት ይታወጃል? አልታወጀም፣ ጭራሽ የመጠየቅ ዕድል አልተሰጣቸውም።
- ዕድል እንዳያገኙ ትዕዛዙን ያስተላለፋችሁት እናንተ ናችሁ ማለት ነዋ?
- ችግኝ ተከላ ላይ ነበርን እያልኩሽ? በየት በኩል እናስተላልፋለን?
- እኛን የሚያህል የማኅበራዊ ሚዲያ ተከታይ ያለው የለም ስትል አልነበር እንዴ?
- ብልስ… እንዴት አድርገን ትዕዛዝ እናስተላልፋለን?
- በኢንቦክስ ነዋ፡፡
- አንቺ ደግሞ… እስኪ ተይኝ፡፡
- ሳስበው ግን ትክክል ነው።
- ምኑ?
- ፓርላማው የሐዘን ቀን አለማወጁ ትክክል ይመስለኛል።
- እንዴት እንደዚያ አልሽ?
- አንዴ ከጀመረ በየሳምንቱ የሐዘን ቀን ማወጅ ሊሆን ነዋ ሥራው።
- ለምን እንዲህ እንደምትብከነከኚ ሳልረዳ ቀርቼ መስሎሽ ነው? እረዳሻለሁ፡፡
- አይመስለኝም፡፡
- እረዳሻለሁ፣ የንፁኃን ዜጎች ሕይወት በየጊዜው መቀጠፉ እንዳሳሰበሽ እረዳለሁ። ግን እመኚኝ፣ አረጋግጥልሻለሁ፡፡
- ምኑን?
- ምንም ቢሆን ኢትዮጵያ አትፈርስም፣ ይህንን አረጋግጥልሻለሁ!