Friday, September 22, 2023

በፍትሕ ተቋማት የተደረገው ሪፎርም የተጠበቀውን ያህል መሻሻል አለማሳየቱ ተገለጸ

- Advertisement -spot_img

በብዛት የተነበቡ

ከሕግ ውጪ ማሰርና ተጠርጣሪዎች የት እንደታሰሩ አለማወቅ ተባብሶ ቀጥሏል

ማረሚያ ቤቶች የደኅንነቶች ዓይነት ሥራ እየሠሩ ነው

አራት ዓመታት በፊት ከተካሄደው የመንግሥት ሥርዓት ለውጥ በኋላ ሪፎርም ቢደረግም እምብዛም ውጤት አለመታየቱ ተገለጸ፡፡

የፍትሕና ሕግ ኢንስቲትዩት በአራት የፍትሕ ተቋማት በተለይም በፍትሕ ሚኒስቴር፣ በፍርድ ቤቶች፣ በፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽንና በፌዴራል ማረሚያ ቤቶች አጠቃላይ አገልግሎት አሰጣጥና የደንበኞችን እርካታን በተመለከተ ላለፉት አምስት ወራት ያህል ሲያካሂደው የነበረውን ጥናት ሰኞ ሰኔ 13 ቀን 2014 ዓ.ም. ይፋ አድርጓል፡፡

በፍትሕ ሥርዓቱ ውስጥ የሚታዩ የመልካም አስተዳደር ችግሮችና ከሕዝብ የሚነሱ ቅሬታዎች ጥናት እንዲደረግባቸው በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ተጠይቆ ነበር፡፡ ጥናቱ የተቋማቱን የበላይ ኃላፊዎች፣ ሠራተኞች፣ ተገልጋዮችና መዛግብቶችን በመዳሰስ የተካሄደ መሆኑ ተገልጿል፡፡

በአራቱ የፍትሕ ተቋማት ላይ የተከናወነው ጥናት እንደሚያሳው፣ የፍትሕ ተቋማቱ ቁመና በአብዛኛው በዝቅተኛና በመካከለኛ ደረጃ ላይ ይገኛሉ፡፡

በፍትሕና በሕግ ኢንስቲትዩት የሕግ ባለሙያ አቶ ሙሉዓለም አበራ፣ የፍርድ ቤቶችን ቁመና የተመለከተውን ጥናት ሲያቀርቡ፣ የጥናቱ ውጤት ከአራት ዓመታት በፊት ይነሱ የነበሩ ችግሮችን በግልጽ ያሳየ፣ በቀደሙት ጊዜያት ይነሱ የነበሩ ቅሬታዎች አሁንም መቀጠላቸውን ያመላከተ እንደሆነ ተናግረዋል፡፡

በአራት ዓመታት ውስጥ የተካሄደው ‹‹የለውጥ ሥራ ምን ለውጥ አመጣ?›› በሚል የተደረገው ይህ ጥናት፣ ላለፉት ዓመታት ምንም እንኳ የተለያዩ የሕግ ማዕቀፎች ቢወጡም፣ ከ43 በመቶ በላይ የሚሆነው የጥናቱ ውጤት የሚያሳየው አገልግሎቱ በጣም ዝቅተኛ ደረጃ ላይ መሆኑን አቶ ሙሉዓለም አስረድተዋል፡፡

‹‹በዓለም አቀፍ ደረጃም ሆነ በአገር አቀፍ ደረጃ ዕውቅና የተሰጣቸው የፍትሕ ሥርዓት መለኪያዎችን መሠረት አድርጎ የተከናወነው ጥናት እንደሚያሳየው፣ የተቋማቱ አገልግሎት አሰጣጥ ለብልሹ አሠራር የተጋለጠና አሁንም ሕዝብን ለእንግልት የሚዳርጉ አሠራሮች አሉ፤›› ብለዋል።

በፍትሕ ተቋማት ውስጥ በርካታ ቁጥር ያላቸው ሠራተኞች ‹‹በተቋማቸው ውስጥ የሚካሄደውን የለውጥ ሥራ እንዴት አገኛችሁት?›› ተብለው ሲጠየቁ፣ ሰለሚባለው ነገር ምንም ዓይነት መረጃ እንደሌላቸው አቶ ሙሉዓለም ገልጸዋል፡፡

በሌላ በኩል ከደንበኞች የሚጠየቁ ጉቦና ጥቅማ ጥቅም፣ ምርመራን ማዘግየት፣ የዓቃቤ ሕጎች በሰዓቱ አለመገኘት፣ የጉዳይ መጓተት፣ ሙስና፣ የመረጃ መጥፋት፣ ቅንጅታዊ አሠራር አለመኖር፣ በሚያጠፉ ዳኞች ላይ የሚወሰኑ ቅጣቶች ይፋ አለመደረግና መሰል ጉዳዮች በስፋት እንደሚንፀባረቁ ተጠቁሟል፡፡

የፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽን በተመለከተ ጥናት ያቀረቡት አቶ ደርሶልኝ የኔአባት በበኩላቸው፣ በፌዴራል ፖሊስ ተጠርጣሪዎችን ከሕግ ውጪ የማሰርና መብት አለማክበር፣ እንዲሁም ተጠርጣሪዎች የት እንዳሉ የማይታወቅበት ሁኔታ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ የመሄድ አዝማሚያ መኖሩን አስታውቀዋል፡፡

በፌዴራል ማረሚያ ቤቶች ላይ የሚታየውን አገልግሎት አሰጣጥ በተመለከተ የጥናት ጽሑፍ ያቀረቡት ሙራዱ አብዱ (ዶ/ር)፣ ማረሚያ ቤቶች በወታደራዊ ሥነ ልቦናና ኃይል ውስጥ እንደሚገኙና የደኅንነት ተቋማት የሚያከናውኑት ዓይነት ሥራ ላይ እንደሚያተኩሩ አስረድተዋል፡፡

በተመሳሳይ አክብሮት የሌለው መስተንግዶ፣ ማስፈራራትና ዛቻ፣ ለታራሚዎች ምቹ አለመሆን፣ ለታራሚ ቤተሰቦች ተገቢውን ክብር አለመስጠትና የመንግሥት ንብረትን ለግል የማዋል ዝንባሌ እንደሚስተዋል ተናግረዋል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ትኩስ ጽሑፎች

ተዛማጅ ጽሑፎች

- Advertisement -
- Advertisement -