Monday, December 4, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -

የተመረጡ ፅሑፎች

የደስታ ምንጭ!

እነሆ መንገድ! ከመገናኛ ወደ ሲኤምሲ ልናቀና ነው። የቀናው ከድካሙ ሊያርፍ ያላለለት የነገ ዕድሉን ሊሞክር ተስፋውን ሩቅ ጥሎ ወደ ቤቱ ሊገባ ይጣደፋል። ተማሪው፣ ሠራተኛው፣ ወዲያ ወዲህ የሚለው ሳይቀር መንገዱን ሞልቶታል። ለትራንስፖርት ጥበቃ ብዙኃኑ የሠልፍ አጥር ሠርተው ቆመዋል። ከሠልፈኞች መሀል አንዳንዱ ይነጫነጫል፡፡ አንዳንዱ ደግሞ በዝምታ ያለፈውን፣ ያለውንና የሚመጣውን ሊታዘብ ቆሟል። ‹‹እኔማ እግሬ በሽተኛ ሊሆን ምንም አልቀረው!›› ትላለች አንዲት ተሠላፊ። ከእሷ ቀጥላ የተሠለፈች ሌላ እንስት ስታሽሟጥጣት እናያለን። ‹‹ለእሷ ብቻ ነው እንዴ ሠልፍ? በእሷ ብቻ የመጣ ይመስል ለብቻዋ ምን ያማርራታል?›› ትላለች አፏን አጣማ ጆሮዋን ልታስነካው ምንም አይቀራት። ከአሽሟጣጯ ጀርባ የላፕቶፕ ቦርሳ ያነገተ ወጣት፣ ‹‹ሕመሟን የምታውቀው እሷ ናት…›› ይላታል ‘አንቺ ምን ቤት ነሽ?’ በሚመስል አስተያየት። እንዲያ ነው!

‹‹ቢሆንስ እኛን አያመንም? ቆመን ባለንበት ሳንንቀሳቀስ መኖራችን ተረሳና ነው አሁን እንደ ተዓምር የሚወራው? የወሬ ሱስ ይዞን ነው እንጂ። ሌላው ቀርቶ የአንድ ትውልድ ዕድሜ ብቻ ተጉዘን ቢሆን እንኳ እንዲህ ያለፋን ነበር?›› እያለች ነገር ማያያዝ ስትጀምር፣ ‹‹አቦ ነገር አታክሪ በላት፣ የምን ፖለቲካ መደንጎር ነው ታክሲ እየጠበቅን…›› ሲል ራቅ ብሎ የቆመ ወጣት ጮኸ። ነገሩን ያልሰማ ከመጀመሪያውም ያልነበረበት ምን ተፈጠረ እያለ እርስ በርሱ ይገለማመጥ ጀመር። ወዲያው የሚጭነን ታክሲ ከተፍ እንዳለ ተረኞች ሥርዓት ባለው ‘ዴሞክራሲያዊ ዕድላችን’ ገብተን ሞላነው። ጋቢና ያ የላፕቶፕ ቦርሳ ያነገተ ወጣትና መነጽር ያደረገ ጎልማሳ ተሰይመዋል። ከሾፌሩ ጀርባ ሳይተዋወቁ በነገር መተጋተግ የጀመሩት እንስቶች አሉ። ቀጥሎ እኔና የደስ ደስ ያላቸው አንዲት አዛውንት ተቀምጠናል። ከጀርባችን ሁለት ወጣት ወንድማማቾች፣ መጨረሻ ወንበር ላይ ደግሞ አራት የሁለተኛ ደረጃ እንስት ተማሪዎች ተሳፍረዋል። ጉዟችን ተጀምሯል። ዕድሜ ካለ መንጎድ ነው!

ጉዟችን ከመጀመሩ ወያላችን ‘ሒሳብ አምጡ’ እያለ ያፋጥጠን ይዟል። ‹‹ምናለበት ከገባሁ በኋላ ሒሳብ ብትቀበል? ደርሰህ ትጉህ ለመምሰል አትሞክር…›› ዕድሜያቸው አንቱ የሚያስብላቸው ሾፌራችን በወያላው ይማረራሉ። ወያላው ጭቅጭቅ እንደሰለቸው ሁሉ እጁን እያወናጨፈ በመስኮት አንገቱን አውጥቶ መኪና ያስቆምላቸው ያዘ። ‹‹ገንዘቡ የት ይሄድበታል? አውቆ ሰው ለማደናገር ስለሚፈልግ ብቻ የምነግረውን አይሰማም። አቤት የዘንድሮ ልጆች ከሚሰሙት የማይሰሙት፣ ከሚያለሙት የሚያጠፉት እኮ ነው የሚብሰው፡፡ ይብላኝ ለዚህች አገር እንጂ እኔስ እስከ ዛሬ የኖርኩት በቂዬ ነው…›› እያሉ በዝግታ መስመራቸውን ይዘው ማሽከርከር እንደ ጀመሩ ወያላው ተመልሶ ሒሳቡን መቀበል ቀጠለ። አጠገቤ የተቀመጡት አዛውንት ሴት፣ ‹‹እውነታቸውን እኮ ነው፣ የዘንድሮ ልጆች መቼ የሚሏቸውን ይሰማሉ? አይሰሙም እኮ…›› እየጎሸሙ በግድ ታሪካቸውን ይነግሩኛል። መቀባበል ነው!

‹‹…ይኼው የእኔን ጉድ ልንገርህ። የዩኒቨርሲቲ ትምህርቱን ጨርሶ ከቀበሌ ቤት ያወጣኛል ያልኩት ልጄ፣ እንደ ሰው (የገዛ ተፎካካሪዎቻቸውን ስም ጠርተው) ቢቻል ቪላ ውስጥ ካልሆነ ኮንዶሚኒየም ያኖረኛል ስል ተመርቆ መጥቶ ልትወድቅ አንድ ማገር የቀራት ቤት ውስጥ ተቀመጠ። ምን ትለዋለህ? ንገረኝ እንጂ፣ ‘ምን ሆነህ ነው? ባሳደግኩ ባስተማርኩ’ ስለው ምን እንዳለኝ ታውቃለህ? ተወው ይቅር፡፡ የትናንቶችም የዛሬዎቹም ልጆች አንድ ናችሁ። ማማት ትወዳላችሁ። መንግሥትን ማማት። ወላጅን ማማት፡፡ አገርን ማማት፡፡ ተወው ይቅር ልጄ…›› እንደ መብሰልሰል እያደረጋቸው በሐሳብ ፈረጠጡ። ከሄዱበት ሲመለሱ ቀና ብለው እያዩኝ፣ ‹‹መፈጠሩን አምኖ መቀበል ያቃተው፣ ራሱን ማወቅ ምጥ የሆነበትን ‘ሥራ ፍጠር’ የሚሉት ነገር ምን ይባላል? ሰው እኮ መጀመሪያ ራሱን እንደ ተፈጣሪ መቀበል አለበት። እህ? ይህ ሁሉ አማራሪ ቢሰደድ ምን ይገርማል?›› ብለው ዝም አሉ። የጥያቄዎቻቸው ብዛት ከዕድሜያቸው እኩል አዳክሟቸው ይታያል። መንገድ የማሳየን የብሶት ገጽ ምን አለ!

ወያላው ገንዘቡን ሰብስቦ ጨርሷል። ጉርድ ሾላን እያለፍን ነው። ጠንቃቃው አዛውንት ሾፌራችን የአብዛኞቹ ሞገደኛ አሽከርካሪዎች አነዳድ እያበሳጫቸው በተደጋጋሚ ‘እዩት ይኼን፣ እዩዋት ያቺን’ ይላሉ። አጠገባቸው የተቀመጡት ተሳፋሪዎች ያረጋጉዋቸዋል። ‹‹እርስዎ በራስዎ አነዳድ ብቻ ነው መተማመን ያለብዎት። ሰው እንደሆነ ቀልብ የለውም…›› ሲላቸው አንደኛው ጎልማሳ ጎኑ የተሰየመው ወጣት ቀበል አድርጎ፣ ‹‹ኑሮን እያየኸው? ሮጠንም አልሞላልን…›› ይላል። ‹‹ቆይ! ቆይ! ሮጠንም አልሞላልንም ማለት ምንድነው? ለመሆኑ ማነው የሚሮጠው? ጥቂቶች?›› አዛውንቱ ከያዙ የሚለቁ ዓይነት አይመስሉም። ‹‹ኧረ እኔ እዚያ ውስጥ አልገባሁም…›› መለሰላቸው ወጣቱ። ‹‹ይኼውላችን ያገሬን ሰው። የማይታፈረውን እያፈርን የማይከበረውን እያከበርን እስከ መቼ ነው የምንዘልቀው? ጨዋ በእውነት አይሸሽም…›› እንደ ማፈር ብሎ አዳመጣቸው። የግድ ነው!

ጉዟችን ቀጥሏል። መጨረሻ ወንበር ላይ የተቀመጡት የሁለተኛ ደረጃ ተማሪዎች በተራቸው ጨዋታ ጀመሩ። ‹‹እንዴት ያለ ቢራ ፓርቲ እናደርጋለን ይላሉ? አይደብራቸውም?›› ስትል አንደኛዋ፣ ‹‹አይገርምሽም? ቀሽም ብቻ ተሰብስቦ፡፡ ‘ቀለሜዎቹ’ እኮ ናቸው የሚበጠብጡት። በዓመት አሥር ጊዜ በሰበብ አስባቡ መንግሥት ሴሚናር አስለመዳቸውና አሁን በቃ “ቺል” እናድርግ ሲባል የአባላት ስብሰባ ካላደረግነው? ሆ…ሆ…›› አለች ተቀብላ ሌላዋ። ‹‹ኧረ ማን ይሰማቸዋል፣ እኔ በበኩሌ አሥር ጊዜ ተፈጥሬ አሥር ልጅነት ስለማይኖረኝ ‘ዌስት’ የማደርገው ምንም ‘ኤጅ’ ያለኝ እንዳይመስልሽ። ሕዝባችን በገንዘቡ ዓባይን ይገድባል፡፡ እኔ ደግሞ ደሜ ውስጥ ጌሾ እገድባለሁ። እንችላለን ካልን እንችላለን…›› ብላ እጇን ጨብጣ ፎከረች። ወዲያው ሳይሳቀቁ ታክሲውን በሳቅ ሲያደበላልቁት ተሳፋሪዎች በግርምት እያስተዋሉዋቸው የሚያስቡት እንደ ጠፋባቸው ያስታውቁ ነበር። የትውልድ ልዩነት!

ልጃገረዶቹ ታክሲውን አስቁመው ከወረዱ በኋላ ግን ሁሉም እንደተመቸው እየተነሳ ይዘነጥላቸው ያዘ። ‹‹አቤት ጊዜ! አሁን በእነሱ ይፈረዳል? በእኛ ጊዜ ቢሆን እንኳን የሚያውቀን አይደለም ማንስ ቢሆን እንዲህ አፋችንን ስንከፍት ዝም ይለን ነበር?›› ሲል ከኋላችን ከተቀመጡት ወንድማማቾች አንደኛው ጀመረ። የወዲያኛው ተቀብሎ፣ ‹‹ያኔማ ጎረቤትም እንደ ወላጅ ሆኖ እየቀጣ ያሳድግ ነበረ፡፡ አሁን የዘመኑ ወላጅ ራሱ ተንጋዶ አድጎ ነው መሰል ልጅን በሥርዓት ማሳደግ ችላ ብሎታል…›› እያለ ተመረረ፡፡ ሌላው ደግሞ ጣልቃ ገብቶ፣ ‹‹ግለኝነትና ራስ ወዳድነት ጣራ በነኩበት በዚህ ዘመን ስለማኀበራዊ ኃላፊነት መነጋገር በራሱ ወፈፌ ያሰኛል…›› ብሎ ጨመረበት፡፡ አጠገቤ የተቀመጡት አዛውንት ይኼኔ ጣልቃ ገብተው ‹‹አዬ! ያውም ሴት ልጅ በዚህ ዕድሜዋ ስለመጠጥ በአደባባይ ወሽክታ? ወንዱስ ቢሆን እንዴት አድርጎ ለቁም ነገር አስቦ አጭቶ ያገባታል?›› ብለው ለአፍታ አየር ሰበሰቡ፡፡ ከዚያም፣ ‹‹ለካ ምርጫው አንድ ወጥና ጥቂት ተመሳሳዮች የሚሳተፉበት ሆኗል…›› ብለው ዞረው አዩን። የዘመኑ ነገር ከዬት ወዴት ነው የሚላጋው!

ወደ መዳረሻችን ተጠግተናል። ከታክሲያችን የቴፕ ስፒከር ለታላቁ የህዳሴ ግድባችን ግንባታ መፋጠን ስሜት ቀስቃሽ ማስታወቂያ ይደመጣል። ይኼኔ ነበር ጋቢና የተቀመጠው ጎልማሳ ወደ ተሳፋሪዎች ዘወር ብሎ፣ ‹‹ሰማችሁ ለጊዜው ነው እንጂ ለእርስ በእርስ ፀብና ግጭት ጊዜ የለንም፣ የሚያዋጣን መተባበር ብቻ ነው…›› አለ። እኚያ አዛውንት ደግሞ፣ ‹‹ገና ለስንትና ስንት ትውልድ የሚሆን ሥራና ታሪክ እየተሠራ፣ እኛ ባልተያዘና ባልተጨበጠ ነገር፣ በስህተት በተተረጎመ የታሪክ ሐደት፣ በአሉሽ አሉሽ፣ በወሬና በአሉባልታ ልዩነታችንን ማስፋት አለብን? የምን አውሬ መሆን ነው? ይልቅስ ይቅርታ ተባብለን በሰላም አብረን እየኖርን በነፃነት አገር መገንባት እንለማመድ፡፡ አዎ! ከይቅርታ በላይ ምንም ስለሌለ ሰላም እናስፍን፡፡ ሰላም የነፃነትና የደስታ ምንጭ ነው…›› እያሉ ማሳሰቢያ ሲሰጡ፣ ወያላችን ‹‹መጨረሻ!›› ብሎ ወደ ሌላ ጉዞ ተጣደፍን። መልካም ጉዞ!              

Latest Posts

- Advertisement -

ወቅታዊ ፅሑፎች

ትኩስ ዜናዎች ለማግኘት