Thursday, February 22, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ማኅበራዊለተቀጣሪው የደረሱ የመንገድ ዳር ምግቦች

ለተቀጣሪው የደረሱ የመንገድ ዳር ምግቦች

ቀን:

ከጠዋቱ 2፡00 ሰዓት ነው፡፡ በሸራ የተወጠረችው ምግብ ቤት ጢም ብላለች፡፡ ስድስት ኪሎ ከአዲስ አበባ ትምህርት ቢሮ ጀርባ የምትገኘው ምግብ ቤት ባለቤት ወ/ሮ ያለልሽ መላኩ ናቸው፡፡

በምግብ ቤቱ ለቁርስ ተብለው ከተዘረዘሩት የምግብ ዓይነቶች በብዙዎቹ ተወዳጅ የሆነው ጮርናቄ (ቆቆር) ቀዳሚው ነው፡፡ ሌሎችም የቁርስ ዓይነቶች ለተመጋቢው የሚያቀርቡ ቢሆንም፣ ጠዋት ላይ ከጮርናቄ ውጪ የሚመገቡ ደንበኞቻቸው ቁጥር እጅግ አነስተኛ መሆኑን ይገልጻሉ፡፡ የአንድ ጮርናቄ ዋጋም 15 ብር ሲሆን፣ ሻይ ሲጨመርበት 22 ብር እንደሚደርስ ያስረዳሉ፡፡

ከጮርናቄ በተጨማሪ እንጀራ ፍርፍር፣ እንቁላል ፍርፍር፣ ፓስታና ሌሎች የምግብ ዓይነቶች በምግብ ሜኑ (ዝርዝር) ውስጥ ቢያካትቱም፣ ደንበኞቻቸው ይህንን የሚገዙት ደመወዝ የወጣ ሰሞን ብቻ መሆኑን ያስረዳሉ፡፡ ኑሮ በመወደዱና ለምሳ የሚጠየቁ ዋጋቸው ተቀራራቢ የሆኑ ምግቦችን መጠቀም ስለማይችሉ ነው ብለዋል፡፡

- Advertisement -

Video from Enat Bank Youtube Channel.

አቶ አዱኛ ዓለሙ በአንድ የግል መሥሪያ ቤት ተቀጣሪ ነው፡፡ በወር 4,000 ብር ያህል ገቢ ያለው ሲሆን፣ ከወ/ሮ ያለልሽ የሸራ ምግብ ቤት ውስጥ መመገብ ከጀመረ ዓመት እንደሆነው ይናገራል፡፡

አቶ አዱኛ እንደሚለው ቁርስ በአብዛኛው ጊዜ አይበላም፡፡ ቁርስ በልቶ ምሳና እራትን ከጨመረ የቀን ወጪው ከአቅሙ በላይ ስለሚሆን ወሩን በሙሉ አብቃቅቶ ለመጠቀም በማሰብ ቁርስን እንደዘለለው ያስረዳል፡፡ ሽሮሜዳ አካባቢ በ2,500 ብር በተከራየው ቤት ውስጥ እንደሚኖርና የትራንስፖርት፣ ምግብና ሌሎች ወጪዎች ሲጨመርበ ኑሮው ከአቅሙ በላይ እንደሚሆንበት ይገልጻል፡፡

አነስተኛ ምግብ ቤቶች በምሳ ሰዓት

መገናኛ፣ ስድስት ኪሎ፣ ሽሮሜዳ፣ ሜክሲኮና ሌሎችም አካባቢዎች አነስተኛ ሸራ ቀልሰው ምግብ እያበሰሉ የሚሸጡ ብዙዎች ናቸው፡፡ በዘንቢል ሦስትና አራት ፔርሙዝ ሻይና ቡና አንጠልጥለውና ፓስቲ ወይም አምባሻ ይዘው እየተዘዋወሩና ሰው በሚበዛባቸው አካባቢዎች በጊዜያዊነት እየተቀመጡ የሚሸጡም እንዲሁ፡፡ ከጊዜ ወደ ጊዜ በሸራ ቤቶች ውስጥ ምሳ ለመመገብ የሚመጡ ደንበኞቻቸው ቁጥር ከፍ ማለቱን ይገልጻሉ፡፡

ወ/ሮ ዓለምነሽ አየለ በሜክሲኮ አካባቢ ተደርድረውና ሸራ ቀልሰው ምግብ ከሚሸጡ መካከል አንዷ ናቸው፡፡

በተለይም በምሳ ሰዓት የሚመጡ ደንበኞች ቁጥር ከጊዜ ወደ ጊዜ ከፍ እያለ መሆኑንና በየሬስቶራንቱና ሆቴሎች የምግብ ዋጋ ከፍ ማለቱና ከተመጋቢው አቅም በላይ መሆኑ ምክንያት ሊሆን እንደሚችል ይገምታሉ፡፡

በምሳ ሰዓት የምግብ ዝርዝራቸው በየዓይነት፣ ተጋቢኖ፣ ሽሮ ፈሰስ፣ ጎመንና ሌሎችም ዓይነቶች ለተመጋቢዎች እንደሚያቀርቡ ይናገራሉ፡፡ ዋጋቸውም ከሌሎቹ ሆቴሎችና ሬስቶራንቶች አኳያ እጅግ በጣም የሚቀንስ መሆኑን፣ ለአብነት በየዓይነት 60 ብር፣ ተጋቢኖ 55 ብር፣ ሽሮ ፈሰስ 50 ብር መሆናቸውን በማንሳት ገልጸዋል፡፡ በወ/ሮ ዓለምነሽ የምግብ ቤት ውስጥ አነስተኛ የምግብ ወጪ 50 ብር ሲሆን፣ ከፍተኛ የሚባለው ደግሞ 70 ብር ነው፡፡

ወጣት ዘሪሁን ተካልኝ በሕንፃ ተቋራጭ ውስጥ በጉልበት ሥራ ላይ እንደተሰማራ ይገልጻል፡፡ ‹‹ሰው እንደቤቱ እንጂ እንደጎረቤቱ አይኖርም እንደሚባለው፣ እኔም የምኖረው፣ የምበላውና የምጠጣው እንደ አቅሜ ነው፤›› ይላል፡፡ ደመወዙ ለወር እንዲያደርሰው የወጪ አካሄዱን እንዳስተካከለ፣ አመጋገቡንም ቁርስ ላይ ሻሜታ በአምባሻ፣ ምሳ ላይ ሽሮ ወይም በየዓይነት፣ መሸትሸት ሲል የተቀቀለ ድንች በዳጣ እንዳደረገ ያስረዳል፡፡  ይህን ተመግቦና የትራንስፖርት ተጨምሮበት የቀን ወጪው 150 ብር እንደሆነ ያስረዳል፡፡ የኑሮ ውድነቱ በእጅግ ከባድ መሆኑን የሚገልጸው ወጣቱ፣ ይህ የአዋዋልና የአኗኗር ሥርዓቱን እንዲቀይር እንዳስገደደው ነግሮናል፡፡

ከዚህ ቀደም ከእንቅልፍ የሚነሳው አርፍዶ በመሆኑ፣ የትራንስፖርት ብዙ እንዲያወጣ ያደርገው እንደነበርና አሁን ይህን እንደቀየረና በጠዋት ተነስቶ እንደሚወጣ፣ ምግብ የሚበላባቸውንም ረከስና ዝቅ ወዳሉ ቦታዎች እንደቀየረ ይገልጻል፡፡

የምሽት የመንገድ ዳር ምግቦች

አመሻሽ ላይ በአውራ ጎዳና ዳርና ዳር ላይ የበሰሉ ምግቦች በርከት ማለታቸውን የመዲናዋ መንገዶች በተለይም የሰው እንቅስቃሴ የሚበዛባቸው ምስክር ናቸው፡፡ የድንች ጥብስ፣ ድንች በዳጣ፣ ስኳር ድንች፣ እርጥብ፣ እሸት በቆሎ መንገድ ዳር ላይ ለዓይን አይታጡም፡፡ እነዚህ ምግቦች በእግሩ ለሚያዘግምና ራቱን ቤቱ አብስሎ መመገብ ለማይችሉ ሁሉ መልካም አጋጣሚዎች ናቸው፡፡

በየካ ክፍለ ከተማ ከሚገኘው ማራቶን ሕንፃ ከተደረደሩት ሊስትሮዎች አጠገብ በምሽት ላይ ድንች በዳጣ የሚሸጡ ይገኛሉ፡፡

ድንች በዳጣ የሚመገቡት በአብዛኛው ሊስትሮ የሚሠሩ ወጣቶች፣ በጉልበት ሥራ ላይ የተሰማሩ ዜጎች፣ ተማሪዎችና አንዳንድ በጀርባቸው ቦርሳ ያዘሉ የመንግሥትና የግል ተቀጣሪ ሠራተኞች መሆናቸውን፣ በተመጋቢ ብዛት የተጨናነቁት ሻጭ ይገልጻሉ፡፡

በኑሮ ውድነቱ ምክንያት ድንች በዳጣ የማይመገብ ሰው እንደሌለ የሚገልጹት እኚህ ሻጭ፣ ‹‹በተጠላለፈ ማንኪያና ሹካ፣ ባማረ ጠረጴዛ ቁጭ ብሎ ለመብላት ከ350 ብር እስከ 500 ብር ከማውጣት በ20 ብር ተመግቦ ወደ ቤት መግባት ይሻላል፤›› ይላሉ፡፡

ድንች በዳጣ ዋጋው 20 ብር፣ ስኳር ድንች 25 ብር፣ ግማሽ የተቀቀለ በቆሉ 10 ብር፣ ችብስ 10 ብር፣ እርጥበ በ25 ብር እንደሚሸጡ፣ ሳንቡሳ በምስርና በአትክልት የሚገዟቸው ደግሞ በተለያዩ የንግድ ሱቆች፣ በመንግሥት መሥሪያ ቤቶችና በሌሎችም የሚሠሩ ደንበኞቻቸው እንደሆኑ ይናገራሉ፡፡

የኑሮ ውድነቱ መካከለኛ ገቢ ያላቸውን የኅብረሰብ ክፍሎች ወደታች ያወረደና የደሃ ደሃ የሚባሉ ዜጎችን ደግሞ የዕለት ምግብ አብስሎ ለመመገብ እንኳን የፈተነ መሆኑን እነዚህ የጎዳና ምግቦች ማሳያ ናቸው፡፡

አንዳንዶች የኑሮ ውድነቱ በዚሁ ከቀጠለ በተለይም በአዲስ አበባ ከተማ በመካከለኛ ገቢ የሚኖሩ ዜጎች የደሃ ደሃ ሊሆኑ እንደሚችሉ ይገምታሉ፡፡

በተጨማሪም ግል መሥሪያ ቤቶች፣ በጋራÎች፣ በእንጨት ቤት፣ በፋብሪካዎችና በመሳሰሉት ቦታዎች በጥበቃ፣ በፅዳት እንዲሁም በተለያዩ የሥራ ዘርፎች ተቀጥረው የሚሠሩ አንዳንድ ሠራተኞች ከሆቴሎች የሚገኙ ተረፈ ምግቦችን (ቡሌ) እስከመመገብ መድረሳቸውን ደግሞ እኚሁ መታዘባቸውን እናት ያስረዳሉ፡፡ እነዚህን የምግብ ዓይነቶችም ለችግር ጊዜ መወጣጫ ያደረጉ ዜጎች ብዙ መሆናቸውን ተመልክተናል፡፡

በአንዳንድ ምግብ በሚያቀርቡ መለስተኛ ሆቴሎች ውስጥ ለመመገብ አነስተኛ ዋጋቸው 150 ብር ሲሆን፣ ከፍተኛ የሚባለው እስከ 500 ብር ይደርሳል፡፡ በተለይም ከቅርብ ጊዜ ወዲህ መለስተኛ የሚባሉ ሆቴሎች የምግብ ዝርዝራቸው አስደንጋጭ ነው፡፡ የኑሮ ውድነቱ በሁሉም የኅብረተሰብ ክፍል ተፅዕኖ ቢያሳድርም፣ ለአንድ ቀን በእነዚህ ቦታዎች ለመመገብ የማይደፍሩ ብዙዎች ናቸው፡፡

በኢትዮጵያ እ.ኤ.አ. በ2015 በኋላ ከድህነት ጠለል በታች የሚባሉ ዜጎች የቀን ገቢያቸው 1.9 ዶላር መሆኑን ጥናቶች ያሳያሉ፡፡

እ.ኤ.አ. 2004 39 በመቶ፣ በ2010 29 በመቶ፣ በ2021 ደግሞ 23 በመቶ ዜጎች ከድህነት ጠለል በታች እንደሚኖሩ ይታወቃል፡፡

በእነዚህ ጊዜያት ውስጥ ከድኅነት ጠለል በታች የሚኖሩት ዜጎች የቀን ገበያቸው 1.9 ዶላር ነው፡፡ ይህ ከሕዝብ ቁጥር መጨመር ጋር ሲታይ፣ በርካቶች ከድህነት ወደ ድህነት ጠለል በታች እየገቡ መሆኑን ያመላክታል፡፡

የሴቶችና ማኅበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር በቀድሞ ሠራተኛና ማኅበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር በ2013 ዓ.ም. ያወጣው መረጃም ይህን ይላል፡፡

በኢትዮጵያ 3.7 ሚሊዮን ሠራተኞች በመንግሥትና በግል ተቋማት ተቀጥረው ይሠራሉ፡፡ ከእነዚህ ውስጥ በወር 546,000 ወይም ከግማሽ ሚሊዮን በላይ የሚሆኑት ከ500 ብር እስከ 1,000 ብር ተከፋይ ናቸው፡፡

ከ1.5 ሚሊዮን ዜጎች ደግሞ ከ1,000 ከእስከ 2,000 ብር በወር የሚያገኙ ሲሆኑ፣ 177,000 የሚሆኑት ከ500 ብር በታች የሚያገኙ ናቸው፡፡

ከ1.5 ሚሊዮን በላይ የሚሆኑ ዜጎች ከ2,000 ከእስከ 5,000 ብር በወር የሚያገኙ ሲሆን ከ5,000 ብር በላይ የሚከፈላቸው ዜጎች ቁጥር ዝቅተኛ ነው፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

[ክቡር ሚኒስትሩ የካቤኔ አባል የሆኑት አንድ ከፍተኛ ባለሥልጣን የሚያቀርቡትን ቅሬታ እያዳመጡ ነው] 

ክቡር ሚኒስትር እየሆነ ያለው ነገር በእጅጉ ስላሳሰበኝ ነው በአካል...

የአፍሪካ ኅብረት ጉባዔና የሶማሊያ ፕሬዚዳንት የፈጠሩት አምቧጓሮ

ባለፈው ቅዳሜና እሑድ በአዲስ አበባ የተካሄደው የአፍሪካ ኅብረት 37ኛው...

የብሔራዊ ባንክ የገንዘብ ፖሊሲ ትግበራ የፈጠራቸው አሉታዊና አዎንታዊ ጎኖች

የአገሪቱ ንግድ ባንኮች በዓመት የሚሰጡት የብድር መጠን ላይ የኢትዮጵያ...

ቱግ ቱግ!

የአፍሪካ ኅብረት ጉባዔ ለመታደም የመጡ እንግዶችን ሸኝተን ከፒያሳ ወደ...