Monday, November 28, 2022
ሌሎች ዓምዶች
  - Advertisement -
  - Advertisement -
  ኪንና ባህል‹‹ሀገር ፍቅር›› - አንቲካው ቴአትር ቤት

  ‹‹ሀገር ፍቅር›› – አንቲካው ቴአትር ቤት

  ቀን:

  ዘጠኝ አሠርታትን ሊያስቆጥር ሦስት ዓመታት ብቻ ቀርቶታል፡፡ ‹‹የሀገር ፍቅር ትዝታው ትዝታው አይረሳም ለሚያውቀው›› ከሚለው ዜማ ጋርም የተሳሰረ ነው ተቋሙ፡፡ ከድሮዋ አዲስ አበባ ማዕከል ከአራዳ ጊዮርጊስ በታች ቆልቆል ሲባል ይገኛል፡፡ ይኸው አንቲካ (የዱሮ፣ የቀድሞ፣ ብዙ ዓመት የኖረ) የሆነው የሀገር ፍቅር ቴአትር ቤት በአፍሪካ በአገር በቀል ቴአትር ቤትነትም ይታወቃል፡፡

  ሁለተኛው የጣሊያን (ፋሺስቶች) ወረራ በ1928 ዓ.ም. ከመከሰቱ አንድ ዓመት ቀደም ብሎ ቴአትር ቤቱ የተመሠረተው ‹‹የኢትዮጵያ ሀገር ፍቅር ማኅበር›› በሚል መጠርያ ነው፡፡

  በ1927 ዓ.ም. በምሥራቅ ኢትዮጵያ ወልወል ላይ ግጭት የፈጠረው የጣሊያን ሠራዊት፣ አዝማሚያው ወደ ጠቅላላ ወረራ የሚያዘነብል መሆኑ የተገነዘቡ ኢትዮጵያውያን ሹማምንት እነ አቶ መኰንን ሀብተወልድ ፍቅረ ሀገርን የሚያሠርፅ፣ ትውልዱን ለአገር ክብር የሚያንቀሳቅስ ማኅበር፣ በአዲስ አበባ ማቆም ያስፈልጋል ብለው በመነሳታቸውና በንጉሠ ነገሥቱ ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ (1923-1967) ተቀባይነት በማግኘቱ ነው የሀገር ፍቅር ማኅበር የተሠረተው፡፡

  የሀገር ፍቅር ማኅበር አገርን ከባዕዳን ወራሪዎች ለመታደግ በተለይ መቀመጫውን ባደረገባት አዲስ አበባ ታላላቅ ሰዎችን ንግግር እንዲያደርጉ በመጋበዝ ኅብረተሰቡን በቀረርቶ፣ በሽለላና በፉከራ በታጀበ ጭምር ይቀሰቅስ፣ ያነሳሳ ነበር፡፡

  ከአምስት ዓመታት ተጋድሎ በኋላ ፋሺስት ጣሊያን ከኢትዮጵያ ከተወገደ በኋላ ዳግም ሥራውን የጀመረው ማኅበሩ የቴአትርና የሙዚቃ ክፍል በማቋቋም ሥራውን ቀጥሏል፡፡ መጠርያውንም የሀገር ፍቅር ቴአትር ቤት ከሆነ በኋላም ጎጆው በድል ትዕምርትነት እየታየ እስከዚህ ዘመን ድረስ ዘልቋል፡፡

  በመጪው ሐምሌ ወር 87ኛ ዓመቱን የሚያከብረው ቴአትር ቤቱ በተውኔት፣ በሙዚቃ፣ በባህላዊ ውዝዋዜ በሌሎች የጥበባት ዘርፎች ስመ ጥር ከያንያን አፍርቷል፡፡

  እነ ኢዮኤል ዮሐንስ፣ ንጋቷ ከልካይ፣ ፍሬው ኃይሉ፣ አሰፋ አባተ፣ በሻህ ተክለማርያም፣ ጥላሁን ገሠሠ፣ አብራር አብዶ፣ አልማዝ ቢሆን፣ አሰለፈች አሸኔ ወዘተ ከብዙ በጥቂቱ የሚጠቀሱ ናቸው፡፡

  ለሦስት ዓመታት ያህል በዕድሳት የቆዩት የቴአትር ቤቱ ሕንፃዎች ባለፉት ወራት በአብዛኛው መጠናቀቃቸው ተገልጿል፡፡

  ከቴአትር ቤቱ የተገኘው መረጃ እንደሚያሳየው፣ ዕድሳቱ 610 መቀመጫዎች የሚኖሩት ዋናው የቴአትር ማሳያ አዳራሽን ጨምሮ አርት ጋለሪ፣ አነስተኛ የቴአትር አዳራሽ፣ ዘመናዊ የሙዚቃ መከወኛ ክፍል፣ ካፊቴሪያ፣ የአስተዳደር ሕንፃና ሌሎችም አገልግሎቶች ተካተውበታል፡፡

  በኮቪድ 19 ዋዜማ ጀምሮ በዕድሳት ላይ የቆየው ቴአትር ቤቱ አሁን ላይ የዕድሳት ሥራ እየተጠናቀቀ ሲሆን፣ የወንበር መግጠም፣ መጋረጃና መሰል የማጠናቀቂያ ሥራዎች እየተከናወኑ መሆኑን የቴአትር ቤቱ ሥራ አስኪያጅ አቶ አብዱልከሪም ጀማል ለዜና አገልግሎት ገልጸዋል።

  ቀሪ ሥራዎችን በአጭር ጊዜ በማጠናቀቅ ቢበዛ እስከ ሁለት ወራት ባሉት ጊዜያት ቴአትር ቤቱ ለሥራ ዝግጁ ሆኖ ክፍት ይሆናል ብለዋል።

  45 ሚሊዮን ብር እንደፈጀ የተገመተለት ዕድሳቱ፣ የቀደመ ታሪካዊ ይዘቱን በጠበቀ አግባብ መከወኑና ሒደቱም በአዲስ አበባ የባህል፣ ቱሪዝምና ኪነ ጥበብ ቢሮ የቅርስ ጥበቃ ባለሙያዎች ክትትል እንደተፈጸመ ሥራ አስኪያጁ ገልጸዋል።

  ቴአትር ቤቱ ለሕዝብ ክፍት ሲደረግም ቀደም ሲል ለተመልካች ዕይታ ቀርበው ከተቋረጡ ሁለት ተውኔቶች በተጨማሪ አዳዲስ ተውኔቶች ለመድረክ ዕይታ በዝግጅት ላይ መሆናቸውም ታውቋል፡፡

  spot_img
  - Advertisement -

  ይመዝገቡ

  spot_img
  spot_img

  ተዛማጅ ጽሑፎች
  ተዛማጅ

  በችግር የተተበተበው የሲሚንቶ አቅርቦት

  ሲሚንቶን እንደ ግብዓት ተጠቅሞ ቤት ማደስ፣ መገንባት፣ የመቃብር ሐውልት...

  ‹‹የናይል ዓባይ መንፈስ›› በሜልቦርን

  አውስትራሊያ ስሟ ሲነሳ ቀድሞ የሚመጣው በተለይ በቀደመው ዘመን የባህር...

  ‹‹ልብሴን ለእህቴ››

  ለሰው ልጅ መኖር መሠረታዊ ፍላጎት ተብለው ከተዘረዘሩት ውስጥ ልብስ...

  የአዲስ አበባ ትምህርት ቤቶች የምርመራ ውጤት እስከምን?

  በፍቅር አበበ የትምህርት ጥራትን፣ ውጤታማነትንና ሥነ ምግባርን ማረጋገጥ ዓላማ አድርጎ...