Tuesday, March 5, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

‹‹ኅብረተሰቡ በሚያገኛቸው አጋጣሚዎች ሁሉ የአካል ጉዳተኛ ሴቶች ድምፅ መሆን ይጠበቅበታል›› ወ/ሮ ድባቤ ባጫ፣ የኢትዮጵያ አካል ጉዳተኛ ሴቶች ብሔራዊ ማኅበር ዋና ሥራ አስኪያጅ

ወ/ሮ ድባቤ ባጫ የኢትዮጵያ አካል ጉዳተኛ ሴቶች ብሔራዊ ማኅበር ዋና ሥራ አስኪያጅና የአዲስ አበባ ከተማ የሴቶች ፌዴሬሽን ምክትል ሊቀ መንበር ናቸው፡፡ ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በሶሺዮሎጂና በሶሻል አንትሮፖሎጂ የመጀመርያ ዲግሪ ያገኙ ሲሆን፣ በህንድ ኢንድራ ጋንዲ ዩኒቨርሲቲ በሶሻል ወርክ የድኅረ ምረቃ ትምህርታቸውን በመከታተል ላይ ናቸው፡፡ ባለትዳርና የአራት ልጆች እናት የሆኑትን ወ/ሮ ድባቤ፣ በብሔራዊ ማኅበሩ እንቅስቃሴና ተያያዥ ጉዳዮች አስመልክቶ ታደሰ ገብረማርያም አነጋግሯቸዋል፡፡

ሪፖርተር፡- የኢትዮጵያ አካል ጉዳተኛ ሴቶች ብሔራዊ ማኅበር መቼ እንደተቋቋመና ምን ያህል አባላት እንዳሉት ቢገልጹልን?

ወ/ሮ ድባቤ፡- ብሔራዊ ማኅበሩ የተቋቋመው በ1995 ዓ.ም. ነው፡፡ መሥራቾቹም ስምንት ሴቶች ሲሆኑ ከመሥራቾቹም መካከል ሰባቱ የአካል ጉዳት፣ አንዷ ደግሞ ጉዳት አልባ ናቸው፡፡ ማኅበሩን ለማቋቋም ቀደም ሲል በተካሄደው እንቅስቃሴ በርካታ ተግዳሮቶችና ጥያቄዎች ከየአቅጣጫው ሲንፀባረቁ ነበር፡፡ ይህም ሆኖ ግን የተጋረጡትን ተግዳሮቶች በመቋቋምና ጠንከር ያለ ሥራም በመከናወኑ የተነሳ ማኅበሩ ሊመሠረት እንደቻለና በአሁኑ ጊዜም በአምስት ዓይነት የአካል ጉዳት ያለባቸውን ከ10,500 በላይ ሴቶችን በአባልነት አቅፏል፡፡

ሪፖርተር፡- በማኅበሩ አባላት የታቀፉት ሴቶች ምን ዓይነት የአካል ጉዳት ያለባቸው ናቸው? ማኅበሩን ለማቋቋም ስትንቀሳቀሱ ምን ዓይነት ተግዳሮት አጋጠማችሁ?

ወ/ሮ ድባቤ፡- የማኅበሩ አባላት ዓይነስውራን፣ የእንቅስቃሴ አካል ጉዳት፣ መስማትና መናገር የተሳናቸው፣ የሥጋ ደዌ ተጠቂ አካል ጉዳትና የአዕምሮ ውስንነት ያለባቸው ሴቶች ናቸው፡፡ ማኅበሩ ጎንደር፣ ባህር ዳር፣ መንዝ መሀልሜዳ፣ አዳማ፣ ጅማ፣ አምቦ፣ ሐዋሳ፣ አርባ ምንጭ፣ አደስ አበባና ድሬዳዋ እየተንቀሳቀሰ ይገኛል፡፡ ማኅበሩን በ1980ዎቹ ለማቋቋም ደፋ ቀና በተባለበት ወቅት ተስፋ አስቆራጭ የሆኑ ተግዳሮቶች ተደቅነውብን ነበር፡፡ ካጋጠሙን መካከል አካል ጉዳተኛ ሴቶች ሆናችሁ ማኅበርን ማቋቋም ምን ይፈይድላችኋል የሚልና ሌሎችም በርካታ አዘናጊና ኋላቀር አስተሳሰቦች ነበሩ፡፡ እነዚህንም አስተሳሰቦች በማንፀባረቅ ሊያደናቅፉን የሞከሩትም በወቅቱ ፈቃድ የመስጠት ኃላፊነት የተጣለባቸው ጭምር ናቸው፡፡

ሪፖርተር፡- ብሔራዊ ማኅበሩን ለማቋቋም ያነሳሳችሁ ምክንያቶች ምንድን ናቸው?

ወ/ሮ ድባቤ፡- በመጀመርያ በሥርዓተ ፆታ የነበረው አስተሳሰብ ሴት ለጓዳ ወይም ለማጀት የሚል ነበር፡፡ ይህ ዓይነቱን አስተሳሰብ ለመስበር በየአቅጣጫው የሴቶች እንቅስቃሴ ይካሄድ ነበር፡፡ የአካል ጉዳተኛ ሴቶችን በተመለከተ ግን በሴትነታቸው ከሚደርስባቸው ልዩ ልዩ ተፅዕኖዎች ባሻገር አካል ጉዳቱ ሲታከልበት ደግሞ ችግሩን በይበልጥ ውስብስብና አስቸጋሪ ያደርገዋል፡፡ ይህ እንደተጠበቀ ሆኖ ደግሞ አካል ጉዳተኛ ሴቶች የማይታይ እምቅ ሀብትና ችሎታ እንዳላቸው አሌ የማይባል ሀቅ ነው፡፡ ስለዚህ ከፍ ብሎ  በተጠቀሰው አስተሳሰብ ሳይጠለፉ ወደፊት እንዲወጡ፣ ችሎታቸውንና አቅማቸውን በሥራ እንዲያስመሰክሩ ማድረግ ግድ ይላል፡፡ ለዚህም ዕውን መሆን በማኅበር መደራጀት እጅግ አስፈላጊ ሆኖ ተገኝቷል፡፡ ማኅበር ከማቋቋም ባሻገር ኅብረተሰቡ በሚያገኛቸው አጋጣሚዎች ሁሉ የአካል ጉዳተኛ ሴቶች ድምፅ መሆን ይጠበቅበታል፡፡ በዚህም ራዕያችን ‹‹አካል ጉዳተኛ ሴቶች በሁሉም የልማት ተሳትፎ እኩል ተጠቃሚነትና ተሳታፊ ሆነው የማየት ነው››

ሪፖርተር፡- ማኅበሩ ለአባላቱ ምን እያደረገ ነው?

ወ/ሮ ድባቤ፡- ማኅበሩ አባላቱን ተጠቃሚ የሚያደርግ አራት ዋና ዋና የትኩረት አቅጣጫዎች ላይ እየተንቀሳቀሰ ይገኛል፡፡ ከትኩረት አቅጣጫዎችም መካከል አንደኛው የአቅም ግንባታ ነው፡፡ ይህም በሦስት ይከፈላል፡፡ የመጀመርያው የማኅበሩን አቅም ከማሳደግ አንፃር የተቋማት ግንባታ ላይ የሚሠራ ነው፡፡ በሁለተኛው ክፍል የማኔጅመንቱን፣ የመሪዎችና የአባላቱን አቅም የማጎልበት ሥራ ይከናወናል፡፡ ሌላኛው የትኩረት አቅጣጫ ለአባላት የሥነ ልቦና ድጋፍ መስጠት ላይ ያለመ ነው፡፡ በዚህም ማኅበራዊ ተሳትፎአቸውን ለማሳደግ ተችሏል፡፡ ሦስተኛው ገቢ ማስገኛ ሲሆን ይህም በሁለት ይከፈላል፡፡ አንደኛው ለተማሪዎች የደብተርና የትምህርት ቤት ክፍያን መሸፈን፣ የንፅህና መጠበቂያ (ሳኒታይዘር) ማቅረብ ይገኝበታል፡፡ ሁለተኛው የንግድ ክህሎት ሥልጠና በማጎልበት ነው፡፡ በዚህም የፍላጎት ዳሰሳ በማድረግና የገቢ ማስገኛዎች የወጣቶች የሥነ ተዋልዶ ጤናን የማስረጽ ፕሮጀክቶችን ቀርፆ ሥራ ላይ ማዋል ነው፡፡ አራተኛው የትኩረት አቅጣጫ የጉትጎታ (አድቮኬሲ) ሥራ ማከናወን ነው፡፡ በዚህም ሥራ የአካል ጉዳተኛ ሴቶችና መብት የማስጠበቅ እንቅስቃሴ ይካሄዳል፡፡

ሪፖርተር፡- ለገቢ ማስገኛውና ለሥነ ተዋልዶ ጤና ፕሮጀክቶች የፋይናንስ ድጋፍ የሚያደርግላችሁ ማን ነው?

ወ/ሮ ድባቤ፡- ለገቢ ማስገኛው የሚያስፈልገው ወጪ የሚሸፍነው ዋና መሥሪያ ቤቱ ፊንላንድ የሚገኘው ኤቢሲስ ፋውንዴሽን የተባለ ዓለም አቀፍ ግብረ ሠናይ ድርጅት ነው፡፡ ለንጽህና መጠበቂያና ለወጣቶች የሥነ ተዋልዶ ጤና ማስረጽ ፕሮጀክቶችን የሚደግፈው ደግሞ ፕላን ኢንተርናሽናል ነው፡፡

ሪፖርተር፡- አካል ጉዳተኛ ሴቶችን የምታወያዩበት መድረክ ፈጥራችኋል?

ወ/ሮ ድባቤ፡- አዎ ፈጥረናል፡፡ ይኼውም በወር ሁለቴ ወይም በአሥራ አምስት ቀን አንድ ሐሙስ ከቀኑ ስምንት ሰዓት እስከ 11 ሰዓት የሚካሄድ የቡና ጠጡ ፕሮግራም ነው፡፡ በዚህም ፕሮግራም አባላቱ ራሳቸው ለመወያየት የሚፈልጉትን ርዕስ ይመርጣሉ፡፡ ወይም ከፍ ብሎ በተጠቀሱት ቀናት ካጋጠሟቸው ተግዳሮቶች በመነሳት ግንዛቤና ትምህርት አዘል ውይይቶችን ይካሄዳሉ፡፡ የውይይቱን ሒደት የሚያመቻች ፀሐፊ ተወያዮቹ ይመረጣሉ፡፡ የማኅበሩ ጽሕፈት ቤት ደግሞ ቡናና ተያያዥ ጉዳዮችን ያቀርባል፡፡

ሪፖርተር፡- በማኅበሩ በሚያካሂደው እንቅስቃሴ ገጥሞታል የሚሉት ችግር ሊያብራሩልን ይችላሉ?

ወ/ሮ ድባቤ፡- ዋናው ችግራችን ለቢሮ ሥራ የምንገለገልበት ቤት አለመኖር ነው፡፡ ማኅበሩ በኪራይ ቤት ውስጥ ነው ያለው፡፡ ቤት ወይም ቦታ እንዲሰጠን ጉዳዩ ለሚመለከታቸው መንግሥታዊ አካላት በተደጋጋሚ ጊዜ በደብዳቤ ጠይቀን መልስ አላገኘንም፡፡ ቤት ብናገኝ ለኪራይ የምናወጣውን ገንዘብ የአካል ጉዳት ያለባቸውን የብዙ ሴቶችን ሕይወት እንለውጥበት ነበር፡፡ ቤት ከጠፋ ቦታ ቢሰጠን ሕንፃ የመገንባት አቅም አለን፡፡ ለዚህም የሚረዱን ግለሰብ አሉ፡፡ መንግሥታችሁ ቦታ ከሰጣችሁ እኔ ዲዛይኑን አሠርቼ ሕንፃውን አስገነባላችኋለሁ ብለው ቃል ገብተውልናል፡፡ እንዲህ ዓይነት ትብብር ለማሳየት ፈቃደኛ የሆኑትም በእንግሊዝ አገር የሚኖሩ ግለሰብ ሲሆኑ እስካሁንም ወደ 20 የሚጠጉ የአካል ጉዳተኛ ሴት ተማሪዎች የትምህርት ቤት ክፍያ እየሸፈኑና ልዩ ልዩ ዓይነት ክራንችና የአካል ድጋፍ እያቀረቡ ይገኛሉ፡፡

ሪፖርተር፡- የከፋ ችግር የደረሰባችሁ በየትኛው የሥራ እንቅስቃሴያችሁ ላይ ነው?

ወ/ሮ ድባቤ፡- የከፋ ችግር የደረሰብን ፆታዊ ጥቃት የደረሰባቸውን አካል ጉዳተኛ ሴቶች የምክር አገልግሎት ከሰጠናቸው በኋላ ከደረሰባቸው ጥቃት የሚያገግሙበት ሰላማዊ ማረፊያ አለመኖር ነው፡፡ በዚህም የተነሳ ወደ ተደፈሩበት ቤት ተመልሰው እንዲሄዱ ነው የምናደርጋቸው፡፡ ሌላው ችግራችን ቡና ጠጡ ፕሮግራም ላይ ነው፡፡ ለዚህ የሚሆን ክፍል ወይም አዳራሽ ስለሌለን በማኅበሩ ጽሕፈት ቤት ግቢ ውስጥ ተጣበው እንዲወያዩ እናደርጋቸዋለን፡፡ ዝናብ በጣለ ቁጥር ውይይቱ ይቋረጣል፡፡

ተዛማጅ ፅሁፎች

- Advertisment -

ትኩስ ፅሁፎች ለማግኘት

በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች

ተዛማጅ ፅሁፎች

ከሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች እስከ ግለሰቦች የሚደርሰው ወገን ፈንድ

ወገን ቴክኖሎጂ ሶሉሽንስ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማኅበር፣ ሕጋዊ ዕውቅና በማግኘት ከኢትዮጵያና ከተለያዩ አገሮች ልገሳን ለማሰባሰብ ‹‹ወገን ፈንድ›› የሚባል የበይነ መረብ (ኦንላይን) የድጋፍ ማሰባሰቢያ ድረ...

ግዴታን መሠረት ያደረገ የጤና መድኅን ሥርዓት

የኢትዮጵያ ጤና መድኅን ተቋቁሞ ወደ ሥራ ከገባ ዓመታትን አስቆጥሯል፡፡ ማኅበረሰብ አቀፍና የማኅበራዊ ጤና መድኅን ሥርዓቶችን መሠረት አድርጎም ይሠራል፡፡ የማኅበረሰብ አቀፍ ጤና መድኅን ሥርዓት በኢመደበኛ...

የመሠረተ ልማት ተደራሽነት የሚፈልገው የግብርና ትራንስፎርሜሽን

የኢትዮጵያ ግብርና ትራንስፎርሜሽን ተቋም አርሶ አደሩን የዘመናዊ ቴክኖሎጂ ተጠቃሚ በማድረግ የግብርና ክፍለ ኢኮኖሚውን የማሳደግ ዓላማ ይዞ የተመሠረተ ነው፡፡ ተቋሙ የግብርናውን ዘርፍ ሊያሳድጉ የሚችሉ ጥናቶችን...