ለነዳጅ የሚደረገውን ድጎማ ደረጃ በደረጃ ለማስቀረት መንግሥት ውሳኔ ላይ ደርሷል፡፡ እስከዚያም ድጎማው በትክክል ይገባዋል ተብሎ ለተለየው የኅብረተሰብ ክፍል ለማድረስ ያስችላል የተባለው አሠራር ከሁለት ሳምንታት በኋላ በይፋ መተግበር ይጀምራል ተብሎ ይጠበቃል፡፡
ለዚህም ወደ ሰባት የሚደርሱ መንግሥታዊ መሥሪያ ቤቶች በጋራና በተናጠል የየራሳቸውን ዝግጅት ሲያደርጉ የቆዩ ሲሆን፣ ሥራውን ለመጀመር የሚያስችላቸው ቁመና ላይ ስለመሆናቸውም እየገለጹ ነው፡፡
ገንዘብ ሚኒስቴር ይፋ እንዳደረገውም ይህ አሠራር ከሐምሌ 1 ቀን 2014 ዓ.ም. ጀምሮ የሚተገበር ሲሆን፣ መልካም ውጤት የሚጠበቅበት እንደሆነም አመልክቷል፡፡ ኢትዮጵያ በአሁኑ ወቅት ለነዳጅ የምታደርገው ድጎማ ወደ 130 ቢሊዮን ብር የተጠጋ መሆኑን የሚያመለክተው የገንዘብ ሚኒስቴር መረጃ፣ ይህንን ድጎማ ይዞ መቀጠል የማይቻል መሆኑንም በይፋ አስታውቋል፡፡
መንግሥት ከነዳጅ ድጎማ ለመውጣት የቀየሰው አዲስ ስትራቴጂ የጊዜ ገደብ የተቀመጠለትና ድጎማ ያስፈልጋቸዋል የተባሉ የትራንስፖርት ዘርፎችን በመለየት፣ ድጎማውን ደረጃ በደረጃ በመቀነስ መንግሥት ከነዳጅ ድጎማ ከአምስት ዓመታት በኋላ ሙሉ ለሙሉ ይወጣል መባሉ ይታወሳል፡፡
የነዳጅ ዋጋ ማስተካከያና የታለመ ድጎማ ትግበራ ቴክኒክ ኮሚቴ የተገኘው መረጃ እንዳመለከተውም፣ የነዳጅ ድጎማ በዋናነት የሚደረግላቸው የሕዝብ ትራንስፖርት አገልግሎት የሚሰጡ ተሽከርካሪዎች ብቻ ናቸው፡፡
ትግበራው በሚጀመርበት ወቅት ድጎማው የሚመለከታቸው የሕዝብ ትራንስፖርት አገልግሎት ዘርፎች ደግሞ አምስት ናቸው፡፡ እነዚህም በከተሞች አካባቢ ያሉ እንደ አንበሳ፣ ሸገርና የመሳሰሉ የሕዝብ ትራንስፖርት አገልግሎት የሚሰጡ ድርጅቶች በመጀመርያው ረድፍ ተቀምጠዋል፡፡ እንደ ሃይገርና ቅጥቅጥ በመባል የሚታወቁ የከተማ የሕዝብ ትራንስፖርት አገልግሎት የሚሰጡ ተሽከርካሪዎች፣ ኮድ አንድና ኮድ ሦስት ሚኒባስ ተሽከርካሪዎች፣ በተለምዶ 12 እስከ 45 ሰዎች የሚጭኑ ታክሲዎችና የአገር አቋራጭ የትራንስፖርት አገልግሎት የሚሰጡ ተሽከርካሪዎች ነዳጅ ድጎማው የሚመለከታቸው ይሆናሉ፡፡ ከእነዚህ ሌላ በኢትዮጵያ ከፍተኛ ቁጥር ያላቸውና በአሁኑ ወቅት ከ190 ሺሕ በላይ ይደርሳሉ ተብለው የሚገመቱት የባለ ሦስት እግር ተሽከርካሪዎች ወይም ባጃጆች የዚህ ድጎማ ተጠቃሚዎች እንዲሆኑ መወሰኑን የኮሚቴው አንድ የሥራ ኃላፊ ለሪፖርት ገልጿል፡፡
እነዚህ የትራንስፖርት ተሽከርካሪዎች የሚሰጣቸው ድጎማ በየዓመቱ እየቀነሰ፣ በአምስተኛው ዓመት ላይ ሙሉ በሙሉ ከድጎማ ወጥተው በገበያ ዋጋ ነዳጅ እየገዙ አገልግሎታቸውን የሚቀጥሉ ይሆናል፡፡ መንግሥት ይህንን የወሰነው የትራንስፖርት ዋጋ እንዳይንርና ታች ያለው የኅብረተሰብ ክፍል እንዳይጎዳ በማለም እንደሆነ በተደጋጋሚ አስታውቋል፡፡ በአንፃሩ ግን መንግሥት በኢትዮጵያ ኢኮኖሚና ለዋጋ ንረት ቀጥተኛ አስተዋጽኦ ያላቸው የደረቅ ጭነት ተሽከርካሪዎች በዚህ አሠራር ያለመካተታቸው ጥያቄዎችን እያስነሳ ነው፡፡ እንደ ሕዝብ ማመላለሻ ተሽከርካሪዎች ሁሉ የደረቅ ጭነት ተሽከርካሪዎች ከድጎማ ውጪ መሆናቸው የዋጋ ንረቱን ሊያባብስ ይችላል የሚል ሥጋት አሳድሯል፡፡
መንግሥት ነዳጅ ከመደጎም ለመውጣት እተገብረዋለሁ ባለው አሠራርና በተለይም የደረቅ ጭነት ተሽከርካሪዎች ድጎማው የማይመለከታቸው በመሆኑ፣ ሊኖረው በሚችለው ተፅዕኖ ዙሪያ ያነጋገርናቸው የኢኮኖሚ ባለሙያ አቶ ሞሼ ሰሙ ግን፣ ችግሩ ከጭነት ተሽከርካሪዎች አለመደጎም ጋር ብቻ የተያያዘ ያለመሆኑን ያስረዳሉ፡፡
በአጠቃላይ አንዱን ወገን በመደጎም፣ ሌላውን ደግሞ ባለመደጎም ይተገበራል የተባለው የጉራማይሌ አሠራር፣ ኢኮኖሚው ላይ ችግር መፍጠሩ አይቀርም ይላሉ፡፡ የደረቅ ተሽከርካሪዎች አለመደጎማቸው ብቻ ሳይሆን ነዳጅ የማይነካካው ነገር ስለሌለ፣ የተወሰነው ስለተደጎመ ወይም የተወሰነው ስላልተደጎመ ኢኮኖሚው ላይ ችግር አይፈጥርም ማለት እንደማይቻል ይጠቅሳሉ፡፡ ድጎማው የማይመለከተውና የነዳጅ ዋጋ የጨመረባቸው ማንኛቸውም የንግድ ድርጅቶች በተጨመረባቸው የነዳጅ ላይ ዋጋ ከመጨመር አይመለሱም፡፡
‹‹ድጎማ አይደረግላቸውም የተባሉ ተሽከርካሪዎችን የሚይዙ ነጋዴዎች የተጨመረባቸውን የነዳጅ ዋጋ ይሸከማሉ ማለት የዋህነት ነው፤›› የሚሉት አቶ ሞሼ፣ እነዚህ የኅብረተሰብ ክፍሎች ነዳጅን የሚወስዱት እንደ ሥራቸው ወጪ አካል አድርገው በመሆኑ፣ በሽያጫቸው ወይም በአገልግሎታቸው ላይ ዋጋ ይጨምራሉ፡፡ ስለዚህ ጉራማይሌ አሠራሩ ለዋጋ ንረት መንስዔ መሆኑ የማይቀር ስለመሆኑ ያስረዳሉ፡፡ ምክንያቱም በቂ አቅርቦትና ውድድር ስለሌለ የኢትዮጵያን ገበያ የተቆጣጠሩት ውስን ነጋዴዎች ስለሆኑ፣ የፈለጉትን ዋጋ ጠርተው የፈለጉትን ነገር የማድረግ ዕድላቸው ሰፊ ይሆናል የሚል እምነት አላቸው፡፡ በትራንስፖርቱ ላይ ዋጋ ቀነሰ ተብሎ ሌላውን አይነካም ማለት የማይቻል መሆኑን የገለጹት ሌላው የኢኮኖሚ ባለሙያ ሰርካለም ገብረ ክርስቶስ (ዶ/ር)፣ አዲሱ አሠራር ለመንግሥት ከፍተኛ ሥራ የሚፈጥር መሆኑ አንድ ጉዳይ ሆኖ፣ አሠራሩ ለዋጋ ንረት መንስዔ መሆኑ አይቀርም የሚል አመለካከታቸውን አንፀባርቀዋል፡፡
በጥቅል ሲታይ አሠራሩ ግርታ የሚፈጥር ስለመሆኑ የሚገልጹት አቶ ሞሼ፣ በአንድ በኩል ነዳጅ እደጉማለሁ፣ በሌላ በኩል ደግሞ ነዳጅ አልደጉምም መባሉ በራሱ ከመርህ ውጪ መሆን ነው የሚል እምነት አላቸው፡፡ ምክንያቱም በትራንስፖርት የሚጠቀሙ ሰዎች ሲደጎሙ እነዚህን ሰዎች ለመጥቀም የተወሰደ ዕርምጃ ከሆነ በአንፃሩ ግን ሌላው ዜጋ የተለየ ዋጋ ለምን ይወጣለታል ይባላል? ይህ ለእኔ ለዜጎች የተለያየ ደረጃ ማውጣት ነው የሚል አመለካት አላቸው፡፡ መንግሥት በድጎማ አምንበታለሁ ካለ ለሁሉም መደጎም ወይም ድጎማውን አልቀበልም ካለ ደግሞ ለሁሉም አለመደጎም ይቻላል፡፡ ‹‹ለምንድነው ለግማሹ የምትደጉመው ለግማሹ የማትደጉመው›› በማለት አሠራሩን በመርህ ደረጃ የሚጣረስ ነገር አለው ብለው ይከራከራሉ፡፡
የፌዴራል ትራንስፖርትና የሎጅስቲክስ ሚኒስቴር የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ አቶ ታጠቅ ነጋሽ ለሪፖርተር እንደገለጹት ደግሞ፣ የደረቅ ትራንስፖርት አገልግሎት የሚሰጡ ተሽከርካሪዎች በድጎማው ውስጥ አለመካተታቸው ለዋጋ ንረት መንስዔ ይሆናሉ ብለው አያምኑም፡፡ ነገር ግን የነዳጅ ዋጋ ማስተካከያና የታለመ ድጎማ ትግበራ የቴክኒክ ኮሚቴ የጭነት ተሽከርካሪዎች የማይደጎሙበት ምክንያት አደረጃጀታቸው የተለየ መሆኑ እንደሆነ መታወቅ አለበት፡፡ ዘርፉ በነፃ ገበያ የሚመራ በመሆኑ፣ የደረቅ ጭነት ተሽከርካሪዎች ዋጋ ላይ መንግሥት ቁጥጥር ስለሚያደርግ በዚህ ድጎማ ውስጥ አልተካተቱም፡፡ በገበያው መሠረት ዋጋ የመወሰን ሥልጣን ስላላቸው መንግሥት ዋጋ ስለማይተምንላቸው፣ እነሱን በአዲሱ ድጎማ አሠራር ማዕቀፍ ውስጥ የሚካተቱ አይሆኑም፡፡ የታለመለት የነዳጅ ድጎማ የሕዝብ ትራንስፖርት አገልግሎት የሚሰጡ፣ እኛ ዋጋቸውንና ታሪፋቸውን የምንቆጣጠርላቸው ብቻ የሚመለከት ይሆናልም በማለት አቶ ታጠቅ ተናግረዋል፡፡ ነዳጅ በጨመረ ቁጥር የዚህን ያህል አጓጉዙ የሚል መመርያ የሚሰጣቸው ከባጃጅ ጀምሮ ከፍተኛ የአገር አቋራጭ የትራንስፖርት አገልግሎት የሚሰጡት ላይ በመሆኑ፣ ከዚህ ድጎማ ውጪ መሆናቸውን ጠቅሰዋል፡፡
መንግሥት የደረቅ ጭነት ማመላለሻዎችን በድጎማ ውስጥ ያላቀፈው የፖሊሲ ለውጥ ስለሚጠይቅ ነው የሚሉት የነዳጅ ዋጋ ማስተካከያና የታለመ ድጎማ ትግበራ ቴክኒክ ኮሚቴ አንድ የሥራ ኃላፊ ደግሞ፣ መንግሥት አቅጣጫ የሚያስቀምጥ ከሆነ በድጎማ ማዕቀፍ ውስጥ ሊገቡ የሚችሉ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡
የደረቅ ትራንስፖርት አገልግሎት ሰጪዎች በድጎማ ውስጥ ያለማለፋቸው ሊያመጣ የሚችለው ተፅዕኖ አነስተኛ ስለመሆኑም ያስረዳሉ፡፡ ነገር ግን አሁን ሥራው ከተጀመረ በኋላ የሚታዩ ክፍተቶች ካሉ ግን እየታዩ ዕርምት የሚወሰድባቸው ይሆናል ብለዋል፡፡
አቶ ሞሼም ሆኑ በጉዳዩ ላይ ያነጋገርናቸው የኢኮኖሚ ባለሙያዎች ግን የታለመ የነዳጅ ድጎማው አሠራር በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ የነዳጅ ዋጋ እስካሁን ከነበረበት እየጨመረ የሚሄድ በመሆኑ፣ ኢኮኖሚው ላይ በተለይ የዋጋ ንረቱ ላይ የሚያደርሰው ተፅዕኖ እንደ ቀላል የሚታለፍ አለመሆኑን ነው፡፡ ሌላው ያነጋገርናቸው የማክሮ ኢኮኖሚው ባለሙያም ይህንኑ ሐሳብ ይጋራሉ፡፡ እንደማይክሮ ኢኮኖሚ ባለሙያው ገለጻ ከሕዝብ ትራንስፖርቱ በበለጠ መደጎም የነበረበት የደረቅ ጭነት ተሽከርካሪዎች መሆን የነበረባቸው፡፡ ለዋጋ ንረት መንስዔ ከሆኑ ምክንያቶች አንዱ የትራንስፖርትና ሎጂስቲክ አገልግሎት በመሆኑ፣ ይህንን ዋነኛ ጉዳይ ታሳቢ ያላደረገ ድጎማ ወይም ቁጥጥር የማይደረግበት አሠራር ተፅዕኖ እንደሚኖረው አስረድተዋል፡፡
በተለይ ምግብ ነክ ምርቶችን የሚያጓጉዙ ተሽከርካሪዎችን በመለየት መደጎም ካልቻሉ፣ የምግብ ዋጋን የበለጠ ሊያንረው ስለሚችል ይህንን ጉዳይ መንግሥት መልሶ ሊያጤነው ይገባል ይላሉ፡፡
አቶ ሞሼ በዚሁ ጉዳይ ጨምረው እንዳስረዱት መንግሥት ከነዳጅ ድጎማ እጁን ሲያነሳ፣ ቀድሞ መሥራት የነበረበት ሥራዎች እንደነበሩ ያመለክታሉ፡፡ ይህም የዚህ አገር የኑሮ ደረጃ የገቢ መጠን ዝቅተኛ በመሆኑ፣ እንዲሁም የአቅርቦትና የፍላጎት ኢኮኖሚው በጣም ጤናማ ስላልሆነ ይህንን ለማስተካከል በተለየ መንገድ የሰዎች ሕይወት ድጋፍ የሚፈልጉ በመሆኑ ነው፡፡ ድጋፍ የሚፈልገውም ወዶ አለመሆኑን የሚገልጹት አቶ ሞሼ፣ ለሠራተኛው በቂ ደመወዝ ሳይከፈል፣ በዓለም አቀፍ ዋጋ መሠረት ነዳጅ ክፈል ሊባል አይገባም ይላሉ፡፡ በዓለም ዋጋ ነዳጅ መክፈል አለብህ ከተባለ ደግሞ ሠራተኛውን በዓለም አቀፍ ደረጃ ደመወዝ ሊከፈለው ይገባል በማለት ይሞግታሉ፡፡ ዝቅተኛ በሆነ ገቢ የሚኖር ሰው የዓለም አቀፍ ዋጋን ተሸከም ማለት ተገቢ ስለማይሆን፣ መንግሥት ይህንን ባላደረገበት ሁኔታ ሌላ ኑሮውን ሊያከብድ የሚችል ጫና መፍጠር ተቀባይት ይኖረዋል ብለው አያምኑም፡፡
ይህንን አባባላቸውን ለማጠናከር የጎረቤት አገሮችን በተለይም ኬንያን ምሳሌ ያደርጋሉ፡፡ የጎረቤት አገሮች ኑሮ ውድ መሆኑ የሚነገረው ያለምክንያት አይደለም፡፡ እነዚህ አገሮች የነፍስ ወከፍ ገቢያቸውና የመግዛት አቅማቸው ከኢትዮጵያ ደመወዝተኛ ጋር ሲወዳደር የሦስት ዕጥፍ ልዩነት አለው፡፡ በዚህ የሦስት እጥፍ ልዩነት ምንም ዓይነት የዓለም አቀፍ ገበያን ለመቋቋም ይችላሉ፡፡ የኢትዮጵያ ደመወዝ ግን የወረደ በመሆኑ ተጨማሪ የኑሮ ውድነትን ለመሸከም ይቅርና የዕለት ኑሮውን ለመግዛት በሆነበት ወቅት ነዳጅ አልደጉምም ብሎ መነሳት ተገቢ እንደማይሆን አስረድተዋል፡፡ ይህ ከሆነ ደግሞ ድጎማው ከተነሳ በኋላ ለድጎማ ይውል የነበረውን ትርፍ ብር ወደ ደመወዝ በመቀየር የሠራተኛው የመግዛት አቅም ከፍ ማድረግ ያስፈልጋል የሚል ሐሳብ ያቀርባሉ፡፡
አብዛኛውን ደመወዝ የሚከፍለው መንግሥት በመሆኑ የሠራኞችን ጉልበት እየተጠቀመ ተገቢ ደመወዝ መክፈል አለበት የሚል ጽኑ አቋም ያላቸው አቶ ሞሼ፣ ከዚህች የደከመች ደመወዝ ላይ ሠራተኛው ቫት እንዲከፍል እንዲሁም ታክስ እንዲከፍል እየተደረገ እንደ ገና ደግሞ በዓለም አቀፍ ገበያ ነው ዕቃ የሚቀርብላችሁ ማለት አይቻልም በማለት ጥቅል አሠራሩን ይኮንናሉ፡፡
ስለዚህ መንግሥት ዜጎች በዓለም አቀፍ ገበያ ተወዳድረው ግብይት ውስጥ እንዲገቡ ከፈለገ፣ በኢትዮጵያ አቅም ያሉ አገሮች የሚከፈለውን ደመወዝ መክፈል አለበት፡፡
እንደ ሊብራል ዴሞክራት እምነቴ በድጎማ የማምን ሰው አይደለሁም፣ ‹‹በድጎማ አላምንም›› የሚሉት አቶ ሞሼ፣ ነገር ግን ነባራዊ ሁኔታው ካስገደደ ድጎማ ይኖሪል፡፡ አሜሪካ የኢኮኖሚ መቀዛቀዝ (ሪሴሽን) ውስጥ ስትገባ ለዜጎቿ ገንዘብ ትሰጣለች፡፡ ስለዚህ አንድ አገር የዜጎቹ የኑሮ ሁኔታ በሚፈለገው ደረጃ ባልተስተካከለበት፣ ገቢያቸው በጣም ዝቅተኛ በሆነበት ጊዜ የእነዚህን ሰዎች ሕይወት መታደግ ያስፈልጋል፡፡
መንግሥት ድጎማ የሚያስገድደው ነገር የሌለ መሆኑን የሚጠቁሙት አቶ ሞሼ እንደ ፖሊሲ ይህን መከተል ይችላል፡፡ ነገር ግን የዜጎችን የኑሮ ሁኔታ ለማሻሻል ምን እየተደረገ ነው? ደመወዙን ለማሻሻል ምን እየተሠራ ነው? ምርት በበቂ ሁኔታ ወደ ገበያ ገብቶ በካሽ የሚያገኝበት ሁኔታን እንዴት እየተመቻቸ ነው? ለሚሉት ጥያቄዎች መንግሥት መልስ መስጠት አለበት፡፡
ሰርካለም (ዶ/ር) ደግሞ፣ አዲሱ አሠራር ብዙ ነገር የሚነካካ ይሆናል ብለዋል፡፡ የነዳጅ ዋጋ የተወሰነ ለውጥ ካመጣ የዋጋ ንረት ላይ ተፅዕኖ መፍጠሩ አይቀርም፡፡ ነገሩን የበለጠ ሊያወሳስበው ይችላል የሚል ሥጋትም አላቸው፡፡ በእሳቸው እምነት መንግሥት ለተወሰነ ጊዜ እንደ ቀድሞ ድጎማውን እያደረገ የተወሰነ ጭማሪ እያደረገ ቢቀጥል ይሻል ነበር የሚል እምነት አላቸው፡፡ አሁን ይተገበራል የተባለውን በቀላሉ መሬት ላይ ማውረድ እንደሚከብድም ይናገራሉ፡፡ ይሠራበታል የተባለው እንደ ኩፖን ዓይነት አሠራር ለሙስና የበለጠ ተጋላጭ ሆኖ አሠራሩን ያወሳስባል የሚል ሥጋት አላቸው፡፡ ሰርካለም (ዶ/ር) ከዚሁ ሁሉ ነገር ቁጥጥሩን በማጥበቅ ለተወሰነ ጊዜ የቀድውን አሠራር መተግበር ጥሩ መፍትሔ ይሆናል ብለው ያምናሉ፡፡
አቶ ሞሼም ቢሆኑ በተለያየ ዋጋ ተከፋፍሎ ለገበያ ይቀርባል የተባለው አሠራር ለሙስና የተመቸ እንደሚሆን ተናግረዋል፡፡ በአጠቃላይ ግን አሠራሩ የዋጋ ንረት መፍጠሩ ያሳስበኛል ብለዋል፡፡ ሰሞኑን ከኢቲቪ ጋር ቆይታ የነበራቸው የገንዘብ ሚኒስትር ዴኤታው ኢዮብ ተካልኝ የታለመ የነዳጅ ድጎማው ለምን እስካሁን ዘገየ በሚያስብል ደረጃ ጥሩ ውጤት የሚመዘገብበት ይሆናል በማለት በእርግጠኝነት ተናግርዋል፡፡
ከድጎማው ለመውጣት አራት ሩብ ዓመታት የተቀመጡ ሲሆን ሐምሌ 2014 ላይ 25 በመቶ፣ ኅዳር ላይ 50 በመቶና መጋቢት ላይ 75 በመቶ አድርገን ሰኔ ላይ ለማጠቃለል ነው፡፡ ድጎማ የሚደረግበትን ደግሞ በየስድስት ወራት አሥር አሥር በመቶ ድጎማውን በማስቀረት በአምስት ዓመት ከድጎማው ለመውጣት ነው፡፡