Friday, June 9, 2023

በምዕራብ ወለጋ ጭፍጨፋ ከ400 በላይ ሰዎች መገደላቸውን የዓይን እማኞች ተናገሩ

- Advertisement -spot_img

በብዛት የተነበቡ

መንግሥት የተገደሉ ሰዎች አጠቃላይ ቁጥር ለማወቅ መረጃ በመሰብሰብ ላይ መሆኑን አስታውቋል

በኦሮሚያ ክልል በምዕራብ ወለጋ ዞን ጊምቢ ወረዳ ቶሌ ቀበሌ ቅዳሜ ሰኔ 11 ቀን 2014 ዓ.ም. በተፈጸመው ጭፈጨፋ የተገደሉ ከ400 በላይ ሰዎች ቀብር መፈጸሙን፣ ሪፖርተር ያነጋገራቸው ሦስት የዓይን እማኞች ተናገሩ፡፡

እማኞቹ ወደ አከባቢው በገቡት የመከላከያ ሠራዊትና የኦሮሚያ ልዩ ኃይል አባላት እጀባ በታጣቂዎች ጥቃት የተገደሉ ሰዎች አስከሬን እየተሰበሰበ በጅምላ ቀብር መፈጸሙን ገልጸው፣ እስከ ማክሰኞ ሰኔ 14 ቀን 2014 ዓ.ም. ምሽት ድረስ ያልተገኙና አስከሬናቸው ያልተነሳ ሰዎች መኖራቸውን አስረድተዋል፡፡

ሪፖርተር ያነጋገራቸው የቶሌ ቀበሌ ነዋሪዎች እንደገለጹት፣ ታጣቂዎች በንፁኃን ላይ ግድያ የፈጸሙት ከጠዋት 2፡30 ሰዓት አከባቢ ጀምሮ ሲሆን፣ ይህ ጥቃት እስከ ቀኑ ማብቂያ እንደቀጠለ ተናግረዋል፡፡ ነዋሪዎቹ የፀጥታ ኃይሎች ወደ ቀበሌው የገቡት ከ11፡00 ሰዓት በኋላ መሆኑንም አክለዋል፡፡

አቶ አህመድ ሀሰን የተባሉ በአከባቢው ለ24 ዓመታት የኖሩ ግለሰብ፣ ታጣቂዎቹ ጥቃቱን የከፈቱት የቀበሌው አባወራዎች ለእርሻ ከአካባቢው ከራቁ በኋላ መሆኑን  አስረድተዋል፡፡ ሌሎቹም ምስክሮች ይህንን ያረጋገጡ ሲሆን፣ ጥቃቱ ከመከፈቱ በፊት በአካባቢው ከበባ ተፈጽሞበት እንደነበር ገልጸዋል፡፡ ምስክሮቹ ጥቃት የፈጸሙት ታጣቂዎች ቁጥር በሺዎች እንደሆነ ገምተዋል፡፡

‹‹ሴትና ልጆችን አንድ ላይ እያጎሩ በ50፣ በ30 እያሠለፉ ነው የረሸኗቸው፤›› ያሉት አቶ አህመድ፣ እርሻ ላይ የነበሩ ወደ ቤታቸው ለመመለስ ቢሞክሩም መንገዱ በመከበቡ በበቆሎ እርሻ ውስጥ መደበቃቸውን ተናግረዋል፡፡

ከጥቃቱ በኋላ አስከሬኖች ተሰብስበው ሲቀበሩ እንደተሳተፉ የገለጹት አቶ አህመድ፣ ‹‹በአንድ ቦታ ብቻ 61 ሰው ቀብሬያለሁ፣ 51 ሕፃናት ከአሥር ዓመት በታች ናቸው፣ ሦስት ደግሞ የአሥር ዓመት፣ አንድ 15 ዓመት ሴት ልጅና የአራት ቀን አራስ ነበሩ፤›› ብለዋል፡፡

ስማቸው እንዳይጠቀስ የጠየቁ ሌላ የዓይን እማኝ በ1991 ዓ.ም. በአከባቢው መኖር ጀምረው ከመሠረቱት ትዳር አሥር ልጆችን እንዳፈሩ ገልጸው፣ አሁን የተረፉት ሁለቱ ብቻ መሆናቸውን አስረድተዋል፡፡ የሁለት ዓመት ልጅን ጨምሮ ስምንት ልጆቻቸው፣ ባለቤታቸው፣ እናትና አባታቸው ጭምር መገደላቸውን ተናግረዋል፡፡ ‹‹የልጅ ልጅም ሞቶብኛል አልቆጠርኩም፣ እነሱን ሳይጨምር ይኼ ሁሉ ሰው ያለቀብኝ፣ ቤት ውስጥ በተሰበሰቡበት ስለጨረሷቸው ነው፤›› ብለዋል፡፡

አቶ መሐመድ የተባሉና ሙሉ ስማቸው እንዳይጠቀስ የጠየቁ ሌላ ነዋሪ በበኩላቸው፣ በቀበሌው ቀላ የተባለ መንደር ውስጥ ታጣቂዎች 12 ሕፃናትና ሴቶችን በአንድ ቤት ውስጥ አጉረው እንዳቃጠሏቸው ተናግረዋል፡፡

የዓይን እማኞቹ እንደገለጹት፣ ታጣቂዎቹ ጥቃቱን ያደረሱት ጥይትና ገጀራ ተጠቅመው ነው፡፡ ሦስቱም ምስክሮች ታጣቂዎቹ ስናይፐር መጠቀማቸውን ሲናገሩ፣ ሁለቱ ዲሽቃ የተባለውን መሣሪያ በመተኮስ ነዋሪዎችን መግደላቸውን አክለዋል፡፡

በቀበሌው የተገደሉ ሰዎችን ቁጥር በተመለከተ ትክክለኛው ቁጥር ከሦስቱም እማኞች ባይገኝም፣ ከ400 በላይ እንደሆነ ተናግረዋል፡፡ የአስከሬን ‹‹ለቀማ›› እና ቀብር ላይ መሳተፋቸውን የገለጹት አቶ አህመድ ሀሰን፣ ‹‹መዝግቤ የያዝኩት›› በሚል ያጋሩት የአስከሬኖች ቁጥር ድምር 438  ነው፡፡

አቶ መሐመድ የተባሉት ነዋሪ በቡላቸው፣ ይኼ ቁጥር ሰኞ ሰኔ 13 ቀን 2014 ዓ.ም. ድረስ የተቀበሩት ሰዎች ብዛት እንደሆነ ገልጸው፣ ‹‹እስከዛሬ [ማክሰኞ] ከመከላከያ ጋር አስከሬን ስናነሳ ነው የዋልነው፣ 582 እና 583 ላይ ነው የደረስነው፣ ከእሑድ እስከ ዛሬ ድረስ፤›› በማለት ተናግረዋል፡፡ ሦስተኛው የዓይን ምስክር ይህንን ቁጥር ወደ 900 አድርሰውታል፡፡

ሦስቱም ምስክሮች እንደገለጹት፣ ቀብር የተፈጸመው አስከሬኖቹ በተገኙበት አከባቢ ተሰብስቦ በጅምላ ነው፡፡ አቶ መሐመድ፣ ‹‹አስከሬኖችን ጅብና አሞራ ከሚበላቸው ተብሎ በጅምላ ነው የተቀበሩት፡፡ 63 ሰዎች አንድ መቃብር ገብተዋል፤›› በማለት ተናግረዋል፡፡ አቶ አህመድ የተባሉት እማኝ የአንዲት ባልቴት አስከሬን በአውሬ በመበላቱ እንዳልተቀበረ አስረድተዋል፡፡ እስከ ማክሰኞ ድረስ ያልተሰበሰቡና ያልተቀበሩ አስከሬኖች እንዳሉ ሁሉም እማኞች አረጋግጠዋል፡፡

ከጥቃቱ የተረፉ የቶሌ ቀበሌ ነዋሪዎች አሁን ጨቆርሳ፣ አርጆና ሌሎች መንደሮች ተፈናቅለው እንደሚገኙ ተናግረዋል፡፡ ጥቂት ሰዎች ደግሞ በመከላከያ ሠራዊትና በኦሮሚያ ልዩ ኃይል ጥበቃ ተደርጎላቸው በመንደሩ ውስጥ መቅረታቸውን ገልጸዋል፡፡

ቅዳሜ ዕለት በተፈጸመው ጥቃት የተገደሉ ሰዎችን ብዛት ምን ያህል እንደሆነ ከሪፖርተር ጥያቄ የቀረበላቸው የኦሮሚያ ፖሊስ ኮሚሽን ኮሚሽነር አራርሳ መርዳሳ፣ ከጥቃቱ ጋር የተያያዙ መረጃዎችን የሚሰጠው በመንግሥት ኮሙዩኒኬሽን አገልግሎት በኩል መሆኑን ተናግረዋል፡፡

የመንግሥት ኮሙዩኒኬሽን አገልግሎት ሚኒስትር ደኤታዋ ወ/ሮ ሰላማዊት ካሳ በበኩላቸው፣ ‹‹ይፋዊ የሆነ መረጃ ከማውጣታችን በፊት የተጣራ መረጃ ከፀጥታ አካላት መሰብሰብ ስላለብን፣ ይህንን እያደረግ ነው፤›› የሚል ምላሽ ሰጥተዋል፡፡ መረጃው እንደተጠናቀረ በይፋ መግለጫ እንደሚወጣ አስታውቀዋል፡፡

የመንግሥት ኮሙዩኒኬሽን አገልግሎት ሰኞ ሰኔ 13 ቀን 2014 ዓ.ም. ባወጣው መግለጫ፣ የበርካታ ሰዎች ሕይወት መቀጠፉን ከመግለጽ ውጪ ጥቃት የደረሰባቸውን ሰዎች ቁጥር አልጠቀሰም፡፡

‹‹የሸኔ የሽብር ቡድን›› ጥቃቱን እንደፈጸመ ያስታወቀው የአገልግሎት መግለጫ፣ ቡድኑ ይኼንን ጥቃት ያደረሰው በቅርቡ በጋምቤላ፣ በደምቢዶሎና በጊምቢ ከተሞች ላይ የሰነዘራቸው የሽብር ጥቃቶች በፀጥታ ኃይሉ ቅንጅት ሲከሽፍ በበቀል ተነሳስቶ መሆኑን ገልጿል፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) በበኩላቸው፣ ሰኞ ሰኔ 13 ቀን 2014 ዓ.ም. በፌስቡክ ገጻቸው ላይ ባሰፈሩት ጽሑፍ፣ “በንፁኃን ዜጎች ላይ በሕገወጥና በኢመደበኛ ኃይሎች በሚደርስ ጥቃት መተዳደሪያን ማውደም ተቀባይነት የለውም፤›› ብለዋል፡፡ አክለውም በቤኒሻንጉልና በኦሮሚያ ክልሎች ዋና ዓላማቸው ‹‹ኅብረተሰቡን ማሸበር›› የሆኑ አካላት እንዳሉ ገልጸው፣ ‹‹የተፈጸመው የሰው ልጆችን ሕይወት የሚቀጥፍ ዘግናኝ ድርጊት የምንታገሰው አይደለም፤›› ብለዋል፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ማክሰኞ ዕለት በአረንጓዴ አሻራ መርሐ ግብር ማስጀመሪያ ላይ ባደረጉት ንግግር፣ የአገር መከላከያ ሚኒስቴር ከሰኞ ምሽት ጀምሮ ኦፕሬሽን መጀመሩን አስታውቀዋል፡፡

የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳደር ይልቃል ከፋለ (ዶ/ር) ድርጊቱን ‹‹ዘግናኝ ጭፍጨፋ›› በማለት የገለጹት ሲሆን፣ ‹‹[ድርጊቱ] አገራችንን ከአሸባሪዎች ለማፅዳት የጀመርነውን ዘመቻ አጠናክረን ከመቀጠል ውጪ ሌላ አማራጭ እንደሌለን ማሳያ ነው፤›› ብለዋል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ትኩስ ጽሑፎች

ተዛማጅ ጽሑፎች

- Advertisement -
- Advertisement -