Tuesday, February 27, 2024

የጋምቤላ ትኩሳት

- Advertisement -spot_img

በብዛት የተነበቡ

ባለፉት አራት ዓመታት በኢትዮጵያ በየአቅጣጫው ብዙ ግጭትና ፍጅት ሲፈጠር፣ በጋምቤላ ክልል ያለው ሁኔታ ግን በአንፃራዊነት ሰላምና መረጋጋት የሚታይበት ይመስል ነበር፡፡ አለፍ ገደም እያለ በክልሉ ሲፈጠር የቆየው ጥቃትና የዜጎች ግድያ ባለፈው ሰሞን ከበድ ያለ ውጊያ ተብሎ ሊጠቀስ የሚችል ግጭት ማስከተሉ ይታወሳል፡፡ ከዚህ ቀደም ደም አፋሳሽ ግጭቶች የጎበኘው የጋምቤላ ክልል ከሰሞኑ የደረሰውን ግጭት ተከትሎ፣ ወደ በለጠ አለመረጋጋት እንዳያመራ የብዙዎች ሥጋት ሆኗል፡፡

ሰኔ 7 ቀን 2014 ዓ.ም. በክልሉ መዲና ጋምቤላ ከተማ የኦነግ ሸኔና የጋምቤላ ነፃነት ግንባር (ጋነግ) ታጣቂ ቡድኖች ባደረሱት ጥቃት፣ ለቀናት የዘለቀ የተኩስ ልውውጥና አለመረጋጋት ማስከተሉ አይዘነጋም፡፡ የክልሉ መንግሥት ባለሥልጣናት አሸባሪ ያሏቸውን የሁለቱ ቡድን ታጣቂዎችን በመደምሰስ ሰላምና መረጋጋት ዳግም ማስፈን መቻላቸውን ይናገራሉ፡፡ በከተማው ዳግም የንግድ እንቅስቃሴና መደበኛ ሕይወት መመለሱንም ገልጸዋል፡፡

ይሁን እንጂ የፀጥታ መደፍረሱን ያስከተለው ግጭት ዳግም ሊያገረሽ ይችላል ብለው የሚሠጉ ወገኖች በርካታ ናቸው፡፡ ከዚህ ጎን ለጎን አጋጣሚውን የፈጠረው ችግር በዘላቂነት መፈታቱን የሚጠራጠሩ ወገኖችም አሉ፡፡

ጥቃቱን አደረሱት ከተባለው አንዱ የጋምቤላ ነፃነት ግንባር ቡድን ማነው? ኦነግ ሸኔ በሰፊው ከሚንቀሳቀስበት ከኦሮሚያ ወይም ከደቡብና ከአማራ ክልሎች አልፎ በጋምቤላ ጥቃት ለማድረስ ምን አነሳሳው? ከእነዚህ ኃይሎች በስተጀርባ የተሠለፉ የፖለቲካ ፍላጎት ያላቸው ወገኖች ካሉስ እነማን ናቸው የሚሉ ቁልፍ ጥያቄዎችን የሰሞኑ የጋምቤላ ግጭት አስነስቷል፡፡

የሰሞኑ የጋምቤላ ግጭት በተለይ በግለሰቦች ላይ የተፈጸሙ አሰቃቂ ግድያዎችን ማስከተሉና ይህም በቪዲዮ ተቀናብሮ በማኅበራዊ የትስስር ገጾች መሠራጨቱ፣ ብዙ ዘግናኝ ውጤት የተከሰተበት ግጭት ነው የሚል ግምት አሳድሯል፡፡ ይህን መሰል አሰቃቂ ግጭት ሳይታሰብና በድንገት ከመድረሱ በፊት፣ ገምቶ ድርጊቱ ሳይፈጠር እንዴት መከላከል አልተቻለም የሚለው ጥያቄ ጎልቶ እየተደመጠ ነው፡፡

የጋምቤላ ክልል ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ኃላፊ ኡጉት አዲንግ የጋምቤላ ነፃነት ግንባርና የኦነግ ሸኔ ታጣቂዎች፣ ሲቪል ለብሰው ጥቃቱን መክፈታቸውን ይናገራሉ፡፡ የፀጥታ ኃይሎች ሰላማዊውን ሲቪል ሕዝብ ‹‹አሸባሪ›› ከሚሏቸው ኃይሎች በነጠለ መንገድ ዕርምጃ ለመውሰድ መቸገራቸውንም ይገልጻሉ፡፡ አልፎ አልፎ አንዳንድ የፀጥታ ኃይሎች በእልህና በቁጣ ያልተመጣጠነ ኃይል መጠቀማቸውንም አምነዋል፡፡ ሆኖም በቪዲዮ ተቀርፀው የወጡ የደቦ ግድያ ምሥሎች በዋናነት ብሔርን ከብሔር ለማጋጨት፣ በተለይም ጋምቤላን ከኦሮሚያ ጋር ለማጣላት ያለመ ሴራ አካል ናቸው ብለው እንደሚያምኑ ነው አቶ ኡጉት የተናገሩት፡፡

‹‹ሕዝብ ውስጥ ተቀላቅሎ ሲቪል ለብሶ የሚዋጋ ኃይልን መልቀም ቀላል አይደለም፡፡ የሕወሓት ተላላኪ የሆኑት ጋነግና ኦነግ ሸኔ የብሔር ግጭት መቀስቀስና በተለይ ጋምቤላን ከኦሮሚያ ጋር የማጋጨት ዓላማ ይዘው ነው ያጠቁን፤›› በማለት ነው የኮሙዩኒኬሽን ኃላፊው አቶ ኡጉት ያስረዱት፡፡

የጋምቤላ ክልል ርዕሰ መስተዳድር የማኅበራዊ ጉዳይ አማካሪ ፒተር አማን፣ አሸባሪዎቹ ከባድ ኪሳራ ደርሶባቸው እንደ አመጣጣቸው መመለሳቸውን ይናገራሉ፡፡ ‹‹ሆኖም ጠላት ስለማይተኛ አንዘናጋም፤›› ያሉት አቶ ፒተር፣ ‹‹በአምስቱም ቀበሌዎች ሕዝቡን ሰብስበን ለአሸባሪዎቹ መደበቂያ ዋሻ እንዳይሆን በማሳሰብ ራሱን እንዲከላከል መልዕክት አስተላልፈናል፤›› ብለዋል፡፡

የጋምቤላ ሕዝብ ነፃነት ዴሞክራሲያዊ ንቅናቄ ፓርቲ (ጋህነዴን) ሊቀመንበር ሻምበል ኡኬሎ ኡክዲ፣ ባለፉት ሦስት ዓመታት በጋምቤላ ሰዎች ቢሞቱም ነገር ግን እንደ ሰሞኑ ዓይነት ውጊያ አጋጥሞ አያውቅም ይላሉ፡፡

ኦኬሎ (ሻምበል) እንደሚናገሩት ጥቃቱን የከፈቱት ኃይሎች ዋና ዓላማ የብሔር ግጭት ማስነሳት ነበር፡፡ ‹‹የአጥቂዎቹ ጥቃት በጅምላ ሳይሆን፣ መርጦ የተወሰኑ ማኅበረሰቦች ላይ ያተኮረ ቢሆን ኖሮ ግጭቱ ወደ በቀል ያመራ ነበር፤›› በማለትም ተናግረዋል፡፡

ስማቸው እንዲጠቀስ ያልፈለጉ አንድ የክልሉ ባለሥልጣን በበኩላቸው፣ ጥቃቱ በተቀነባበረ ሴራ መካሄዱን ነው የሚናገሩት፡፡ ‹‹ምንም ሳይፈጠር አስቀድመው ወደ ጋምቤላ ከተማ ሰዎች በማስገባት ሲዘጋጁ ነበር፡፡ በጥቃቱ ቀን ድንገት ወደ ከተማ ገብተው ተኩስ ከከፈቱት በላይ፣ ከተማው ውስጥ ቀድመው ሰርገው የገቡት ሲቪል ለብሰው የፀጥታ ኃይሎች ላይ ጉዳት አድርሰዋል፡፡ ሕንፃዎችን ተቆጣጥረውና ወሳኝ ቦታዎችን ቀድመው ይዘው በስናይፐርና በከባድ መሣሪያ የተጠና ጉዳት ለማድረስ ሞክረዋል፤›› በማለት የተናገሩት አስተያየት ሰጪው፣ ጥቃቱ በበቂ ዝግጅት የተደረገ መሆኑን አመልክተዋል፡፡

ከአንድ ዓመት በፊት እ.ኤ.አ. ሰኔ 21 ቀን 2021 ዓ.ም. ኢትዮጵያ ኢንሳይት (Ethiopia Insight) በተባለ ድረ ገጽ ላይ የወጣ አንድ ጽሑፍ፣ የአሁኑን ዓይነት ግጭት በጋምቤላ ሊደርስ እንደሚችል ጥቆማ የሚሰጥ ነበር፡፡ ‹‹ግድ የለሽነት የሚንፀባረቅበት የማዕከላዊ መንግሥት አቋም በጋምቤላ ማኅበረሰቦች ዘንድ የተፈጠረውን የጦፈ ፉክክር ይበልጥ ያፋፍማል፤›› በሚል ርዕስ ሰፊ ጥናታዊ ጽሑፍ ያስነበቡት ኦኬሎ ምሩ፣ የጋምቤላ ክልል ፖለቲካ ጥንቃቄ በተሞላው መንገድ ካልተያዘ ትኩሳቱ ለአገር የሚተርፍ መሆኑን በብዙ መረጃዎች አስደግፈው አቅርበው ነበር፡፡ የጋምቤላን የሕዝብ አሰፋፈርና ፖለቲካዊ ውክልና የቀየሩ አጋጣሚዎችን ያነሱት ጸሐፊው፣ በንጉሡ ዘመንና በደርግ ወቅት የኢትዮጵያ መሪዎች አስታመው የያዙትን የጋምቤላ ፖለቲካን የኢሕአዴግ ባለሥልጣናት እንዳበለሻሹት ይገልጻሉ፡፡ በኢሕአዴግ እግር የተተካው የአሁኑ መንግሥትም ልክ እንደ ቀደመው ሁሉ የጋምቤላን ፖለቲካ አያያዙን እንዳልቻለበት ነው የሚተቹት፡፡

ረዥም ዘመናት ያስቆጠረው የደቡብ ሱዳንና የሱዳን ጦርነት የጋምቤላን ዲሞግራፊ ስብጥር ቀይሮታል፡፡ በ1984 ዓ.ም. በተሠራ ጥናት በጋምቤላ 300 ሺሕ ስደተኞች ሰፍረው እንደነበር ያረጋግጣል፡፡ ይህ የዲሞግራፊ ጫና በተለይ በሁለቱ ዋነኛ የክልሉ ጎሳዎች ማለትም በአኙዋና በኑዌር መካከል የግጦሽ፣ የእርሻና የተፈጥሮ ሀብት ፉክክር እንደፈጠረ ኦኬሎ በጽሑፋቸው ያወሳሉ፡፡ በደርግ ወቅት በጋምቤላ እንዲሰፍሩ ከተደረጉ በአሥር ሺዎች ከሚቆጠሩ ‹‹ደገኞች›› በተጨማሪ፣ ወደ ጋምቤላ ክልል የሚደረገው የደቡብ ሱዳኖች ስደት እስከ ቅርብ ጊዜ መቀጠሉ በጎሳዎች መካከል የሚካሄደውን የተፈጥሮ ሀብት ፉክክር የበለጠ እየጨመረው መምጣቱን ያስረዳሉ፡፡ በክልሉ በዚህ መሰል የጎሳ ፖለቲካ ሽኩቻ መነሻነት 2007 እና 2008 ዓ.ም. ጨምሮ በተለያዩ ዓመታት ተደጋጋሚ ግጭቶች እንደጎበኘውም ጸሐፊው ያስታውሳሉ፡፡

‹‹ይህ ሁሉ ነባራዊ ሁኔታ ከግምት ሳይገባና የክልሉ ነባር የችግር ምንጭ ሳይጤን የለውጡ መንግሥት በ2011 ዓ.ም. በጥር 1996 ዓ.ም. የወጣውን የኢትዮጵያን የስደተኞች ሕግ አሻሻለው፡፡ የስደተኞች የመኖሪያ ፈቃድ ማግኘትን ጨምሮ ሥራና ትምህርት ማግኘት እንዲችሉም ፈቀደ፡፡ መንግሥት አዋጁን ያሻሻለው ከውጭ በሚያገኘው ዕርዳታ የኢንዱስትሪ መንደሮችን በመክፈት ለውጭ ስደተኞች ዘላቂ የኑሮ መሠረት እፈጥራለሁ ብሎ ነበር፡፡ ይሁን እንጂ ከ400 ሺሕ በላይ ስደተኞችን በያዘው ጋምቤላ ክልል አንዳችም የኢንዱስትሪ መንደር ሳይቆረቁር፣ ለስደተኞቹ የበለጠ ነፃነትን በመፍቀድ ብቻ ሥራውን ተወው፡፡ ይህ ደግሞ በጋምቤላ ጎሳዎች መካከል የበለጠ ፉክክርና ግጭትን የጋበዘ ሆነ፤›› በማለት ነው አቶ ኦኬሎ የጋምቤላን ውስብስብ የፖለቲካ ትኩሳት የከተቡት፡፡

በምርጫ ዋዜማ ላይ ሆነው ይህን ሰፊ ጽሑፍ ያስነበቡት አቶ ኦኬሎ፣ በጋምቤላ ክልል ያለውን የተፈጥሮ ሀብት ፉክክር፣ የወሰን ግጭት፣ ከስደትና ከፍልሰት ጋር በተያያዘ የመጣውን የሕዝብ ቁጥርና ስብጥር ጫና፣ እንዲሁም በፖለቲካ ውክልና ጥያቄ የተነሳ የሚፈጠሩ ውዝግቦችን መንግሥት በጥንቃቄ በማጤን መፍትሔ እንዲሰጥ ጠይቀው ነበር፡፡ ይሁን እንጂ በጊዜው በምርጫው ድግስ እንጂ ለዚህ መሰሉ ጉዳይ ትኩረት የሰጠ አለመኖሩ ነው የሚነገረው፡፡ ምርጫው በጋምቤላ ከተደረገ በኋላ የጋምቤላ ብልፅግና ፓርቲ አንዳንድ ተቃዋሚ ኃይሎችን አሰባስቦና ሥልጣን አጋርቶ መንግሥት መሠረተ፡፡

በምርጫው ሲፎካከሩ ከነበሩ ፓርቲዎች መካከል የጋምቤላ ሕዝቦች ፍትሕ ለሰላምና የልማት ዴሞክራሲያዊ ንቅናቄ ከተባለው ፓርቲ ውስጥ፣ በምርጫው የተከፉ ኃይሎች ተገንጥለው ወደ ትጥቅ ተቃውሞ ገቡ ይላሉ ጉዳዩን በቅርበት የሚከታተሉ ወገኖች፡፡

ስሜ አይጠቀስ ብለው አስተያየት የሰጡት የክልሉ ባለሥልጣን፣ ‹‹የጋምቤላ ነፃነት ግንባር ዛሬ የሚመራውና በክልሉ ላይ ጥቃት የከፈተው ሰው ለውጡ ሲመጣ የፌዴራሊስት ኃይሎች ነን ብለው መቀሌ ከሕወሓት ጋር ስብሰባ ከሚሳተፉ ፖለቲከኞች አንዱ ነበር፡፡ እሱና የሸኔ ኃይሎች የሕወሓትን ተልዕኮ ተቀብለው የሚንቀሳቀሱ ኃይሎች ናቸው፡፡ ሰውየው ወደ ምርጫ የገባውም ሥልጣን እንደማያጣ እርግጠኛ ሆኖ ነበር፡፡ ሲሸነፍ ግን መሸነፉን ባለመቀበል በክልሉ ላይ ጦርነት አወጀ፤›› በማለት ነው የተናገሩት፡፡ በጋምቤላ የዲሞግራፊ ስብጥሩ መቀያየሩም ሆነ በተፈጥሮ ሀብት ይገባኛል የሚነሳው ግጭት ከፍተኛ ቢሆንም፣ ነገር ግን ‹‹የጋነግ ሰዎች ፍላጎት የሥልጣን ጥማት ነው፤›› በማለት ይህ ደግሞ በኃይል እንደማይሳካ ባለሥልጣኑ ተናግረዋል፡፡

የጋምቤላ ርዕሰ መስተዳድር የማኅበራዊ ጉዳዮች አማካሪው ፒተር አማን በበኩላቸው፣ ከጋነግ ጀርባ ሕወሓትና ኦነግ ሸኔ የመሳሰሉ ቡድኖች መሠለፋቸው ዋና ችግር ቢሆንም፣ ነገር ግን የቡድኑ እንቅስቃሴ ከዚህ ባለፈ መታየት እንዳለበት ይናገራሉ፡፡ ‹‹የጉሙዝ ነፃ አውጪ ነን የሚሉ ኃይሎችም ከቡድኑ ጋር ተሠልፈዋል፡፡ ስደትና የደቡብ ሱዳን ድንበር ጥብቅ ቁጥጥር የማይደረግበት መሆኑ ትልቅ ራስ ምታት ነው፡፡ በዚህ ድንበር አካባቢ ግብፆችና ሱዳኖች ጭምር ሥልጠና እየሰጡ የሚያሰርጉት ኃይል መኖሩን መረጃው አለን፤›› በማለት ይናገራሉ፡፡

‹‹ትልቁ ጥቃታችን እንግዳ ተቀባይ መሆናችን ነው፤›› በማለት የሚናገሩት አቶ ፒተር፣ ዋና አስጠቂዎቹ ደግሞ ‹‹ከውስጣችን የወጡት የጋነግ ኃይሎች ናቸው፤›› በማለትም ያክላሉ፡፡ ሕወሓት ነባሮቹን አኙዋና ኙዌርን ማጋጨትን እንደ አንድ የፖለቲካ ስትራቴጂ ይጠቀምበት እንደበር የጠቀሱት አቶ ፒተር፣ ይህን አሁን ለመድገም መሞከሩ ያለፈበት ፋሽን ነው ብለውታል፡፡

ኦኬሎ ኡክዲ (ሻምበል) በበኩላቸው ታጣቂዎቹም ሆነ ከጀርባቸው አሉ የሚባሉ ቡድኖች፣ የጋምቤላን የተፈጥሮ ሀብትና ሥልጣን ለመቆጣጠር አልመው የተነሱ ቡድኖች ናቸው የሚል መላምት ጎልቶ እንደሚነሳ ይናገራሉ፡፡ ‹‹በምርጫ ወቅት ምርጫውን አንቀበለውም ብለው በመውጣት መሣሪያ አነሱ፡፡ ብሔርን በተመለከተ የእኛ ብዙ  ነው የተሻለ ውክልና ይገባናል የሚል ጥያቄም አንስተዋል፡፡ ነገር ግን በሁለቱም መንገድ ካየነው ጉዳዩ የሥልጣን ሽኩቻና የበላይነት ፍላጎት የፈጠረው ነው፤›› ሲሉ ነው አቶ ኦኬሎ የተናገሩት፡፡

‹‹መንግሥት ሁሉንም ኃይሎች በውይይት መድረክ አሰባስቦ ችግራቸውን በጠረጴዛ ዙሪያ እንዲፈቱ ሁኔታዎችን በማመቻቸት ብዙም አልሠራም፤›› ሲሉ ያከሉት አቶ ኦኬሎ፣ ‹‹በፖለቲካ ካረጁና ከግትር ሰዎች ይልቅ ሕዝቡ ቢወያይ የበለጠ መፍትሔ ያመጣል፤›› ሲሉ መፍትሔ የሚሉትን ነጥብ አቅርበዋል፡፡

ሰሞነኛው የጋምቤላ ግጭት ከተራ የሽብር ቡድኖችና ታጣቂዎች ጋር ሕግ ለማስከበር የተደረገ ተራ የተኩስ ልውውጥ ነው ብሎ ለመቀበል የሚቸገሩ በርካታ ናቸው፡፡ በክልሉ ምክር ቤት ሕንፃ ላይ ጭምር ጥቃት በመክፈት አንድ የጥበቃ ባልደረባን መግደላቸውን የጠቀሱ ወገኖች፣ ታጣቂዎቹ የክልሉን መንግሥታዊ መዋቅር ለመቆጣጠር አልመው የተቀናጀ ውጊያ መክፈታቸውን ሲናገሩ ይደመጣል፡፡

ይህን በተመለከተ የተጠየቁት አቶ ፒተር አማን፣ ‹‹ይህን ያህል ጉዳት ያደርሳሉ ተብሎ ባልታሰበ ሰዓትና ሁኔታ ነው ከተማውን ለመውረርና ጥቃት ለማድረስ የሞከሩት፤›› ብለዋል፡፡ ‹‹ጋምቤላ ከመሀል አገርም፣ ከጎረቤት አገርም ሁሉም መጥቶ ሠርቶ የሚለወጥባት ክልል እንጂ፣ ጥቃትና ግጭት የሚከፍቱባት አይደለችም፤›› ሲሉ ያከሉት ፒተር፣ የጥቃት ፈጻሚዎቹ ዓላማ ‹‹የጋምቤላ ሕዝቦችን እርስ በርስ ማፋጀት፣ የጋምቤላ ሕዝቦችን ከሌሎች ብሔሮች ጋር ማጋጨት፣ ከተቻለም ከጎረቤት አገሮች ጋር ማናከስ ነበር፤›› በማለት ረዥም የሴራ ድር ያለው መሆኑን ጠቁመዋል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ትኩስ ጽሑፎች

ተዛማጅ ጽሑፎች

- Advertisement -
- Advertisement -