Friday, December 8, 2023

የሰላም አስከባሪ የሚያዋጡ አገሮች የሴቶችን ቁጥር እንዲያሳድጉ ተጠየቀ

- Advertisement -spot_img

በብዛት የተነበቡ

አገሮች ለሰላም አስከባሪነት የሚመለምሏቸው የውትድርናና ሌሎች ባለሙያዎች ስብጥር ተመጣጣኝ በሆነ መልኩ የሴቶችን ቁጥር እንዲያካትት ተጠየቀ፡፡

አምስት መካከለኛ የኢኮኖሚ ደረጃ ላይ የሚገኙ የዓለም አገሮችን ያቀፈውና “MIKTA” ቡድን በመባል የሚጠሩት ሜክሲኮ፣ ኢንዶኔዥያ፣ ኮሪያ፣ ቱርክንና አውስትራሊያን በአንድ ይዞ የተሰባሰበው ጥምረት ሰኔ 14 ቀን በአዲስ አበባ በሚገኘው የኢንዶኔዥያ ኢምባሲ ቅጥር ግቢ የዓለም የሰላም አስከባሪ አባላት ቀን አክብሯል፡፡

በየዓመቱ እ.ኤ.አ ግንቦት 29 ቀን የሚከበረውን የዓለም የሰላም አስከባሪ አባላት መታሰቢያ ቀን፣ የአምስቱ አገሮች አምባሳደሮች፣ የኢትዮጵያ ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ኃላፊዎቸ፣ ከመከላከያ ሚኒስቴርና የሌሎች ተቋማት ተወካዮች በተገኙበት ‹‹ሴት የሰላም አስከባሪ አባላት ቁልፍ ለሆነ የሰላም ስኬት›› በሚል የፓናል ውይይት ተካሂዷል፡፡

በውይይቱ ንግግር ያደረጉት በኢትዮጵያ የኢንዶኔዥያ አምባሳደር አልቡስራ ባሰኑር፣ ግጭቶች በሚከሰቱባቸው የዓለም አካባቢዎች በሚሰማሩ የሰላም አስከባሪ አባላት ውስጥ የሴቶች ቁጥር በብዛት መኖር፣ ሴቶች ከሚያከናውኑት የሰላም ማስከበር ሚና ባለፈ በተሰማሩባቸው አካባቢዎች ካለው ማኅበረሰብ ጋር በአጭር ጊዜ የመግባባትና የመረዳዳት አቅም እንዲሁም በሕዝቡ ዘንድ መተማመንን በቀላሉ የመፍጠር አቅም እንዳላቸው ተናግረዋል፡፡

በመሆኑም አገሮች አሁን ዓለም ላይ የሚታየውን ግጭት ለመፍታት የሚያሰማሯቸው የሰላም አስከባሪ አባላት መካከል፣ ሴቶችን በከፍተኛ ሁኔታ በማሳተፍ በተፈጥሮ ባላቸው ልዩ ችሎታ ግጭት ውስጥ የገቡ አካባቢዎችን በቶሎ መልሰው እንዲያገግሙና በጤና፣ በትምህርት፣ በማኅበራዊ ዘርፍ ኅብረተሰቡ በቀላሉ ተግባብቶ ለመሥራት የሚኖራቸው ሚና የማይናቅ መሆኑን አምባሳደር አልቡስራ ተናግረዋል፡፡

በሰላም አስከባሪ ብዛት በቁጥር 2,800 አባላትን በማሳተፍና አስተዋፅኦ በማድረግ በዓለም ሰባተኛ ደራጃ ላይ የምትገኘው ኢንዶኔዥያ ስትሆን፣ ከጥቂት ዓመታት በፊት በሦስተኛ ደረጃ ላይ የነበረችው ኢትዮጵያ ደግሞ፣ በቅርቡ ከአብዬ ግዛት ለቃ መውጣቷን ተከትሎ ወደ ስድስተኛ ደረጃ መውረዷን የገለጹት በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የዓለም አቀፍ ድርጅቶች ጉዳይ ዳይሬክተር አቶ አየለ ሊሬ ናቸው፡፡

ዳይሬክተሩ በገለጻቸው፣ በአብዬ ግዛት የነበረው የኢትዮጵያ የሰላም አስከባሪ ኃይል በቅርቡ ጨርሶ ሲወጣ፣ ኢትዮጵያ ለዓለም በሰላም አስከባሪ አባላት በምታደርገው አስተዋጽኦ ከነበረችበት ከፍ ያለ ደረጃ ዝቅ ማለቱን ተናግረዋል፡፡

 ይሁን እንጂ ኢትዮጵያ በየትኛውም ጊዜ በፖሊሲ ጭምር የታገዘ ዝግጁነት እንዳላትና ለወደፊት በማንኛውም የሰላም ማስከበር ሚና ላይ ለመሳተፍ እንደምትሠራ ተናግረዋል፡፡

 አገሮች በሚያሰማሯቸው የሰላም አስከባሪ አባላት ውስጥ የሴቶች ተሳትፎ ሚና እንደ ዋና አጀንዳ በማድረግ መሥራት እንደሚገባ የጠየቁት የተባበሩት መንግሥታት ሴቶች ተቋም (UN Women) ተወካይ ወ/ሪት ደሴት አበበ ናቸው፡፡ ወ/ሪት ደሴት የሴት የሰላም አስከባሪዎች ቁጥር መብዛት ሴቶች በማኅበረሰቡ ውስጥም ሆነ በሰላም አስከባሪ አባላት መካከል የሚደርሰባቸውን ማንኛውም ሁኔታ በቀላሉ የመረዳትና መልስ የመስጠት አቅም እንደሚሰጣቸው ተናግረዋል፡፡

በኢትዮጵያ የቱርክ አምባሳደር ያብራክ አልፕ (አምባሳደር) በበኩላቸው አምስቱ አገሮች ከዘጠኝ ዓመት በፊት የፈጠሩት ጥምረት በሰላም ግንባታ፣ ለዓለም መረጋጋት እንዲሁም ዴሞክራሲዊ ሥርዓት መፈጠር ጥረት የሚያደርግ መሆኑን የገለጹ ሲሆን፣ በዚህ ረገድ በሰላም አስከባሪነት ሚና ውስጥ የሴቶች ውክልናና ተሳትፎን በሚገባው ልክ ማሳደግ እንደሚገባ አስረድተዋል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ትኩስ ጽሑፎች

ተዛማጅ ጽሑፎች

- Advertisement -
- Advertisement -