Thursday, June 8, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ስፖርትየኦሪገን የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና መሰናዶ

የኦሪገን የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና መሰናዶ

ቀን:

የአሜሪካዋ ኦሪገን ከተማ የምታዘጋጀው የዘንድሮ የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና ሊጀምር የሦስት ሳምንታት ዕድሜ ብቻ ይቀረዋል፡፡ ከሐምሌ 8 እስከ 17 ቀን 2014 ዓ.ም. የሚከናወነው ሻምፒዮናው ላይ የበርካታ አገሮች ፌዴሬሽኖች አትሌቶች ይካፈላሉ፡፡ ሻምፒዮናው ከኦሊምፒክ ቀጥሎ በበርካቶች ዘንድ የሚጠበቅ የአትሌቲክስ ትልቁ ድግስ መሆኑን ተከትሎ ብሔራዊ ቡድኖች ዝግጅት እያደረጉ ይገኛል፡፡

ዓምና ሊከናወን የነበረው ሻምፒዮናው በኮቪድ-19 ወረርሽኝ ምክንያት ወደ ዘንድሮ የተላለፈ ሲሆን፣ እ.ኤ.አ. 2019 በዶሃ ከተከናወነ በኋላ ከሦስት ዓመት በኋላ በኦሪገን ከተማ የሚከናወን ይሆናል፡፡ የዘመኑ ድንቅ አትሌት ስብስቦች የሚታደሙበት ሻምፒዮናው አዳዲስ አትሌቶችን ያመለክታል ተብሎ ይጠበቃል፡፡

የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ብሔራዊ ቡድንም በሻምፒዮና ለ18ኛ ጊዜ ለመካፈል ዝግጅቱን ጀምሯል፡፡ የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን በተለያዩ ርቀቶች የሚወዳደሩ አትሌቶችን ስም ይፋ ያደረገ ሲሆን፣ ሆቴል አርፈው መደበኛ ልምምዳቸውን መጀመራቸውን ገልጿል፡፡ በረዥም፣ በመካከለኛና በአጭር ርቀቶች ኢትዮጵያን ወክለው የሚሳተፉ አትሌቶች ስማቸው የተጠቀሰ ሲሆን፣ በግል ውድድሮች ላይ ያገኙት ውጤትን ተከትሎ ከፍተኛ ግምት አግኝተዋል፡፡

የኦሪገን የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና መሰናዶ | Ethiopian Reporter | ሪፖርተር
በ18ኛው የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና ላይ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድንን በተለያዩ ርቀቶች የሚወክሉ አትሌቶች

እ.ኤ.አ. 1983 በፊንላንድ ሄልሲንኪ በጀመረው የዓለም ሻምፒዮና ኢትዮጵያ ከበደ ባልቻ በማራቶን የብር ሜዳልያ በማግኘት ተሳትፎዋን የጀመረች ሲሆን፣ በሁሉም ዓለም ሻምፒዮናዎች ላይ መሳተፍ ችላለች፡፡    

በዘንድሮ ሻምፒዮና ላይ እንደሚካፈሉ ስማቸው ከተጠቀሱ አትሌቶች መካከል በ10 ሺሕ ሜትር ወንዶች ሰለሞን ባረጋ፣ ታደሰ ወርቁና ምልኬሳ መንገሻ በርቀቱ የሚጠበቁ አትሌቶች ናቸው፡፡ በተለይ የጊዜው የረዥም ርቀት ድንቅ አትሌት ሰለሞን ባረጋ፣ የቶኪዮ ኦሊምፒክ የ10 ሺሕ ሜትር ወርቁን በኦሪገኑ ሻምፒዮና ላይ ይደግመዋል ተብሎ ይጠበቃል፡፡

ሌላው በዓለም ሻምፒዮናው የመጀመርያ ተሳትፎውን የሚያደርገው ታደሰ ወርቁ ከሰለሞን ጋር ይሠለፋል፡፡ ታደሰ በኬንያው ከ20 ዓመት በታች የዓለም ሻምፒዮና በ3,000 ሜትር ወርቅ እንዲሁም በ5,000 ሜትር የብር ሜዳልያ ማግኘቱ ይታወሳል፡፡ አትሌቱ በኔዘርላንድ ሄንግሎ ላይ ባደረገው የ10 ሺሕ ሜትር የቅድመ ማጣሪያ ውድድር ሰለሞን ባረጋን ተከትሎ በ26፡45.91 በማጠናቀቅ ተስፋ የተጣለበት አትሌት ሆኗል፡፡ በርቀቱ ሁለቱ አትሌቶች የተሰጣቸው ከፍተኛ ግምት ነው፡፡

በሌላ በኩል ኢትዮጵያ በ5,000 ሜትር በበሪሁ አረጋዊ፣ ዮሚፍ ቀጄልቻና ሙክታር እድሪስ የምትወከል ይሆናል፡፡ በርቀቱ ዮሚፍና ሙክታር ልምድ ያካበቱ ቢሆንም፣ በሪሁ አረጋዊ ካለው ወቅታዊ አቋም ከፍተኛ ግምት የተሰጠው አትሌት ሆኗል፡፡ አትሌቱ በቶኪዮ ኦሊምፒክ 10 ሺሕ ሜትር ሰለሞን ባረጋ ወርቅ እንዲያመጣ በቡድን ሥራው ከመደገፉም በላይ፣ ዘንድሮ በተከናወኑ በርካታ የግል ውድድሮች ላይ ስኬታማ ጊዜን ማሳለፉ ትልቅ ግምት የተሰጠው አትሌት አድርጎታል፡፡

በሪሁ የቶኪዮ ኦሊምፒክን ጨምሮ፣ የወጣቶች ኦሊምፒክ ጨዋታ፣ የዓለም  ታዳጊዎች ሻምፒዮናና የአፍሪካ ወጣቶች ኦሊምፒክ ጨዋታ ላይ የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ብሔራዊ ቡድንን ወክሎ መካፈል የቻለ ሲሆን፣ በዓለም ሻምፒዮና በኦሪገን ለመጀመርያ ጊዜ ይሳተፋል፡፡

በሻምፒዮናው ከፍተኛ ትኩረት ከተሰጣቸው ውድድሮች መካከል የወንዶች ሦስት ሺሕ መሰናከል አንዱ ነው፡፡ እ.ኤ.አ. 2019 ዶሃ የዓለም ሻምፒዮና የብር ሜዳልያ እንዲሁም በቶኪዮ ኦሊምፒክ በሦስት ሺሕ መሰናክል የብር ሜዳልያ ማግኘት የቻለው ለሜቻ ግርማ የጊዜው የመካከለኛ ርቀት ቀዳሚ ሥፍራ የሚሰጠው አትሌት ሆኗል፡፡

አትሌቱ በሻምፒዮና የወርቅ ሜዳልያን እንደሚያመጡ ግምት ከተሰጣቸው አትሌቶች መካከል አንደኛው ሲሆን፣ በተለይ ዘንድሮ በግል ውድድሮች ላይ ሲያሳይ የነበረው ወጥ አቋም ተስፋ እንዲጣልበት አስችሏል፡፡ አትሌቱ በኦስተራቭ የቤት ውስጥ ሻምፒዮና የሦስት ሺሕ ሜትር መሰናክል ውድድር 7፡58፡68 የገባበት ጊዜ ብሔራዊ ክብረ ወሰኑ እንዲጨብጥ አድርጎታል፡፡ በርቀቱ ጌትነት ዋለ በሁለተኛነት ኢትዮጵያን የሚወክል ሲሆን፣ ከቶኪዮ ኦሊምፒክ ጨዋታ ቀርቶ፣ በምትኩ ሌሜቻ እንዲሄድ የተደረገበት ኃይለ ማርያም አማረ ይሠለፋል፡፡

በዘንድሮ ሻምፒዮና ከወንዶችም በዘለለ በሴቶቹ የምትወከለው ኢትዮጵያ ከፍተኛ ግምት ልታገኝ ችላለች፡፡ በተለይ በ800 ሜትር፣ 5,000 ሜትር፣ 3,000 መሰናክልና በ10 ሺሕ ሜትር ርቀቶች ላይ ኢትዮጵያን የሚወክሉ አትሌቶች ከፍተኛ ግምት አግኝተዋል፡፡

በተለይ በ800 ሜትር ርቀት ላይ በተለያዩ የቤት ውስጥና የዳይመንድ ሊግ ውድድሮች ላይ እየደመቀች የመጣችው ድሪቤ ወልተጂ፣ ፍሬ ወይኒ ኃይሉ እንዲሁም ሀብታም ዓለሙ ይጠበቃሉ፡፡

ከዚያም ባሻገር በ5,000 ሜትር እጅጋየሁ ታዬ፣ ዳዊት ሥዩምና ጉዳፍ ፀጋይ ጥሩ የውድድር ጊዜን ማሳለፋቸውን ተከትሎ፣ ድንቅ ብቃት ሊያስመለክቱ እንደሚችሉ ግምት ከተሰጣቸው አትሌቶች መካከል በቀዳሚነት ይጠቀሳሉ፡፡

በ10 ሺሕ ሜትር ለተሰንበት ግደይ፣ ቦሰና ሙላቴና ግርማዊት ገብረ እግዚአብሔር ይጠበቃሉ፡፡ ከዚህም የሪዮ ኦሊምፒኳ 10 ሺሕ ሜትር ባለ ክብረ ወሰኗ አልማዝ አያና በተጠባባቂነት ተካታለች፡፡ አልማዝ በወሊድና በጉልበቷ ላይ አድርጋ በነበረው ቀዶ ሕክምና ምክንያት ለዓመታት ከሩጫው ዓለም ርቃ የቆየች ሲሆን፣ በቅርቡ በተለያዩ ውድድሮች ላይ መካፈሏን ተከትሎ በተጠባባቂነት ተይዛለች፡፡

በሴቶች ረዥም ርቀት ላይ ከሚኖረው ፉክክር ባሻገር፣ በሴቶች 3,000 ሜትር መሰናክል ላይ የሚሳተፉ አትሌቶችም ይጠበቃሉ፡፡ በርቀቱ መቅደስ አበበ፣ ወርቅ ውኃ ጌታቸውና ዘርፌ ወንድምአገኝ ትልቅ ግምት አግኝተዋል፡፡

በሻምፒዮናውን ኢትዮጵያን የሚወክሉ አትሌቶችን ስም ዝርዝር ይፋ ያደረገው የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን፣ የተመረጡ አትሌቶች ሆቴል ገብተው ዝግጅት እንዲጀምሩ ማሳሰቡ ይታወሳል፡፡ የተመረጡት አትሌቶች ገሚሱ ወደ ሆቴል መግባታቸው የተገለጸ ሲሆን፣ ቀሪዎቹም በቅርቡ ወደ ሆቴል እንደሚገቡ ፌዴሬሽኑ አስታውቋል፡፡

ብሔራዊ ፌዴሬሽኑ የብሔራዊ ቡድኑን አሠልጣኞች ስም ዝርዝር ግን እስካሁን ይፋ አላደረገም፡፡ ፌዴሬሽኑ የመጨረሻዎቹን አሠልጣኞች ስም መርጦ ማጠናቀቁንና በቅርቡም ይፋ እንደሚያደርግ የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ጽሕፈት ቤት ኃላፊ አቶ ዮሐንስ እንግዳ ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡

ብሔራዊ ፌዴሬሽኑ ከሳምንታት በፊት የማራቶን አትሌቶችን ስም ዝርዝር ያሳወቀ ሲሆን፣ ምርጫውን ተከትሎ ትችት ሲገጥመው ነበር፡፡ ከዚህ ጋር ተያይዞም በሻምፒዮናው ላይ የሚካፈሉትን የመጨረሻዎችን አትሌቶች ስም ያሳወቀበት ጊዜ ዘግይቷል የሚሉ አስተያየቶች ሲሰጡ ሰንብተዋል፡፡

በቅብብሎሽ የዘለቀው የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ብሔራዊ ቡድን ተሳትፎ፣ በየሻምፒዮናው የራሳቸውን አሻራ ማኖር የቻሉ አትሌቶች መመልከት አስችሏል፡፡ ኢትዮጵያ መሳተፍ ከጀመረችበት ጊዜ አንስቶ 29 ወርቅ፣ 26 ብር እና 30 የነሐስ ሜዳልያዎች በአጠቃላይ 85 ሜዳልያዎችን በመሰብሰሰብ ከዓለም ሰባተኛ ደረጃ ላይ መቀመጥ ችላለች፡፡

በዘንድሮ የዓለም ሻምፒዮና ከ200 በላይ አገሮች በ2,000 አትሌቶች የሚወከሉ ሲሆን፣ በዩክሬን ላይ ጦርነት የከፈተችው ሩሲያ እንዳትሳተፍ ታግዳለች፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ከቀጣዩ ዓመት በጀት ውስጥ 281 ቢሊዮን ብሩ የበጀት ጉደለት ነው ተባለ

ለቀጣዩ በጀት ዓመት ከቀረበው 801.65 ቢሊዮን ብር አጠቃላይ በጀት...

የኢትዮጵያ ምርት ገበያ ከተለመደው አሠራር ወጣ ያለውን ‹‹የወደፊት ግብይት›› ሥርዓት በይፋ አስጀመረ

የኢትዮጵያ ምርት ገበያ ከተለመደው የማገበያየት ተግባሩ ወጣ ያለና በኢትዮጵያ...

የባንክ ማቋቋሚያ መሥፈርት እንደሚጠነክር ሚኒስትሩ ተናገሩ

 ባንኮች ስለውህደት እንዲያስቡም መክረዋል በኢትዮጵያ ውስጥ ባንክ ለማቋቋም የሚያስፈልገው መሥፈርት...