የቸርቻሪዎች የትርፍ ህዳግ አምስት በመቶ እንዲሆን ተወስኗል
የነዳጅ ማደያ በሌለባቸው ከተሞችና አከባቢዎች በሕገወጥ ንግድ ለሚከናወነው የነዳጅ ችርቻሮ ሽያጭ የወጣ አዲስ መመርያ፣ የነዳጅ ማደያ ካለበት በ20 ኪሎ ሜትር በሚርቁ አካባቢዎች የነዳጅ ውጤቶች በቸርቻሪዎች እንዲሸጡ ፈቀደ፡፡
አዲሱ መመርያ ማደያ በሌለባቸው አካባቢዎች የነዳጅ ውጤቶች የሚሸጡበትን የዋጋ ተመን የሚሰላበትን መንገድ ያስቀመጠ ሲሆን፣ ቸርቻሪዎች የትርፍ ህዳጋቸው አምስት በመቶ እንደሚሆን ወስኗል፡፡ ይህ የትርፍ ህዳግ መንግሥት ለመደበኛ የነዳጅ ማደያዎች ካወጣው የ0.23 በመቶ ትርፍ ህዳግ አንፃር ከፍተኛ ነው ተብሏል፡፡
የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስቴርና የነዳጅና ኢነርጂ ባለሥልጣን በጋራ ያወጡት ይህ መመርያ በችርቻሮ የሚቀርበው ነዳጅ ተገቢ ባልሆነ ዋጋና በሕገወጥ ንግድ መልክ የሚከናወን በመሆኑ፣ ይህንኑ የአሠራር ክፍተት ለመሙላት ታስቦ የተዘጋጀ መሆኑ ተገልጿል፡፡ መመርያው የነዳጅ ችርቻሮ ንግድ የሚመራበት፣ የነዳጅ ዋጋ የሚወሰንበት፣ ቁጥጥር የሚደረግበትና የአካባቢ ደኅንነት የሚጠበቅበት የአሠራር ሥርዓት የሚዘረጋ ነው፡፡
ኢትዮጵያ ውስጥ ያሉት 1‚200 ገደማ የነዳጅ ማደያዎች ካለው ፍላጎት አንፃር በቂ ባለመሆናቸው ምክንያት፣ ማደያ በሌለባቸው አካባቢዎች ከማደያዎች የሚገዛ ነዳጅ በችርቻሮ መሸጥ የተለመደ ነው፡፡ ይሁንና ሽያጩ በምን ዓይነት መንገድ ይመራ የሚለው ባለመደንገጉ አንድ ሊትር ነዳጅ እስከ 80 ብር እንደሚሸጥ፣ ነዳጁ አግባብ ባለው መንገድ የሚጓጓዝ ባለመሆኑ ለትነት እንደሚዳረግ የነዳጅና ኢነርጂ ባለሥልጣን ኮሙዩኒኬሽን ዳይሬክተር በቀለች ኩማ ለሪፖርተር ተናግረዋል፡፡ ከመሸጫው ዋጋ ባሻገርም ከደኅንነት አንፃር የችርቻሮ ገበያው ሥጋት ያለበት በመሆኑ፣ ቸርቻሪ የሚሆኑ አካላት ሊያሟሉ የሚገባቸውን ቅድመ ሁኔታዎች ለማስቀመጥ የታለመ መሆኑንም አስረድተዋል፡፡
በአዲሱ መመርያ መሠረት ይህንን አሠራር በበላይነት የሚመራው የነዳጅና ኢነርጂ ባለሥልጣን ሲሆን፣ የክልልና የከተማ አስተዳደር ንግድ ቢሮዎች የነዳጅ ውጤቶችንና የችርቻሮ ንግድ አፈጻጸም መረጃዎችን በማደራጀት በየወሩ ለባለሥልጣኑ ሪፖርት የማድረግ ግዴታ ተጥሎባቸዋል፡፡
ለባለሥልጣኑና ለክልሎች የነዳጅ ማደያ የሌለባቸው ከተሞችና አከባቢዎች እነ ማን እንደሆኑ ለይቶ መረጃ የማቅረብ ኃላፊነት የተጣለው በዞኑ ያሉ የንግድ መምርያዎች ላይ ነው፡፡ የዞን መምርያዎች ከየወረዳው የሚቀርብላቸውን የነዳጅ ፍላጎት መሠረት በማድረግ፣ ማደያ ባለባቸው ከተሞችና አካባቢዎች ነዳጅ በችርቻሮ የሚያቀርቡ ቸርቻሪዎችን ብዛት የመወሰን ሥልጣን ተሰጥቷቸዋል፡፡
ዞኖች የነዳጅ ችርቻሮ ፈቃድ የሚሰጣቸው ቸርቻሪዎች የሚገኙት የነዳጅ ማደያ ካለበት አካባቢ ቢያንስ 20 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ መሆኑን የማረጋገጥ ኃላፊነት ያለባቸው ሲሆን፣ የተፈቀደላቸውን ቸርቻሪዎች ወርኃዊ የነዳጅ ፍላጎት ዓይነትና መጠን በመጥቀስም ትስስር የተደረገላቸው የነዳጅ ማደያዎች እንዲሸጡላቸው ይጠይቃሉ፡፡
መመርያው እንደሚገልጸው ማደያ በሌለባቸው አከባቢዎች ያለው የነዳጅ ፍላጎት ዓይነትና መጠን ምን ያህል ነው የሚለው የሚወስኑት ወረዳዎች ናቸው፡፡ ይህንን ለማድረግም የወረዳ ንግድ ጽሕፈት ቤቶች በወረዳው የሚገኙትን የነዳጅ ውጤቶች የሚጠቀሙ ተሽከርካሪዎች፣ ኢንዱስትሪዎች (ወፍጮ)፣ ጄኔሬተሮችና ሌሎች የነዳጅ ውጤቶችን ፍላጎት ዓይነትና መጠን በማጥናት ለዞኖች ያቀርባሉ፡፡
በእነዚህ አካባቢዎች የነዳጅ ችርቻሮ ፈቃድ ለማግኘት ፈቃድ የሚጠይቁ አካላት ነዳጁን የሚያገኙት፣ የሚፈልጉትን የነዳጅ መጠንና ዓይነት የሚገልጽ ደብዳቤ ከወረዳ ወይም ከከተማ መስተዳድር ንግድ ጽሕፈት ቤት የድጋፍ ደብዳቤ ለዞኖች ሲያቀርቡ ነው፡፡ ከዚህም ጋር ተያይዞ የጠየቁትን የነዳጅ መጠን ለመያዝ የሚያስችል ማከማቻ ያላቸው መሆኑ ከንግድ ጽሕፈት ቤቱ መቅረብ አለበት፡፡
የችርቻሮ ነዳጅ ሻጮቹ ፈቃድ ካገኙም በኋላ ቢሆን ነዳጅ እንዲያቀርብላቸው ከተዋዋሉት የነዳጅ ማደያ ውጪ መግዛትና ከተፈቀደላቸው የመሸጫ ቦታ ውጪ መሸጥ ተከልክለዋል፡፡ ነዳጅ አዳዮችም በተመሳሳይ ከተፈቀደለትና ውል ከፈጸመው የነዳጅ ውጤቶች ቸርቻሪ ነጋዴ ውጪ ላልተፈቀደለት ሌላ ቸርቻሪ መሸጥ እንደማይችሉ በመመርያው ተደንግጓል፡፡
መመርያው የችርቻሮ ነዳጅ መሸጫ ዋጋ እንዴት መሠራት እንዳለበትም አስቀምጧል፡፡ በመመርያው መሠረት የነዳጅ ውጤቶች የችርቻሮ መሸጫ ዋጋ ሲተመን ነዳጁ በማደያ የሚሸጥበት ዋጋ፣ የትራንስፖርት ወጪ፣ የመጫኛና የማራገፊያ ወጪ፣ ብክነትና ትነት፣ እንዲሁም የቸርቻሪው የትርፍ ህዳግ ሒሳብ ውስጥ ይገባሉ፡፡
በአስፋልት ወይም በጠጠር የሚለየው የትራንስፖርት ወጪን ጀምሮ ሁሉም ወጪዎች ከተደመሩ በኋላ፣ የቸርቻሪዎች የትርፍ ህዳግ የሆነው የድምር ውጤቱ አምስት በመቶ ሒሳቡ ውስጥ ተጨምሮ ነዳጁ ለገበያ ይቀርባል፡፡
የኮሙዩኒኬሽን ዳይሬክተሯ በቀለች እንደሚያስረዱት፣ የቸርቻሪዎች የትርፍ ህዳግ ከፍ የተደረገው ቸርቻሪዎች መሠረተ ልማት በሌለባቸው አካባቢዎች ጭምር በመግባት ነዳጅ የሚያቀርቡ በመሆናቸው ነው፡፡
በመመርያው ላይ በተቀመጠው ተዋረድ መሠረት በእነዚህ አካባቢዎች ቸርቻሪዎች ይኖራሉና ምን ያህል ነዳጅ ያስፈልጋቸዋል የሚለው መረጃ እንደሚሰበሰብ አስረድተዋል፡፡ ከመመርያው ባሻገር ቸርቻሪ ለመሆን ፈቃድ የሚያገኙ አካላት ሊያሟላቸው የሚገቧቸው ዝርዝር ቅድመ ሁኔታዎችም ወደፊት እንደሚገለጹ አክለዋል፡፡
መመርያው ነዳጅ በችርቻሮ መሸጥ የሚቻለው ማደያ ካለበት በ20 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ ባሉ አካባቢዎች እንደሆነ ቢያስቀምጥም፣ ዳይሬክተሯ ይህ አሠራር አዲስ አበባ ከተማን እንደማይመለከት ተናግረዋል፡፡