Wednesday, September 27, 2023

የወለጋው ጭፍጨፋ በአገር ቤትና በውጭ ውግዘት እየደረሰበት ነው

- Advertisement -spot_img

በብዛት የተነበቡ

በኦሮሚያ ክልል ምዕራብ ወለጋ ጊምቢ ወረዳ ሰኔ 11 ቀን 2014 ዓ.ም. የተፈጸመው የንፁኃን ዜጎች ጭፍጨፋ፣ በአገር ውስጥና በውጪ ውግዘት እየደሰበት ነው፡፡ የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ መሥሪያ ቤትና የኢራን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ድርጊቱ እንዳሳሰባቸው ገልጸዋል፡፡ በአገር ቤት የሚንቀሳቀሱ የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) እና የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ጉባዔ (ኢሰመጉ) ጥቃቱን አስጊ ብለውታል፡፡ የተፎካካሪ ፖለቲካ ፓርቲዎች በበኩላቸው ድርጊቱን አውግዘው መግለጫ አውጥተዋል፡፡

በኦሮሚያ ክልል ‹‹በአማራ ማኅበረሰብ ላይ የደረሰው አሳዛኝ ጥቃት በእጅጉ ያሳስበናል›› ሲል የጀመረው የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ መሥሪያ ቤት ቃል አቀባይ ኔድ ፕራይስ መግለጫ፣ ለተጎጂ ቤተሰቦች መፅናናትን ተመኝቷል፡፡ ‹‹ኢትዮጵያውያን ወደ ሰላም እንዲመጡ እንደግፋለን፤›› ያሉት ቃል አቀባዩ፣ የሰብዓዊ መብት ጥቃት እንዲፈጸም ያደረጉ ተጠያቂ ሊሆኑ እንደሚገባ በመጠየቅ ነው መግለጫቸውን የቋጩት፡፡

የምዕራብ ወለጋውን ጥቃት በተመለከተ መግለጫ ካወጡ አገሮች አንዷ የሆነችው ኢራን በበኩሏ፣ ‹‹በኢትዮጵያ የደረሰውን የሽብር ጥቃት እናወግዛለን›› በማለት ነው በውጪ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባዩ ሳኢድ ሀቲብዛዴ በኩል መግለጫ አውጥቷል፡፡ በምዕራብ ኦሮሚያ በመቶዎች የሚቆጠሩ ንፁኃን ዜጎች መገደላቸው እንዳሳዘናቸው የገለጹት ቃል አቀባዩ፣ ‹‹ኢራን ድርጊቱን አጥብቃ ታወግዛለች›› ማለታቸው በአገሪቱ የዜና ምንጮች በሰፊው ተዘግቧል፡፡

ከዚህ ቀደም በኢትዮጵያ በሚፈጠሩ ጥቃቶችና ግጭቶች ቀድመው መግለጫ ሲያወጡ የቆዩት ሂዩማን ራይትስ ዎችና አምነስቲ ኢንተርናሽናልን የመሳሰሉ የሰብዓዊ መብት ተቋማት ኅትመት እስከገባን ጊዜ ድረስ ያሉት ነገር የለም፡፡ ይሁን እንጂ የአገር ውስጥ የሰብዓዊ መብት ድርጅቶች ግን ‹‹አሳሳቢ›› ሲሉ መግለጫ ሰጥተዋል፡፡

የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) በተለያዩ አካባቢዎች በመንግሥትና በታጠቁ ኃይሎች አማካይነት በንፁኃን ላይ እየተፈጸሙ ያሉ ጥቃቶችን በቅርበት እንደሚከታተል በመግለጫው ይፋ አድርጓል፡፡

የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ጉባዔ (ኢሰመጉ) በበኩሉ በምዕራብ ወለጋ በሰፊው የሚንቀሳቀሰው የኦነግ ሸኔ ቡድን በርካታ ንፁኃንን መግደሉን እንዳረጋገጠ ተናግሯል፡፡ ኢሰመጉ በመግለጫው ከወለጋ ጊምቢ ባለፈ በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ሚዥንጋ ወረዳ ተጨማሪ የፀጥታ ኃይል ካልተሰማራ በስተቀር ጥቃቱ እንደሚባባስ ነው ሥጋቱን የገለጸው፡፡

የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት ፕሬዚዳንት ተቀዳሚ ሙፍቲ ሀጂ ኡመር ኢድሪስ እስከ ማክሰኞ ድረስ የ400 ሰዎች ሞት መረጃ እንደደረሳቸው በማመልከት፣ በድርጊቱ እንዳዘኑ የሚጠቁም መግለጫ አውጥተዋል፡፡

‹‹ሰው ሰውን ለመግደል ቀርቶ ራሱንም ለመግደል መብት አልተሰጠውም፡፡ ሞት ትክክል የሚሆነው ሰውን የፈጠረው አላህ ፍጡሩን ሲወስድ ብቻ ነው፤›› በማለት የተፈጸመውን የግፍ ግድያ ያሳዘናቸው መሆን የገለጹት ተቀዳሚ ሙፍቲ ሀጂ ኡመር ኢድሪስ፣ ንፁኃንን በተደበቁበት መስጂድ መጨፍጨፍ ጉዳዩን ከባድ እንደሚያደርገው አስታውቀዋል፡፡

የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) ዋና ኮሚሽነር ዳንኤል በቀለ (ዶ/ር)ን ትናንት በጽሕፈት ቤታቸው እንዳነጋገሩ የገለጹት የአገሪቱ ርዕሰ ብሔር ሳህለወርቅ ዘውዴ ‹‹ከሰሞኑ የተፈጸመውን ድርጊት በፅኑ አወግዛለሁ›› ሲሉ አመሻሽ ላይ በፕሬዚዳንት ጽሕፈት ቤት ይፋዊ የፌስቡክ ገጽ ላይ መግለጫ አውጥተዋል፡፡ 

በሌላም በኩል የተለያዩ የተፎካካሪ ፓርቲዎች ድርጊቱን አውግዘው ተከታታይ መግለጫዎችን በማውጣት ላይ ይገኛሉ፡፡ ከእነዚህ ፓርቲዎች አንዱ የሆነው የኢትዮጵያ ዜጎች ለማኅበራዊ ፍትሕ (ኢዜማ)፣ በተለያዩ አካባቢዎች እየደረሱ ያሉ ጭፍጨፋዎችን እንደሚያወግዝ ይፋ አድርጓል፡፡

‹‹እንዲህ ያሉ ጭፍጨፋዎች እንዳይፈጠሩ አስቀድሞ መሥራት ያለበት መንግሥት፣ ለሚረግፉ ዜጎቻች ሕይወት ተጠያቂ መሆኑን እናስታውቃለን፤›› በማለት ነው ኢዜማ በመግለጫው ያስታወቀው፡፡

ባልደራስ ለእውነተኛ ዴሞክራሲ ፓርቲ በበኩሉ ‹‹ወለጋ ሰሞኑን ለተፈጸመው የንፁኃን አማሮች የዘር ጭፍጨፋ ዋና ተጠያቂው የብልፅግና መንግሥት ነው›› በማለት መረር ያለ መግለጫ አውጥቷል፡፡ እናት ፓርቲም በተመሳሳይ ግድያውን የሚያወግዝ መግለጫ ያወጣ ሲሆን፣ ድርጊቱን ‹‹ለረዥም ጊዜ የቀጠለ ግድያና ፍጅት›› ሲልም ጠርቶታል፡፡ ፓርቲዎቹ በመግለጫዎቻቸው መንግሥት እየደረሰ ላለው የንፁኃን ሞት ዋና ተያቂነት እንዳለበት ነው የጠቀሱት፡፡

የቅዳሜው የምዕራብ ወለጋ የጊምቢ ጥቃት ከመድረሱ አስቀድሞ ሰኔ 10 ቀን 2014 ዓ.ም. የኦሮሞ ፌዴራላዊ ኮንግረስ (ኦፌኮ) ባወጣው መግለጫ ደግሞ፣ በአካባቢው ያለው የፀጥታ መደፍረስ እንደሚያሳስበው ይፋ አድርጎ ነበር፡፡

በኦሮሚያ ክልል በመንግሥትና ‹‹በኦሮሞ ነፃነት ሠራዊት›› መካከል እየተካሄደ ያለው ግጭት ለንፁኃን ዜጎች ሥጋት ሆኗል ይላል የኦፌኮ መግለጫ፡፡ በምዕራብ ኦሮሚያ ጊምቢን ጨምሮ በደምቢዶሎ፣ እንዲሁም በጋምቤላ የመንግሥትና የታጣቂዎች ግጭት ጉዳት እያደረሰ ነው ያለው ኦፌኮ፣ የሁለቱ ግጭት የንፁኃንን ሕይወት አደጋ ላይ የጣለ ነው ሲል በአካባቢው ያለውን ሥጋት አስታውቆ ነበር፡፡

spot_img
- Advertisement -

ትኩስ ጽሑፎች

ተዛማጅ ጽሑፎች

- Advertisement -
- Advertisement -