‹‹አረንጓዴ አሻራ›› በማለት ከአራት ዓመታት በፊት በተጀመረው ችግኝ የመትከል ንቅናቄ ትናንት ሰኔ 14 ቀን 2014 ዓ.ም. የተተገበረ ሲሆን፣ የተተከሉ ችግኞች የመዳንና የማደግ መጠን ወደ 84 በመቶ እንደሚጠጋ ተገለጸ፡፡
በአራተኛው አረንጓዴ አሻራ ንቅናቄ ማስጀመርያ ፕሮግራም ላይ የግብርና ሚኒስትሩ አቶ ዑመር ሁሴን ባደረጉት ንግግር እንደገለጹት፣ ንቅናቄው ሲጀመር በአራት ዓመታት ለመትከል ታስቦ ከነበረው 20 ቢሊዮን ችግኞች ውስጥ እስካሁን በተደረጉት ሦስት ዓመታት 18 ቢሊዮን ችግኞችን መትከል ተችሏል፡፡
በዚህ በአራተኛው ንቅናቄም ሰባት ቢሊዮን ችግኞች ለመትከል እንደታሰበ ሚኒስትሩ ገልጸዋል፡፡ በዚህም አጠቃላይ የአራት ዓመቱ ችግኝ ተከላ ሥሌት ወደ 25 ቢሊዮን የሚጠጋ እንደሚሆን አክለዋል፡፡
‹‹አሁን በክልሎች ከተዘጋጁት ሰባት ቢሊዮን ችግኞች ውስጥ 52 በመቶ የሚሆኑትን በአግሮ ፎረስትሪ ምድብ ውስጥ የሚካተቱ ሲሆን፣ 47 በመቶ ደግሞ በደንነት (ፎረስት) ብቻ ይሆናሉ፡፡ ቀሪው አንድ በመቶ ደግሞ ማስጌጫ ተክል (አርኖ ሜንታል) ውስጥ የሚካተት ነው፤›› በማለት አቶ ዑመር ገልጸዋል፡፡
በዚህ የችግኝ ተከላ ንቅናቄ ውስጥ 20 ሚሊዮን ዜጎች ተሳታፊ እንደሆኑ የተገለጸ ሲሆን፣ ወደ አምስት የሚጠጉ አገሮችም ተሳትፈዋል፡፡ ችግኞቹ ወደ 121 ሺሕ በሚሆኑ የችግኝ ጣቢያዎች እንደተመረቱ ሚኒስትሩ ገልጸዋል፡፡
አራተኛውን የአረንጓዴ አሻራ ችግኝ ተከላ ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር)፣ በጉለሌ ቦታኒክ ጋርደን ያስጀመሩ ሲሆን፣ ሁሉም ሚኒስትሮች፣ የክልሎች ፕሬዚዳንቶች፣ የተለያዩ ተቋማት ሹማምንቶች፣ እንዲሁም አፍሪካ ኅብረት ሊቀመንበር ሚስተር ሙሳፋኪ፣ የተለያዩ አገሮች አምባሳደሮችና ዲፕሎማቶች በችግኝ ተከላው ተሳትፈዋል፡፡