Friday, September 22, 2023
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

የኃይል አቅርቦትና የጥሬ ዕቃ እጥረት የአግሮ ኢንዱስትሪ ፓርኮችን እንቅስቃሴ እየተገዳደረ መሆኑ ተነገረ

ተዛማጅ ፅሁፎች

በኦሮሚያ ሁለተኛው የተቀናጀ አግሮ ኢንዱስትሪል ፓርክ በግንባታ ላይ ይገኛል

የግብርና ምርቶችን በማቀናበር የውጭ ምንዛሪ ገቢ ለማስገኘት በተቋቋሙት የተቀናጀ የግብርና ኢንዱስትሪ ፓርኮች ያጋጠመው የኃይል አቅርቦትና የጥሬ ዕቃ እጥረት፣ የፓርኮቹን ውጤታማነት እየተገዳደረ ነው ተባለ፡፡

ይህ የተገለጸው አገር በቀል የአግሮ ኢንዱስትሪ ዘርፉን ለማሳደግ ሚና አላቸው ከተባሉት ዓለም አቀፍ የልማት አጋር ተቋማት ጋር፣ ማክሰኞ ሰኔ 13 ቀን 2014 ዓ.ም. በኢሊሌ ሆቴል በተደረገ የዓውደ ጥናት መድረክ ላይ ነው፡፡

በመድረኩ በአገሪቱ ግንባታቸው ተጠናቆ አገልግሎት እየሰጡ የሚገኙት የይርጋለም፣ የቡልቡላና የቡሬ የተቀናጀ አግሮ ኢንዱስትሪ ፓርኮች አሁናዊ የሥራ እንቅስቃሴ የሚያሳይ ገለጻ ለተሳታፊዎች ቀርቦ ሰፊ ውይይቶች ተደርጎበታል፡፡

የሲዳማ ኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽን ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ መምሩ ሞኬ እንደገለጹት፣ የፓርኩ አስተዳደር የይርጋለም የተቀናጀ ኢንዱስትሪ ፓርክ እንዲሁም በበንሳ፣ በአለታ ወንዶና በሞሪቾ የሚገኙ የገጠር የትራንስፎርሜሽን ማዕከላትን ያስተዳድራል፡፡

ፓርኩ በ294.7 ሔክታር መሬት ላይ የተዋቀረ ሲሆን፣ 152 ሼዶችን መያዝ ይችላል፡፡ በዚህ ወቅት በተቀናጀ የኢንዱስትሪ ፓርኩ 11 ሼዶች ተገንብተው ከእነዚህ ውስጥ አምስት የሚደርሱት ወደ ሥራ መግባታቸው ተገልጿል፡፡

የኤሌክትሪክ ኃይል፣ የመንገድ፣ የቴሌኮም አገልግሎቶችና የተለያዩ የመሠረተ ልማቶች የተሟሉለት ይርጋለም፣ በውስጡ የተለያዩ ንዑስ ዞኖች አሉት፡፡ የአትክልትና ፍራፍሬ፣ የወተት፣ የሥጋ፣ የቡና፣ የማር፣ የጥራጥሬና የሥራ ሥር ሰብሎችን፣ እንዲሁም የእንቁላል ምርት የሚጠቀሱ ናቸው ተብሏል፡፡ በዚህ ወቅት ሁለት በአቦካዶ፣ አንድ በወተት፣ አንድ በማር እንዲሁም አንድ በቡና ማቀናበር ሥራ ወደ ሙከራ ምርት የገቡ ድርጅቶች በውስጡ እንደሚገኙ ተገልጿል፡፡

ዋና ሥራ አስፈጻሚው እንዳስረዱት፣ ለተቀናጀ የኢንዱስትሪ ፓርኩ ትልቁ ጉዳይ የአቅርቦት ሒደቱ ሲሆን፣ ይህንንም ታሳቢ በማድረግ ከአካባቢው አርሶ አደሮች ጋር ትስስር ተፈጥሯል፡፡

አቶ መምሩ እንዳስታወቁት፣ በተቀናጀ የአግሮ ኢንዱስትሪ ፓርኩ ውስጥ ከሚያጋጥሙ ማነቆዎች ውስጥ ትልቁ የጥሬ ዕቃ አቅርቦት ነው፡፡ ፋብሪካዎች እየጨመሩ በሄዱ ቁጥር አሁን ባለው ልክ የሚቀርበው ምርት አይበቃቸውም ብለዋል፡፡

የኅብረት ሥራ ማኅበራት ተደራጅተው ጥሬ ዕቃ እያቀረቡ ቢገኝም፣ በሌላ በኩል ደላሎች በዚህ አሠራር ውስጥ የሚገቡበት ሁኔታ መስተዋሉ ትልቁ ችግር መሆኑ ተገልጾ፣ ደላሎች የገበያውን ሒደት በዋጋ፣ በጥራት በብዛት የሚያዛቡበት ሁኔታ ተፅዕኖ መፍጠሩን አቶ መምሩ ተናግረዋል፡፡

የአማራ ክልል ኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽን የፕሮጀክት አስተባባሪ አቶ ነጋ ደምሴ፣ የቡሬ የተቀናጀ ኢንዱስትሪ ፓርክ በ260 ሔክታር መሬት ላይ ያረፈ፣ ከዚህም 169 ሔክታር የሚሆነው ለማምረቻ የተዘጋጀ ነው ብለዋል፡፡ በቡሬ 22 የሚደርሱ ፕሮጀክቶች 13 ዓይነት የግብርና ምርቶችን ለማቀነባበር ፍቃድ ወስደው መሬት የተረከቡ መሆናቸውን፣ ከእነዚህም አራት የሚደርሱ ፕሮጀክቶች በግንባታ (ኮንስትራክሽን) ሲገኙ፣ አንድ ፋብሪካ ምርት ወደ ውጭ መላክ መጀመሩ ገልጸዋል፡፡

በፓርኩ ውስጥ ከሚገኘው መሬት 111 ሔክታር የሚሆነው አሁንም ባለሀብት የሚፈልግና ለባለሀብቱ የሚተላላፍ መሬቱ መሆኑ ተገልጿል፡፡ በቡሬ ፓርክ ውስጥ ወደ ሥራ የገባው የሪችላንድ ፋብሪካ ትልቅ ካፒታል ያለው፣ አኩሪ አተርን በማቀነባበር የፕሮቲን ፓውደር፣ የምግብ ዘይትና የእንስሳት መኖ አምራች መሆኑ የተገለጸ ሲሆን፣ ፋብሪካው በጥር 2013 ዓ.ም. ወደ ምርት ገብቶ እስከ ተያዘው ወቅት ድረስ 21 ሚሊዮን ዶላር ገቢ ማስገኘቱ ተገልጿል፡፡

አቶ ነጋ እንዳስታወቁት፣ ድርጅቱ እያመረተ የሚገኘው ከአጠቃላይ የማምረት አቅሙ በ20 ከመቶ ብቻ ነው፡፡ ኢንዱስትሪ ፓርኩ ሁለት መሠረታዊ ችግሮች ያሉበት ሲሆን፣ የመጀመሪያው ከኃይል አቅርቦት ጋር በተያያዘ ያለው ችግር መሆኑን ተናግረው፣ የኃይል አቅርቦቱ ባለመስተካከሉ አዲስ ለመግባት ያሰቡ ደርጅቶች ካላቸው ሥጋት ባሻገር፣ የገቡትም በሙሉ አቅማቸው ለማምረት አላስቻላቸውም ብለዋል፡፡

ከኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ጋር በቅርቡ ስምምነት መደረጉ የተገለጸ ሲሆን፣ ነገር ግን እርግጠኛ መሆን የሚቻለው መብራት ተዘርግቶ አገልግሎት መስጠት ሲቻል መሆኑን አቶ ነጋ አስረድተዋል፡፡

የቡሬ ኢንዱስትሪ ፓርክን ለማቋቋም ጥናት ሲደረግ በከተማው የሚገኘውን የኃይል አቅርቦት ይበቃል ወይም ተመጣጣኝ ይሆናል በሚል ዕሳቤ ቢሆንም፣ ከዚያ ባሻገር ለፓርኩ ራሱን የቻለ 48 ሜጋቮልት አምፒር የኃይል ማከፋፈያ (ሰብስቴሺን) ይገነባል ተብሎ አገሪቱ ባጋጠማት የውጭ ምንዛሪ እጥረት የመሠረት ልማቱ ቶሎ ሊጀመር አለመቻሉን የፕሮጀክት አስተባባሪው ገልጸዋል፡፡

ሌላው በአውደ ጥናቱ ላይ የተገኙት የኦሮሚያ ኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽን ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ ሲሳይ ገመቹ እንዳስታወቁት፣ በክልሉ የሚገኘው ቡልቡላ የተቀናጀ ኢንዱስትሪ ፓርክ  በ271 ሔክታር መሬት ላይ ያረፈ፣ ለ250 እና ከዚያ በላይ ለሆኑ የፋብሪካ ኃላፊዎች የሚያገለግል የጋራ መኖሪ ቤት የተገነባለት፣ አምስት ንዑስ ዞኖች ያሉት፣ ትልቅ ኢንቨስትመንት ነው፡፡ የቡና ማቀነባበሪያ፣ የሥጋና የዶሮ ማቀነባበሪያ፣ የወተትና የማር ማቀነባበሪያ፣ የአትክልትና የፍራፍሬ፣ እንዲሁም የእህል ውጤቶች ማቀነባበሪያ ንዑስ ዞኖች በፓርኩ ውስጥ እንደሚገኝም ተገልጿል፡፡

ከቡልቡላ አግሮ ኢንዱስትሪ ፓርክ በተጨማሪ በነቀምት ከተማ ተመሳሳይ ፕሮጀክት እየተሠራ እንደሚገኝ አቶ ሲሳይ ገመቹ ለሪፖርተር ተናግረዋል፡፡ በዚህ ዓመት የተጀመረው ፕሮጀክት በቀጣይ ሁለት ዓመታት ተገንብቶ ሙሉ በሙሉ የሚጠናቀቅ መሆኑ ተመላክቷል፡፡

በ250 ሔክታር ላይ የሚገነባው ፓርክ በነቀምት ከተማ የሚገኝ ሲሆን፣ የግንባታ አሠራሩም ከቡልቡላ አግሮ ኢንዱስትሪ ፓርክ ጋር ተመሳሳይ የሆኑ የግብርና ውጤቶችን ወስዶ የሚያቀነባብር ይሆናል ተብሏል፡፡

በነቀምት የሚገነባው ፓርክ ላይ ከዚህ ቀደም ከተገነባው የቡልቡላ አግሮ ኢንዱስትሪ  ልምዶች ተወስዶ ተግባራዊ እንዲደረግበት የታሰበ መሆኑን የተመላከተ ሲሆን፣ ለዚህም የመሠረተ ልማት፣ የፍሳሽ አወጋገድ ቴክኖሎጂ (ዌስት ዋተር ትሪትመንት)፣ የውኃ፣ የመብራትና የቴሌኮም ሥራዎች ጎን ለጎን ጥናቶች እየተካሄደ ይገኛል ተብሏል፡፡

ግንባታው በጅምር ላይ የሚገኘው የተቀናጀ የኢንዱስትሪ ፓርክ አሥር በመቶ ያህል ሥራው እንደተንቀሳቀሰና ግንባታውን የሚያከናውኑት ተቋራጮች አገር በቀል መሆናቸው ታውቋል፡፡ የፓርኩ ግንባታ በሁለት ዓመት ውስጥ የሚጠናቀቅ ነው ሲሉ አቶ ሲሳይ  ለሪፖርተር ተናግረዋል፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች