ጠቅላይ ሚኒስትሩ የኃላፊዎችን ትብብርና አንድነት ጠይቀዋል
ባለፈው ሳምንት መጨረሻ ሰኔ 11 ቀን 2014 ዓ.ም. ጀምሮ በተለይ በምዕራብ ወለጋና በተለያዩ አካባቢዎች ንፁኃንን በጨፈጨፉ ግፉአን ላይ፣ የአገር መከላከያ ሠራዊት ከሰኞ ሰኔ 13 ቀን 2014 ዓ.ም. ጀምሮ ዕርምጃ እየወሰደ መሆኑን፣ ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) ትናንትና ሰኔ 14 ቀን 2014 ዓ.ም. አስታወቁ፡፡
‹‹ንፁኃን ዜጎችን እንደ ችግኝ እየጨፈጨፉ ነው›› ብለው በገለጿቸው ኃይሎች ላይ መከላከያ የጀመረው ዕርምጃ፣ የአመራሮችን ትኩረት የሚሻ ጉዳይ ነው በማለት አስገንዝበዋል፡፡
‹‹ዛሬ ከወታደርና ከፖሊስ ጋር በቀጥታ መግጠም የማይችሉ ተላላኪ ባንዳዎች፣ ንፁኃን ኢትዮጵያውያንን ልክ እንደ ችግኝ ይጨፈጭፋሉ፤›› ብለዋል፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትሩ በጉለሌ የዕፅዋት ማዕከል (ቦታኒካል ጋርደን) ውስጥ በተካሄደው በአራተኛው አረንጓዴ አሻራ ፕሮግራም ማስጀመርያ ላይ ባደረጉት ንግግር፣ ሁሉም ኃላፊዎች ይህንን ጭፍጨፋ ለማስቆም መተባበር እንዳለባቸው አሳስበዋል፡፡
‹‹ንፁኃን ኢትዮጵያውያን መኖር የማይችሉባት ምድር ለማድረግና የያዝናቸውን ሐሳቦች ለማጨናገፍ የሚሞክሩ ተላላኪ ኃይሎች ህልሞቻቸው እንዳይሳካ መከፋፈል ሳይሆን፣ በተደመረ ክንድ ጨፍጫፊዎችን በሕግ አግባብ ማስተማር ይጠበቅብናል፤›› ብለዋል፡፡
ቅዳሜ ሰኔ 11 ቀን 2014 ዓ.ም. በኦሮሚያ ክልል ምዕራብ ወለጋ ዞን በጊምቢ ወረዳ በቶሎ ቀበሌ በንፁኃን ዜጎች ላይ የተፈጸመውን ጭፍጫፋ በማስመልከት፣ ጠቅላይ ሚኒስትሩ መግለጫ ማውጣታቸው ይታወሳል፡፡
እስካሁን በጭፍጨፋው የሞቱ ሰዎች ቁጥር ባይታወቁም፣ የዓይን እማኞች በብዙ መቶዎች የሚቆጠሩ ሰዎችን እንደቀበሩ ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡ ሪፖርተር ያነጋገረው አንድ የዓይን እማኝ እንደገለጸው፣ ወደ 400 የሚጠጉ አስከሬኖች ሲቀበሩ በሥፍራው ተገኝቷል፡፡
የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን በበኩሉ በሰላማዊ ሰዎች ላይ የሚደርሰው ጥቃት በእጅጉን እንዳሳሰበው ገልጾ፣ መንግሥት ተጨማሪ ጥቃት እንዳይፈጸም አስፈላጊ መከላከሎችን በማድረግ ዘላቂ መፍትሔ ማምጣት እንዳለበት ባወጣው መግለጫ አሳስቧል፡፡